ዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስና አፍሪቃ | ኤኮኖሚ | DW | 18.02.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስና አፍሪቃ

ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ያስከተለው የኤኮኖሚ ችግር ይበልጥ ሥር አሰደደ እንዳይሄድ ባለፉት ወራት በተለይ በምዕራቡ ዓለም ያልተደረገ ሙከራ የለም።

የፊንላንድ ባንክ

የፊንላንድ ባንክ

የፊናንሱን ገበያ ሁኔታ ለማረጋጋትና ለኤኮኖሚ ማነቃቂያ ዕቅድ በብዙ ሚሊያርድ ዶላር የሚገመት ገንዘብ ፈሷል። በአሜሪካ ብሄራዊው ሸንጎ ያጸደቀው የ 790 ሚሊያርድ ዶላር በጀት ትናንት በፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ፊርማ እንዲጸና ተደርጓል። በአውሮፓም በጀርመን፣ በእንግሊዝ በፈረንሣይና በሌሎች አገሮች በተመሳሳይ ሁኔታ የፈሰሰው ገንዘብ ግዙፍ ነው። ከዚሁ ሌላ በዓለም የፊናንስ ጉባዔ የወቅቱን መሰል ችግር እንዳይደገም መቆጣጠሪያ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ጥረት መያዙ አልቀረም። ለመሆኑ የአስካሁኑ ዕርምጃ ዓለምአቀፉን ቀውስ ለመግታት በቂ ነወይ? በዓለምአቀፍ ደረጃ ሥር መስደድ የያዘው የኤኮኖሚ ቀውስ ሂደት ወደፊት ምን መፍትሄን ይጠይቃል፤ የአፍሪቃስ የልማት ዕጣ ምንድነው የሚሆነው?

ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ያስከተለው የምጣኔ-ሐብት ችግር ከ 30ኛዎቹ ዓመታት የዓለም ኤኮኖሚ ውድቀት ወዲህ አቻ ያልታየለት ነው። ክስረት ላይ የወደቁት ታላላቅ ባንኮችና ኩባንያዎች ብቻ አይደሉም። በዚህ የፊናንስ ቀውስ ለምሳሌ አይስላንድ እንደ መንግሥት ከስራለች። 300 ሺህ ነዋሪ ያላት ደሴት ዛሬ ያለ ውጭ ዕርዳታ ልትንቀሳቀስ በምትችልበት ሁኔታ ላይ አትገኝም። ኤኮኖሚዋ በከፊል በአሣ ማጥመድ ላይ ጥገኛ የሆነው አይስላንድ ለዚህ ችግር የበቃችው ባለፉት ዓመታት በዓለምአቀፍ ደረጃ እየተስፋፉ የመጡት ሶሥት ባንኮቿ በፊናንሱ ቀውስ ክስረት ላይ መውደቃቸው ነው።

መንግሥት አቅሙ የተወሰነ በመሆኑ ባንኮቹን በመደገፍ ይህን መሰሉን ትልቅ ችግር ለመጋተር አልቻለም። ለግንዛቤ ያህል የሶሥቱ ባንኮች ገንዘብ ከአገሪቱ አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት ሲነጻጸር በአሥር ዕጅ ከፍ ያለ ሆኖ ነው የሚገመተው። ቀውሱ ለአይስላንድ መንግሥት መውደቅም ምክንያት ሆኗል። ችግሩ በዚህ መጠን የጠነከረ ሲሆን የዛሬይቱ ዓለማችን ጨርሶ ጥልቅ ከሆነ ከለየለት የኤኮኖሚ ቀውስ ላይ እንዳትወድቅ ብርቱ ስጋት መፈጠሩ ብዙም አያስደንቅም። ለዚህም ነው አዲስ የፊናንስ ገበዮች ደምብ በማስፈን ክስረቱ እንዳደገም ለማድረግና ብዙ ገንዘብ በማፍሰስ የኤኮኖሚውን ቀውስ ለማሸነፍ ትግል የሚደረገው።

የፊናንሱ ቀውስ በተነሣባት በአሜሪካ ብሄራዊው ሸንጎ ብርቱ ችግር ላይ የወደቀውን የአገሪቱን ኤኮኖሚ ለማነቃቃት 800 ሚሊያርድ ዶላር ገደማ የሚጠጋ በጀት እንዲጸድቅ አድርጓል። በዚሁ ገንዘብ ሶሥት ሚሊዮን ተኩል ያህል የሥራ ቦታዎች ለማቆየትና አዳዲሶችንም ለመክፈት ሲታሰብ መንግሥት የሚያቅደው ከገንዘቡ 500 ሚሊያርድ ዶላር የሚሆነውን በመዋቅራዊ ግንባታ፣ በኤነርጂና ትምሕርትን በመሳሰሉ ዘርፎች ለማዋል ነው። በሌላ አነጋገር ሥራ አጥነት እንዳይስፋፋ ለማድረግ፤ ግብርን በመቀነስ የሕዝብን የገንዘብ አቅም ለማጠናከርና የኤኮኖሚ ዕድገትን ለማዳበር ነው የሚታሰበው። በዚህ በአውሮፓም ሂደቱ ከዚህ የተለየ አይደለም።

ሆኖም ግን እስካሁን የተወሰደው ዕርምጃ ሁሉ ገና ይህ ነው የሚባል ውጤት ሲያስከትል አይታይም። ከሰባ ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያው የሆነው ከባድ ቀውስ መቼና በምን ፍጥነት መፍትሄ ሊያገኝ እንደሚችል መናገሩም ዛሬ የሚያዳግት ነገር ነው። በአኮኖሚው ማነቃቂያ ግዙፍ በጀት የተነሣ የበለጸጉት መንግሥታት ዕዳ በሰፊው ጨምሯል። ይህም ቢቀር በአማካይ ጊዜ ጠቃሚ የልማት ፕሮዤዎችን ማራመዱን ሊያከብድ የሚችል ነው። በሌላ በኩል የምዕራባውያኑ መንግሥታት የኤኮኖሚ ማነቃቂያ ዕቅድ ብሄራዊ ችግሮችን በመፍታት ላይ ማተኮሩ ዓለምአቀፉን ችግር ለማስወገድ ማስቻሉ ብዙ ማጠያየቁ አልቀረም።

በአጽናፋዊው የኤኮኖሚ ትስስር ዘመን በብሄራዊ ፈውስ ፍለጋ ላይ ያተኮረው ጥረት ለዘለቄታው የሚበጅ መሆኑ ብዙ የሚያጠያይቅ ነው። በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት ቀደምት መንግሥታት የቡድን-ሰባት የፊናንስ ሚኒስትሮችና የማዕከላዊ ባንክ አስተዳዳሪዎች ባለፈው ሣምንት ሮማ ላይ ተሰብስበው በፊናንሱ ቀውስ ላይ ሲወያዩ ዓቢይ ርዕስ ያደረጉት ይህንኑ ጎጂ የብሄራዊ ገበያ እገዳ ጉዳይ ነበር። በአሜሪካ መንግሥት የኤኮኖሚ ማነቃቂያ ዕቅድ ውስጥ ሰፍሮ የነበረው “የአሜሪካን ምርት ግዛ” የሚል መርሆ ነው ለዚሁ መንስዔ የሆነው። ለነገሩ የአሜሪካ የፊናንስ ሚኒስትር ቲሞቲይ ጋይትነርና የአውሮፓ መሰሎቻቸው ገደቡ እንደማይጠቅም በሃሣብ ተስማምተዋል። ጋይትነር ችግሩ ትብብርን መጠየቁን ሳይጠቅሱም አላለፉም።
“ከአንግዲህ በዚህ መጠን የጠነከረ ቀውስ እንዳገጥመን የፊናንሱን ሥርዓት መጠገን መጀመር ይኖርብናል። ይህ የብሄራዊ መንግሥታት ሃላፊነት ነው። ግን ገበዮቻችን ዓለምአቀፍ በመሆናቸው ጥረታችን ጠንካራ የሆነ ዓለምአቀፍ ትብብር ሳይኖር ፍቱን ሊሆን አይችልም። በዚሁ መንፈስ በቡድን-ሰባትና በቡድን-ሃያ ስብስቦች ውስጥ የፊናንስ ማረጋጊያ ለውጥ ለማስፈን የተያዙትን ጥረቶች በመደገፍ እንደምንቀጥል ለማስረገጥ እፈልጋለሁ።

ጥያቄው ነገ ከነገ በስቲያ በተግባር ምን ይከተላል ነው። ለነገሩ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉትንና እንደ ቻይና በተፋጠነ ዕድገት ሲራመዱ የቆዩ አገሮችን የጠቀለለው ስብስብ ቡድን-ሃያ ባለፈው ታሕሣስ ዋሺንግተን ላይ የዓለም የፊናንስ ጉባዔ አካሂዶ ችግሩን በጋራ ለመወጣት በሚቻልበት ሁኔታ መክሯል። በቅርቡ መጋቢት 24 ቀን ደግሞ ተከታዩ ጉባዔ ለንደን ላይ ይካሄዳል። ይሁን እንጂ ዓለምአቀፉን ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት የሚያስችለው መሠረታዊ የፊናንስና የኤኮኖሚ ስርዓት ለውጥ ገሃድ ሊሆን መቻሉን የሚያመለክት ቁርጠኝነት እስካሁን አይታይም። ስርዓቱ የታዳጊውን ዓለም ልማትና ድህነትን መታገሉን የሚጠቀልል ሆኖ ካልተለወጥ ከቀውሱ መላቀቁ ቀላል የሚሆን አይመስልም። ቻይና በበኩሏ የታዳጊ አገሮች ድምጽ በዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቁዋም ውስጥ ጎላ እንዲልና በቡድን-ሃያ ጉባዔ ላይ የአፍሪቃ ሕብረት እንዲሳተፍም ጠይቃለች።

በታዳጊው ዓለም በተለይም በአፍሪቃ የፊናንሱ ቀውስ ባስከተለው ችግር ከአሁኑ የልማት ማቆልቆል አዝማሚያ ጎልቶ እየታየ ነው የሚገኘው። የተፈጥሮ ሃብት ያላቸው አገሮች በጥሬ ዋጋ ማቆልቆል የተነሣ ከአሁኑ ገቢያቸው መቀነስ ይዟል። አንጎላንና ናይጄሪያን በመሳሰሉት ከነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር ሲጠቀሙ የቆዩ አገሮች በዚሁ ዋጋ መቀነስ አሁን ዕድገታቸውን መቀነስ እየተገደዱ ነው። በዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎ የውጭ ባለሃብቶች 48 የማዕድን ፕሮዤዎችን ጥለው ወጥተዋል። የተቀሩት ታዳጊ የአፍሪቃ አገሮችም በፊናንሱ ቀውስ በሁለት በኩል እየተጎዱ ናቸው። በአንድ በኩል የልማት ዕርዳታው ገንዘብ ሲጓደል በሌላም በውጭው ዓለም የሚኖሩ ተወላጆቻቸው ለቤተሰብ የሚልኩት ገንዘብ መቀነስ ይዟል።

መለስ ብሎ ለማስታወስ ያለፉት አሥር ዓመታት በአፍሪቃ ያልተቁዋረጠ የኤኮኖሚ ዕድገት የታየባቸው ነበሩ። ባለፈው ዓመት አማካዩ የምጣኔ-ሐብት ዕድገት ከአምሥት እስከ ስድሥት በመቶ ይሆን ነበር። የውጭ መዋዕለ-ነዋይም በሰፊው ሲፈስ ቆይቷል። ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቁዋም እንደሚገምተው ወደ አፍሪቃ የፈሰሰው የውጭ መዋዕለ-ነዋይና ብድር ወደ 53 ሚሊያርድ ዶላር ከፍ ያለ ነበር። ይህም ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በ 2000 ዓ.ም. ከነበረው ሲነጻጸር በአምሥት ዕጅ ከፍ ያለ መሆኑ ነው። አሁን ግን የፊናንሱ ቀውስ የተፈጥሮ ሃብት ያላቸውንም ሆኑ ሌሎቹን የአፍሪቃ አገሮች እኩል ፈተና ላይ እንደሚጥል ነው የአፍሪቃ የልማት ባንክ ፕሬዚደንት ዶናልድ ካቤሩካ የሚናገሩት’።

“የፊናንሱንና የኤኮኖሚውን ቀውስ ለያይተን ማየት ይኖርብናል። እስካሁን በቀውሱ የተጎዳ አንድም የአፍሪቃ ባንክ የለም። በአንጻሩ ብሄራዊ ኤኮኖሚዎች ግን ተነክተዋል። በመሆኑም በዚህ በ 2009 ዓ.ም. በአማካይ ቢበዛ ከ 4 እስከ 4,5 በመቶ ዕድገት ነው የምንጠብቀው። ከዚህ በላይ አይኬድም። እንዲያውም አነስ ሊልም ይችላል። የሚፈለገው አፍሪቃ ውስጥ ያለውን ካፒታል ማንቀሳቀስ ነው”

ካቤሩካ በጣም ሃብታምና በጣም ድሆች የሆኑ አገሮች ባሉባት በአፍሪቃ በመላው ክፍለ-ዓለም ባይቻልም የልማት ባንኩ በአካባቢ ደረጃ መዋዕለ-ነዋይን ለማነቃቃት ያደረገው ጥረት ስኬታማ እንደነበርም ይጠቅሳሉ። እንደ አሕጉራዊው ልማት ባንክ ፕሬዚደንት ሁሉ የአፍሪቃ ልማት እንዳያቆለቁል የሚሰጉ ሌሎችም አልታጡም። ከነዚሁ አንዱም የተባበሩት መንግሥታት የልማት ዕቅድ የ UNDP ወኪል አድ ሜልከርት ናቸው።

“ይህ ሁሉ የሚሆነው በርካታ የአፍሪቃ አገሮች ባለፉት ዓመታት የማይናቅ የኤኮኖሚ ዕርምጃ እያደረጉ ከመጡ በኋላ ነው። ጥሩ የኤኮኖሚ ዕድገት፣ የሥራ ቦታዎች መስፋፋትና የመዋዕለ-ነዋይ መጨመር ታይቷል። አሁን ወደ ኋላ እየተመለሱ ነው። የዓለም ሕብረተሰብ፤ ቡድን-ሃያ በቅርቡ እንደገና ለፊናንስ ጉባዔ ለንደን ላይ ሲሰበሰብ ዓለምአቀፉን አጀንዳ አንስቶ መነጋገር ይኖርበታል። ጉዳዩ አፍሪቃንም የሚመለከት መሆኑን ማረጋገጥ አለበት። ምክንያቱም ችግሩ በመላው ዓለም ላይ ተጽዕኖ ያለው ዓለምአቀፍ የፊናንስ ቀውስ ነውና!”

አድ ሜልከርት አያይዘው እንዳሉት ዓለምአቀፍ መፍትሄ ለማግኘት በሚደረገው ጥረት ታዳጊ አገሮች መሳተፋቸው ግድ ነው። ቡድን-ሃያ መንግሥታት በቅርቡ የለንደን ጉባዔያቸው በዚህ ጉዳይ ግልጽ አቁዋም እንደሚወስዱም ተሥፋ ያደርጋሉ። አለበለዚያ በርሳቸው ዕምነት ከተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም የልማት ግቦች መድረሱ የማይቻል ነገር ነው የሚሆነው።

“ለልማት ግቡ የገንዘብ ድጋፍ ከመስጠት ሌላ አማራጭ የለም። የቡድን-ሃያ ስብሰባ በዚህ በኩል እንደሚረዳ፤ በባራክ ኦባማ የሚመራው የአሜሪካ መንግሥት የሚሌኒየሙን ዕቅድ ጠንከር ባለ መልክ እንደሚደግፍና አውሮፓውያንም በያመቱ ዕርዳታቸውን ለማሳደግ በገቡት ቃል እንደሚጸኑ ተሥፋ አደርጋለሁ። ከዚሁ ሌላ በአፍሪቃ፣ በብራዚል ወይም በሕንድ እያደገ የሚሄደው መካከለኛ የሕብረተሰብ መደብ ድህነትን ለመታገል ይረዳ ዘንድ ግብር አንደሚከፍልም ተሥፋዬ ነው”

ድህነትን መታገሉ ለነገሩ በአጠቃላይ በዓለምአቀፍ ደረጃ ዕርምጃ ታይቶበታል። ሆኖም ግን በአፍሪቃ የተፋጠነ የሕዝብ ቁጥር መናር ታክሎበት የድሃው መጠን ገና አልቀነሰም። ዛሬም በአስከፊ ድህነት የሚኖረው ሕዝብ ድርሻ በሃምሣ ከመቶ ባለበት እንደቀጠለ ነው። አሁን ደግሞ የፊናንሱ ቀውስ ሁኔታውን ይበልጥ እንዳያባብሰው ያሰጋል። እንግዲህ ሂደቱን ከመቀልበስ ሌላ አማራጭ አይኖርም። ለዚህ ደግሞ ዓለምአቀፉን የኤኮኖሚ ስርዓት ከጊዜው የተጣጣመ አድርጎ መለወጡ ግድ ይሆናል።


MM

ተዛማጅ ዘገባዎች