ዓለምአቀፍ ስፖርት | ስፖርት | DW | 14.05.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ዓለምአቀፍ ስፖርት

የአውሮፓ እግር ኳስ ሊጋዎች ውድድር ከሞላ ጎደል ሲጠናቀቅ የየአገሩ ብሄራዊ ቡድኖች በኡክራኒያና በፖላንድ የጋራ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ለመጪው ወር የአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ የመጨረሻ ዝግጅት እየጀመሩ ነው። የአውሮፓ እግር ኳስ ሊጋዎች ውድድር

የአውሮፓ እግር ኳስ ሊጋዎች ውድድር ከሞላ ጎደል ሲጠናቀቅ የየአገሩ ብሄራዊ ቡድኖች በኡክራኒያና በፖላንድ የጋራ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ለመጪው ወር የአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ የመጨረሻ ዝግጅት እየጀመሩ ነው። የአውሮፓ እግር ኳስ ሊጋዎች ውድድር ከሞላ ጎደል ሲጠናቀቅ የየአገሩ ብሄራዊ ቡድኖች በኡክራኒያና በፖላንድ የጋራ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ለመጪው ወር የአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ የመጨረሻ ዝግጅት እየጀመሩ ነው። ከታላላቆቹ ሊጋዎች መካከል የጀርመንም ሆነ የስፓኝ ሻምፒዮና ቀደም ብሎ ሲጠቃለል የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አንደኛ ማንነት የለየለት ግን ትናንት በመጨረሻው ግጥሚያ ነበር።

የሁለቱ የማንቼስተር ክለቦች ፉክክር መለያው ሆኖ የቆየው የፕሬሚየር ሊጉ ውድድር ዘንድሮ በማንቼስተር ሢቲይ የበላይነት ተፈጽሟል። ማንቼስተር ሢቲይና ማንቼስተር የናይትድ ውድድሩን በእኩል 89 ነጥብ ሲፈጽሙ ሢቲይ ሻምፒዮን ሊሆን የበቃው በጎል ብልጫ ብቻ ነው። ዩናይትድ በትናንት ግጥሚያው ሰንደርላንድን 1-0 በማሸነፉ ሢቲይ ድሉን ለማረጋገጥ እስከመጨረሻው መታገል ነበረበት።

የሆነው ሆኖ ቡድኑ በማለቂያ ሰዓት ላይ ሁለት ወሣኝ ጎሎችን በማስቆጠር ኩዊንስ ፓርክ ሬንጀርስን 3-2 ሲሸኝ ከ 44 ዓመታት ቆይታ በኋላ የእንግሊዝ ሻምፒዮን ሊሆን በቅቷል። ውሣኞቹን ጎሎች ያስቆጠሩት የቦስናው ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ኤዲን ጄኮና ሴርጂዮ አጉዌሮ ነበሩ። በስፓኝ ፕሬሜራ ዲቪዚዮን ወይም በጀርመን ቡንደስሊጋ እንደታየው ሁሉ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግም ሻምፒዮናው የለየለት በሁለት ክለቦች መካከል ነው።

ሶሥተኛው አርሰናል ከሁለቱ ቀደምት ክለቦች በ 19 ነጥቦች ዝቅ ብሎ ውድድሩን ሲያጠቃልል በሶሥተኛነት ለመጨው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ተሳትፎ መድረሱ ተሳክቶለታል። አርሰናል ሶሥተኝነቱን ያረጋገጠው አልቢዮንን 3-2 ከረታ በኋላ ነበር። ቶተንሃም ሆትስፐር ደግሞ ፉልሃምን 2-0 በማሸነፍ አራተኛ ሲወጣ ለአውሮፓው ሻምፒዮና ሊጋ የመድረስ ዕድል አለው።

እርግጥ ቼልሢይ በፊታችን ቅዳሜ በሚካሄደው በዘንድሮው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ፍጻሜ ግጥሚያ ባየርን ሙንሺንን ካሸነፈ ቦታው ለርሱ የተያዘ ነው የሚሆነው። በነገራችን ላይ ቼልሢይ የፕሬሚየር ሊጉን ውድድር የፈጸመው በስድሥተኝነት ነው። በተቀረ ቦልተን ወንደረርስ፣ ብላክበርን ሮቨርስና ዎልበርሃምፕተን ወንደረርስ ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን ተከልሰዋል።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ ውድድሩ ከሣምንት በፊት በሬያል ማድሪድ ሻምፒዮንነት ቢለይለትም የትናንቱ ማጠቃለያ ዕለት ግጥሚያዎችም ትልቅ ፉክክር የሰፈነባቸው ነበሩ። በፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ ውድድር ዘንድሮ አስደናቂ ሆነው ከታዩት አነስተኛ ክለቦች መካከል ማላጋ የአውሮፓ ሊጋውን ትኩስ የዋንጫ ባለቤት አትሌቲኮ ማድሪድን ከኋላው አስቀርቶ አራተኛ በመሆን ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ተሳትፎ በቅቷል። ማላጋ አራተኛነቱን ያረጋገጠው ትናንት ጊዮንን 1-0 ከረታ በኋላ ነበር።

ሌላው መለስተኛ ክለብ ሌቫንቴም እንዲሁ ቢልባዎን 3-0 ሲረታ የመጨው የአውሮፓ ሊግ ውድድር ተሳታፊ ነው። በጣሙን የሚያሳዝነው ባለፈው ውድድር ወቅት አራተኛ የነበረው ቪላርሬያል ዘንድሮ 18ኛ በመሆን ከፕሬሚየር ሊጉ ማቆልቆሉ ነው። ከቪላርሬያል ሌላ ስፖርቲንግ ጊዮንና ሣናታንዴርም ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን ተከልሰዋል። በነገራችን ላይ ሻምፒዮኑ ሬያል ማድሪድ በውድድሩ 100 ነጥቦችና 121 ጎሎችን በማስቆጠር የሊጋ ክብረ-ወሰን ማስመዝገቡም ሳይጠቅስ ሊታለፍ አይገባውም።

የጀርመን ፌደሬሺን ዋንጫ

በዚህ በጀርመን የቡንደስሊጋው ውድድር ከሣምንት በፊት ሲጠቃለል ያለፈው ሰንበት የፌደሬሺኑ ዋንጫ ፍጻሜ የተካሄደበት ነበር። በርሊን ላይ በተካሄደው የፍጻሜ ግጥሚያ የዘንድሮው የቡንደስሊጋ ሻምፒዮን ቦሩሢያ ዶርትሙንድና የቅርብ ተፎካካሪው ባየርን ሙንሺን ሲጋጠሙ በተከታታይ ለ 27 ጨዋታዎች መሸነፍን የረሳው ዶርትሙንድ 5-2 በሆነ ከፍተኛ ውጤት በመርታት ድሉን ድርብ ሊያደርግ በቅቷል። ዶርትሙንድ ባየርንን ባለፉት አምሥት ግጥሚያዎቹ በሙሉ ሲያሸንፍ እንዳለፈው ቅዳሜ ምሽት ግን ልዕልናው እጅግ ጎልቶ የታየበት ጊዜ የለም።

ክለቡ የጀርመኑን እግር ኳስ ፌደሬሺን ዋንጫ ሲያገኝ ለሶሥተኛ ጊዜ ሲሆን በአንድ የውድድር ወቅት ለድርብ ድል ሲበቃ ደግሞ በክለቡ የ 103 ዓመታት ሕልውና ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። የጀርመኑን ሬኮርድ ሻምፒዮን ባየርንን ረትቶ ዋንጫ ማግኘት እንዲያው ቀላል ነገር አይደለም። በመሆኑም ዶርትሙንድ አምሥት ጎሎች ማስቆጠሩ ጨርሶ የተጠበቀ አልነበረም። የቡድኑ አምበል ዜባስቲያን ኬህል እንዲህም ሆኖ ድሉ በቀላል የተገኘ እንዳልሆነ ነው የተናገረው።

«ባየርን እጅግ በጣም ጠንካራ ቡድን ነው። እናም ዛሬ ለማሸነፍ በእርግጥ መጣር ነበረብን። ሆኖም ግን በዘንድሮው የውድድር ወቅት በሚገባ ሻምፒዮንና የፌደሬሺኑም ዋንጫ አሸናፊ ለመሆን ችለናል ብዬ ነው የማስበው። ሁሌም ጠንካሮቹ ነበርን። ዓመቱ በሙሉ ሊገልጹት በሚያዳግት ሁኔታ ግሩም ሆኖ ሲያልፍ የዛሬው ደግሞ ዘውድ የመጫንን ያህል ነው»

ይህ በዕውነትም የተጋነነ አስተያየት አይደለም። 76 ሺህ ተመልካች በተገኘበት የበርሊን ኦሎምፒያ ስታዲዮም ለዶርትሙንድ ጎሎቹን ጃፓናዊው ሺንጂ ካጋዋ፣ ማትስ ሁምልስና ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ ሲያስቆጥሩ ለባየርን ሁለቱን ጎሎች ያስገቡት ደግሞ አርየን ሮበንና ፍራንክ ሪቤሪይ ነበሩ። በተለይ የዕለቱ ኮከብ ግን ሶሥት ጎሎች ያስቆጠረው የፖላንድ ብሄራዊ ቡድን አጥቂ ሌቫንዶቭስኪ ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። የባየርንን ተከላካዮች መሳለቂያ ነው ያደረጋቸው። ይሄው የመከላከል ድክመት ለቡድኑ መቅሰፍት እንደሆነም አሰልጣኙ ዩፕ ሃይንከስ ራሱ በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጧል።

«በመከላከል ረገድ ተገቢው ትኩርት እንዳልነበረን የታየው ገና ከሶሥተኛው ደቂቃ ጀምሮ ነው። ለተጋጣሚያችን ብዙ ሽልማት አድርገናል። በአጠቃላይ የመከላከል አጨዋወታችን በጣሙን አስከፊ ነበር»

ባየርን ሙንሺን ዘንድሮ የቡንደስሊጋውንና የፌደሬሺኑን ዋንጫ ውድድር በሁለተኝነት ፈጽሟል። ሆኖም በፊታችን ቅዳሜ ሚዩኒክ ላይ ቼልሢይን በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ፍጻሜ ግጥሚያ የሚያስተናግድ ሲሆን ባዶ ዕጁን እንዳይቀር አንድ ተልቅ የመጨረሻ ዕድል ይቀረዋል። ጥያቄው ለዚህ ከባድ ግጥሚያ የተጫዋቾቹን መንፈስ ለማደስ ቀሪው ጊዜ ይበቃል ወይ ነው።

በሌላ በኩል ባየርን ሙንሺን በሴቶች ለመጀመሪያ ጊዜ የፌደሬሺኑ ዋንጫ አሸናፊ ለመሆን በቅቷል። የባየርን ሴቶች ባለፈው ቅዳሜ ኮሎኝ ከተማ ውስጥ በተካሄደው ፍጻሜ ግጥሚያ የቀድሞውን የዋንጫ ባለቤት የፍራንክፉርትን ቡድን 2-0 ሲረቱ ይህም ያለሙት አልነበረም። በመሆኑም እንደ በረኛዋ እንደ ካትሪን ሌንገርት ሁሉ የተጫዋቾቹ ደስታ ወሰን ያለፈ ሆኖ ታይቷል። በተቀረ በፈረንሣይ ሊጋ ሞንትፔሊየር አንድ ግጥሚያ ቀርቶ ሳለ በሶሥት ነጥቦች ብልጫ በመምራት ለሻምፒዮንነት ተቃርቧል።

አትሌቲክስ

ባለፈው አርብ ምሽት ዶሃ ላይ ተካሂዶ በነበረው የአትሌቲክስ ዳያመንድ ሊግ ውድድር በወንዶች መቶ ሜትር አሜሪካዊው ጀስቲን ጋቲን የጃማይካ ተፎካካሪዎቹን አሳፋ ፓውልንና ሌሮን ክላርክን ከኋላው በማስቀረት ግሩም በሆነ 9,87 ሤኮንድ ጊዜ አሸናፊ ሆኗል። የአሜሪካ አትሌቶች በአጭር ርቀቱ ሩጫ አይለው ሲታዩ በሁለት መቶ ሜትር ዋልተር ዲክስ፤ እንዲሁም በአራት መቶ ሜትር ላሻውን ሜሪት ግንባር ቀደም ሆነዋል። በስምንት መቶ ሜትር ኬንያውያኑ ዴቪድ ሩዲሻና ጆብ ኪኞር በቀዳሚነት ተከታትለው ከግባቸው ሲደርሱ የኬንያ አትሌቶች በመካከለኛ ርቀትም የሚበገሩ አልነበሩም። መኮንን ገ/መድህን በዚሁ ሩጫ ሰባተኛ ወጥቷል።

በሶሥት ሺህ ሜትር አውጉስቲን ቾጌና ኤሊዩድ ኪፕቾጌ ሲያሸንፉ ሩጫውን በሶሥተንነት የፈጸመው የኡጋንዳው ሞሰስ ኪፕሢሮ ነበር። ከኢትዮጵያ ቀነኒሣ በቀለ ሰባተኛ፤ እንዲሁም አበራ ኩማ ስምንተኛ ሆነዋል። በሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክልም ኬንያውያኑ ፓውል ኮችና ሪቻርድ ማቴሎንግ ሲቀድሙ የኢትዮጵያው ጋሪ ሮባ ሶሥተኛ ወጥቷል። በተቀረ ሩጫው ከአንድ እስከ ስምንት ኬንያውያን የተቆጣጠሩት ነበር። በ 1,500 ሜትርም ቢሆን ኬንያውያን ከአንድ እስከ ሶሥት በመከታተል ለድል በቅተዋል።

በሴቶች መቶ ሜትር አሜሪካዊቱ አሊሰን ፌሊክስ ስታሸንፍ በስምንት መቶ ሜትር ኬንያዊቱ ፓሜላ ጀሊሞ ፋንቱ ማጊሶን ቀድማ ከግቧ ደርሳለች። በሶሥት ሺህ ሜትርም ኬንያዊቱ ቪቪያን ቼሩዮት ስታሸንፍ መሠረት ደፋር ደግሞ ሁለተኛ ሆናለች። ገለቴ ቡርቃ አራተኛ! የጃማይካ ሴቶች ብሪጂት ፎስተርና ሜላኒ ወከር ደግሞ በመቶ ሜትር መሰናክልና በአራት መቶ ሜትር አሸናፊዎቹ ነበሩ።

ከዚሁ ሌላ በትናንትናው ዕለት ቼክ-ሬፑብሊክ ውስጥ በተካሄደ የፕራግ ማራቶን ሩጫ በወንዶች የኢትዮጵያው አትሌት ደሬሣ ጪምሣ አሸናፊ ሆኗል። ደሬሣ ሩጫውን በሁለት ሰዓት ከስድሥት ደቂቃ 25 ሤኮንድ ጊዜ ሲፈጽም ከሁለት እስከ አምሥት ተከትለውት የገቡት በሙሉ ኬንያውያን ነበሩ። በሴቶች ኬንያውያኑ አግነስ ኪፕሮፕና ፍሎሜና ቼፕቺርቺር መሠረት ደበሌን በሶሥተኝነት በማስከተል አሸንፈዋል። አልጄሪያዊቱ ሣቫድ ሣሌም አራተኛ ስትወጣ ምስክር መኮንን ደግሞ ሩጫውን በአምሥተኝነት ፈጽማለች።

Flash-Galerie Australian Open Serena Williams Tennis

ቴኒስ

በትናንትናው ዕለት ስፓኝ ውስጥ በተጠናቀቀው የማድሪድ ማስተርስ ውድድር አንጋፎቹ ሮጀር ፌደረርና ሴሬና ዊሊያምስ የየበኩላቸውን ግጥሚያ በግሩም ጨዋታ በማሸነፍ ለቅጣዩ የፈረንሣይ ኦፕን በጥሩ ይዞታ ላይ እንደሚገኙ አስመስክረዋል። የስዊሱ ተወላጅ ሮጀር ፌደረር የቼኩን ቶማስ ብርዳሪችን በሶሥት ምድብ ጨዋታ ሲያሸንፍ በዚሁ ድሉ በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ የስፓኙን ራፋኤል ናዳልን ከሁለተኛው ቦታ ለመፈንቀልም በቅቷል።

ለፌደረር የትናንቱ ድል 74ኛው የውድድር ድል ሲሆን በማድሪድ ድሉ የተለየ ደስታ የተሰማው መሆኑን ነው የተናገረው። በሴቶች አሜሪካዊቱ ሴሬና ዊሊያምስ ደግሞ የዓለም አንደኛዋን የቤላሩሷን ቪክቶሪያ አዛሬንካን በለየለት 6-1, 6-3 ውጤት በማሸነፍ እንደገና በማየል ላይ መሆኗን አስመስክራለቸ።

በፎርሙላ-አንድ ለማጠቃለል ትናንት ስፓኝ ውስጥ ተካሂዶ በነበረው እሽቅድድም በዙም የማይታወቀው የቬኔዙዌላ ዘዋሪ ፓስቶር ማልዶናዶ በማሸነፍ ታዛቢዎችን እጅጉን አስደንቋል። የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶ ሁለተኛ ሲወጣ እሽቅድድሙን በሶሥተናነት የፈጸመው የፊንላንዱ ኪሚ ራይኮነን ነበር። ያለፉት ሁለት ዓመታት ሻምፒዮን ጀርመናዊው ዜባስቲያን ፌትል ደግሞ በስድሥተኛነት ተወስኗል። በአጠቃላይ ነጥብ ፌትልና አሎንሶ እያንዳንዳቸው 61 ነጥብ ይዘው ይመራሉ።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 14.05.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14vCj
 • ቀን 14.05.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14vCj