1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዐቢይ ሥልጣን የያዙበትን አምስተኛ ዓመት ለመዘከር በተካሔደው ሰልፍ ምን ተባለ?

እሑድ፣ መጋቢት 24 2015

በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን የያዙበትን አምስተኛ ዓመት የሚዘክሩ ሰልፎች በዛሬው ዕለት ተካሒደዋል። ዐቢይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፈቃዳቸው ሥልጣን ከለቀቁት ኃይለማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን የተረከቡት የዛሬ አምስት ዓመት መጋቢት 24 ቀን 2010 ነበር።

https://p.dw.com/p/4Pbfn
 Ethiopia I Public demo held in Oromia
ምስል Seyoum Getu/DW

ዐቢይ ሥልጣን የያዙበትን አምስተኛ ዓመት ለመዘከር በተካሔደው ሰልፍ ምን ተባለ?

አቶ ዓለማየሁ ባልቻ የተባሉ አስተያየት ሰጪ አዲስ ከተመሰረተው ሸገር በተሰኘው ከተማ ኩራ ጂዳ ከተባለ ክፍለ ከተማ ነው በሰልፉ ላይ የታደሙት፡፡በሰልፉ ላይ በታደሙበት ወቅት አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው እኚህ አስተያየት ሰጪ ልክ የዛሬ አምስት ዓመት ወደ ስልጣን መጥተው ኢትዮጵያን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት ዶ/ር ዐቢይ ብርቱ ፈተናዎችን ተሻግረው አገር ያስቀጠሉ መሪ ስለመሆናቸው አውስተዋል፡፡

“ዶ/ር ዐቢይ በሰላማዊ ምርጫ ወደ ስልጣን የመጡ፣ በልጅነታቸው ለአገራቸው ሲሉ የተፈተኑ፣ አገራቸውንም ለማዳን በጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው የዘመቱ ናቸው፡፡ አሁንም ኢትዮጵያን ለማራመድ ለማሻገር የሚጥሩ እንደሆኑ ነው የምንረዳቸው፡፡ አደጋ ያንጃበባትን አገር ታድጓልም ብለን ስለምናምን ነው በዛሬው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተገኘነው፡፡ እሳቸው የወጡበት የኦሮሞ ማህበረሰብም የአገር ስጋት ሳይሆን የኢትዮጵያ ምሰሶ እንደሆነ ነው የምንረዳው” ሲሉም አስተያየታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ 

አቶ ዓለማየሁ ባልቻ
አቶ ዓለማየሁ ባልቻ አዲስ በተመሰረተው ሸገር ከተማ ኩራ ጂዳ ከተባለ ክፍለ ከተማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን የያዙበትን አምስተኛ ዓመት ለመዘከር በተካሔደ ሰልፍ ከታደሙ መካከል ናቸው።ምስል Seyoum Getu/DW

ከባ የተባለች ወጣት ደግሞ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የታደመችው ከሰበታ ክፍለ ከተማ ነው፡፡ እሷም ሰልፉ ላይ የታደመችበትን ምክኒያት ስታስረዳ “ይህ መጋቢት 24 የኦሮሞ ህዝብ ለዘመናት ታግሎ የእኩልነት ድል ያገኘበት ነው ብዬ ስለማምን ነው እዚህ ተገኝቼ ለማክበር ለማስታወስ የወጣሁት፡፡ ብዙ ለውጦች በመጥቷል በዚህ አምስት ዓመት እና ያንኑን ለመዘከር ነው የመጣነው፡፡ እንደ ወጣትም ተጠቃሚ ያደርገኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በዚህ ላይ ያልተደሰቱ የጽንፍ ፖለቲካ የሚከተሉ አሉና እነሱንም ለመቃወም ነው በዚህ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተገኘነው፡፡ ለህዝባችን አንድነት ነው የሚያስፈልገው፡፡ ያ እውን ከሆነ የማይሳካ አይኖርም” ብላለች፡፡

በድጋፍ ሰልፉ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዶ/ር ተሾመ አዱኛ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አምስተኛ የስልጣን ዘመን ማስታወስ ያስፈለገው አስደናቂ እምርታ ያሉት በአስተዳደራቸው የተመዘገቡ ውጤቶችን ለመዘከር ነው ብለዋል፡፡

“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያን በመሩበት ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ ለውጦች በአገራችን ብመጣም ጢቂት እንኳ ለማንሳት፤ ኢትዮጵያ ሁሌቴ ሳተላይት በታሪኳ ያመጠቀችበት ነው፡፡ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ከመጀመር ባለፈ መጨረስም የተቻለበት ነው ይህ ወቅት፡፡ በጦርነት ውስጥ እንኳ ሆነን ልማት ያልተቋረጠበት እና አገራችን ዕድገትን ያሳየችበት በዚህ ወቅት ነውና ይህንንም እንደ ስኬት እናያዋለን፡፡ በታሪካችን ስንዴን በገፍ በማምረታችን ወደ ውጪ መላክ የቻልነውም አሁን ነው፡፡ ይህን እንደ አገር ብናየው እንደ ኦሮሚያም በርካታ እምርታዎች ተገኝተዋል፡፡ ለአብነትም ከአምሰርት ዓመታት በፊት 10 ቢሊየን ብር የነበረውን የኦሮሚያ ገቢ አሁን ወደ 85 ቢሊየን ማሳደግ ተችሏል፡፡ ዓመታዊ የግብርና ምርትም በክልሉ ብቻ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ከ200 ሚሊየን ኩንታሎች መሻገር የቻለው” ሲሉ ተናግረዋል 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን የመጡበት እና አስተዳደራቸው ባለፉት አምስት ዓመታት አከናውኗል ያሏቸውን እምርታዎች የሚያሞግሱ የድጋፍ ሰልፎች ዛሬ በኦሮሚያ በተለያዩ ከተሞችም ታውሶ ውሏል፡፡ በዚህም በአምስት ዓመቱ ተሳኩ የተባሉ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እምርታዎች በመፈክሮች ተስተጋብተዋል፡፡ ጂማ፣ ያበሎ፣ ቡሌሆራ፣ ሆለታ፣ ወሊሶ፣ አዶላ ወዩ፣ ባቱ፣ አምቦ፣ ቡኖ በደሌ፣ ነጌሌ ቦረና፣ አሰላ፣ ጭሮ፣ ባሌ ሮቤ እና ነቀምቴ የድጋፍ ሰልፉ ከተካሄደባቸው ከተሞች መሆናቸውንም የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን መረጃ ያሳያል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን የያዙበትን አምስተኛ ዓመት ለመዘከር የተካሔደ ሰልፍ
በሰልፉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን የሚያወድሱ የተለያዩ መፈክሮች ታይተዋል።ምስል Seyoum Getu/DW

ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር የቆየው የአራት ፖለቲካ ድርጅቶች ጥምረት የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ፈርሷል፡፡ የግንባሩን መፍረስ ተከትሎ አዲስ በተመሰረተው እና አሁን አገሪቱን እያስተዳደረ ባለው ብልጽግና ፓርቲ እና ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል በተፈጠረው አለመግባባት በኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው አስከፊ ጦርነትም በዚሁ ወቅት የተከሰተ ነበር፡፡ 
ከዚህም ባሻገር ኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ በአገሪቱ የተለያዩ አከባቢዎች በተፈጠረው አለመረጋጋት ህዝብ በጎላ ድምጽ ስለሰላም የተማጸነበትም ነበር ያለፉት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አምስት ኣመታት የስልጣን ዘመን፡፡ ጎልተው በተስተዋሉት በግጭቶቹ ከተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችም ተፈናቅለው የሰላም እጦቱ ሰለባ መሆናቸውም አይዘነጋም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ልክ የዛሬ አምስት ዓመት መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ስልጣን ተረክበው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቃለ መሃላ መፈፀማቸው ይታወሳል፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን የያዙበትን አምስተኛ ዓመት ለመዘከር የተካሔደ ሰልፍ
ባለፉት አምስት ዓመታት ኢሕአዴግ ፈርሶ ብልጽግና ተመስርቷል። ኢትዮጵያም በብርቱ ግጭቶች እና ጦርነት ውስጥ አልፋለች። ዐቢይ ሥልጣን የያዙበትን አምስተኛ ዓመት ለመዘከር ሰልፍ የወጡ ደጋፊዎቻቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳኩ ያሏቸውን ሥራዎች እየጠቀሱ አሞግሰዋቸዋልምስል Seyoum Getu/DW

ሥዩም ጌቱ 

እሸቴ በቀለ