ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ስርዓትና ችግሩ | ኤኮኖሚ | DW | 02.03.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ስርዓትና ችግሩ

ዓለም በ 2008 ዓ.ም. ከደረሰበት ከባድ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ እርግጥ ቀስ በቀስ እያገገመ መሄዱ አልቀረም። ይሁን እንጂ ቀውሱ በተለይም በዓለምአቀፉ የምንዛሪ ስርዓት ላይ ጥሎት የሄደው ችግር በቀላሉ የሚገመት አይደለም።

default

ሚሼል ካምዴሱስ

እንደቀድሞው የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም የአይ.ኤም.ኤፍ. አስተዳዳሪ እንደ ሚሼል ካምዴሱስ ከሆነ ዛሬ የዓለም የምንዛሪ ስርዓት ስር-ነቀል ለውጥ ሊካሄድበት የሚገባው ነው። በሌላ በኩል መሪ ወይም የጋራ መለዋወጫ ገንዘብ ሆኖ የኖረው የአሜሪካ ዶላርም እንደቀድሞው አስተማማኝ የነበረበት ጊዜ እየተለወጠ በመሄድ ላይ ሲሆን ከቻይና በኩል ብርቱ ፉክክር የገጠመው ነው የሚመስለው።

በአሁኑ ጊዜ የቡድን-ሃያ መንግሥታት ሊቀመንበር የሆኑትን የፈረንሣዩን ፕሬዚደንት ኒኮካይ ሣርኮዚይን የሚያማክሩት ሚሼል ካምዴሱስ የተሃድሶ ለውጥ እንዲደረግ የሚያሳስቡት በምንዛሪ ገበዮች ላይ አዘውትሮ ውዥቀት እየታየ መሆኑን በማስገንዘብ ነው። ባለሙያው በጉዳዩ “ዲ-ትሣይት” ከተሰኘው የጀርመን ሣምንታዊ ጋዜጣ ጋር ሰሞኑን ባደረጉት ቃለ-ምልልስ እንዳስረዱት የምንዛሪዎቹ መለዋወጫ ተመን ከተጨባጩ የኤኮኖሚ ይዞታ ጋር ጨርሶ የሚታጣም አይደለም። እና ለውጥ ማስፈለጉም ለዚሁ ነው።

በዛሬው ሁኔታ ብዙዎቹ የኤኮኖሚ ጉዳይ ተራኪዎች መለስ ብለው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተደረገውን አዲስ ጅማሮ መናፈቃቸው አልቀረም። በጊዜው ጽናት ያለው የመለዋወጫ መስፈርት ነበር። ወለዱ ዝቅተኛ፤ ዶላርም እንደ መሪ ምንዛሪና እንደ መለዋወጫ ገንዘብ በየቦታው ዕውቅና ነበረው። ለዚህም ምክንያት የሆነው እጎ.አ. በ 1944 ዓ.ም. በአሜሪካ-በብሬተን ዉድስ በጦርነት የወደመውን የዓለም ኤኮኖሚ መልሶ ለመገንባት ዓለምአቀፍ የመልሶ ግንባታና ልማት ባንክ፤ በአጭሩ የዓለም ባንክና የምንዛሪው ተቋም መመስረታቸው ነበር።

በጊዜው የዓለም ባንክ በአውሮፓ፤ እንዲሁም በታዳጊዎቹ የእሢያ፣ የአፍሪቃና የላቲን አሜሪካ ሃገራት መልሶ ግንባታን እንዲያራምድ ይወሰናል። የገንዘቡ ተቋም የአይ.ኤም.ኤፍ ሚና ደግሞ በብሄራዊ የኤኮኖሚ ችግሮች የተወጠሩትን ምንዛሪዎች ማረጋጋት ይሆናል። ከሁሉም ይልቅ ታላቁ የብሬተን ዉድስ ጉባዔ ውጤት ግን ጦርነቱን ተከትሎ የተፈጠረው የዓለም የኤኮኖሚ ስርዓት በወርቅና በአሜሪካ ዶላር መሪ ምንዛሪነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን መደረጉ ነበር። ዶላርን ለዚህ ያበቃውም በተለይ አሜሪካ በዓለም ላይ የአብዛኛው፤ ማለትም የሁለት-ሶሥተኛው የወርቅ ክምችት ባለቤት በመሆኗ ነበር።

አሜሪካ ከዚህ አንጻር ጦርነቱን በተከተለው ጊዜ በፖለቲካና በወታደራዊ ሃይል ብቻ  ሣይሆን በኤኮኖሚና በፊናንስ መስክም በቀላሉ በዓለም ላይ ቀደምቱን ሚና ትይዛለች። ጊዜው የዕርምጃ ነበር። በቪየና የምጣኔ-ሐብት ጥናት ኢንስቲቲዩት ተመራማሪ የሆኑት ባለሙያ ሽቴፋን ሹልማይስተር እንደ ብዙዎች መሰሎቻቸው ያንን ጊዜ በናፍቆት ነው የሚያስቡት።

Dossier Teil 3 IWF warnt vor Währungskrieg

 “የ 50ኛና የ 60ኛዎቹ ዓመታት ዕድገት በተቀናበሩ ተግባራትና የማትረፍ ዝንባሌ ላይ በመመስረት የከበርቴው ስርዓት አንቀሳቃሽ ሃይል ይሆናል። በተጨባጭ የምዛሪው መለዋወጫዎች ቋሚ፣ ወለዱ ዝቅተኛ ሲሆን፣ የአክሢዮን ገበዮች ሲረጉና የጥሬ ዕቃ ዋጋ ሲረጋጋ በፊናንሱ ኤኮኖሚ ዘርፍ በትርፍ ማጋበስ ስሜት መካበት አይቻልም። በዚህም የተነሣ ነበር ገቢ የማግኘቱ ጥረት በፊናንሱ ሣይሆን በአምራቹ ኤኮኖሚ ላይ ያተኮረው። ይህ ደግሞ ያለማቋረጥ ከሚያቆለቁል የመንግሥት ዕዳ ጋር ተጣምሮ ለኤኮኖሚ የዕድገት ተዓምር፣ ለስራ አጥነት መወገድና ለማሕበራዊ ስርዓት ግንቢያ በር ከፍቷል”

ሆኖም 36ኛው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ሊንደን-ቢ-ጆንሰን በቪየትናም የፈረንሣይን ወራሪ ሃይል ለመደገፍ መነሣት ሁኔታውን ይቀይረዋል። ጦርነቶች ወጪ የሚጠይቁ፣ ገንዘብ የሚፈጁ በመሆናቸው የአሜሪካ ዶላርም ዋጋውን እያጣ መሄድ ይጀምራል። ቀጥሎም ፈረንሣይና ከዚያም ተከትሎ ሌሎች መንግሥታት የዶላር ክምችታቸውን በወርቅ የመለወጥ መብታቸውን መጠቀም ሲፈልጉ የአሜሪካን ዶላር ወደ ወርቅ የመለወጡ ግዴታ በነሐሴ ወር 1971 ዓ.ም. በፕሬዚደንት ኒክሰን እንዲነሣ ይደረጋል። ታዲያ በዚህ ሳቢያ የቪያናው የምጣኔ-ሐብት ምርምር ኢንስቲቲዩት ባልደረባ ሽቴፋን ሹልማይስትር እንደሚሉት የመለዋወጫው መጠን ብቻ አይደለም ነጻ ሊሆን የበቃው። እንዲያውም በስርዓቱ ላይ አጠቃላይ ለውጥ ይከተላል።

“የፊናንስ ካፒታሊዝም ማለትም የፊናንሱ የገበያ ስርዓት ባለፉት አርባ ዓመታት የመለዋወጫው መስፈርት ያልተረጋጋበት፣ የወለዱ መጠን ከፍተኛና ዋዣቂ የሆነበት፣ እንዲሁም የአክሢዮንኑ ገበዮች አንዴ ሲያብቡና ሌላ ጊዜም ቀውስ ላይ ሲወድቁ፣ የጥሬ ዕቃም እንዲሁ ሲንር የታየበት ሞዴል ሆኖ ነው ያለፈው። በዚህ ሁኔታ ደግሞ የማትረፉ ቁማሮ ይበልጥ እየጨመረ መምጣቱ አልቀረም። ይህም የኋላ ኋላ የዋጋ ዝቤትን ነው ያስከተለው። ዝቤቱም በፊናው ኩባንያዎች መዋዕለ-ነዋይ እንዲቀንሱና በአንጻሩ በምንዛሪው ገበያ ትርፍ ለማጋበስ እንዲሞክሩ ነው ያደረገው”

የዓለም የምንዛሪ ስርዓት እንግዲህ የግድ ከጊዜው ሁኔታ ተጣጥሞ መለወጥ ይኖርበታል። ከአርባ ዓመታት በፊት የነበረው የተረጋጋ ሁኔታ እርግጥ ሊመለስ የሚችል ነገር አይደለም። ዛሬ የአሜሪካ ኤኮኖሚ ከቅርቡ የዓለም የፊናንስ ቀውስ ወዲህ ከወደቀበት አዘቅት መልሶ መውጣቱ ተስኖት ነው የሚገኘው። የመንግሥቱ ዕዳ ከዚህ ቀደም ካልታየ ከፍተኛ ጣራ ሲደርስ የስራ አጡ ቁጥር ከ 15 ሚሊዮን የሚበልጥ ነው። የዶላር ዋጋም እያቆለቆለ ነው የመጣው። ይህ ደግሞ የብዙዎችን አገሮች የውጭ ምንዛሪ የዶላር ክምችት የሚጎዳ ነው የሚሆነው። እንደ ምሳሌ ሶሥት ቢሊዮን ዶላር ተቀማጭ ያላትን ቻይናን መውሰድ ይቻላል።

እርግጥ በቅርቡ ጃፓንን በዓለም የኤኮኖሚ ልዕልና ከሁለተኛው ቦታ የፈነቀለችውና ጀርመንንም እንደ ውጭ ንግድ የዓለም ሻምፒዮን ያስከነዳችው ቻይና ጉዳዩን በቸልታ አትመለከተውም። ለነገሩ የአገሪቱ ምንዛሪ ሬንሚንቢ ወይም ዩዋን እስካሁን በዓለም የፊናንስ ስርዓት ላይ ብዙም ሚና አልነበረውም። አሁን ግን ቻይና ገንዘቧን ደረጃ በደረጃ ወደ ዓለም ምንዛሪነት ለመለወጥ በመነሣቷ ሁኔታው እየተቀየረ በመሄድ ላይ ነው። ሕዝባዊት ቻይና ከአንድ አገር ጋር እንበል ከብራዚል ጋር ንግድ ስታካሂድ የምርቱም ሆነ የአልግሎቱ ዋጋ በመሠረቱ የሚከፈለው በዶላር ነው። ዶላር ዓለም ያወቀው መለዋወጫ በመሆኑ!

ነገር ግን የአዳጊው ገበዮች አዋቂ የሆኑት የጀርመኑ የባንክ ባለሙያ በርናርድ ኤሰር እንደሚያስረዱት ከ 2009 ዓ.ም. ዓለምአቀፍ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀወስ ወዲህ በቤይጂንግም የሃሣብ የተግባር ተሃድሶ መደረጉ አልቀረም።

“የቻይና የውጭ ንግድ ኤኮኖሚ በዓለም ንግድ መዳከም ሳቢያ ሰፊ ተጽዕኖ ላይ መውደቁ አልቀረም። እናም ቻይናውያን ምርታቸውን በዓለም ላይ በዝቅተኛ ዋጋ መሸጥ ሲገደዱ በችግሩ ላይ ተጨማሪ የምንዛሪ ልውውጥ አደጋ መፈጠሩን አይፈልጉም። በመሆኑም የልውውጡን አደጋ ወደ ውጭ ተፎካካሪዎቻቸው በመግፋት የአገሪቱን የውጭ ንግድ ለመርዳት ነው የሚጥሩት። ለቻይና ማዕከላዊ ባንክ የተገለጠለት ሁለተኛው ልምድ ደግሞ አገሪቱ በገፍ ያከማቸችው የዶላር ተቀማጭ አደጋ ላይ ሊወድቅ የመቻል ሃቅ ነው”

ቻይና ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ግዙፍ በሆነ በሶሥት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ክምችት ላይ ተቀምጣ ነው የምትገኘው። ከዚሁ ሁለት-ሶሥተኛውን ድርሻ የሚይዙትም የአሜሪካ መንግሥት ወይም ኩባንያዎች የዕዳ ሰነዶች ናቸው። ስለዚህም የአሜሪካ የገንዘብ ሕትመት ባንክ ፖሊሲውን ለቀቅ በማድረግ የዶላርን ዋጋ ወደታች ቢጫን ቻይና የሚኖራት ምርጫ ሃብቷ እየመነመነ ሲሄድ መመልከት ብቻ ይሆናል። በሌላ በኩል ችግሩን ፈርቶ ቶሎ ዶላሩን ለመሸጥ መሞከሩም ዋጋውን ይብስ የሚያወርድ በመሆኑ የባሰ ጉዳትን ሊያስከትል የሚችል ነው። በሌላ አነጋገር የዶላር ውድቀት ማለት የክምችቱ መመንመን ማለት ነው የሚሆነው።

ለማንኛውም ሕዝባዊት ቻይና ከዶላር ጥገኝነት ለመላቀቅ ከ 2009 ዓ.ም. ወዲህ የሙከራ ፕሮዤ በማካሄድ ላይ ነው የምትገኘው። በዚሁ በሬንሚንቢ ሂሣብን የማካሄድ ፕሮግራም መርህ መሠረት የአገሪቱ ምንዛሪ ደረጃ በደረጃ ዓለምአቀፍ ሚና እንዲኖረውና ከዶላር ጋር እንዲሰለፍ ለማድረግ ነው የሚፈለገው። ፕሮግራሙ በወቅቱ ወደ ሃያ ክፍለ-ሃገራት ሲስፋፋ 95  በመቶውን የቻይናን የውጭ ንግድ ያዳርሳል። እስካሁን በሬንሚንቢ ዓለምአቀፍ ውሎችን ለመፈራረም የበቁት ኩባንያዎች ሰባ ሺህ ገደማ ይጠጋሉ።

ንግዱን በቻይና ምንዛሪ ከሚያካሂዱት ኩባንያዎች መካከል የጀርመኑ ሜትሮም ለምሳሌ አንዱ ነው። ኩባንያው በወቅቱ ለቻይና ምርት አቅራቢዎቹ ዕዳውን የሚከፍለው በዩዋን ነው። እርግጥ የዚህ ንግድ መጠን በጥቅሉ ገና ከሶሥት በመቶ አይበልጥም። ሆኖም የቤይጂንግ መንግሥት የሚያልመው በአምሥት ዓመት ጊዜ ውስጥ ግማሹን የአገሪቱን የውጭ ንግድ በዩዋን ለማጠናቀቅ ነው። በአጠቃላይ ቻይና በዓለም የምንዛሪ ስርዓት ላይ በሚደረግ ለውጥ ጠቃሚ ሚና ይኖራታል።

መሥፍን መኮንን                     ሂሩት መለሰ