ዓለምአቀፉ ስፖርት በ 2011 ዓ.ም. | ስፖርት | DW | 12.12.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ዓለምአቀፉ ስፖርት በ 2011 ዓ.ም.

በመገባደድ ላይ ያለው የጎርጎሮሣውያኑ 2011 ዓ.ም. በአትሌቲኩ ዓለም ኬንያ የተሳካ የውድድር ዓመት በማሳለፍ ታሪካዊ ድሎችን ስትጎናጸፍ ወቅቱ በአንጻሩ ለኢትዮጵያ ያን ያህል የቀና አልነበረም።

default

ማካው

ባለፈው ነሐሴ ወር ደቡብ ኮሪያ-ዴጎ ላይ የተካሄደው 13ኛው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር በዝግጅቱ ብቻ ሣይሆን በውጤቱም እጅጉን ያስደነቀ ነበር። በአጭር ርቀት ሩጫ እንደተጠበቀው የጃማይካና የአሜሪካ አትሌቶች አይለው ሲታዩ ከመካከለኛ እስከ ረጅም ሩጫ ከዚያ ቀደም ባልታየ ጥንካሬ ድል በድል የሆነችው ደግሞ ኬንያ ነበረች። በዴጉው ሻምፒዮና ዩ,ኤስ.አሜሪካ በጥቅሉ 12 የወርቅ፣ አምስት የብርና ስምንት የናስ ሜዳሊያዎችን በማግኘት አንደኛ ስትሆን፤ ሩሢያ በዘጠኝ ወርቅ፣ ስምንት ብርና አምሥት ናስ ሁለተኛ ወጥታለች።

የሚያስገርም ሆኖ ጀርመንን መሰል አገር ከኋላቸው አስቀርተው ሶሥተኛና አራተኛ የሆኑት ኬንያና ጃሜይካ ነበሩ። የኬንያ አትሌቶች ለሶሥተኝነት የበቁት ከስምንት መቶ ሜትር እስከ ማራቶን ግንባር ቀደም በመሆን ሰባት የወርቅ፣ ስሥት የብርና አራት የናስ ሜዳሊያዎችን ለመሰብሰ በመቻላቸው ነው። ምሥራቅ አፍሪቃይቱ አገር እንዲህ ግዙፍ ልትሆን የቻለችው ደግሞ እርግጥ ያለ ምክንያት አይደለም። ዕርምጃው የኬንያ አትሌቲክስ ፌደሬሺን አገሪቱን ከኢትዮጵያ ጥላ ስር ለማውጣት ባለፉት ዓመታት ያደረገው ጥረት ውጤት ነው። ታላቅ የሥልጠና ዲሲፕሊን፣ በርካታ አገር-አቀፍ ውድድሮችና የሰከነ አሠራር ኬንያ በያንዳንዱ ርቀት ብዙ ተፎካካሪ የሆኑ አትሌቶችን እንድታፈራ ጠቅሟል።

በኢትዮጵያ በአንጻሩ ሃይሌ ገ/ሥላሴን፣ ቀነኒሣን ወይም ጥሩነሽ ዲባባን የመሳሰሉትን ዓለምአቀፍ ከዋክብት የሚተኩ አትሌቶች ዛሬ እንኳን በቅርብ በርቀትም አይታዩም። የዴጉው የዓለም ሻምፒዮናም ሆነ የተለያዩት የዓመቱ የማራቶን ሩጫዎች አጉልተው ያሳዩት ይህንኑ ሃቅ ነው። በዴጉው የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ኢብራሂም ጄይላን በአሥር ሺህ ሜትር ባስገኛት አንዲት የወርቅ ሜዳሊያ ስትወሰን ከአካል ጉዳቱ በሚገባ ሳያገግም በውድድሩ የተሳተፈው ቀነኒሣ በቀለ ሩጫውን ማቋረጡ ግድ ነበር የሆነበት። ኢትዮጵያ በው’ድድሩ ስምንተኛ ወጥታለች። የምሥራቃዊው አፍሪቃ የአትሌቲክስ ሃያል አገር እንግዲህ ለጊዜውም ቢሆን ከዙፋኗ ወርዳለች ለማለት ይቻላል።

ለዚህ ደግሞ በአገሪቱ ያለው የአሠለጣጠን ሁኔታና የአትሌቶች አያያዝ ትልቅ አስተዋጽኦ ሳይኖረው አልቀረም። ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሺን በኩል እንደሰማነው በቂ የሥልጠና ቦታዎች የሉም። አትሌቶች የዴጉውን ለመሳሰለው ዓለምአቀፍ ውድድር ለመጓዝ በራሳችሁ ተዘጋጅታችሁ ተገኙ እስከመባል መድረሳቸው ስለ ኢትዮጵያ አትሌቲክስ መጥፎ ይዞታ ስንክሣር ይናገራል። ኢትዮጵያ አበበ ቢቂላንና ማሞ ወልዴን፣ ሃይሌንና ቀነኒሣን፣ ደራርቱ ቱሉንና ፋጡማ ሮባን፣ ጥሩነሽ ዲባባንና መሠረት ደፋርን የመሳሰሉ ዓለም ያወቀ፤ ያደነቃቸው አትሌቶችን ያፈራች አገር ናት። አትሌቶቿ በረሃብና በድርቅ የጎደፈ ገጽታዋን ሲያሳድሱ፤ ሰንደቅ ዓላማዋ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ሲያደርጉ ኖረዋል። ታዲያ ሃቁ ይህ ሲሆን መንግሥትና ፌደሬሺን ተገቢውን ክብርና ክብደት ሰጥተው ስፖርቱን የሚገባውን ያህል አለመንከባከባቸው በጣሙን ያሳዝናል’፤ የሚያሳፍር ነው።

በመገባደድ ላይ ባለው 2011 ዓ.ም. ኢትዮጵያ የዓለም የማራቶን ክብረ-ወሰኗንም ተነጥቃለች። ሃይሌ ገ/ሥላሴ ከሁለት ሰዓት አራት ደቂቃ በታች በመሮጥ በማራቶን ታሪክ የመጀመሪያ ሰው ሆኖ ሲቆይ ክብረ-ወሰኑ በዚያው በተመዘገበበት በበርሊን ባለፈው መስከረም ወር በኬንያዊው አትሌት በፓትሪክ ማካው ሊሰበር በቅቷል። ማካው የሃይሌን ክብረ-ወሰን በ 21 ሤኮንዶች ወደ ሁለት ሰዓት ከሶሥት ደቂቃ 38 ሤኮንድ ጊዜ ነበር ያሻሻለው። ታዲያ ለሃይሌ የሚያሳዝነው በውድድሩ ክብረ-ወሰኑን ማጣቱ ብቻ አይደለም። ትንፋሽ አጥሮት ከ 35 ኪሎሜትር በኋላ ሩጫውን አቋርጦ መውጣቱ ጭምር እንጂ! እንግዲህ ዓመቱ የሚገባደደው ኢትዮጵያ ልዕልናዋን ለኬንያ ማስረከቧ ለይቶለት ነው።

Frauen Fußball WM Japanische Nationalmannschaft

የጃፓን ብሄራዊ ቡድን

የዓለም እግር ኳስ በ 2011 ዓ.ም.

በመገባደድ ላይ ባለው 2011 ዓ.ም. አንዱ ታላቅ የእግር ኳስ ዝግጅት በዚህ በጀርመን የተካሄደው የሴቶች የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ነው። በዘጠኝ ግሩም ስታዲዮሞች የተካሄደው ውድድር በዝግጅቱም ሆነ በድምቀቱ እስከዚያው አቻ ያልታየለት ነበር። ብዙ የስፖርት አፍቃሪዎች ወደ ስታዲዮሞች ሲጎርፉ በቴሌቪዥን አማካይነትም ውድድሩን በዓለም ዙሪያ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ተከታትሎታል። ጀርመን ያስተናገደችው ይሄው የዓለም ዋንጫ ውድድር የሴቶች እግር ኳስ ከፍተኛ የቴክኒክና የአካል ጥንካሬ ዕርምጃ ማድረጉ የተመሰከረበትም ነበር። በምድብ ዙር ጀምሮ በጥሎ ማለፍ ግጥሚያዎች በቀጠለው ውድድር በመጨረሻ ፈረንሣይ፣ አሜሪካ፣ ስዊድንና ጃፓን ለግማሽ ፍጻሜ ሲደርሱ የሃያላኑ ቡድኖች የብራዚልና የጀርመን በሩብ ፍጻሜው መቀጨት ብዙዎችን ነበር ያስደነቀው። ሆኖም ግን የኋላ ኋላ እንደታየው ጃፓን የሁለት ጊዜዋን የዓለም ዋንጫ ባለቤት ጀርመንን ያስወጣችው እንዲያው በዕድል አልነበረም። የጀርመኗ አሠልጣኝ ሢልቪያ ናይድም ሽንፈቱን በመጨረሻ በጸጋ ነበር የተቀበለችው።!

“ቡድናችን የተቻለውን ሁሉ ነው ያደረገው። ከቡድናችን በስተጀርባ የቆመው ቡድንም እንዲሁ። ስለዚህም ማንንም ለመውቀስ አልችልም”

በቴክኒክ ረገድ ባልተጠበቀ ሁኔታ ጠንካራ ሆኖ የተገኘው የጃፓን ቡድን በፍጻሜው አሜሪካን ከተጨማሪ ሰዓት በኋላ በፍጹም ቅጣት ምት 5-3 በማሸነፍ ዋንጫውን ሲወስድ ድሉ ትሱናሚ ከባድ ጥፋት ባደረሰባት አገር ታላቅ መጽናኛ፤ የተሥፍ ምንጭ ነበር የሆነው።

በወንዶች እግር ኳስ በክለቦች ደረጃ በዚህ ዓመትም በድንቁ አርጄንቲናዊ በሊዮኔል ሜሢ የሚዘወረው ኤፍ.ሢ.ባርሤሎና የሁሉም ነገር መለኪያ እንደሆነ ሲቀጥል ብሄራዊ ቡድኖችን በተመለከተ የተለመደው የብራዚል ልዕልናም ሆነ የአዳዲስ ከዋክብት ትንሣዔ እምብዛም ገሃድ አልሆነም። የአምሥት ጊዜዋ የዓለም ዋንጫ ባለቤት ብራዚል እንዲያውም እንደያዝነው ዓመት ደካማ በሆነ ሴሌሣዎ፤ ማለት ብሄራዊ ቡድን የተወከለችበት ጊዜ ጨርሶ አይታወስም። ታላቁ ፔሌ ከማራዶና ይበልጣል ሲል ያወደሰው ወጣት ኮከብ ንያማርም ቢሆን ባለፈው ኮፓ አሜሪካ እንደታየው ያን ያህል የሚደነቅ አልነበረም። የማራዶናን ጫማ አጥልቆ ካልመጣ በስተቀር! እንግዲህ ዓለም በዚህ ዓመትም ያሏት ድንቅ ተጫዋቾች ሜሢ፣ ክቲስቲያኖ ሮናልዶ፣ ሻቪ፣ ኢኒየስታ ወዘተ. እንደሆኑ ይቀጥላሉ።

አርጄንቲናም ቢሆን በርካታ ግሩም ተጫዎቾች ማፍራቷን ብትቀጥልም ቅሉ እንደቀድሞው ጥሩ ብሄራዊ ቡድን መቅረጽ ግን አልሆነላትም። በላቲን አሜሪካ በአንጻሩ ሃያል በመሆን ትንሣዔ ያደረገችው የሁለት ጊዜዋ የዓለም ዋንጫ ባለቤትና የዚህ ዓመቱ የኮፓ አሜሪካ አሸናፊ ኡሩጉዋይ ናት። ኡሩዎች ባለፈው ዓመት የደቡብ አፍሪቃ የዓለም ዋንጫ ውድድር እስከ ግማሽ ፍጻሜ ከደረሱ ወዲህ ደቡብ አሜሪካ ውስጥ ግንባር ቀደም እየሆኑ ነው። በጥቅሉ የዓለም እግር ኳስ ብዙ ባይጠነክርም በዚህ በአውሮፓ ጀርመን ወጣት ቡድን በመቅረጽ ያደረገችው እመርታ ግን ሊደነቅ የሚገባው ነው። አሠልጣኙ ዮአኺም ሉቭ ያነጸው ወጣት ቡድን በወዳጅነት ግጥሚያዎች ጠንካሮቹን ብራዚልንና ኔዘርላንድን በልዕልና ሲረታ በአውሮፓ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድርም በአሥር ግጥሚያዎች አሥር ጊዜ ነው ያሸነፈው። እናም የመጪውን ዓመት የአውሮፓ ዋንጫ ውድድር የማሽነፍ ታላቅ ዕድል ነው የሚሰጠው። ያስደስታል፤ የጀርመን ብሄራዊ ቡድን በታንኮች የሚመሰልበት ጊዜ ማለፉ!

በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ኢትዮጵያ ለሚቀጥለው ዓመት የአፍሪቃ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር በተደረገው ማጣሪያ እንደገና ለማለፍ ሳትችል ስትቀር በዘንድሮው የምሥራቅና ማዕከላዊ አፍሪቃ ዋንጫ ውድድርም ተሳትፎዋ እንዳለፈው ዓመት አልሰመረላትም። በመጀመሪያው የምድብ ዙር ተሰናክላ ቀርታለች። በነገራችን ላይ ዋንጫውን ባለፈው ሰንበት የወሰደችው ሩዋንዳን ከተጨማሪ ሰዓት በኋላ በፍጹም ቅጣት ምት 3-2 ያሸነፈችው ኡጋንዳ ናት።

Sebastian Vettel in Sao Paulo Brasilien 2011 Formel 1

የአውቶሞቢል ስፖርት

በፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም ወጣቱ ጀርመናዊ የሬድ-ቡል ዘዋሪ ዜባስቲያን ፌትል በዚህ ዓመትም በተለየ ልዕልና ድሉን ደግሞታል። ፌትል በ 19 እሽቅድድሞች 11 ጊዜ ሲያሸንፍ ድሉን ያረጋገጠው ገና አምሥት ውድድሮች ቀርተው ሳለ ነበር። የ 24 ዓመቱ ወጣት በዚህ ከቀጠለ በመጪዎቹ ዓመታትም ስኬት እንደማይለየው አንድና ሁለት የለውም። በቴኒስ ደግሞ የሰርቢያው ኖቫክ ጆኮቪችና የዴንማርኳ ካሮሊን ቮዝኒያችኪ በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ቀደምቱ እንደሆኑ ነው ወደ አዲሱ ዓመት የሚሻገሩት።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic