ዓለምአቀፍ ስፖርት | ስፖርት | DW | 18.02.2013
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ዓለምአቀፍ ስፖርት

የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውድድር፤ የአፍሪቃ ሻምፒዮና ሊጋ፤ አትሌቲክስ

በእግር ኳስ እንጀምርና የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውድድር የዘንድሮ ግቡን ቀስ በቀስ በመቃረብ ላይ ሲሆን በአፍሪቃም ሰንበቱን የመጀመሪያዎቹ የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌደሬሺን የካፍ የክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ግጥሚያዎች ተካሄደዋል። የአፍሪቃ ዋንጫ አሸናፊዋ የናይጄሪያ ክለብ ካኖ-ፒላርስና የደቡብ አፍሪቃው ኦርላንዶ ፓይረትስ በየበኩላቸው ግጥሚያ በርካታ ጎሎችን ሲያስቆጥሩ ውድድሩ የጀመረው በግብ ፌስታ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ከአራት ዓመታት በፊት እስከ ግማሽ ፍጻሜ ደርሶ የነበረው የካኖው ክለብ የማዕከላዊት አፍሪቃ ሬፑብሊክ ተጋጣሚውን ኦሎምፒክ ሬያል ባንጉዊን 5-1 ሲቀጣ ኦርላንዶ ፓይረትስ ደግሞ ሶዌቶ ላይ የኮሞሮ ደሴቱን ተጠሪ ጃባልን 5-0 አሸንፏል። የዛምቢያው ዛናኮ የስዋዚላንዱን እምባባኔ ስዋሎውስን 3-2 ሲረታ የኢትዮጵያው ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ለዚያውም በውጭ ግጥሚያው የዛንዚባሩን ጃምሁሪን 3-0 ማሸነፉ ሆኖለታል።

የደቡብ አፍሪቃው የኢትዮጵያ የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ተሳትፎ በቅዱስ ጊዮርጊስ ከለብ ተጫዋቾች ዘንድም በራስ መተማመንን ይበልጥ ሳያጠናክር የቀረ አይመስልም። የሰንበቱ 3-0 ውጤት ቢቀር ለተከታዩ ዙር ለመድረስ የሚያበቃ ነው። ከዚሁ ሌላ በአፍሪቃ ሻምፒዮና ሊጋ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሳተፈው የሞሮኮው ክለብ ማግሬብ ቴቶዋን የሴኔጋል ተጋጣሚውን ካዛ ስፖርትን 1-0 ሲሸኝ የኬንያው ታስከር ደግሞ የሴይሽልሱን ሚሼል ዩናይትድን 4-1 አሸንፏል። የአንጎላው ፕሬሚየሮ አጎስቶም እንዲሁ ሉዋንዳ ላይ ባካሄደው ግጥሚያ ማላጋሲን 4-2 ረትቶ ነው ያሰናበተው።

በአውሮፓ ሊጋዎች ሻምፒዮና ባርሤሎናና ባየርን ሙንሺን የበላይነታቸውን እንዳስረገጡ ሲቀጥሉ በፈረንሣይ በአንጻሩ ቀደምቱ ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን ከዘጠኝ ድሎች በኋላ ሰንበቱን በሽንፈት ማሳለፉ ግድ ሆኖበታል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሣምንቱ የፌደሬሺኑ ዋንጫ የ FA Cup አምሥተኛ ዙር ግጥሚያዎች የተካሄዱበት ነበር። በዚሁ ውድድርም በተለይ አርሰናል ለዚያውም በገዛ ሜዳው በሁለተኛው ዲቪዚዮን ክለብ በብላክበርን ሮቨርስ 1-0 ተሸንፎ ሲሰናከል ይህ ውጤት ማንም የጠበቀው አልነበረም። ሽንፈቱ አርሰናል ከስምንት ዓመታት ወዲህ እንደገና የመጀመሪያ ዋንጫውን እንዲያገኝ የነበረውን ቀሪ ዕድል ከንቱ ነው ያደረገው።

በተቀሩት ግጥሚያዎች ያለፈው ውድድር ወቅት የፌደሬሺን ዋንጫ ባለቤት ቼልሢይ ከብሬንትፎርድ 4-0፤ ኢልድሃም አትሌቲክ ከኤቨርተን 2-2፤ ማንቼስተር ሢቲይ ከሊድስ ዩናይትድ 4-0 ሲለያዩ ማንቼስተር ዩናይትድ ደግሞ ዛሬ ማምሻውን ከሪዲንግ ይጋጠማል። ቼልሢይና ማንቼስተር ዩናይትድ አምሥተኛ ዙር ግጥሚያቸውን ካሸነፉ በሩብ ፍጻሜው እርስበርስ ሊገናኙ ይችላሉ። ይህም ብዙዎች የቀደምቱ ክለቦች ደጋፊዎች በተለየ ጉጉት የሚጠብቁት ነገር ነው። ሩብ ፍጻሜው ግጥሚያዎች በመጋቢት ወር መጀመሪያ ሣምንት ውስጥ ይካሄዳሉ።

ወደ መደበኛው የአውሮፓ ሊጋዎች ውድድር እንሻገርና ቀደምቱ ባርሤሎና ባለፈው ሰንበትም ግራናዳን 2-1 በማሸነፍ የ 12 ነጥቦች አመራሩን አስከብሯል። ጎሎቹን ያለፉት ዓመታት የዓለም ድንቅ ተጫዋች ሊዮኔል ሜሢ ሲያስቆጥር ለባርሣ ያገባቸው ጎሎች በጠቅላላው ከ 300 ማለፋቸው ነው። ሁለተኛው አትሌቲኮ ማድሪድም ሬያል ቫላዶሊድን 3-0 ሲረታ ሬያል ማድሪድ ደግሞ ራዮ ቫሌካኖን 2-0 አሸንፎ በሶሥተኝነቱ ቀጥሏል። ማላጋ አራተኛ፤ ቫሌንሢያ አምሥተኛ!

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ባየርን ሙንሺን ቮልፍስቡርግን 2-0 ሲረታ በፍጹም የበላይነት ሻምፒዮንነቱን በመውሰድ አቅጣጫ ለብቻው እያመራ ነው። በ 15 ነጥቦች ልዩነት ይመራል። ሁለተኛው ቦሪሢያ ዶርትሙንድም ፍራንክፉርትን 3-0 ለማሸነፍ በቅቷል። ሶሥቱንም ጎሎች ያስቆጠረው የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ማርኮ ሮይስ ነበር። ባየር ሌቨርኩዝን ደግሞ ከዶርትሙንድ በአንዲት ነጥብ ዝቅ ብሎ ሶሥተኛ ሲሆን ፍራንክፉርት አራተኛ ነው።

በፈረንሣይ ሻምፒዮና ከ 19 ዓመታት ወዲህ እንደገና የዋንጫ ባለቤት ለመሆን በሚያበቃ አቅጣጫ ሲገሰግስ የቆየው ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን ከዘጠኝ ድሎች በኋላ ሰንበቱን የመጀመሪያው ሽንፈት ገጥሞታል። ክለቡ ምንም እንኳ አመራሩን ባይለቅም ሽንፈቱ ከሁለተኛው ከኦላምፒክ ሊዮን ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ ሶሥት እንዲጠብ ነው ያደረገው። ፓሪስ አሁን በ 51 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ሊዮን በ 48 እንዲሁም ማርሤይ በ 42 የቅርብ ተፎካካሪዎቹ ናቸው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ቀደምቱ ጁቬንቱስ በሮማ 1-0 ሲረታ ሁለተኛው ናፖሊ በበኩሉ ግጥሚያ ከሣምፕዶሪያ በእኩል ለእኩል በመወሰን አመራሩን ለመቃረብ የነበረውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጁቬንቱስ ቢሸነፍም ቅሉ ሊጋውን በአራት ነጥቦች ልዩነት መምራቱን እንደቀጠለ ነው። በወቅቱ በጠቅላላው 55 ነጥቦች አሉት። ኤ ሲ ሚላን ፓርማን 2-1 አሸንፎ በ 44 ነጥቦች ሶሥተኛ ሲሆን በተመሳሳይ ነጥብ አረተኛው ላሢዮ ዛሬ ማምሻውን ከሢየና ቀሪ ግጥሚያ ይኖረዋል።

በተረፈ በፖርቱጋል ሻምፒዮና ፖርቶና ቤንፊካ እኩል 49 ነጥቦች ይዘው በጦፈ ፉክክራቸው እንደቀጠሉ ነው። ባለፈው ሰንበት የፖርቱጋል ሊጋ 19ኛ ግጥሚያ ቤንፊካ አካዴሚካን 1-0 ሲረታ ፖርቶም ባያራን 2-0 አሸንፏል። 14 ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሶሥተኛው ፓኮስ-ዴ-ፌሬኢራ ነው። በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮን ደግሞ አይንድሆፈን ኡትሬኽትን 2-1 በማሸነፍ በሶሥት ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ቀጥሏል። አያክስ አምስተርዳም ቫልቫይክን 2-0 በመርታት ሁለተኛ ሲሆን ትዌንቴ ኤንሼዴ በ 1-1 ና ፋየኖርድም በ 3-2 ሽንፈት በየፊናቸው ጠቃሚ ነጥቦችን አጥተዋል።

ባለፈው ቅዳሜ በርሚንግሃም ላይ ተካሂዶ በነበረው የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር የአዳራሽ ውስጥ ውድድር ከሶማሊያ የመነጨው እንግሊዛዊ ሞ ፋራህ በ 3 ሺህ ሜትር ሩጫ በማሸነፍ አገሬውን ተመልካች እጅጉን አስደስቷል። የ 29 ዓመቱ ፋራህ በለንደኑ ኦሎምፒክ የአምሥትና አሥር ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ሞ በዚህ ዓመት ግማሽ ማራቶን በመሮጥ ከተለማመደ በኋላ በሚቀጥለው 2014 ዓ-ም ሙሉ ማራቶን ለመሮጥ ማሰቡን አስታውቋል። እንደ አሠልጣኙ እንደ አልቤርቶ ሣላዛር ከሆነ ደግሞ የእንግሊዙ ኮከብ ከሶሥት ዓመታት በኋላ ብራዚል ውስጥ በሚካሄደው የኦሎምፒክ ጨዋታ በ 42ቱ ኪሎሜትር ሩጫ ለመወዳደር የሚበቃ ነው።

በበርሚንግሃሙ የአዳራሽ ውስጥ ውድድር በ1,500 ሜትር በወንዶች የሞሮኮው አብዳላቲ ኢጉደር ሲያሸንፍ በሴቶች ደግሞ ገንዘቤ ዲባባ ቀዳሚዋ ኮከብ ሆናለች። በአጭር ርቀት ሩጫ፣ዝላይና ውርወራ በአብዛኛው የአሜሪካና የብሪታኒያ አትሌቶች ጠንክረው ታይተዋል።

የሞ ፋራህን የማራቶን ሕልም ካነሣን ለንደን ላይ በፊታችን ሚያዚያ ወር በሚካሄደው የማራቶን ውድድር አዲስ ክብረ-ወሰን የመመዝገቡ ዕድል ከፍተኛ መሆኑ ተነግሯል። ይህን የሚለው ያለፈው 2012 አሸናፊ ኬንያዊው ዊልሰን ኪፕሣንግ ሲሆን ለዚህም እንደ ምክንያት የጠቀሰው የተሳታፊዎቹን አትሌቶች ጥንካሬ ነው። አሥር ቢቀር ከሁለት ሰዓት ከአምሥት ደቂቃ በታች መሮጥ የሚችሉ አትሌቶች በውድድሩ እንደሚካፈሉ ነው የሚጠበቀው።

ከኬንያ ከኪፕሣንግ ሌላ የዓለም ሻምፒዮኑ አቤል ኪሩዊ፣ የበርሊን ማራቶን ባለድል ጆፍሪይ ማታይና የሶሥት ጊዜው የለንደን አሸናፊ ማርቲን ሌል፤ እንዲሁም የኡጋንዳው የለንደን ማራቶን አሸናፊ ስቴፈን ኪፕሮቲች፣ ከኢትዮጵያም እንዲሁ ጸጋዬ ከበደ፣ አየለ አብሸሮና ፈይሣ ሊሊሣ በዕውነትም ብዙ የሚጠበቅባቸው ናቸው። ለማንኛውም ሁሉም በጊዜው የሚታይ ይሆናል።

ከዚህ ሌላ ሰንበቱን ኬንያ ውስጥ በተካሄደ ብሄራዊ የአገር አቋራጭ ሩጫ ውድድር በወንዶች 12 ኪሎሜትር ፊልሞን ሮኖ ሲያሸንፍ ቲሞቲይ ኪፕቱ ሁለተኛ፤ እንዲሁም ጆፍሪይ ኪሩዊ ሶሥተኛ ሆኗል። በሴቶች ደግሞ ማርግሬት ዋንጋሬ አንደኛ ስትሆን ኢሬነ ቼፕታይና ጃኔት ኪሻ ተከትለዋት ከግብ ደርሰዋል። ኬንያን ካነሣን አትሌቶቿ ሕገ-ወጥ አካል አጎልባች መድሃኒቶችን እንደሚወስዱ ባለፈው ሣምንት መገለጹ በጉዳዩ ላይ እንደገና ውይይት መቀስቀሱ አልቀረም።

ሕግ መጣሱን የተናገረው ደግሞ የሩቅ ሰው ሣይሆን የቀድሞው የአገሪቱ የሶሥት ጊዜ የ 3 ሺህ ሜትር መሰናክል ሩጫ የዓለም ሻምፒዮን ሞሰስ ኪፕታኑዊ ነው። የአንዴው ግሩም ሯጭ የሚናገረውን በትክክል ያውቃል። ድርጊቱ በየልምምድ ካምፑ የተለመደ መሆኑን ነው ያመለከተው። ኪፕታኑዊ የአፍሪቃ አትሌቶች በታላላቅ ውድድሮች ጠንክሮ ለመገኘት መድሃኒቱን እንደሚወስዱ ሲጠቅስ ለዚህም የአንዳንድ የኬንያ አትሌቶች ብቃት ተቀያያሪነት ጭብጥ መረጃ ነው ባይ ነው።

ዛሬ ፈጣን ነገ ደካማ! በዕውነትም ጉዳዩ ብዙ ያነጋግራል። በነገራችን ላይ የጀርመን ቴሌቪዥን በለንደኑ ኦሎምፒክ ዋዜማ የኬንያ አትሌቶች በረቀቀ ዘዴ አጎልባች መድሃኒት እንደሚወስዱ ለማጋለጥ መሞከሩ አይዘነጋም። ይሁንና የኬንያ ባለሥልጣናት በጊዜው አባባሉን አስተባብለው ነበር። የኢትዮጵያ አትሌቶች ስም ከዚህ ሁሉ ጉድ የጠራ ሆኖ እንዲቀጥል ተሥፋችን ነው።

በሣምንቱ አሳዛኝና ከሁሉም በላይ አስደንጋጭ ሆኖ ያለፈው ከስፖርት ጋር የተያያዘ ዜና እርግጥ የደቡብ አፍሪቃዊው አካለ-ስንኩል አትሌት የኦስካር ፒስቶሪዩስ ሴት ጓደኛውን ተኩሶ በመግደል መጠርጠርና መታሰር ነው። አትሌቱ ክሱን ሲያተባብል ከወንጀል ምርመራው እሥራት በዋስትና ይለቀቅ አይለቀቅ የሚለየው ምናልባት በነገው ዕለት ነው።

ሁኔታው የደቡብ አፍሪቃን ሕብረተሰብ ለሁለት ሲከፍል ግለሰቡን አስመልክቶ ከዚህ ቀደም የነበሩ አንዳንድ አጋጣሚዎች ጥርጣሬው እንዲጠነክር ማድረጋቸው አልቀረም። የለንደኑ ኦሎምፒክ ተሳታፊ ፒስቶሪዩስ ንጹህ ሆኖ ካልተገኘ እስካሁን ያገኘው ክብርና ዝና ሁሉ እንዳልነበረ ሆኖ መቅረቱ ነው። ወኪሎቹ ለማንኛውም ለወደፊት የታቀዱ ውድድሮችን መሰረዛቸውን አስታውቀዋል።

በተቀረ በዚህ ሣምንት ነገና ከነገ በስቲያ የአውሮፓ እግር ኳስ ሻምፒዮና ሊጋ የጥሎ ማለፍ ዙር የመጀመሪያ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። በስታዲዮሞች ተገኝቶም ሆነ በቴሌቪዥን አማካይነት ውድድሩን ለመከታተል ለሚሹ የኳስ አፍቃሪዎች ደግሞ በዕውነትም የሚማርኩ ታላላቅ ጨዋታዎች አይታጡም። በነገው ምሽት ሁለቱ የአይቤሪያ ክለቦች ፖርቶና ማላጋ የሚጫወቱ ሲሆን እርግጥ በአያሌ ተመልካች በጉጉት የሚጠበቀው ግን የአርሰናልና የባየርን ሙንሺን ግጥሚያ ነው። በማግሥቱም ኤ ሲ ሚላን ከባርሤሎና የዚያኑ ያህል በጉጉት ይጠበቃል።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 18.02.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17gVl
 • ቀን 18.02.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17gVl