ዓለምአቀፉ ኤኮኖሚ ይዞታ | ኤኮኖሚ | DW | 14.11.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ዓለምአቀፉ ኤኮኖሚ ይዞታ

ከአራት ዓመታት በፊት ከአሜሪካ ተነስቶ ዓለምን ያዳረሰው የፊናንስ ቀውስ ያስከተለውን የኤኮኖሚ ተጽዕኖ በኢንዱስትሪ ልማት ከበለጸጉት መንግሥታት ይልቅ በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት ሃገራት በተሻለ ሁኔታ መቋቋም መቻላቸው ዛሬ በገሃድ የሚታይ ነገር ነው።

ከአራት ዓመታት በፊት ከአሜሪካ ተነስቶ ዓለምን ያዳረሰው የፊናንስ ቀውስ ያስከተለውን የኤኮኖሚ ተጽዕኖ በኢንዱስትሪ ልማት ከበለጸጉት መንግሥታት ይልቅ በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት ሃገራት በተሻለ ሁኔታ መቋቋም መቻላቸው ዛሬ በገሃድ የሚታይ ነገር ነው። በኤኮኖሚ አቅሟ በዓለም ላይ ቀደምቷ የሆነችው ዩ ኤስ አሜሪካ በከፍተኛ የበጀት ኪሣራና በሥራ አጥ ብዛት ተወጥራ እንደቀጠለች ሲሆን በአውሮፓም ከግሪክ እስከ ስፓኝ በርካታ ሃገራትን ማናጋት የያዘው የኤውሮ ዞን የዕዳ ቀውስ መዘዝ ቢቀር በፍጥነት ማሰሪያ የሚያገኝ አይመስልም።

እንግዲህ ዛሬ ቻይናንና ሕንድን የመሳሰሉት በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙ ሃገራት በሃይል አሰላለፍ ረገድ የጊዜው ተጠቃሚ ናቸው። የኤኮኖሚ ጥንካሬያቸውም ከጊዜ ወደጊዜ እየጠነከረ ነው የመጣው። የዕዳውን ይዞታ አስመልክቶ ታላቁ የጀርመን የገንዘብ ተቋም ዶቼ ባንክ ባካሄደው አዲስ ጥናት መሠረት እነዚሁ በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙ ሃገራት ባለፉት ዓመታት ዕዳቸውን በግማሽ ለመቀነስ ችለዋል።

መለስ ብሎ ለማስታወስ ባለፈው ምዕተ-ዓመት የመጨረሻ አሠርት፤ ማለትም በዘጠናኛዎቹ ዓመታት ከሞላ ጎደል ሁሉም ታላላቅ በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙ ሃገራት ቢቀር አንድ ጊዜ ከባድ ከሆነ የፊናንስ ቀውስ ላይ መውደቃቸው የሚዘነጋ አይደለም። በመጀመሪያ ሕንድ ከጎርጎሮሳውያኑ 1989 እስከ 1991 በአንድ በኩል በከፍተኛ የመንግሥት ወጪና በአንጻሩ አቆልቋይ በሆነ የግብር ገቢ የተነሣ ከኤኮኖሚና ከፊናንስ ቀውስ ላይ ትወድቃለች። በዚሁ የተነሣም የአገሪቱ ብድር የማግኘት አመኔታ እጅግ የመነመነ ነበር የሆነው።

በ 1994 ሜክሢኮ በዶላር አንጻር የተመደበውን የምንዛሪዋን የፔዞን ተመን ለመጠበቅ ባለመቻሏ የኋላ ኋላ ተኪላ የሚል ስያሜ በተሰጠው ቀውስ ትወጠራለች። ሶሥት ዓመታት ዘግየት ብሎም ደቡብ ኮሪያና ኢንዶኔዚያ፤ ከዚያ በዓመቱ ደግሞ ሩሢያና ብራዚል ችግር ይገጥማቸዋል። በ 2001 አርጄንቲናን የክፍያ አቅም ማሳጣቱ የሚታወሰው መንግሥታዊ ክስረትማ እስከዚያው ከደረሰው ቀውስ ሁሉ ታላቁ ነበር።

እንግዲህ በኤኮኖሚ ጠበብት ዘንድ ቀደምት ሆነው ከሚታዩት አሥር ዋና ዋና በተፋጠነ ዕድገት ላይ ያሉ ሃገራት መካከል በ90 ኛዎቹ ዓመታት ከከባድ ቀውስ ለማምለጥ የቻሉት ቻይናና ሳውዲት አረቢያ ብቻ ናቸው። ግን ለዶቼ ባንክ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉት የምጣኔ-ሐብት ባለሙያ ማርኩስ ዬገር እንደሚያስረዱት አሁን አብዛኞቹ ሃገራት ይገኙበት የነበረው ያ ሁኔታ ተለውጧል።

«ሁኔታው በጣሙን ነው የተሻሻለው። ይህ ደግሞ እነዚህ ሃገራት ከሞላ ጎደል በሙሉ ጤናማ የሆነ የኤኮኖሚ ፖሊሲ በማስፈናቸው የተገኘ ውጤት ነው። በተፋጠነ ዕድገት በሚራመዱት ሃገራት መንግሥታዊው ዕዳ እየቀነሰ ሲመጣ በአማካይ መስፈርት የውጭ ዕዳቸውም እንዲሁ ዝቅ ሊል በቅቷል»

በእርግጥም የአሥሩ ታላላቅ በተፋጠነ ዕድገት የሚራመዱ ሃገራት መንግሥታዊ ዕዳ አዲሱ ሚሌኒየም ከገባ ከ 2000 ዓመተ-ምሕረት ወዲህ ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርታቸው አንጻር በአማካይ ከ 50 ወደ 25 በመቶ ነው የቀነሰው። በግማሽ ማለት ነው። በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉት በቡድን 7 መንግሥታት ዘንድ በሌላ በኩል ዕዳው ይባስ ብሎ ከአጠቃላዩ ብሄራዊ ምርት አንጻር ከ 80 ወደ 120 በመቶ ክፍ ብሏል። ይህ የዶቼ ባንክ ተመራማሪ ማርኩስ ዬገር በጥናታቸው የደረበት ውጤት ነው።

ጥናቱ አያይዞ እንደሚያመለክተው በተፋጠነ ዕደገት ላይ የሚገኙት ሃገራት የውጭ የኤኮኖሚ ይዞታቸውንም አሻሽለዋል። ዛሬ አሥሩ ታላላቅ ተራማጅ ሃገራት ከአንድ አሠርተ-ዓመት በፊት ከነበረው ሲነጻጸር በጠነከረ ሁኔታ ከዓለም ኤኮኖሚ የተሳሰሩ ሆነው ነው የሚገኙት። ሆኖም ይህ ሌላ ተጽዕኖ መፍጠሩም አልቀረም። የነዚህ ሃገራት ከዓለም ንግድ ጠበቅ ባለ መልክ መተሳሰር ከውጭ ለሚፈጠር ጎጂ ተጽዕኖ እንዲጋለጡም ነው ያደረገው።

«የኤኮኖሚ ዕድገትን በተመለከተ ለውጩ ተጽዕኖ እየተጋለጡ መሄዳቸው በግልጽ የሚታይ ነገር ነው። ግን በተመሳሳይ ጊዜ ብዙዎቹ ሃገራት ችግሩን የመቋቋም ብቃት ለማዳበርም በቅተዋል። ይህም ዛሬ በፊናንስ ረገድ የተረጋጉ ሆነው የመገኘታቸው ውጤት ነው። ከዚህ በተረፈ እነዚሁ መንግሥታት በአብዛኛው በፊናንስ ገበዮች ዘንድም አመኔታን እያገኙ ነው የመጡት። ይህ ደግሞ የውጭ ባለሃብቶች በነዚህ ሃገራት መዋዕለ-ነዋይ እንዲያደርጉ የሚያበረታታ ነገር ነው»

በጥቅሉ የተሻሻለው የምጣኔ-ሐብት ይዞታ በተፋጠነ ዕርምጃ ላይ ለሚገኙት ሃገራት ግፊትን የሚያለዝብ ሰፊ የኤኮኖሚ ፖሊሲ ዕድልን ነው የፈጠረው። ምክንያቱም የዕዳው መለዘብ መንግሥታቱ ቀውስ በሚፈጠርበት ጊዜ በጀት የመቁረጥ ጫና እንዳይኖርባቸውና ከዚህ ባሻገርም አስፈላጊ ከሆነ ኤኮኖሚን ለማንቀሳቀስ ገንዘብ እንዲያወጡ የሚያደርግ ነው። ይህን ደግሞ ዬገር መለስ ብለው እንደሚያስታውሱት የ 2008ቱ ዓለምአቀፍ የፊናንስ ቀውስ አሳይቷል።

«አብዛኞቹ በተፋጠነ ዕድገት የሚራመዱ ሃገራት ከ80 እና ከ 90ኛዎቹ ዓመታት ሲነጻጸር በተከተለው አሠርተ-ዓመት በኤኮኖሚም ሆነ በፊናንስ ፖሊሲ ረገድ ችግሮቹን ለመቋቋም የበቁ ነበሩ። ይህ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው»

በጥቅሉ ሲታይ ቀደምቱ በተፋጠነ ዕድገት የሚራመዱ ሃገራት ዛሬ የፊናንስ ይዞታቸውን በጣሙን አሻሽለው ነው የሚገኙት። በአንጻሩ የበለጸጉት የቡድን 7 መንግሥታት የዕዳ ይዞታ ወቅታዊ ግምት እንደሚጠቁመው እስከያዝነው አሠርተ-ዓመት አጋማሽ፤ ማለትም እስክ 2015 ገደማ የባሰ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሳይደርስ አይቀርም። ይህም በዓመታዊ የኤኮኖሚ አቅም ሲሰላ ዕዳው ከተራማጁ ሃገራት አንጻር ስድሥት ዕጅ ከፍ ያለ ይሆናል ማለት ነው። እንግዲህ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት በተፋጠነ ዕርምጃ በመገስገስ ላይ የሚገኙትን ሃገራት በአርአያነት ቢከተሉ የሚበጃቸው ነው የሚመስለው።

«ጥያቄው አርቆ አስተዋይነት የሰፈነበት የኤኮኖሚና የፊናንስ ፖሊሲን ዕውን ማድረግ ነው። ይህ ደግሞ የምንዛሪና የፊናንስ ስርዓት ዕርጋታን ለማስፈን የግድ አስፈላጊ ይሆናል»

እርግጥ በተፋጠነ ዕርምጃ በመገስገስ ላይ ያሉትን ሃገራት በአርአያነት መውስዱ ቢጠቀስም እነዚህ መንግሥታትም ቢሆኑ ከችግር ነጻ ናቸው ማለት አይደለም። የኤውሮው ቀውስ ለምሳሌ ከበድ ካለ ችግር ተሰውረው በቆዩት በቻይና፣ በሕንድ፣ በብራዚልና፣ በሩሢያ ኤኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አልቀረም።

እነዚህ ባልተቋረጠ ዕድገት የኖሩት ሃገራት አጣዳፊ የሆነውን መዋቅራዊ ለውጥ በጊዜው አለማካሄዳቸው አሁን እየጎዳቸው ነው። ችግሩን በጥሩ ሁኔታ ተቋቁማለች ልትባል የምትችለው ምናልባትም ብራዚል ናት። አገሪቱ በዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም መረጃ መሠረት በኤኮኖሚ ግዙፍነት ኢጣሊያን ፈንቅላ ስድሥተኛው ቦታ ለመያዝ በቅታለች። አሁን ደግሞ አገሪቱ በተከታታይ በምታዘጋጃቸው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫና የኦሎምፒክ ጨዋታ ሳቢያ የያዘችው መዋቅራዊ ግንቢያና ሰፊ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ በመጨዎቹ ዓመታት ተጨማሪ እመርታ መሆኑ የማይቀር ነው።

በቻይና በአንጻሩ የኤኮኖሚው ዕድገት እንደቀድሞው ዓመት ከዓመት አሥር በመቶ እየሆነ የሚገሰግስበት ጊዜ ለጊዜው አልፏል። የወቅቱ 8 ከመቶ ገደማ የሚጠጋ የኤኮኖሚ ዕድገት ደግሞ ሰፊ ለሆነ ሕዝቧ በቂ የሥራ ቦታዎችን ለመክፈትና ማሕበራዊ ችግሮችን ለመቋቋም በቂ አይሆንም። በሕንድ አሮጌው መዋቅራዊ ይዞታ፣ የለውጥ መጓተት፣ ቢሮክራሲና ሙስና የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶችን የሚያስፈራራ ሆኖ ሲቀጥል በድሃና በሃብታም መካከል ያለው ልዩነትም ለኤኮኖሚ ዕርምጃ ለዘለቄታው አስፈላጊ የሆነው እርጋታ እንዳይሰፍን እንቅፋት ነው።

ሩሢያና ብራዚል በአንድ ወጥ የጥሬ ሃብት ይዞታ ላይ ሲያተኩሩ ለምሳሌ በሩሢያ ኤኮኖሚው የኤነርጂውን ዘርፍ ዋና መሠረቱ ያደረገ ነው። መንግሥታዊው ጣልቃ ገብነትም ለጤናማ የኤኮኖሚ ዕድገት የሚስማማ አልሆነም። እናም መዋቅራዊ ግንባታን በማፋጠን ሁል-ገብ ኤኮኖሚን ማራመድ እጅግ አጣዳፊ ይሆናል። ይህ ቢቀር በሩሢያ በአጭር ጊዜ ገቢር መሆኑ ያጠራጥረል።

ለማንኛውም የያዝነውን ሊገባደድ የተቃረበ ዓመት የ 2012-ን የኤኮኖሚ ይዞታ በተመለከተ የምጣኔ-ሐብት ጠበበት የሚሰጡት ግምት ወይም የሚያቀርቡት ትንበያ ለአብዛኞቹ የዓለም አካባቢዎች ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው የከፋ ነው። የዘንድሮው የኤኮኖሚ ዕድገት ካለፈው 2011 ሲነጻጸር ዝቅ ያለ እንደሚሆን አጠቃላይ ስምምነት አለ። አካባቢዎቹን በተናጠል ብንዳስስ በሰሜናዊው አሜሪካ አካባቢ ላይ የሚቀርበው ግምት ኤኮኖሚው የተረጋጋ እየሆነ እንደሚሄድ ነው።

ባለፈው ዓመት አጋማሽ ችግር ገጥሞት የነበረው የአሜሪካ ኤኮኖሚ መሻሻል ይታይበታል። የሥራ ገበያው ሁኔታም እንዲሁ! በጃፓን ሱናሚ ያስከተለው የኤኮኖሚ ቀውስ ተገትቷል ለማለት ይቻላል። ሆኖም በኤውሮ ዞን የዕዳ ቀውስ የተነሣ በፊናንስ ገበዮች ላይ የሚታየው ውዥቀት በአሜሪካና በተቀሩት ኤኮኖሚም ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ነው። በነገራችን ላይ በወቅቱ አበረታች ሂደት የሚታየው በነዳጅ ዘይት በታደሉት የመካከለኛ ምሥራቅ፣ የሰሜን አፍሪቃና ከሣሃራ በስተደቡብ ሃገራት ነው።

በአውሮፓ የያንዳንዱ አገር ቀውስ ላይ የመውደቅ አደጋ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ከፍተኛ እንደሆነ ይቀጥላል። የአንዳንድ የኤውሮ ሃገራት ቀውስ ገና በአስተማማኝ ሁኔታ አልተወገደም። እናም ግሪክን በመሳሰሉት በቀውሱ ክፉኛ በተጠመዱ ሃገራት በወቅቱ የኤኮኖሚ ዕድገት ጨርሶ ሊጠበቅ አይችልም። እናም ሁኔታው በኤውሮና በአውሮፓ የፊናንስ ገበዮች ላይ አደገኛ እንደሆነ የሚቀጥል ነው።

ዓመቱ በአጠቃላይ ሲታይ የኤኮኖሚ ዕድገት ማቆልቆል ነው የሚጠበቀው። ሌላው ቀርቶ ባለፈው ዓመት በሶሥት ከመቶ ዕድገት የአውሮፓ የኤኮኖሚ መንኮራኩር የነበረችው ጀርመን እንኳ ዘንድሮ ከ 0,4 ከመቶ ዕድገት በላይ ከፍ ማለቷ ያጠራጥራል። በእሢያ-ፓሢፊክ አካባቢ ግን የኤውሮን ቀውስ ተጽዕኖ ከእሢያ ለማራቅ ከተቻለ መጨው ጊዜ ብሩህ ነው።

የሆነው ሆኖ የረጅም ጊዜው ግምት የሚያሳየው በመጨረሻ በተፋጠነ ዕድገት ላይ ያሉት ቀደም ሲል የጠቀስናቸው የብሪክ ሃገራትና መሰሎቻቸው፤ ደቡብ ኮሪያ፣ ኢንዶኔዚያ፣ ኮሉምቢያ፣ ፔሩ፣ ቱርክ፣ ደቡብ አፍሪቃ ወዘተ እንደሚጠናከሩ ነው። ከዓለም ሕዝብ አርባ በመቶውን ለሚያቅፉት ለነዚህ ሃገራት ከእንግዲህ የወደፊት እንጂ የኋልዮሽ ዕርምጃ የሚኖር አይመስልም። የቅርቡን ዓለምአቀፍ የፊናንስ ቀውስ ከበለጸጉት መንግሥታት በተሻለ ሁኔታ መቋቋም መቻላቸው የሚያመለክተውም ይህንኑ አቅጣጫ ነው።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 14.11.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/16ii9
 • ቀን 14.11.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/16ii9