1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዐብይና የለማ ፍቅርና ጠብ

ሰኞ፣ ኅዳር 22 2012

በተለይ አቶ ለማ ከኦሮሚያ ርዕሠ-መስተዳድርነት ወደ መከላከያ ሚንስትርነት ከተቀየሩ ጊዜ ጀምሮ ሁለቱ ፖለቲከኞች መቃቃራቸዉ በሰፊዉ ሲነገር ነበር።ሁለቱ ፖለቲከኞችም ሆኑ ደጋፊዎቻቸዉ ግን ልዩነት መኖሩን እስካለፈዉ ሳምንት ማብቂያ ድረስ በይፋ አልተናገሩም

https://p.dw.com/p/3U6i4
Lema Megerssa
ምስል DW/S. Teshome

ማሕደረ ዜና፦ ዐብይና ለማ የአንድነት-ፍቅር ጊዜዉ «ፍፃሜ»

መጋቢት 2010።አዲስ አበባ።

ኃምሌ 2010።ዋሽግተን።

አብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ አንድም ሁለትም ናቸዉ አለ።ዛሬስ? ያፍታ ዝግጅታችን ጥያቄ ነዉ።አብራችሁን ቆዩ።

የሩሲያን ዛራዊ ፈላጭ-ቆራጭ አገዛዝ በመቃወማቸዉ በየፊናቸዉ ከሐገራቸዉ የተሰደዱት ሁለቱ በሳል፣ ጠንካራ፣ ፅኑዕ፣ አርቆ አሳቢ ሩሲያዉያን ለንደን ብሪታንያ ላይ ፊት ለፊት ተገናኙ።1900።

«ከዚያ ወደ ለንደን ሔደ።እዚያ በሚኖርበት ባንዱ ቀን ትሮትስኪ በሩን አንኳኳ።ሌኒን በትሮስትስኪ የአቀራራብ ለዛ፣ በፖለቲካ ብስለትና እዉቀቱ ተማረከ።ወዲያዉም ቶሮትስኪን የነፀብራቅ (ኢስክራ) ጋዜጣ የአርታኤ ቡድን አባል አደረገዉ።ርዕሠ-አንቀፅ እና የፖለቲካ መጣጥፍ ፀሐፊ ሆነ።

ቭላድሚር ኢሊየች ኡሉያኖቭ (ሌኒን) እና ሊዮ ዳቪዶቪች ብሮኒስቲን (ትሮትስኪ)በክፍለ ዘመኑ መጀመሪያ ላይ የመሰረቱትን  ወዳጅነት አፅንተዉ፣ ከሞስኮ እስከ ሐቫና፣ ከቤጂንግ እስከ አዲስ አበባ ዓለምን ያጥለቀለቀዉን ርዕዮተ ዓለምን ሞስኮ ላይ ገቢር አደረጉ።

ዓለምን ለበጎ ይሁን ለመጥፎ የለወጡት ኃይለኞች ጥብቅ ወዳጅነት ግን አልቀጠለም።እንዲያዉም ጠቡ ንሩ የሌኒን ተካዮች ትሮትስኪን እስከማጥፋት በደረሰ ክፋት አሳርጓል።

አዲስ አበባ ላይ «ለትሮትስካዮቶች ዉርዉር የስታሊን በትር» እየተባለ ከመዛት መፎከሩ በፊት የማኦ ዜ ዱንግ እና የዴንግ ሺዮፒንግን፣ የፊደል ካስትሮና የቼ ጉቬራን ጥብቅ ወዳጅነትና ልዩነት የሚጥቀሱ አሉ።የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማርያምና የኮሎኔል አጥፋ አባተ፣ የመለስ ዜናዊና የነተወልደ ወልደማርያም ጓዳዊ ፍቅርን እና ጠላትነትንስ ያጤና እና ያጠናዉ አለ ይሆን?

የሌኒንና የትሮትስኪ ወዳጅነት በተመሰረተ በመቶኛ ዓመቱ ግድም ሁለት የምዕራብ ጀርመን ፖለቲከኞች የጀመሩት ፖለቲካዊ ትስስር ለካፒታሊስቱ ዓለም ምናልባትም ለዘመኑ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ፍቅርና ጠብ እንደቅርብ ጊዜ አብነት የሚጠቀስ ነዉ።

ምናልባት የጀርመንን የቅርብ ዘመን ፖለቲከኞች የሚያዉቁ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይን ያዉ በቴሌቪዥን ሲያዩ ያስታዉሷቸዉ ይሆናል።ወይም ይቅር። እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ከ1990ዎቹ አጋማሽ እስከ 2 ሺ አስራዎቹ ድረስ፣ መድረክ ላይ እንደ ጥሩ ተዋኝ እየተንጎራደደ፣ ማይክሮፎን ካሜራ ፊት እንደ በሳል ጋዜጠኛ እየተዝናና ፖለቲካዉን የሚሰልቅ፣ ነጎድጓዳ ድምፅን፣ ከማራኪ ተክለ ሰዉነት ጋር የተሰጠዉ ጀርመናዊ ፖለቲከኛ ካያችሁ እሱን ጌርሐርት ሽረደር በሉት።

Friedensnobelpreis 2019 Äthiopien | Ministerpräsident Abiy Ahmed
ምስል picture-alliance/dpa/B. Pedersen

ሰዉዬዉ፣ ከማርክሳዊዉ አስተሳሰብ ወደ ቀኝ ፈንጠር፣ ከካፒታሊስቱ ሶሻል ዴሞክራሲ ወደ ግራ ዘንበል፣ ለታችኛዉ መደብ ወገን፣ ካፒታሊስቱ ላይ ጨከን የሚል መርሕ የሚያቀነቅን፣ የማደራጀት ክሒልን ከፖለቲካ ጥበብ ጋር የተካነ ከሆነ ግን እሱ ኦስካር ላፎንቴ ነዉ።

ለማ መገርሳን ይመስሉ ይሆን?

ብቻ ላፎንቴ የምሥራቅና የምዕራብ ጀርመኖች ዳግም አንድነት በተለይም የምጣኔ ሐብቱ ፍፁም ዉሕደት እንዲዘገይ አጥብቀዉ ይከራከሩ ነበር።ይሕ አቋማቸዉ በ1990 በአንዲት ሴት በጩቤ አስወግቷቸዉ ነበርም።

ከ1995 ጀምሮ (እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ተቃዋሚዉን የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (SPD) ሊቀመንበር ነበሩ።በ1998 መስከረም በተደረገዉ ምርጫ ግን  ለመራሔ መንግስትነት እራሳቸዉን ከማጨት ይልቅ ሥፍራዉን ለጌርሐርት ሽረደር ለቀቁ።

በኢትዮጵያ 2010 የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅትን ሊቀመንበርነትን ፤ በዉጤቱም የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ዕጩነት ጎንበስ ብለዉ ለዐብይ ያሳለፉት ፖለቲከኛ ማን ይሆኑ?

እዚሕ ጀርመን የላፎንቴ ብልጠት፣ ጥበብና ሥልት፣ ከሽረደር አቀራረብ፣ የቅስቀሳ ክሒልና አንደበተ ርዕትነት ጋር ተዳምሮ፤  ለ16 ዘመን የመሪነት ልምድ ያካበተዉን የሔልሙት ኮልን ክርስቲናዊ ዴሞክራሲያዊ ሕብረት (CDU)ን መንግሎ የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (SPD)ን ለመሪነት አበቁ።መስከረም 1998 (እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።)

ሥልጣን በያዙ በመንፈቁ ግን የSPD ሊቀመንበርነትን ከገንዘብ ሚንስትርነቱ ሥልጣን ጋር ደርበዉ ይዘዉ የነበሩት ላፎንቴ ሥልጣን ለቀቁ።የሽሩደር-ላፎንቴ ጥብቅ ጓዳዊ ትብብር ፈረሰ።«ካፑት» እንዲል ጀርመን።መጋቢት 1999።

ባለፈዉ ቅዳሜ የአሜሪካ ድምፅ ይሕን አሰማን።አቶ ለማ መገርሳ እንዳሉት የልዩነቱ ምክንያት የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ኢሕአዴግ ወደ ዉሕድ ፓርቲ መቀየር የለበትም-አለበት ነዉ።ዐብይ ሲነግስ ለማ ሲፈርስ እንበል ይሆን? ወይስ ከጥብቅ ጓዳዊ ትብብር «ከሞት በስተቀር አንለያይም» ወዳሰኘ ፍቅር ያደገዉ ወዳጅነት «ጨቤ።» የፖለቲካ ተንታኝ ገረሱ ቱፋ ግን ተስፋ አልቆረጡም።

የደርግ፤ የኢሕአፓ ይሁን የሕወሓት መሪዎች ልዩነት በግድያ አብዛኛዉን ጊዜ አልፎ አልፎ በሹም ሽር እስኪያሳርግ ድረስ ለሕዝብ አይደለም ለየተከታይ፣ ደጋፊዎቻቸዉም ጭምር ስዉር ነበር።የለማና ዐብይ ጥብቅ ወዳጅነትም መላላቱ ሲናፈስ ነበር።በተለይ አቶ ለማ ከኦሮሚያ ርዕሠ-መስተዳድርነት ወደ መከላከያ ሚንስትርነት ከተቀየሩ ጊዜ ጀምሮ ሁለቱ ፖለቲከኞች መቃቃራቸዉ በሰፊዉ ሲነገር ነበር።ሁለቱ ፖለቲከኞችም ሆኑ ደጋፊዎቻቸዉ ግን ልዩነት መኖሩን እስካለፈዉ ሳምንት ማብቂያ ድረስ በይፋ አልተናገሩም።አላስተባበሉምም።የፖለቲካ ተንታኝ ገረሱ ቱፋ እንደሚሉት የለማ መገርሳ የራዲዮ መግለጫ የሚወራዉን ከማረጋገጥ ባለፍ፣ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለሚከታተሉ አያስደንቅም።

Äthiopien EPRDF
ምስል Office of the Prime Minister-Ethiopia

ዶክተር አብይ ዐሕመድ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን እንደያዙ ትልቁን ሥልጣን አሳልፈዉ እንደሰጡ ጀግና ፖለቲከኛ የሚወደሱት ለማ መገርሳ ኢትዮጵያ ሥልጣን «በሰላም የሚሸጋገርበት» አዲስ ታሪክ አስመዘገበች ብለዉ ነበር።

መጋቢት 2010 የነበረዉ ተስፋ ግን ዛሬ ባይጨናጎል መንምኗኗል።ባይደርቅ-ጠዉልጓል።ሥርዓተ አልበኝነት፣ የፖለቲካ ብሽሽቅ፣ የከረረ የጎሳ ጠብ፣ የኃይማኖት ጥላቻና ግጭት ኢትዮጵያዉንን በየስፍራዉ እያጋደለ፣ እያሰደደ፣የደሐ ሐብት ንብረታቸዉን እያወደመ ነዉ።

ፖለቲከኞች ተቃዋሚ ይባሉ ገዢ፣ የትግሬ፣ የአማራ ይሁኑ የኦሮሞ ወይም ሌሎች፣ የፖለቲካ አቀንቃኝ ይሁኑ፣ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ፕሮፓጋንዲስቶች ደም አፋሳሹን ጠብ ግጭት ለማስቆም ከመጣር ይልቅ እርስ በርስ እየተጠለፉ ተራዉን ወጣት እያላተሙት ነዉ።አቶ ገረሱ እንደሚሉት ፖለቲከኞች አሁንም ከነበሩበት አስተሳሰብ አልተላቀቁም።

                        

የለማ-ዐብይ አንድነትም ሆነ ሁለትነት የኢትዮጵያዉያንን አጣዳፊ ሥጋት ለማቃለል አለመፈየዱ በርግጥ ያሳዝናል።የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ኢያሱ-ተፈሪ፣ መንግስቱ-አጥናፉ፣ መለስ-ተወልደ ወይም ስዬ አልንም አንድም ሁኑ ብዙ፣ ተባበሩም ተጣሉ የዛሬዉ ኢትዮጵያዊ ከነገ ይልቅ ትናንትን፣ ከመጪዉ ዓመት ይልቅ አምናን እያለመ መጪዉን እንበለ ተስፋ ከማማተር አለመላቀቁ ነዉ ሐቁ።ድቀቱም።

ነጋሽ መሐመድ 

ኂሩት መለሰ