ዓለምን የከፋፈለው የአሜሪካ የሚሳይል ጥቃት በሶርያ | ዓለም | DW | 10.04.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ዓለምን የከፋፈለው የአሜሪካ የሚሳይል ጥቃት በሶርያ

ዩናይትድ ስቴትስ በሶርያ መንግሥት ላይ ባለፈው ሐሙስ የወሰደችው ጥቃት ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ «አስፈላጊ በቀል» ለሩሲያ እና ኢራን «ጠብ ጫሪነት» ለኧል-አሳድ እና መንግሥታቸው ደግሞ «ግድየለሽ እና ኃላፊነት የጎደለው» እርምጃ ነው።  

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:58

ዓለምን የከፋፈለው የአሜሪካ የሚሳይል ጥቃት በሶርያ

የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በበሺር ኧል-አሳድ መንግሥት ላይ እርምጃ ለመውሰድ ሲሰናዱ አጥብቀው ያወገዙት ዶናልድ ትራምፕ ያሳለፉትን ውሳኔ የአገራቸውን ብሔራዊ ደኅንነት ለማስጠበቅ የታለመ ብለውታል። 
«በዕለተ-ማክሰኞ የሶርያው አምባገነን በሺር ኧል-አሳድ በንጹሃን ሰላማዊ ሰዎች ላይ አደኛ አሰቃቂ የኬሚካል ጥቃት ፈጽመዋል። አሳድ የደካማ ወንዶች፤ ሴቶች እና ሕፃናትን ሕይወት ነጥቀዋል። ዛሬም ምሽት በሶርያ የኬሚካል ጥቃቱ በተጀመረበት የጦር አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ወታደራዊ ጥቃት እንዲፈጸም ትዕዛዝ አስተላልፊያለሁ።»

በሜድትራኒያን ባሕር ላይ ከሚንሳፈፉ የዩናይትድ ስቴትስ መርከቦች የተምዘገዘጉት ሚሳይሎች ከሖምስ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘውን የሻራያት የጦር አውሮፕላኖች ማረፊያ ደብድበዋል።ጥቂት ደቂቃዎች የፈጀው የኃይል እርምጃ የጦር አውሮፕላኖችን ከነ መጠለያቸው የአውሮፕላን ነዳጅ ማጠራቀሚያ፤ የቁሳቁስ መጋዘን፤ የአየር መከላከያ እና ራዳር እንዲሁም የጥይት መጋዘን አውድሟል። 
የሚሳይል ድብደባው ዓለምን ከሁለት ጎራ ከፍሎታል። የዩናይትድ ስቴትስ አጋሮች ይበል ባይ ናቸው። የጀርመኗ መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል እና የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ ባወጡት የጋራ መግለጫ የዩናይትድ ስቴትስን ጥቃት ደግፈዋል። ሁለቱ መሪዎች ለጥቃቱ መፈጸም ኃላፊነቱን የሚወስዱት የየሶርያው ፕሬዝዳንት በሺር ኧል-አሳድ ናቸው ሲሉ ኮንነዋል። የአውሮጳ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ቱስክ የሚሳይል ድብደባው አሰቃቂውን የኬሚካል ጥቃት ለማስቆም አስፈላጊ ነው ሲሉ ተስማምተዋል። የሰሜን ጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት አጋሮች የሆኑት ዩናይትድ ኪንግደም፤ ቱርክ እና ጣልያንም የኃይል እርምጃው አዎንታዊ ነው ባይ ናቸው። 

በሌላ ወገን የቆሙት ሩሲያ እና ኢራን የባላንጣቸውን እርምጃ ኮንነዋል። የበሺር ኧል-አሳድን መንግሥት በፖለቲካ እና ወታደራዊ ኃይል የምትደግፈው ሩሲያ እርምጃው ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ያሻክረዋል ሥትል ሥጋቷን ገልጣለች። የኃይል እርምጃው በሽብር ላይ ለተከፈተው ዓለም አቀፍ ዘመቻም እንቅፋት ነው ባይ ነች ሩሲያ። አገራቸው ከሩሲያ ጋር ያላትን ወዳጅነት ለማረቅ በተደጋጋሚ ቃል የገቡት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሁነኛ ፈተና የገጠማቸው ይመስላል። ሩሲያ ከጥቃቱ በኋላ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በሶርያ የነበራትን ወታደራዊ ሥምምነት ለጊዜው ማቋረጧን አስታውቃለች። ሥምምነቱ የሩሲያ እና የዩናይትድ ስቴትስ ወታደራዊ ኃይሎች በሶርያ በሚወስዱት የኃይል እርምጃ ድንገተኛ/ያልታሰበ ግጭት ውስጥ እንዳይገቡ የታቀደ ነበር። የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መንግሥት የሶርያን የአየር መከላከያ  እንደሚያጠናክር አስታውቋል። የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ባሕራም ጋሴሚ ባወጡት መግለጫ የዩናይትድ ስቴትስ የሚሳይል ጥቃት «እየተዳከሙ የነበሩትን አሸባሪዎች መልሶ የሚያደራጅ» ነው ሲሉ ኮንነዋል። ውጭ ጉዳይ ሚኒስሩ ዣቫድ ዛሪፍ በበኩላቸው ዩናይትድ ስቴትስ በሶርያ እና በየመን ከኧል-ቃዒዳ እና ራሱን 'እስላማዊ መንግስት' ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ኃይል ጎን ወግና እየተዋጋች ነው ሲሉ ወቅሰዋል። 

የጸጥታው ምክር ቤት ከወዴት አለ?

በዕለተ አርብ በተሰበሰበው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ጉባኤ አንዴ የሶርያው በሺር ኧል-አሳድ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ እና አጋሮቿ ተወግዘዋል። ሩሲያም መተቸቷ አልቀረም። ዩናይትድ ስቴትስ በሶርያ የወሰደችውን የኃይል እርምጃ ያወገዙት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቦሊቪያ አምባሳደር ሳቻ ሎሬንቲ ዓለም አቀፍ ሕግ ተጥሷል ብለዋል።  «እያንዳንዱ ነገር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ሊስተናገድ ይገባል። ኃይልን መጠቀም ሕጋዊ የሚሆነው ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንቀፅ 51 ጋር ሲጣጣም እና ራስን ለመከላከል ሲሆን ብቻ ነው። እንዲህ አይነት ተግባር የጸጥታው ምክር ቤት ሊያጸድቀው ይገባል።» የቢሊቪያውን አምባሳደር ወቀሳ ለብሪታኒያ ኧልተዋጠላትም። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር ማቲው ራይክሮፍት «ከእኔ በፊት የተናገሩት ግለሰብ ከአሳድ ይልቅ በዩናይትድ ስቴትስ ድርጊት መበሳጨታቸውን ስመለከት ጥልቅ ሐዘን ይሰማኛል። ባለፈው ማክሰኞ የአሳድ መንግሥት ሆን ብሎ የኬሚካል ጦር መሳሪያ በመጣል አሰቃቂ በሆነ መንገድ በርካታ ሰዎች ገድሏል። ከሦስት ዓመት ተኩል በፊት የሶርያ መንግስት የኬሚካል ጦር መሳሪያ መጠቀም የሚያግደውን ውል የመፈረሙ 189 አገሮችን ለመቀላቀል ቃል ገብቶ ነበር። የኬሚካል ጦር መሳሪያዎቻቸውን ብዛት ለማሳወቅ እና ለማጥፋት ተስማምቶ ነበር። ይኸን ቃል የተከተለው ግን የኬሚካል ጥቃት ነበር። በጉታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተገደሉ።» ሲሉ ተደምጠዋል። የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ቋሚ እና ተለዋጭ አባላት በሶርያ የተፈጸሙ የኬሚካል ጥቃቶችን ለመመርመር የሚያስችል የውሳኔ ኃሳብ አርቅቀዋል። የውሳኔ ኃሳቡ ድምፅን በድምጽ የመሻር ሥልጣን ያላቸው ሩሲያ እና ቻይና ድጋፍ ማግኘቱ ግን አጠራጣሪ ነው። 

የዩናይትድ ስቴትስ አዲስ የጦር ግንባር-ሶርያ? 

ለስድስት ዓመታት በዘለቀው የሶርያ የርስ በርስ ጦርነት ዩናይትድ ስቴትስ ቀጥተኛ ተሳትፎ ስታደርግ የአሁኑ የሚሳይል ጥቃት የመጀመሪያው ነው ።በበሺር ኧል-አሳድ ኃይሎች ሳይፈጸም አይቀርም ለተባለው የኬሚካል ጥቃት የበቀል እርምጃ ነው የተባለው የዶናል ትራምፕ ውሳኔ አሜሪካንን ወደ ውስብስቡ የርስ በርስ ጦርነት ጎትቶ ሊያስገባት ይችላል የሚል ሥጋት እየተደመጠ ነው። በመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው የጀርመኑ ዚነት መፅሔት ዋና አርታኢ ዳንኤል ጌርላክ የዩናይትድ ስቴትስ የሚሳይል ድብደባ  ተምሳሌታዊ መልዕክት ከማስተላለፍ የዘለለ ትርጉም የለውም። 
«ትልቅ ተምሳሌታዊ መልዕክት ነው ብዬ አስባለሁ። ያን ያክል ወታደራዊ ተፅዕኖ የሚያመጣ ግን አይመስለኝም። 60 ሚሳይል መተኮስ አስደናቂ እና ከፍተኛ ጉዳት የሚያመጣ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን የተመታው የጦር አውሮፕላን ማረፊያ ያን ያክል ግልጋሎት የሚሰጥ አልነበረም። ስለዚህ ትረምፕ በዚህ እርምጃ ለሩሲያ ለአጋሮቻቸው እንዲሁም ለሶርያ መንግሥት 'እንዲህ አይነት እርምጃዎች እንወስዳለን፤ ተጠንቀቁ' የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።» 

ትራምፕ በዕለተ-ቅዳሜ ለአገራቸው ምክር ቤቶች በፃፉት ደብዳቤ «አስፈላጊ እና ተገቢ ሲሆን ተጨማሪ እርምጃ እወስዳለሁ ብለዋል። የሚሳይል ጥቃቱ በሺር ኧል-አሳድን የሚደግፉትን ሩሲያ እና ኢራን ሊተነኩስም ይችላል። የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ ጄፍ ዴቪስ አገራቸው ለሩሲያ አስቀድማ ማሳወቋን ተናግረዋል። ከጎርጎሮሳዊው 1980ዎቹ ጀምሮ ከሶርያ ጋር ራስን በጋራ የመከላከል ወታደራዊ ስምምነት ያላት ኢራን በቀጣናው በዩናይትድ ስቴትስ ላይ ጥቃት ሊፈጽሙ የሚችሉ አጋሮች አሏት። የዩናይትድ ስቴትስ እርምጃ ለበሺር ኧል-አሳድ ማስጠንቀቂያ ይሁን ቋሚ የጦር ግንባር እስካሁን በግልፅ የታወቀ ነገር የለም። አሜሪካውያን ግን የፕሬዝዳንታቸውን እርምጃ ተገቢነት ይጠራጠራሉ። 

ከኧል-ቃኢዳ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ታጣቂዎች ጨምሮ በተቃዋሚዎች ቁጥጥር ሥር በሚገኘው ሰሜናዊ ሶርያ የኢድሊብ ከተማ በኬሚካል የጦር መሳሪያ በተፈጸመው ጥቃት ወደ 100 የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል። የሶርያ ሰብዓዊ መብቶች ታዛቢ ቡድን እና የሕክምና ባለሙያዎች እንደገለጡት ከሟቾቹ መካከል 20 ሕፃናት ይገኙበታል። የዓለም ጤና ድርጅት የጥቃቱ ሰለባዎች ሳሪን የተሰኘው ገዳይ ኬሚካል መጋለጣቸውን አስታውቋል። ጥቃቱን የፈጸመው ወገን ማንነት ግን እስካሁን በውል አልታወቀም። ለስድስት ዓመታት ከዘለቀው የርስ በርስ ጦርነት በኋላም ዓለም ለጥቃቱ የሰጠው ምላሽ ከቀደሙት የተለየ አልነበረም። የሶርያ መንግሥት ጥቃቱን አልፈጸምኩም ሲል ካደ፤ ሩሲያ የሶርያ አየር ኃይል በተቃዋሚዎች የጦር መሳሪያ ማከማቻ ላይ የፈመጸው ጥቃት መርዛማ ኬሚካል ወደ አየር እንዲገባ አድርጓል ስትል አስተባበለች፤ ምዕራባውያኑ አምባገነን የሚሏቸውን የሶርያ መሪ አወገዙ። 

«ሶርያ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ለመጠቀሟ ምንም ክርክር ሊኖር አይገባም። በዚህም የኬሚካል ጦር መሳሪያ ላለመጠቀም የተላለፈውን ድንጋጌ ጥሳለች። የአሳድን ጠባይ ለመቀየር ለዓመታት የተደረገው ጥረት አልሰመረም። በዚህም ምክንያት የስደቱ ቀውስ እየከፋ የቀጣናው ደኅንነትም እየተቃወሰ መሔዱን ቀጥሏል። ይኸ ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ እና አጋሮቿን ያሰጋል።»
ከአራት ዓመታት በፊትም ከደማስቆ አቅራቢያ በተፈጸመ ተመሳሳይ ጥቃት 1400 ሶርያውያን ተገደሉ። የያኔው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ቀይ መስመር አሰመሩ። ሩሲያ የበሺር ኧል-አሳድ መንግስት የኬሚካል ጦር መሳሪያውን እንደሚያስወግድ ቃል ገባች። ዓለም አቀፍ አጣሪ ቡድን የጦር መሳሪያዎቹ መውደማቸውን አስታወቀ። ከአራት ዓመታት በኋላ ተደገመ-በኢድሊብ። የብሪታንያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንም እንደ ትራምፕ ሁሉ ኃላፊነቱን በበሺር ኧል-አሳድ ትከሻ ላይ ጥለውታል።  «ከተገደሉት ወደ 400,000 የሚገመቱ ሶርያውያን ለአብዛኞቹ ሞት ኧል-አሳድ ተጠያቂ ናቸው» ይላሉ የብሪታኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር። ቦሪስ ጆንሰን በጎርጎሮሳዊው 1925 ዓ.ም የተፈረመው የጄኔቫ ሥምምነት የኬሚካል ጦር መሳሪያ መጠቀምን እንደሚከለክል አስታውሰዋል። የጀርመኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒሥትር ዚግማር ጋብርኤል ይሕ ድርጊት ኧል-አሳድን የጦር ወንጀለኛ ያደርጋቸዋል ባይ ናቸው። ውጭ ጉዳይ ሚኒሥትሩ ጀርመን ለሶርያ እርዳታ ካዘጋጀችው 1.2 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ አሳድ ሥልጣን ካለቀቁ በቀር ሽራፊ ሳንቲም ለመሰረተ-ልማት ግንባታ እንደማይውል አስታውቀዋል።ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሶርያ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚመረምር ገለልተኛ ወገን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በኩል ባለፈው ታኅሳስ ቢያቋቁምም በቂ ገንዘብ ማግኘት ተስኖታል። ገለልተኛ እና እና ነፃ ይሆናል የተባለው ዓለም አቀፍ መርማሪ በሶርያ የሚፈጸሙ የጦር ወንጀሎችን የተመለከቱ መረጃዎችን በመሰብሰብ እና በማጠናቀር በሒደት በደል ፈፃሚዎቹን ለፍርድ ያቀርባል ተብሎለት ነበር። ይኸው መርማሪ ሥራውን ለመጀመር 13 ሚሊዮን ዶላር ቢያስፈልገውም በቂ ገንዘብ አላገኘም። 

ተፈልጎ የጠፋው ፖለቲካዊ መፍትሔ 

ገንዘብ፤ሥልጣን እና ኃይል ያላቸው ልዕለ ኃያላን ወገን ለይተው ሲወቃቀሱ እና ሲወጋገዙ የርስ በርስ ጦርነቱ ሲከፋ፤ የሟቾቹ ቁጥር ሲጨምር ስድስት ዓመታት ተቆጠሩ። የብሪታኒያው መከላከያ ሚኒሥትር ሚሼል ፋሎን ሰንደይ ታይምስ በተሰኘው የአገራቸው ጋዜጣ በዕለተ-እሁድ ባስነበቡት የግል አስተያየታቸው በኬሚካል ጥቃት ለሞቱት ሶርያውያን በተዘዋዋሪም ቢሆን ሩሲያ ተጠያቂ ነች ብለዋል። ወደ ሞስኮ ለጉብኝት የማቅናት እቅድ የነበራቸው ውጭ ጉዳይ ሚኒሥትር ቦሪስ ጆንሰን ጉዟቸውን መሰረዛቸውን የገለጡ ሲሆን የዩናይትድ ስቴትሱ አቻቸው ሬክስ ቴይለርሰን ደግሞ ሩሲያን በማስረጃ እሞግታለሁ ብለዋል። በሺር ኧል-አሳድ ገለል የማለት አዝማሚያ አላሳዩም። ሩሲያን ጨምሮ ልዕለ ኃያላኑ እዚህም እዚያም የሞከሯቸው ድርድሮችም አልሰመሩም። 


እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች