ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋምና የ 60 ዓመታት ጉዞው | ኤኮኖሚ | DW | 28.02.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋምና የ 60 ዓመታት ጉዞው

ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም 27 ዓባል መንግሥታትን ይዞ ተግባሩን ከጀመረ ልክ በነገዋ ዕለት 60 ዓመት ይሆነዋል። የምንዛሪው ተቋም፤ ለምን ዓላማ፣ ከየት፣ እንዴትና ወዴት?

የዋሺንግተኑ የምንዛሪ ተቋም

የዋሺንግተኑ የምንዛሪ ተቋም

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መገባደጃ ገደማ በ 1944 ዓ.ም. አሜሪካ ውስጥ በኒው ሃምፕሻየር ተራራማ መዝናኛ ስፍራ በብሬተን-ዉድስ ጉባዔ የተሰበሰቡት የምጣኔ-ሐብትና የፊናንስ ጠበብት በጊዜው በጋራ የተስማሙበት አንድ ነጥብ ነበር። ይሄውም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የዓለም ኤኮኖሚን ማረጋጋቱና የፊናንስ ቀውሶች እንዳይደርሱ መከላከል ነበር። ይህም ያለ ምክንያት አልነበረም። የሰላሣኛቹ ዓመታት ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ቀውስ የዓለም ንግድ ተንኮታኩቶ እንዲወድቅና የገበያ አጠራ የኤኮኖሚ ፖሊሲ እንዲከተል በማድረግ መሠረታዊ ድርሻ ነበረው።

ከመሥራቾቹ አንዱ ለዓለም የኤኮኖሚና የፊናንስ ዕርጋታ የፖሊሲ ጽንሰ-ሃሣብ ያረቀቁት የጊዜው የብሪታኒያ መንግሥት አማካሪ ጆን-ማይናርድ-ኬይንስ ነበሩ። የምንዛሪው ተቋም የተጓዘው ጉዞ ረጅም ነው። ዛሬ ጊዜው የመቀየሩን ያህል ዋሺንግተን ላይ ተቀማጭ የሆነው ድርጅት ተግባሩን ከጊዜው ሁኔታ በማጣጣምና በአዲስ መልክ በማቀናጀት ግፊት ላይ መገኝቱም አልቀረም።

ወደ ኋላ መለስ እንበልና ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም በጊዜው የተመደበለት ዓቢይ ተግባር የክፍያ ቀውስን ማስወገድ፣ የንግድ መለዋወጫ ምንዛሪዎችን ማረጋጋትና በመንግሥታት መካከል የሚደረግ የምንዛሪን ዋጋ የማውረድ ፉክክርን መቋቋም ነበር። ተቋሙ ይህን ለማድረግ ሁለት በቀደምትነት የሚጠቀሱ መሣሪያዎች ነበሩት። አንደኛው የክፍያ ችግር ላይ ለወደቁ ሃገራት ብድር በመስጠት ማገዝ፤ ሁለተኛው ደግሞ ለሁሉም ዓባል መንግሥታት በምጣኔ-ሐብት፣ በፊናንስና በምንዛሪ ፖሊሲ ረገድ የማማከር ተልዕኮ ነው። እርግጥ የሚሰጠው ብድር መከበር ባለባቸው ቅድመ-ግዴታዎች ላይ ጥገና ሆኖ ቆይቷል።

በአሠራሩ እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት “አንድ አገር አንድ ድምጽ” በሚል ዓላማ ሣይሆን በተቋሙ ውስጥ ባሉት ሃብታምና ሰፊ የገንዘብ ድርሻ ባላቸው መንግሥታት ተጽዕኖ ሲመራ ነው የኖረው። በአጠቃላይ 270 ሚሊያርድ ዶላር ገደማ የሚጠጋው የተቋሙ ካፒታል ድርሻ እንደ ዓባል ሃገራቱ የኤኮኖሚ ሃይል የተቀናበረ ነው። ከፍተኛ መሠረታዊ ካፒታል ያላቸው በኤኮኖሚ የጠነከሩ መንግሥታት ከድሆቹ ወይም ከታዳጊዎቹ አገሮች የበለጠ ተጽዕኖ አላቸው ማለት ነው።

በተቋሙ ውስጥ ታላቁን 17 ከመቶ የሚሆን የድምጽ ድርሻ አሜሪካ ትይዛለች። የአውሮፓው ሕብረት ሃገራት ድርሻ በጠቅላላው 30 በመቶ ገደማ ሲጠጋ ጀርመን ለብቻዋ 6 ከመቶ ድምጽ አላት። እንግዲህ ታዳጊዎቹ አገሮች በምንዛሪው ተቋም ውስጥ ተገቢው ወይም የተጣጣመ ውክልና የላቸውም ማለት ነው። ድርሻቸው ከሚገባው በታች ዝቅ ያለ ነው። ይህም በተለይ ብራዚልን ሕንድንና ቻይናን የመሳሰሉትን በዕድገታችው ከተቀሩት ታዳጊ አገሮች መጠቅ ያሉትን አገሮች ይመለከታል።

እነዚህ አገሮች እርግጥ በምንዛሪው ተቋም ውስጥ ድምጻቸውን ይበልጥ ለማጉላት ለዓመታት ጥሪ ሲያደርጉ ነው የቆዩት። ባለፈው 2006 መገባደጃ አጋማሽ ሢንጋፖር ውስጥ ተካሂዶ በነበረው የምንዛሪው ተቋም ዓመታዊ ጉባዔ ላይም በጥረታቸው የመጀመሪያውን ስኬት ማስመዝገባቸው አልቀረም። የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም ሥራ-አስኪያጅ፤ የቀድሞው የስፓኝ ፊናንስ ሚኒስትር ሮድሪጎ ራቶ በጉዳዩ እንደተናገሩት፤

“ሁሉም መንግሥታት እንዴት እንደሚወከሉና ፍላጎታቸውን እንዴት እንደሚያራምዱ ጭብጥ አድርጎ ማስቀመጡ እጅግ ጠቃሚ ጉዳይ ይሆናል። በዚህ በኩል፤ ማለት መላው ሃገራት በውሣኔያችን የመሳተፍና ተጽዕኖ የማድረግ ዕድል እንዲኖራቸው ተቋሙ እስካሁን ያደረገው አስተዋጽኦ ብዙ ነው”

በሢንጋፑሩ ጉባዔ ላይ በጥቂቱም ቢሆን የቻይና፣ የደቡብ ኮሪያ፣ የሜክሢኮና የቱርክ ኮታ ከፍ እንዲል ተደርጓል። ግን ይህ በዓለም የኤኮኖሚና የፊናንስ ሥርዓት ውስጥ ለነዚህ ሃገራት ክብድት መጨመር ዕውቅና በመስጠቱ ረገድ የመጀመሪያ ዕርምጃ መሆኑ ነው። በሁለተኛ ዕርምጃም የሃገራቱን ኮታ አከፋፈል በተመለከተ አዲስ ዘዴ ወይም ማሻሻያ እንዲሰፍን ተደርጓል። በዚህ ዕርምጃ ከታላላቆቹ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ አገሮች አንዳንዶቹ ለምሳሌ ጀርመንን የመሳሰሉት ደግሞ ዝቅ ማለታቸውና የተወሰነ ድርሻቸውን ማጣታችው አልቀርም።

ይሁንና የጀርመን ፊናንስ ሚኒስትር ፔር ሽታይንብሩክ እንደሚሉት ያለፈውን ዓመታዊ ጉባዔ ተከትሎ የሰፈነው የአገራቸው ድርሻ ማቆልቆል፤ ይህም ከ 6.1 ወደ 5.9 መሆኑ ነው፤ ብዙም ፍቱን ሁኔታን የሚፈጥር አይደለም።

“የኮታውን አቀነባበር በተመለከተ በሁለተኛ ዕርምጃነት ዋና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው አንድ ዘላቂና ቀጣይ የለውጥ ፕሮዤ ለማንቀሳቀሱ ጉዳይ ነው። ይህ ቀላል ነገር አይሆንም። ሆኖም ለጀርመን ጠቃሚው ነገር በምንዛሪው ተቋም ውስጥ ያላትን ተጽዕኖ አጽንቶ ማቆየቱ ነው። ለማለት የምፈልገው፤ ለምሳሌ በተቋሙ ውስጥ ያለንን የአስተዳደር ሥልጣናችንን ምን ጊዜም እንዳናጣ ሆነን መገኘት ይኖርብናል”

በተፋጠነ ዕርምጃ ላይ የምትገኘው የሕዝባዊት ቻይና የድምጽ ድርሻ ባለፈው ዓመት ከ 3 ወደ 3.7 በመቶ ሊያድግ በቅቷል። አገሪቱ በዓለም ኤኮኖሚ ላይ እንዳላት ክብደት ቢሆን ኖሮ ተገቢው ድርሻ 5 ከመቶ መድረስ በተገባው ነበር። ግን ጥያቄው ቻይና ይህን በማን ትከሻ ታግኝ ነው። የጀርመን ኮታ በሌላ በኩል አገሪቱ በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ካላት ክብደት ሲነጻጸር ገና ካለፈው ዓመት ዕርማት በፊት እንኳ ዝቅ ያለ ነበር። አሁን ደግሞ የበለጠ! ይህ የሚሆነው ጀርመን በዓለም ንግድ ላይ ያላት ድርሻ ከጠቅላላው የዓለም ንግድ ይልቅ እየጠነከረ በሚሄድበት ወቅት ነው።

ነገር ግን እጅጉን ተገቢውን ውክልና አጥተው የሚገኙት ታዳጊ አገሮች መሆናችው ሊዘነጋ አይገባውም። WEED በሚል አሕጽሮት የሚጠራው የልማት ድርጅት ሊቀ-መንበር ባርባራ ኡንሙሢግ በዚህ ከሚያማርሩት አንዱ ናችው።

“በዓለም ኤኮኖሚ፣ ማሕበራዊ፣ የተፈጥሮ ጥበቃና በጠቅላላውም የታዳጊው ዓለም ልማት የረጅም ጊዜ ዕጣ ላይ አሁንም አዘውትረው ሁሉንም ነገር የሚወስኑት ሰባት ሃብታም በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ መንግሥታት ናቸው። ስለዚህም ይህ ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ መዋቅር ታዳጊ አገሮች የበለጠ ድርሻና የውሣኔ ተሳትፎ በደሚያገኙት ዴሞክራሲያዊ በሆነ ይዞታ አቅጣጫ መለወጡ ለእኛ እጅግ ጠቃሚ ነው”

የምንዛሪው ተቋም ኮታዎች በተለይ በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙትን ቻይናን የማሳሰሉትን አገሮች ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚና የፊናንስ ድርሻ በሚገባ የሚያንጸባርቁ አይደሉም። እዚህ ላይ የኮታው መጠን አንድ አገር በምንዛሪው ተቋም ውስጥ የሚኖረውን ተጽዕኖ ብቻ ሣይሆን በምንዛሪ ቀውስ ችግር ላይ በሚወድቅበት ጊዜ ከተቋሙ ምን ያህል ገንዘብ ሊበደር እንደሚችልም ልዩ መብቱን እንደሚወስን መዘንጋት የለበትም። ግን የምንዛሪው ተቋም ባለፉት በርካታ ዓመታት በዚህ መሰሉ ቀውስ አልፎ አልፎ እንደሆን እንጂ ብዙ ተወጥሮ አያውቅም።

በቅርብ የሚታወሰው ይህ ነው የሚባል የምንዛሪ ክስረት፤ ከታይላንድ የተነሣው የእሢያ የፊናንስ ቀውስ ራሱ አሥር ዓመት አልፎታል። ከዚህ ሌላ በከፋ ተመሳሳይ የፊናንስ ቀውስ ተጠምደው የነበሩት የላቲን አሜሪካ አገሮች አርጄንቲናና ብራዚል በምንዛሪው ተቋም ዘንድ የተወዘፈባቸውን የብዙ ሚሊያርድ ዶላር ዕዳ ሊወጡት በቅተዋል። በወቅቱ ከመንግሥታቱ ይልቅ ራሱ የምንዛሪው ተቋም ነው ችግር ላይ ወድቆ የሚገኘው።

ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም የማማከር ተፈላጊነቱ እየቀነሰ ሲሄድ በሚያገኘው ወለድ ማቆልቆል ሳቢያም ዋሺንግተን ላይ ተቀማጭ የሆነ ድርጅቱን ማስተዳደሩ ከባድ ፈተና ሳይሆንበት አልቀረም። በተቋሙ ዘንድ ዛሬ ብቸኛዋ ባለዕዳ ቱርክ ናት። በአንጻሩ ቻይና በአንድ ሺህ ሚሊያርድ ዶላር በዓለም ላይ ታላቁን የምንዛሪ ተቀማጭ ልታሰባስብ በቅታለች። ይህም የምንዛሪ ቀውስ ቢገጥማት እንኳ ችግሯን ለመወጣት በ IMF ላይ ጥገኛ አይደለችም ማለት ነው።

በሌላም የዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም ብድር አቅርቦት ጠንካራ ከሆነ የኤኮኖሚ፣ የፊናንስና የምንዛሪ ፖሊሲ ጋር የተሳሰረ በመሆኑ ዕርዳታው በተቀባዮቹ አገሮች ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ፍሬያማነት አይታይበትም። የቀውሶቹ ምክንያትና የተቋሙ ድጋፍ ማስፈለግ መንስዔ አብዛኛውን ጊዜ የተሳሳተ ብሄራዊ ፖሊሲ መሆኑ ብዙ ክብደት ያልተሰጠው፤ ችላ የተባለ ነው የሚመስለው። ይህ ሁኔታ የመንግሥት በጀትን መቆረጥና ጠንካራ የቁጠባ ፖሊሲን የሚያስከትል በመሆኑ ደግሞ ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም የችግሩ ምክንያት ሆኖ መታየቱ ያለ ነው።

እርግጥ የምንዛሪው ተቋም ካለፉ ስሕተቶቹ ብዙ እንደተማረ ነው የሚነገረው። ሆኖም በወቅቱ ተመክሮውን በተግባር መተርጎሙ ተሳክቶለት አይገኝም። ይልቁንም የራሱን ችግር የሚወጣበትን መንገድ ማፈላለጉ ያመዝናል። ከዚሁ ሌላ በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ከተለወጠው ሁኔታ አንጻር አዳዲስ ተግባራትና የአፈጻጸም ዘዴዎች እየተፈለጉ መሆናቸው ነው የሚነገረው። በዚህ አካሄድ ላይ ስጋታቸውን ከሚገልጹት ወገኖች አንዱ የጀርመኑ የፊናንስ ሚኒስትር ፔር ሽታይንብሩክ ናቸው።

“ይበልጥ ገንዘብ የሚጠይቁ ተጨማሪ ተግባራትን መሻቱ ሊሆን የማይገባው ጉዳይ ነው። መሆን ያለበት፤ የምንዛሪው ተቋም ዓባል ሃገራትን እንደሚጠይቀው በመጀመሪያ ደረጃ የተግባሩን ይዘት ጭብጥ ማድረግ ነው። ከዚህ በኋላ ምን ያህል ተቀማጭ አለኝ፤ ብዙ ወይስ ዝቅተኛ ወጩ ይበቃኛል ወይ ብሎ መወሰን ይቻላል”

የምንዛሪው ተቋም አስተዳዳሪ ሮድሪጎ ራቶ በኤኮኖሚ፣ በፊናንስና በምንዛሪ ፖሊሲ ረገድ በድርጅታችውና በመንግሥታት መካከል የሚካሄደው ንግግር የሁለት ወገን ባይላተራል ግንኙነት ብቻ ሆኖ እንዳይቀጥል ሃሣብ አቅርበዋል። ይሁንና ንግግሩ በምን መልክ፣ ስብስብና በምን አሣሪነት መጠን እንደሚካሄድ በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለም። በሌላ በኩል የምንዛሪው ተቋም በጠቅላላው 3,220 ቶን ገደማ የሚጠጋ የወርቅ ተቀማጩን ተግባሩን ለማራመድ የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሽፈን ይሽጥ-አይሽጥ በወቅቱ ማቅማማት የተያዘበት ጉዳይ ነው።
ሮድሪጎ ራቶ በበኩላቸው 400 ቶን የወርቅ ተቀማጭን በመሸጥ የሚገኝ ከስድሥት ሚሊያርድ ዶላር የሚበልጥ ገንዘብ በአንድ ካዝና ተሰብስቦ ተቋሙ ለሚያካሂዳቸው ተግባራት ወጪ እንዲሆን ያሳስባሉ። ሆኖም ግን ይህ ተቀማጭን በመሸጥ ላይ ጥገኛ የሆነ የአሠራር ዘይቤ ለዘለቄታው የሚያዋጣ መሆኑ ሲበዛ የሚያጠራጥር ነው። ያም ሆነ ይህ በምንዛሪው ተቋምና በዕሕት ድርጅቱ በዓለም ባንክ ውስጥ አንድ ትልቅ ተሃድሶ ታይቷል ነው የሚባለው። ይሄውም ሁለቱ የብሬተን-ውድስ ኢንስቲቲቱቶች ከተቺዎቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት መሻሿል!

የገንዘብ ተቋማቱ ተቺዎች የዓለም ባንክንና IMF-ን ለሃብታሞቹ የበለጸጉ መንግሥታትና ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች ጥቅም የቆሙ መሣሪያዎች ሲሉ ሲወቅሱ ቆይተዋል። ከነዚሁ ተቺዎች ጋር ይፋ ንግግር ሲሹ ከቆዩት ባለሥልጣናት መካከል የቀድሞው የምንዛሪው ተቋም አስተዳዳሪ፤ የዛሬው የጀርመን ፕሬዚደንት ሆርስት ኮህለር ይገኙበታል። በኮህለር ዘመን ጥቂት ዕርምጃ መታየቱም አልቀረም። የጀርመኑ ፕሬዚደንት በጊዜያቸው ከዋሺንግተኑ ተቋም ስንብት ሲያደርጉ እንደተናገሩት፤

“በአጠቃላይ የምንዛሪውን ተቋም የዓለምአቀፍ ኩባንያዎች ጥቅም ጠባቂ፤ በዓለም ላይ ለሰፈነው ድህነት ደንታ የሌለው ብሎ በደፈናው መውቀስ የሚቻልበት ጊዜ እንዳለፈና ተቀባይነት የሌለው ነገር እንደሆነ የተረዳን ይመስለኛል። ይህ በቀላሉ ያለፈ ታሪክ ነው”

ለማንኛውም የምንዛሪው ተቋምም ሆነ የዓለም ባንክ የብዙሃኑ ታዳጊ አገሮች ድምጽ ጎልቶ የሚሰማባችው መድረኮች ከመሆን ገና ብዙ ርቀው እንደሚገኙ ጭብጥ ሃቅ ነው። እርግጥ ዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ትስስር፤ ዘመነ-ግሎባይዜሺንና ቻይናን በመሳሰሉ አዳጊ አገሮች መንሰራራት የዓለም ንግድ፤ እንዲያም ሲል የኤኮኖሚው ሚዛን መቀየር መያዙ ሁኔታዎችን መለወጡ አልቀረም። ግን ይህ ብቻውን በቂ አይደለም። የገንዘብ ተቋሟቱ እንደ ተባበሩት መንግሥታት ጸጥታ ም/ቤት ሁሉ የተመሠረቱበት ወቅት ሃቅም ሆነ የሃይል አሰላለፍ ጊዜው ያለፈበት መሆኑ ግንዛቤ አግኝቶ ሥር-ነቀል ለውጥ የግድ መስፈን ይኖርበታል። አለበለዚያ የጥቂት ሃብታም መንግሥታት ተጽዕኖና ወሣኝነት ባለበት ሊቀጥል ነው።