ዓለምአቀፍ ስፖርት | ስፖርት | DW | 25.03.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ዓለምአቀፍ ስፖርት

ያለፈው ሣምንት በመጪው 2014 ዓ-ም ብራዚል ውስጥ ለሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ለማለፍ ከአፍሪቃ እስከ ላቲን አሜሪካ በርካታ ማጣሪያ ግጥሚያዎች የተካሄዱበት ነበር።

በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ኢትዮጵያም የበኩሏን ፈተና በሚገባ ተወጥታለች። ይህን በዝርዝር እንገባበታለን፤ በቅድሚያ አውሮፓ ውስጥ በዘጠኝ ምድብ ተከፍሎ በሚካሄደው ማጣሪያ ላይ እናተኩርና ጀርመንን ወይም ኔዘርላንድን የመሳሰሉት ሃገራት እንደተጠበቀው በልዕልና መራመድ ሲቀጥሉ የዓለም ዋንጫ ባለቤቷ ስፓኝና እንግሊዝ በአንጻሩ መሃል መንገድ ላይ አስጊ ሁኔታ እየገጠማቸው ነው።

በምድብ-አንድ ቤልጂግና ክሮኤሺያ እኩል 13 ነጥቦች ይዘው ቀደምቱ ሲሆኑ የተቀሩትን ተፎካካሪዎቻቸውን በሰባት ነጥቦች ልዩነት በርቀት ያስከትላሉ። በምድብ-ሁለት ኢጣሊያ፣ በምድብ-ሶሥት ጀርመን፣ በምድብ-አራት ኔዘርላንድ የሚመሩ ሲሆኑ ስዊትዘርላንድ፣ ሩሢያ፣ ቦስና፣ ሞንቴኔግሮና ፈረንሣይም ቀደምት ናቸው። በምድብ-ዘጠኝ ውስጥ ስፓኝ በገዛ ሜዳዋ ከፊንላንድ 1-1 ስትለያይ በነገው ምሽት ከአንደኛዋ ከፈረንሣይ በምታደርገው ግጥሚያ ከተሸነፈች በአምሥት ነጥቦች በመበለጥ ትልቅ ችግር የሚገጥማት ነው የሚመስለው።

እንግሊዝም እንዲሁ ምድብ-ስምንት ውስጥ ባለፈው አርብ ምንም እንኳ ሣን-ማሪኖን 8-0 ብታሸንፍም ነገ በሁለት ነጥብ ከምትበልጣት ከሞንቴኔግሮ ጋር የምታደርገው ግጥሚያ ቀላል አይሆንም። ዕጣዋ የስፓኝን መሰል ነው። ፖርቱጋልም ወደ ብራዚል ለማምራት ገና ብዙ ስራ ይጠብቃታል። በወቅቱ በምድብ-ስድሥት ውስጥ ከሩሢያና ከእሥራኤል ቀጥላ ሶሥተኛ ስትሆን ነገ አዘርባይጃንን መርታቷ ግድ ነው።

ኢጣሊያ ምድብ-ሁለት ውስጥ ማልታን በማሸነፍ አንደኝነቷን ለማጠናከር ዕድል ሲኖራት ጀርመንም ነገ ካዛክስታንን ከረታች በምድብ-ሶሥት ውስጥ አመራሯን ወደ ስምንት ነጥቦች ልታሰፋ ትችላለች። ኔዘርላንድ በምድብ-አራት ከሩሜኒያ የምትጋጠም ሲሆን ከተሳካላት በስድሥት ግጥሚያዎች ለስድሥተኛ ድሏ ትበቃለች። አመራሯ የማያሻማ ነው። በምድብ-አንድ በአንጻሩ እኩል ሆነው የሚመሩት የቤልጂግና የክሮኤሺያ ፉክክር የጠበበ ሆኖ ይቀጥላል። ቤልጂግ ከማቄዶኒያ የምትገናኝ ሲሆን ክሮኤሺያ የምትገጥመው ደግሞ ከዌልስ ጋር ነው።

በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ማጣሪያ ኢትዮጵያ በምድብ-አንድ ትናንት አዲስ አበባ ላይ ቦትሱዋናን 1-0 ስትረታ አመራሩን መልሶ በመያዝ ዕድሏን እንደጠበቀች ቀጥላለች። የቦትሱዋና ብሄራዊ ቡድን ከጅምሩ ዘግቶ በመጫወቱ በአዳነ ግርማ ምትክ ተቀይሮ የገባው ጌታነህ ከበደ ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረው በ 88ኛዋ ደቂቃ ላይ ነበር። ኢትዮጵያ አሁን በሰባት ነጥቦች በአንደኝነት የምትመራ ሲሆን አንድ ቀን ቀደም ሲል ባለፈው ቅዳሜ ማዕከላዊት አፍሪቃ ሬፑብሊክን 2-0 ያሸነፈችው ደቡብ አፍሪቃ በአምሥት ነጥቦች ሁለተኛ ናት። ስለ ትናንቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጨዋታ፣ ስለ ቡድኑ አጠቃላይ ይዞታናና ስለ ውድድሩ ቀጣይ ሂደት ዋና አሠልጣኙን አቶ ሰውነት ቢሻውን ዛሬ በስልክ አነጋግሬ ነበር።

ከተቀሩት የአፍሪቃ ማጣሪያ ግጥሚያዎች ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል በምድብ-ሶሥት ታንዛኒያ ሞሮኮን 3-1 ስትረታ ይህም ለማግሬቧ አገር የስንብትን ያህል ነው። በምድብ-አራት ጋና ሱዳንን 4-0 ስታሸንፍ በዚሁ ምድብ ውስጥ ዛምቢያ ከሌሶቶ 1-1 ተለያይታለች። ይህ የኋለኛው ውጤት ምናልባት ማንም ያልጠበቀው ነው። በተቀረ ሞዛምቢክ ከጊኒ እንዲሁም ኮንጎ ከሊቢያ ባዶ-ለባዶ ሲለያዩ ላይቤሪያ ደግሞ ኡጋንዳን 2-0 ረትታለች።

በእሢያ ማጣሪያ የምድብ-አምሥት ግጥሚያዎች ፊሊፒንስ ካምቦጃን 8-0 ስትቀጣ ቱርክሜኒስታን ብሩናይን 3-0 አሸንፋለች። በደቡብ አሜሪካ ማጣሪያ ምድብ አርጄንቲና ቬኔዙዌላን 3-0 ስትረታ ኮሉምቢያም ቦሊቪያን 5-0 አሸንፋለች። ኮሉምቢያ በአሁን አያያዟ ከገፋች ከ 16 ዓመታት በኋላ እንደገና በዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ለመሳተፍ ጥሩ ዕድል ያላት ነው የሚመስለው። ኡሩጉዋይ በአንጻሩ ከፓራጉዋይ 1-1 በመለያየት ጠቃሚ ነጥቦችን አጥታለች።

ኤኩዋዶር ኤል-ሣልቫዶርን 5-0 ስታሸንፍ በምድቡ ውስጥ ከአርጄንቲናና ከኮሉምቢያ ቀጥላ ሶሥተኛ ናት። ኡሩጉዋይ አራተኛ፤ ቬኔዙዌላ አምሥተኛ! በደቡብ አሜሪካው ምድብ የመጀመሪያዎቹ አራት ሃገራት በቀጥታ ለብራዚሉ ፍጻሜ ውድድር የሚያልፉ ሲሆን አምሥተኛው ተጨማሪ ግጥሚያ ይጠብቃዋል። ብራዚል እንደ አዘጋጅ አገር በቀጥታ ስታልፍ የማጣሪያው ተሳታፊ አይደለችም።

በሰሜንና ማዕከላዊ አሜሪካ የኮንካካፍ ማጣሪያ ሜክሢኮ ከሆንዱራስ 2-2 ስትለያይ ዩ ኤስ አሜሪካ ኮስታ ሪካን 1-0 አሸንፋለች። በነገው ዕለት ፓናማ ሆንዱራስን የምታስተናግድ ሲሆን ጃማይካ የኮስታሪካ ተጋጣሚ ናት። በኦሺኒያ-ምድብ ደግሞ ኒውዚላንድ በስድሥት ነጥቦች ልዩነት በበላይነት ትመራለች።

በትናንትናው ዕለት በፖላንድ-ቢድጎሽች ተካሂዶ የነበረው የዓለም አገር አቋራጭ ሩጫ ውድድር አሸናፊዎች ኬንያውያን ሆነዋል። በወንዶች ጃፌት ኮሪር ኢማነ መርጋን አስከትሎ ሲያሸንፍ የኤርትራው ተወዳዳሪ ተክለ ማርያም መድህን ሶሥተኛ ወጥቷል። በሴቶች ደግሞ ኤሚሊይ ቼቤት ስታሸንፍ የኢትዮጵያ አትሌቶች በላይነሽ ኦልጂራና ሕይወት አያሌው ሁለተኛና ሶሥተኛ ሆነዋል።

በቡድን ድሉ በወንዶች የኢትዮጵያ ሲሆን በሴቶች የበላይ የሆኑት ኬንያውያት ናቸው። በወጣቶች ሃጎስ ገ/ሕይወት አሸናፊ ሲሆን በሴቶች ኬንያዊቱ ቼፕንጌቲች ኪፕየጎን ያለፈ ድሏን ደግማዋለች።

ትናንት በማሌይዚያ-ሤፓንግ ተካሂዶ የነበረው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል ሁለተኛ እሽቅድድም ጀርመናዊው የሬድ ቡል ዘዋሪ ዜባስቲያን ፌትል አሸናፊ ሆኗል። ፌትል እርግጥ ቢያሸንፍም ሁለተኛ የሆነውን የሬድ ቡል ዘዋሪ ቅድሚያ ማክበር ሲገባው አደገኛ በሆነ ሁኔታ ደርቦ ከግቡ መድረሱ በሰፊው አስወቅሶታል። ለማንኛውም የሜርሤደስ ዘዋሪዎች ሉዊስ ሃሚልተንና ኒኮ ሮስበርግ ሶሥተኛና አራተኛ ሲሆኑ የፌራሪው ፌሊፔ ማሣ በአምሥተኝነት ተወስኗል።

ፌራሪን ካነሣን ቀደምት ዘዋሪው ፌርናንዶ አሎንሶ ም በግጭት የተነሣ ገና በሁለተኛው ዙር ሲሰናበት ይህም ጠቃሚ ነጥቦችን እንዲያጣ ነው ያደረገው። ባለፈው ሣምንት በመጀመሪያው እሽቅድድም አሸንፎ የነበረው የፊንላንድ ተወላጅ ኪሚ ራይኮነን ሰባተኛ ሆኗል። በአጠቃላይ ነጥብ ፌትል በአርባ የሚመራ ሲሆን ራይኮነን በ 31 ሁለተኛ ነው፤ ዌበር በ 26 ይከተላል።

በተረፈ ባለፈው ሣምንት በታይዋን ተካሂዶ በነበረ ዓለምአቀፍ የቢስክሌት ውድድር የ 21 ዓመቱ ወጣት ኢትዮጵያዊ ጥጋቡ ግርማይ አኩሪ ውጤት ለማስመዝገብ በቅቷል። MTN-Qhubeka ለተሰኘው የደቡብ አፍሪቃ ቡድን የሚወዳደረው ወጣት በአንድ ደረጃ እሽቅድድም ሲያሸንፍና በጠቅላላ በሣምንቱ ውድድርም ሁለተኛ ሲወጣ ይህም አንድ ኢትዮጵያዊ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስመዘገበው ውጤት መሆኑ ነው። ታዛቢዎች ግርማይ የወደፊቱ ኮከብ ሊሆን እንደሚችል እየተናገሩ ነው።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic