ዓለምአቀፍ ስፖርት | ስፖርት | DW | 05.03.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ዓለምአቀፍ ስፖርት

ያለፈው ሣምንት ዓለምአቀፍ የእግር ኳስ የወዳጅነት ግጥሚያዎች የተካሄዱበትም ነበር። የአውሮፓ ሊጋዎች የእግር ኳስ ሻምፒዮና በመልስ ዙሩ ይበልጥ አጓጊ እየሆነ ሲቀጥል በአትሌቲኩ መስክም የለንደን ኦሎምፒክ መቃረብ በተለያዩ ስፖርተኞች ዘንድ ለተሳትፎ ለመብቃት የሚደረገውን

ያለፈው ሣምንት ዓለምአቀፍ የእግር ኳስ የወዳጅነት ግጥሚያዎች የተካሄዱበትም ነበር። የአውሮፓ ሊጋዎች የእግር ኳስ ሻምፒዮና በመልስ ዙሩ ይበልጥ አጓጊ እየሆነ ሲቀጥል በአትሌቲኩ መስክም የለንደን ኦሎምፒክ መቃረብ በተለያዩ ስፖርተኞች ዘንድ ለተሳትፎ ለመብቃት የሚደረገውን

ፉክክር እያጠነከረ ነው። ያለፈው ሣምንት በአጋማሹ በርካታ የእግር ኳስ የወዳጅነት ግጥሚያዎችም የተካሄዱበት ነበር። ግጥሚያዎቹ ከሞላ-ጎደል በሚሉ በዚህ በአውሮፓ ሲደረጉ ሶሥት ወራት ገደማ የቀሩት ኡክራኒያና ፖላንድ በጋራ የሚያስተናግዱት የአውሮፓ ሻምፒዮና ፍጻሜ ውድድር በሚካሄድበት ዓመት ለአንዳንዶቹ የአቅም መፈተሻ መሆኑም አልቀረም። በተለይ ተለቅ ያለ የዋንጫ ባለቤትነት ዕድል የሚስጣቸው ጀርመን ከፈረንሣይ፤ እንግሊዝ ከኔዘርላንድ ወይም ስፓኝ ከቬኔዙዌላ ያካሄዷቸው ግጥሚያዎች በብዙዎች በጉጉት ነበር የተጠበቁት።

የጀርመን ብሄራዊ ቡድን በአገሩ ብሬመን ላይ በፈረንሣይ 2-1 ሲረታ ውጤቱ ለብዙዎች ያልተጠበቀና ያልታለመ ነው የሆነው። የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ቀደም ባሉ የወዳጅነት ግጥሚያዎች ብራዚልን፣ አርጄንቲናንና ኔዘርላንድን ካሸንፈ በኋላ በፈረንሣይ ይደፈራል ብሎ ያሰበ ብዙ አልነበረም። ታዲያ ወጤቱ ባለፉት ዓመታት አቆልቋይ እየሆነ ለመጣው ለፈረነሣይ ብሄራዊ ቡድን የልብ ሙላት የሚሰጥ እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም። ለጀርመን በአንጻሩ ሽንፈቱ በአውሮፓው ሻምፒዮና ዓመት የድክመት ምልክት እንዳይሆን ቢያሰጋም አሰልጣኙ ዮአሂም ሉቭ ግን በበኩሉ ያን ያህል ክብደት አልሰጠውም። ጉድለቱን ማሟላት ይቻላል ባይ ነው።

«ይሄ ከአንድ ትልቅ ውድድር በፊት ሁሌም የለመድነው ነገር ነው። በ 2010-ም እንዲሁ ሽንፈት ደርሶብን ነበር። እናም ይሄ ብዙም የተለየ ትርጉም አይኖረውም። ሆኖም ግን ፊት በማጥቃት አጨዋወታችን አንዳንድ ነገሮችን ገና ማሻሻል አለብን። ግልጽ ነው፤ በከፍተኛ ደረጃ ለሚካሄደው ውድድር ይበልጥ መሻሻላችን ግድ ይሆናል»

የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ምንም እንኳ ያልተጠበቀ ሽንፈት ቢገጥመውም ለአውሮፓ ዋንጫ ባለቤትነት ከፍተኛ ዕድል ኖሮት እንደሚቀጥል አሁንም የብዙዎች ዕምነት ነው። በሌላ በኩል በዓለም እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር በፊፋ የማዕረግ ተዋረድ ላይ ወደ 17ኛው ቦታ ላቆለቆለችው ለፈረንሣይ ድሉ ምናልባት መልሶ መጠናከሪያ ምንጭ ሊሆን ይችል ይሆናል። ጠብቀን የምንታዘበው ነገር ነው።

ለማንኛውም በተቀሩት ግጥሚያዎች ኔዘርላንድ በለንደኑ ዌምብሌይ ስታዲዮም እንግሊዝን 3-2 ስታሸንፍ ስፓኝ ደግሞ ቬኔዙዌላን 5-0 ሸኝታለች። ባለፈው ሣምንት በጥቅሉ 24 የወዳጅነት ግጥሚያዎች ሲካሄዱ ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል ስዊድን ክሮኤሺኢያን 3-1፤ አሜሪካ ኢጣሊያን 1-0፤ አርጄንቲና ስዊትዘርላንድን 3-1፤ ሩሢያ ዴንማርክን 2-0፤ ኡክራኒያ እሥራኤልን 3-2 ሲያሸንፉ ፖላንድ ከፖርቱጋል 0-0፤ አየርላንድ ከቼክ ሬፑብሊክ 1-1፤ ሩሜኒያ ከኡሩጉዋይም እንዲሁ 1-1 ተለያይተዋል።

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውድድር በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፤ በኢጣሊያ ሴሪያ-አ እና በስፓኝ ላ-ሊጋ ሻምፒዮናው የሁለት ክለቦች ፉክክር የሰፈነበት እየሆነ ሲቀጥል በጀርመን ቡንደስሊጋ ግን ዶርትሙንድ ባለፈው ሰንበት ለብቻው ማፈትለኩ የተሳካለት ነው የሚመስለው። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እንጀምርና ቀደምቱ ማንቼስተር ሢቲይ ቦልተን ወንደረርስን 2-0 በመርታት በአመራሩ ሲገፋ ማንቼስተር ዩናይትድም ቶተንሃም ሆትስፐርን 3-1 በማሸነፍ በሁለት ነጥቦች ልዩነት መከተሉን ቀጥሏል።

ሶሥተኛው ሆትስፐር በትናንት ሽንፈቱ ከአንደኛው ከማንቼስተር ሢቲይ በ 11 ነጥቦች ሲርቅ ከእንግዲህ ለሻምፒዮንነት ብዙም ዕድል አይኖረውም። ኤፍ ሲ ቼልሢይ ደግሞ በአነስተኛው ክለብ በብሮንዊች አልቢዮን 1-0 ሲረታ ሽንፍቱ ለአሰልጣኙ ለአንድሬ ቪላስ መባረር ምክንያት ሆኗል። አራተኛው በሣምንቱ ታላቅ ግጥሚያ የፌደሬሺኑን ዋንጫ አሸናፊ ሊቨርፑልን 2-1 የረታው አርሰናል ነው።

በስፓኝ ላ-ሊጋ ቀደምቱ ሬያል ማድሪድ ትናንት ኤስፓኞልን 5-0 ሲሸኝ ኮከብ ተጫዋቹ ክሪስቲያኖ ሮናልዶም 30ኛ የሊጋ ጎሉን ለማስቆጠር በቅቷል። በጨዋታው ጎሎቹን ከሮናልዶ ሌላ ሳሚ ኬዲራ፣ ካካና ጎንዛሉ ሂጉዌይን ሲያስቆጥሩ ሬያል ሊጋውን በአሥር ነጥቦች መምራቱን ብልጫ እንደቀጠለ ነው። ሬያል ማድሪድ 13 ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ ዘንድሮ ከአራት ዓመታት በኋላ መልሶ ሻምፒዮን ለመሆን የተቃረበ ነው የሚመስለው።

ያለፉት ዓመታት ሻምፒዮን ባርሤሎናም በበኩሉ ግጥሚያ ጊዮንን 3-1 ሲያሸንፍ በሁለተኛነት ብቸኛው የሬያል ተፎካካሪ እንደሆነ ይቀጥላል። ሶሥተኛው ቫሌናሢያ ከሬያል ማድሪድ በ 24 ነጥቦች ዝቅ ያለ ሲሆን ከሻምፒዮንነቱ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ቦሩሢያ ዶርትሙንድ ማይንስን 2-1 በማሸነፍ ሻምፒዮንነቱን ለመድገም በሚያስችል አቅጣጫ ትልቅ ዕርምጃ ነው ያደረገው። ዶርትሙንድ የሊጋው ውድድር ሊጠቃለል አሥር ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ አሁን አመራሩን ከአራት ወደ ሰባት ነጥቦች ለማስፋት ችሏል። ለዚህም ምክንያቱ በተለይ ተከታዮቹ ሶሥት ክለቦች ባየርን፣ ግላድባህና ሻልከ በሙሉ ሣምንቱን በሽንፈት ማሳለፋቸው ነው።

ባየርን ሙንሺን ለወትሮው በቀላሉ በሚረታው ክለብ በሌቨርኩዝን 2-0 ተሸንፎ ሲሰናከል ጎሎቹን በመጨረሻዋ ሩብ ሰዓት ውስጥ ያስቆጠሩት ሽቴፋን ኪስሊንግና ካሪም ቤላራቢ ነበሩ። ባየርን ባለፉት ጊዜያት በተለይም በውጭ ግጥሚያዎቹ ድክመት ሲታይበት ዘንድሮ ሻምፒዮንነቱን ሊረሳው ይገባል የሚለው ድምጽ በክለቡ ውስጥ ሳይቀር እየጎላ በመሄድ ላይ ነው። ይሁንና አሰልጣኙ ዩፕ ሃይንከስ ክለቡ ከወዲሁ አክትሞለታል መባሉን አይቀበለውም።

«እርግጥ ነው፤ የሰባት ነጥቦች ብልጫ ምቹ ቅድሚያ መሆኑን መቀበል ያስፈላጋል። ይህን መገንዘቡ ተገቢ ነገር ነው። ሆኖም ግን ከአሁኑ ሻምዮኑን ከመወስን እስክመጨረሻው 34ኛ የግጥሚያ ዕለት ጠብቆ ማየቱ ተገቢ ይመስለኛል። የስባት ነጥብ ልዩነት ትልቅ መሆኑ እርግጥ ሃቅ ነው»

ባለፉት ሣምንታት መደካከም የያዘው ግላድባህም በኑርንበርግ 1-0 በመረታት ባይርንን ደርቦ ሁለተኛውን ቦታ ለመያዝ የነበረው ዕድል አምልጦታል። አሁን ሶሥተኛ ነው። ሻልከም በፍራይቡርግ 2-1 ሲሸነፍ አራተኛ ሆኖ ቀጥሏል። በተረፈ ሽቱትጋርት ሃምቡርግን ለዚያውም በገዛ ሜዳው 4-0 ሲቀጣ በርሊን ከብሬመን 1-0፤ እንዲሁም ሃኖቨር ከአውግስቡርግ 2-2 ተለያይተዋል።

በኢጣሊያ ሴሪያ-አ ኤሲ ሚላን ፓሌርሞን 4-0 በማሸነፍ አመራሩ በሶሥት ነጥቦች ሲያሰፋ ሁለተኛው ጁቬንቱስ ከቺዬቮ ቬሮና 1-1 በሆነ ውጤት ተወስኗል። ጁቬንቱስ ይሁንና ገና አንድ ጨዋታ ይጎለዋል። ላሢዮ ሮማ ደግሞ ከጁቬንቱስ ሶሥት ነጥቦች ወረድ ብሎ ሶሥተኛ ነው። በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ሞንትፔሊዬር ከዲጆን 1-1 በመለያየቱ ፓሪስ-ሣናት-ዠርማን አመራሩን መልሶ ሊያዝ በቅቷል። የፓሪሱ ክለብ መልሶ ቁንጮ የሆነው ኤሲ አጃቺዮን 4-1 በማሸነፍ ነው። በፖርቱጋል ሻምፒዮና ቀደምቱ ቤንፊካና ፖርቶ ሰንበቱን እርስበርስ ሲጋጠሙ ፖርቶ 3-2 በመርታት በሶሥት ነጥቦች ብልጫ መምራቱ ሆኖለታል።

በተረፈ በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ነገና ከነገ በስቲያ የሩብ ፍጻሜ መልስ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። በነገው ምሽት ቤናፊካ ሊዝበን ከዜኒት-ሣንት-ፒተርስበርግ የሚገናኝ ሲሆን በተለይ የአርሰናልና የኤሲ ሚላን ግጥሚያ በታላቅ ጉጉት ይጠበቃል። በማግሥቱ ረቡዕ ደግሞ አፖል ኒኮዚያ ከኦላምፒክ ሊዮን፤ እንዲሁም ባርሤሎና ከሌቨርኩዝን ተረኞቹ ናቸው።

Daegu 2011Leichtathletik Weltmeisterschaft in Süd-Korea Flash-Galerie

አትሌቲክስ

ጃፓንን መቀመጫው ያደረገው ኬንያዊ አትሌት ሣሙዔል እንዱንጉ ትናንት በዚያው በሌክ-ቢዋ ሩጫ ባደረገው የመጀመሪያ የማራቶን ተሳትፎ አሸናፊ ሆኗል። የ 23 ዓመቱ ወጣት በ 32ኛው ኪሎሜትር ላይ የቅርብ ተፎካካሪዎቹን ጥሎ ሲያመልጥ ሩጫውን የፈጸመው በሁለት ሰዓት፣ ሰባት ደቂቃ ከአራት ሴኮንድ ጊዜ ነው። ፖላንዳዊው ሄንሪክ ሾስት ሁለተኛ ሲወጣ የሞሮኮው ተወዳዳሪ አብደላህ ታግራፌት ደግሞ ሶሥተኛ ሆኗል።

በሜልበርን የዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ውድድር ቀደምቱ የአውስትራሊያ አትሌቶች ጥሩ ወጤት በማስመዝገብ በለንደን ኦሎምፒክ የመሳተፍ ዕድላቸውን ለማረጋገጥ በቅተዋል። ዋነኞቹን ለማንሣት ያህል የአገሪቱ የመቶ ሜትር መስናክል የዓለም ሻምፒዮን ሴሊያ ፒርሰን ግሩም ጊዜ በማስመዝገብ ለለንደን ተፎካካሪዎቿ ጠንካራ መልዕክት ስታስተላልፍ የቀድሞው የእውስትራሊያ የዓለም ሻምፒዮና የናስ ሜዳይ ተሸላሚ ክሬግ ሞትራምም በ 5 ሺህ ሜትር በማሸነፍ በአገሪቱ የኦሎምፒክ ቡድን ውስጥ ቦታውን ይዟል።

ኬንያዊው ዴቪድ ሩዲሻ በ 800 ሜትር ሲያሸንፍ ሌላው የኦሎምፒክና የዓለም ሻምፒዮና የ 1500 ሜትር ባለድል አስቤል ኪፕሮፕ በሜልበርኑ ውድድር አምሥተኛ በመውጣቱ ልዩ የቅልጥፍና ልምምድ ለማድረግ ማቀዱን አስታውቋል። በፍልሥጤም ምድር በጋዛ ደግሞ ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ሁለተኛው ማራቶን ሲደረግ በሺህ የሚቆጠሩ ሯጮች ጥቂት ከዜሮ ዲግሪ በላይ የተመዘገበበት ቀዝቃዛ አየር ሳይበግራቸው ተሳትፈውበታል። ውድድሩን በሶሥት ሰዓት ከአሥር ደቂቃ ጊዜ በቀደምትነት የፈጸመው ያለፈው ዓመት አሸናፊ ፍልሥጤማዊ ናደር-አል-ማስሪ ነበር።

Roger Federer

ቴኒስ

የስዊዙ ሮጀር ፌደረር የብሪታኒያ ተጋጣሚውን ኤንዲይ መሪይን በሁለት ምድብ የፍጻሜ ጨዋታ 7-5, 6-4 በመርታት ለአምሥተኛ ጊዜ የዱባይ ሻምፒዮና አሸናፊ ሊሆን በቅቷል። በፍሎሪዳ-የዲልሪይ ቢች ፍጻሜም ደቡብ አፍሪቃዊው ኬቪን አንደርስን ትናንት የአውስትራሊያ ተጋጣሚውን ማሪንኮ ማቱሴቪችን በመርታት ባለድል ሆኗል። በማሌዚያ-ኦፕን ደግሞ የታይዋኗ ሂሤህ-ሱ-ዋይ ክሮኤሺያዊቱን ፔትራ ማርቲችን በማሸነፍ ለመጀመሪያ ታላቅ ድሏ በቅታለች።

በሜክሢኮ -አካፑልኮም የስፓኝ ተጫዋቾች እርስብርስ በተገናኙበት የወንዶች ፍጻሜ ዴቪድ ፌሬር ፌርናንዶ ቫርዳስኮን ሲረታ በሴቶች ፍጻሜ ኢጣሊያዊቱ ሣራ ኤራኒ የአገሯን ልጅ ፍላቪያ ፓኔታን አሸንፋለች።

ቡጢ

በቡጢ ለማጠቃለል ኡክራኒያዊው የዓለም የከባድ ሚዛን ሻምፒዮን ቭላዲሚር ክሊችኮ ባለፈው ቅዳሜ በዚህ በጀርመን ዱስልዶርፍ ከተማ ውስጥ በተካሄደ ግጥሚያ ፈረንሣዊ ተጋጣሚውን ዣን-ማርክ-ሞርሜክን በአራተኛው ዙር ላይ በመዘረር አሸንፏል። ክሊችኮ እስካሁን ተጋጣሚውን በዝረራ ሲያሸንፍ ለ 50ኛ ጊዜ መሆኑ ነበር። የኡክራኒያው ተወላጅ በዚሁ ድሉ የተለያዩት የቡጢ ድርጅቶች፤ የዓለም ቡጡ ድርጅት WBO፣ የዓለምአቀፉ ቡጢ ፌደሬሺን IBF-ና የዓለም ቡጡ ማሕበር WBA ሻምፒዮን እንደሆነ ይቀጥላል።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 05.03.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14FPM
 • ቀን 05.03.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14FPM