ዓለምአቀፍ የአፍጋሃኒስታን ጉባዔ በበርሊን | ኤኮኖሚ | DW | 09.04.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ዓለምአቀፍ የአፍጋሃኒስታን ጉባዔ በበርሊን

የበርሊኑ ጉባዔ ዓለምአቀፉ ሕብረተሰብ በሚቀጥሉት ዓመታትም ከአፍጋሃኒስታን ጎን ቆሞ የሚቀጥል የመሆኑን ስሜት ነው በካቡል ባለሥልጣናት ዘንድ ያሳደረው። በሌላ አነጋገር አበዳሪ መንግሥታት በጦርነት ለወደመችው አገር መልሶ-ግንባታ ወደፊትም የገንዘብ ዕርዳታ ለማቅረብ ቃል መግባታቸው የካቡልን ባለሥልጣናት ከመጠን በላይ አስደስቷል። የጀርመኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዮሽካ ፊሸር በሚቀጥሉት ሶሥት ዓመታት ለአፍጋሃኒስታን 8.2 ሚሊያርድ ዶላር ለማቅረብ መወሰኑ ለመልሶ-ግንባታው የሚጠቅም ብቻ ሣይሆን የዓለም ሕብረተሰብ የረጅም ጊዜ የፖለቲካ፣ ቁሳቁሳዊና የሞራል ግዴታውን ለመወጣት ቆርጦ መነሣቱን የሚያመለክት ነው ሲሉ ነበር ዕርምጃውን ያወደሱት። ጥያቄው ወደፊት የአበዳሪዎቹ መንግሥታት ቃልና ተግባር ተጣጥሞ መገኘቱ ላይ ነው። ከዚህ ቀደም በዚህ መልክ የተገባ ቃል ባዶ ሆኖ የታየባቸው ጊዜያት በመሠረቱ ጥቂቶች አይደሉም። የአፍጋሃኒስታንን ዕጣ ምናልባት የተለየ የሚያደርገውና ተሥፋ የሚሰጠው አበዳሪዎቹ መንግሥታት የራሳቸውን ጸጥታ ከአገሪቱ መረጋጋትና ለሽብር መሠረት ማሳጣት ጋር አጣምረው መመልከት መያዛቸው ነው።

የጉባዔው ተሳታፊዎች አፍጋሃኒስታን በራሷ ወታደሮችና ፖሊሶች ብሄራዊ ጸጥታን ማስከበር እስከምትችል ድረስ ዓለምአቀፉን የጸጥታ ጥበቃ ሃይል አገሪቱ ውስጥ እንደሚያቆዩ ቃል ገብተዋል። ከዚሁ ሌላ የሰሜን አትላንቲኩ ወታደራዊ ድርጅት ናቶ የማዕከላዊውን መንግሥት ተጽዕኖ ለማጠንከር ከካቡል ውጪ አምሥት ተጨማሪ የአካባቢ መልሶ-ግንባታ ቡድኖች ለማሰማራት ያቅዳል። እርግጥ ሰባት መቶ ገደማ የሚጠጉት የ 56 መንግሥታት ተጠሪዎች ወደ በርሊን የመጡት ተጨማሪ ገንዘብና ወታደሮች የማቅረብ ቃል ለመግባት ብቻ አልነበረም። ከአፍጋሃኒስታን የሚጠብቁት ዋስትናም መኖሩ አልቀረም። ይሄውም የካቡል መንግሥት በአፍጋሃኒስታን እያበበ የሄደውን የሱስ ዕጽዋት መመረት አጥብቆ መታገሉ ሲሆን ጉዳዩ ከበርሊኑ ጉባዔ ማዕከላዊ የአጀንዳ ነጥቦች መካከል አንዱ ሆኖ ነው የሰነበተው። ፕሬዚደንት ሃሚድ ካርዛይ ራሳቸው የሱስ ዕጽዋት እርሻዎችን ለማጥፋትና ሕገ-ወጥ ንግድን ለማስወገድ ሰፊ ዘመቻ ለማካሄድ ይፈልጋሉ። እርግጥ የዓለም ሕብረተሰብ ድጋፍ የማይለያቸው ከሆነ! አፍጋሃኒስታንና ስድሥት ተጎራባቾቿም ለዚሁ ዓላማ አንድ ጸረ-ሱስ ዕጽዋት ውል ተፈራርመዋል።

ሃሚድ ካርዛይ እንዳስረዱት የሱስ ዕጽዋት ምርት፣ አፈንጋጭ የአካባቢ አበጋዞችና ሽብር እርስበርሳቸው የሚደጋገፉ ሶሥት ችግሮች ናቸው። በመሆኑም አፍጋሃኒስታን ውስጥ ሰላምን ማስፈን ከተፈለግ ሶሥቱንም ባንድላይ ከመታገል ሌላ ዘዴ የለም። ምርጫ የለም፤ ለአገሪቱና ለሕዝቡ ጥቅም ይህን ዕርምጃ መውሰዱ ግድ ነው። አበዳሪዎቹ አገሮች አፍጋሃኒስታንን ከጦርነት፣ ከዓመጽና ጭቆና ወደ ነጻነት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ለማሻገር መሻታቸው በሞራል ግዴታ ብቻ ሣይሆን የራስ ጥቅምም ስለሚታያቸው ጭምር ነው። አፍጋሃኒስታንን በማረጋጋት ዓለምአቀፉን ሽብር ለአንዴና ለሁልጊዜ መነሻ ምድር ለማሳጣት ይፈልጋሉ። የሱስ ዕጽዋት ንግድ ችግርንም ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ማዋል ቢያቅት እንኳ ማለዘብ የሚቻለው በአገሪቱ ሰላምና ዴሞክራሲ መስፈን ሲችል ብቻ መሆኑ ነው የሚታመነው። አፍጋሃኒስታን በዓለም ላይ ቀደምቷ የሱስ ዕጽዋት አምራች አገር ስትሆን ሁኔታው ቢቀየር ሕገ-ወጡን ንግድ በመታገሉ በኩል እጅግ ታላቅ ዕርምጃ እንደሚሆን አያጠራጥርም። ይህ የጋራ ጥቅም ባይኖር ኖሮ አፍጋሃኒስታንን በመርዳቱ በኩል ባለፉት ዓመታት ያልተቆጠበ ዝግጁነት ሊታይ መቻሉ ያጠያይቃል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግምት በ 2002 ዓ.ም. በዓለም ላይ 4,600 ቶን የሱስ ዕጽዋት“ኦፒዬም”ሲመረት ከዚሁ አብዛኛው ማለትም 3,400 ቶን የሚመዝነው የተገኘው ከአፍጋሃኒስታን ነበር። በዚህ በኩል ካቡል ብቻ ሳትሆን ዓለምም ብዙ ጥረት ይጠብቀዋል ማለት ነው።

የአፍጋሃኒስታንን መንግሥት ከሚጠብቁት ግዴታዎች መካከል በአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ መቶ ሺህ ሚሊሺያ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታቱም ተግባር ይገኝበታል። ከካርዛይ መንግሥት ተግባራት ውስጥ ምናልባት ከባድ የሚሆነውም ይሄው ነው። ጊዜያዊው ፕሬዚደንት ካርዛይ አሁንም ከካቡል አልፈው በተለያዩ የጎሣ መሪዎችና የጦር አበጋዞች ተጽዕኖ ሥር ያሉ ብዙዎች ክፍለ-ሃገራትን መቆጣጠር እንደተሳናቸው ነው የሚገኙት። አንዳንድ የሚያፌዙባቸው ታዛቢዎች “ከዋና ከተማይቱ ውጭ ማንነታቸው የማይታወቅ በካቡል የታገቱ ከንቲባ” በማለት ያናንቋቸዋል። መፍቀረ-ዋሺንግተን የሆኑት ካርዛይ ያለ አሜሪካ ደህንነት ጠባቂዎቻቸው እስካሁን በሕይወት ባልቆዩ ነበር የሚሉም አሉ። ሁኔታው ወደፊትም በቀላሉ የሚለወጥ አይመስልም። እርግጥ አገሪቱን የማረጋጋቱ ጥረት ቢሳካ የጸጥታው ሁኔታ በሰፊው እንደሚያሻሽል አንድና ሁለት የለውም። ከፊታችን ሰኔ ወደ መስከረም ለተሸጋሸገው ምክርቤታዊና ፕሬዚደንታዊ ምርጫ መካሄድም የተረጋጋ ሁኔታ መስፈኑ እንዲሁ የግድ አስፈላጊ ነው የሚሆነው።

በበርሊኑ ጉባዔ የተሳተፉት አበዳሪ መንግሥታት በዚህ በኩል በተለይ አስቸጋሪ ሆኖ የተገኘውን የመራጮች ምዝገባ ተግባር ለማቃለል ተጨማሪ ዕርዳታ ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል። የጀርመኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዮሽካ ፊሸር እንዳሉት ምርጫውን ለአፍጋሃኒስታን ሕዝብ ጥቅም ሲባል በተሳካ ሁኔታ ነጻና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለማካሄድ ሁሉም ነገር እየተደረገ መሆኑን ጉባዔው ግልጽ ነው ያደረገው። ሆኖም ምርጫው በሰላም ወይም ከናካቴው በታቀደው ግዜ መካሄድ መቻሉን ራሱ ዛሬ ያላንዳች ጥርጥር ለመናገር የሚደፍር የለም። ምርጫው ከሰኔ ወደ መስከረም ወር የተሸጋሸገበት ምክንያት በቅርቡ እንደተገለጸው ከካቡል ውጭ የጸጥታው ሁኔታ ሊሟላ አለመቻሉና የመራጭ ምዝገባው እንደታሰበው አለመራመዱ ነበር። አሁንም በአምሥት ወራት ጊዜ ውስጥ የጎደለው ሊሟላ መቻሉ ቢቀር የሚያሳስብ ነው የሚሆነው። የአፍጋሃኒስታንን ችግር በገንዘብ ብቻ መፍታት የሚቻል አይሆንም። እዚህም ገንዘብ ጠቃሚ መሆኑ አያከራክር እንጂ ለሁሉም ነገር ወሣኝ አይደለም። የሚያሳዝነው የበርሊኑን መሰል የአበዳሪዎች ስብሰባ አዘጋጆች የጉባዔውን ስኬት ወይም ክስረት በገንዘቡ መጠን መለካት ይችላል የሚል ዕምነት መያዛቸው ነው።

የአፍጋሃኒስታን ተጠሪዎች ለሚቀጥሉት ሰባት ዓመታት ያስፈልገናል ካሉት የ 28 ሚሊያርድ ዶላር ዕርዳታ አንጻር ለሶሥት ዓመታት የሚሆን ሥምንት ሚሊያርድ መገኘቱ ትልቅ ስኬት ነው። በሌላ በኩል አሜሪካ፣ ጃፓንና የአውሮፓው ሕብረት ዋነኞቹ ገንዘብ አቅራቢዎች መሆናቸው ቢገለጽም ማን ምን ያህል ድርሻ እንደሚያዋጣ ገና በግልጽ አይታወቅም። በአበዳሪዎች ጉባዔ የሚገባው ቃል ሁሉ እንዳለ ገቢር እንደማይሆን የተለመደ እንደመሆኑም መጠን ገንዘቡ በሙሉ መቅረቡ ራሱ ከአሁኑ የማይመስል ነገር ነው። እርግጥ አፍጋሃኒስታንን በፖለቲካና በኤኮኖሚ ማረጋጋቱ ባይሳካ አሁን ከተገመተው ዕርዳታ የበለጠ ወጪ እንደሚከተል ዓለም ጠንቅቆ ያወቀው ይመስላል። የሆነው ሆኖ ዓለምአቀፉ ሕብረተሰብ በአፍጋሃኒስታን እምብዛም የኤኮኖሚ ጥቅም ሳይኖር ንቃተ-ሕሊናውን መዳበሩ ራሱ የበርሊኑን ጉባዔ ስኬታማ ያደርገዋል። አፍጋሃኒስታን ለነገሩ ትኩረትን የሚስብ የነዳጅ ዘይት ሃብት የላትም፤ ወይም በቅርብ ጊዜ ብቁ የኤኮኖሚ ሸሪክ ለመሆን የምትበቃ አይደለችም። የሂንዱ ኩሿ ግዛት ከገፍ የሱስ ዕጽዋት ባሻገር የምትነሣበት ነገር ቢኖር ድህነትና ኋላ ቀርነት ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ዛሬ ወይም ከታሌባኖች ወዲህ ጀምሮ ሳይሆን የዘመናት መለያዋ ሆኖ ቆይቷል። ይህ እንዲለወጥ ፍትሃዊ ምርጫ ተካሂዶ አገር አቀፍ ተደማጭነት ያለው ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እንዲቋቋም መድረጉ የመጀመሪያው ወሣኝ ዕርምጃ ነው የሚሆነው።