ዓለምአቀፍ የአውቶሞቢል ትዕይንት በጀርመን | ኤኮኖሚ | DW | 18.09.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ዓለምአቀፍ የአውቶሞቢል ትዕይንት በጀርመን

63ኛው ዓለምአቀፍ የአውቶሞቢል ትዕይንት የጀርመን የፊናንስ ማዕከል በሆነችው ከተማ በፍራንክፈርት ተከፍቷል። በዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ ብርቱ ፈተና የደረሰበት ይሄው ዘርፍ የዘንድሮ ትዕይንቱን የሚያካሂደው ከቀውሱ የማገገም የተሥፋ ጭላንጭል በሚታይበት ወቅት ነው።

default

ትዕይንቱን ትናንትና ዛሬ አያሌ ጋዜጠኞችና ባለሙያዎች ሲያጅቡ ከነገው ዕለት አንስቶ ለሚቀጥሉት አሥር ቀናት ተራው የጎብኚዎች ነው። በዝግጅቱ ሂደት ደግሞ ደጋግሞ የሚነሣው ዓቢይ ጥያቄ የአውቶሞቢሉ ዘርፍ፤ በአጠቃላይም የዓለም ኤኮኖሚ እንዴት ከቀውሱ አዘቅት ሊወጣ ይችላል? የሚለው ሲሆን በሌላ በኩል በርካታ ዓለምአቀፍና የጀርመን የምጣኔ-ሐብት ጠበብት ችኩል ተሥፋ እንዳይጣል ማስጠንቀቅ ይዘዋል። በፍራንክፈርት ኤግዙቢሽን ማዕከል በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በሚካሄደው ዓለምአቀፍ የአውቶሞቢል ትዕይንት ላይ ከሰላሣ ሃገራት የመጡ 750 ያህል አምራቾች አዳዲስ የሥራ ውጤቶቻቸውን ለተመልካች ያቀርባሉ።

የአውቶሞቢሉ ኢንዱስትሪ በዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ ክፉኛ ከተመቱት የኤኮኖሚ ዘርፎች መካከል አንዱ ነው። የዘርፉ የዓለም ንግድ በዚህ በያዝነው ዓመት ብቻ 14 በመቶ ነው ያቆለቆለው። ከዚሁ የተነሣም ዘንድሮ ወደ ፍራንክፈርቱ ትዕይንት የመጡት አውቶሞቢል አምራቾች ብዛት ካለፈው ዓመት ሲነጻጸር በሲሶ ቀንሷል። ለምሳሌ ኒሣንና ሚሱቢሺን የመሳሰሉት የጃፓን አምራጮች ወይም ቻይና የትዕይንቱ ስፍራ ኪራይ ይወደድብናል ሲሉ ወደ ቦታው ብቅ ለማለት እንኳ አልደፈሩም። ይህም ሆኖ ግን የጀርመን አውቶሞቢል ኢንዱስትሪ ማሕበር ፕሬዚደንት ማቲያስ ቪስማን አዳዲስና ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ግኝቶች የሚቀርቡበት ትዕይንት በቀውሱ የተመታውን ዘርፍ ለማነቃቃት ጥርጊያ ይከፍታል ባይ ናቸው።

“ዋነኛው የአውቶሞቢል ትዕይንት ማዕከል እንደሆንን እንቀጥላለን። ዓቢይ ማተኮሪያችን “አረንጓዴ” ማለት ለተፈጥሮ አካባቢ የተስማማ ምርት ነው። ይህን የምናደርገው ደግሞ ከሌህማን-ብራዘርስ የመዋዕለ-ነዋይ ባንክ ክስረት በኋላ የተከሰተው ከባድ ቀውስ ማብቂያው በሚታይበትና በተደረሰበት በትክክለኛው ሰዓት ነው። ከቀውሱ መላቀቅ የሚቻልበትን መንገድ እናሳያለን። የምንሰጠው ምልክት ለሌሎች ገበዮችም አነቃቂ ሊሆን የሚችል ነው። እና ዓለምአቀፉን የአውቶሞቢል ትዕይንት ከዚህ ቀደም እንደነበረው መልሶ ማራኪ እንዲሆን እናደርጋለን። እርግጥ ጊዜው አስቸጋሪ ቢሆንም”

በፍራንክፈርቱ ትዕይንት ,ላይ በዓለምአቀፍ ደረጃ መቶ ገደማ የሚጠጉ አዳዲስ ምርቶች ለተመልካች መቅረባቸው ምናልባትም የቪስማንን ዕምነት የሚያጠናክር ነው። ይህ ለፍራንክፈርቱ ትዕይንት የጥራት መለያ ሲሆን ከአዳዲሶቹ ግኝቶች ግማሹ በጀርመን አምራቾች የቀረቡ መሆናቸውም ለአገሪቱ የተሽከርካሪ ኢንዱስትሪ የማገገም ተሥፋን ማዳበሩ አልቀረም። ፎልክስ ዋገንንና ኦፔልን የመሳሰሉት አነስተኛና መካከለኛ አውቶሞቢሎችን የሚያቀርቡ ኩባንያዎች መንግሥት አሮጌ መኪናዎቻቸውን እየጣሉ አዳዲሶችን እንዲገዙ በነፍስ ወከፍ 2,500 ኤውሮ ማበረታቻ ገንዘብ በመክፈል በወሰደው ዕርምጃ እስካሁን ተጠቃሚ ሆነዋል።
ግን ይህ ዘመቻ አሁን ከስምንት ወራት በኋላ አብቅቷል። በሌላ በኩል ሜርሤደስንና ቢ.ኤም.ደብልዩን የመሳሰሉት ቀደምት ወይም የቅንጦት አውቶሞቢል አምራቾች ብርቱ የገበያ ክስረት ነው የደረሰባቸው። ከዚህ አንጻር በርካታ የዘርፉ አዋቂዎች የወደፊቱን ጊዜ ጨለም ያለ አድርገው ቢመለከቱትም የጀርመን የአውቶሞቢል ኢንዱስትሪ ማሕበር ፕሬዚደንት ግን አይሆንም ባይ ናቸው።

“ግልጽ የሆነ አንድ ነገር ቢኖር በጀርመን ገበዮች ላይ በአነስተኛ አውቶሞቢሎች ረገድ ድክመት የሚታይ መሆኑ ነው። ይህ ገና ከጅምሩ ግልጽ እንደሆነ እኔም በጊዜው ተናግሬያለሁ። ድክመቱ ምን መጠን እንደሚኖረው እርግጥ ዛሬ ለመናገር የሚችል ማንም የለም። ወሣኙ ጥያቄ የውጩ ንግድም በተመሳሳይ ጊዜ መረጋጋቱን ይቀጥላል ወይ ነው። ከተሣካ ይህ ለመጪው 2010 ዓ.ም. ወሣኝ ምልክት ነው የሚሆነው። የጀርመን ኢንዱስትሪ ከሚያመርተው ከአራት ሶሥቱ አውቶሞቢል በውጭ ገበያ ላይ የሚሸጥ መሆኑ መዘንጋት የለበትም”

ወቅታዊ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ የውጩ ገበያ የማገገም አዝማሚያ ነው የሚታይበት። የጀርመን አውቶሞቢሎች የውጭ ንግድ ባለፈው ነሐሴ ወር የሶሥት ከመቶ ማቆልቆል ቢታይበትም ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው ሲነጻጸር ባለበት የጸና ነው ለማለት ይቻላል። ከዚያ ቀደም ሲል በሩብ ያነሰ ነበር። እርግጥ የወቅቱ አዝማሚያ ችግሩ ተወግዷል ለማለት የሚያስደፍር አይደለም። ምክንያቱም ዘርፉ ቀድሞ መደረግ በነበረት አዲስ የአቀነጃጀት ተግባር ላይ ነው የሚገነው። የተትረፈረፈ አመራረቱን መቀየር ይኖርበታል። ዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ ደግሞ በዚህ የለውጥ ሰዓት ብዙም አመቺ አይደለም። ሆኖም ግን የጀርመን ኢንዱስትሪ ችግሩን ለመቋቋም ብቃት ብቻ ሣይሆን ትግሉን በማሸነፍ እንደሚወጣው ነው የሚያምነው።

“ለምሳሌ የአረብ አገሮችን መዋዕለ-ነዋይ ተሳትፎ ከዚህ አንጻር ነው የምመለከተው። በዚሁ የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት በጀርመን የቴክኖሎጂ ጥንካሬ፤ እንዲሁም በአምራቾቹና በልዋጭ ዕቃ አቅራቢዎቹ የካበተ የተሃድሶ ብቃት ላይ ዓመኔታ መኖሩን ግልጽ ያደርገዋል። አንዳንዴ እንዲያውም እንከን ማየት ከበዛበት ከዚህ ከጀርመን ይልቅ በውጭ አመኔታው የተለቀ ነው። ምክንያቱም የጀርመን ኩባንያዎች በዓለምአቀፉ የአውቶሞቢል ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተወዳዳሪ እንደሌላቸው የውጭው ዓለም በቀላሉ ያውቀዋል”

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የጀርመን የአውቶሞቢል ምርቶች ለአካባቢ ተፈጥሮ የተስማሙ እየሆኑ መሄዳቸውም መኩራሪያ መሆኑ አልቀረም። ጉዳዩ የሚመለከተው የጀርመን ፌደራል ባለሥልጣን ባቀረበው አዲስ መረጃ መሠረት በዚህ ዓመት በአገሪቱ ፈቃድ ተሰጥቷቸው መሽከርከር ከጀመሩት አዳዲስ አውቶሞቢሎች መካከል ከአሥር ዘጠኙ ከውጭ ከሚገቡት ሲነጻጸር ዝቅተኛ በካይ ጋዝ ካርቦን-ዳዮክሣይድ ወደ አየር የሚያተኑ ነበሩ። ጀርመን በወቅቱ የኢንዱስትሪው ማሕበር ፕሬዚደንት ማቲያስ ቪስማን እንደሚሉት በመቶ ኪሎሜትር ከአምሥት ሊትር ያነሰ ቤንዚን የሚፈጁ፣ የበካይ ጋዝ መጠናቸውም በኪሎሜትር ከ 130 ግራም በታች የሆነ ከመቶ የሚበልጡ ሞዴሎች ለገበያ ታቀርባለች።

እርግጥ ለአካባቢ አየር ያመቸ ቴክኖሎጂ ከተነሣ በኤሌክትሪክና ላሌ ንጹህ ሃይል የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ዘንድሮም በትዕይንቱ ላይ ተደርድረው መታየታቸው አልቀረም። ይሁንና ለገበያ ቀርበው ለዕለታዊ ጥቅም መዋላቸው ግን አሁንም የወደፊት ታሪክ ሆኖ ይቀጥላል። ለማንኛውም ለአሥር ቀናት የሚዘልቀውን የአውቶሞቢል ትዕይንት ከ 750 ሺህ የሚበልጥ ሕዝብ እንደሚጎበኝ ነው የሚጠበቀው። ይህ ደግሞ ከወትሮው ቢቀንስም በቀውስ ጊዜ የሚያስከፋ አሃዝ አይሆንም።

በሌላ በኩል በአውቶሞቢሉ ዘርፍ ብቻ ሣይሆን በአጠቃላይ በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ከቀውሱ የመላቀቅ ሂደት ገሃድ መሆን መቻልና ቀጣይነት ማግኘት አለማግኘት ሰሞኑን መንግሥታትና ጥበብትን ብዙ ያነጋገረ ጉዳይ ነው። የአሜሪካው የፊናንስ ሚኒስትር ቲሞቲይ ጋይትነር በመዳንና በዕድገት አቅጣጫ መካከል በመንሸራሸር እያገገመ ነው ይላሉ። እርግጥ በወቅቱ የሚቀርቡት መረጃዎች ተሥፋን የሚያዳብሩ ይሁኑ እንጂ በአንጻሩ ዘላቂና አስተማማኝ ሂደት መስፈኑን ለመናገር የሚደፍር የለም።

እንግዲህ በአጭር ጊዜ የሚጠበቅ ነገር የለም ማለት ነው። ለወቅቱ የማገገም አዝማሚያ እርግጥ መንግሥታት ከአሜሪካ እስከ አውሮፓ ቀውስ የተጣባውን ኤኮኖሚያቸውን መልሶ ለማነቃቃት ያፈሰሱት በሚሊያርዶች የሚቆጠር ገንዘብ ታላቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። የኤኮኖሚው ጠቢብ ፕሮፌሰር ሮበርት ሺለር እንደሚሉት ለምሳሌ ያለ መንግሥታቱ ዕርምጃ ቀውሱ የሃያኛዎቹን ዓመታት የዓለም ኤኮኖሚ ቀውስ አጥፊ አካሄድ በያዘ ነበር።

“ከ 1929/30 ታላቅ ቀውስ ሲነጻጸር አንዳንድ የተሻሉ ዕርምጃዎች ወስደናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ብዙ ባንኮች ከውድቀት ድነዋል። ያኔ ብዙ ሰዎች ነበሩ ባንኮች ውስጥ ያስቀመጡትን የቁጠባ ገንዘባቸውን ያጡት። ይህ ደግሞ ተሥፋ እንዲያጡና ውድቀቱም እንዲጠናከር ነው ያደረገው። አሁን መንግሥታት ትክክለኛውን ነገር እያደረጉ ነው ብዬ ነው የማስበው። በመሆኑም ከረጅም ጊዜ አንጻር ተሥፋ አለኝ። ይህም ሆኖ ግን ስለሚቀጥሉት አምሥት ዓመታት ሳስብ ጥቂትም ቢሆን መስጋቴ አልቀረም”

አጠቃላዩ መልዕክት በወቅቱ የማገገም አዝማሚያ ይታያል፤ ግን ቀውሱ አልተረታም የሚል ነው። እንግዲህ ከተጋነነ ተሥፋ መቆጠብ ያስፈልጋል። ይህን ከሚያስገነዝቡት መካከል ደግሞ የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም የ IMF ሃላፊ ዶሚኒክ-ሽትራውስ-ካህንም ይገኙበታል። ሽትራውስ-ካህን ሰሞኑን እንዳስረዱት በብዙዎች አዕምሮ፤ በቀደምት ፖለቲከኞች ሳይቀር ቀውሱ ያለፈ ነገር ሆኗል። ይህ አስተሳሰብ ደግሞ በጣም አደገኛ ነው። ባለሥልጣኑ እንዳስረዱት ችግሩ ገና ይቀጥላል። የፊናንሱ ቀውስ ያስከተለው የኤኮኖሚ ቀውስን ብቻ ሣይሆን ገና ከፍተኛ ደረጃ ላይ አይድረስ እንጂ ማሕበራዊ ቀውስንም ጭምር ነው።

መሥፍን መኮንን፣

ተክሌ የኋላ፣


ተዛማጅ ዘገባዎች