ውጥረት በግብፅ፣ | አፍሪቃ | DW | 22.06.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ውጥረት በግብፅ፣

በግብፅ ባለፈው ቅዳሜና እሁድ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከተካሄደ ወዲህ፣ ውጤቱ ትናንት በይፋ ይገለጣል ተብሎ ሲጠበቅ ፣ ነገ ቅዳሜ ፣ ወይም እሁድ ይነገራል መባሉ፣ በተፎካካሪዎቹ፤ የሙስሊም ወንድማማች ማኅበር የተሰኘው የፖለቲካ ፓርቲ እጩ ሙሐመድ

ሞርሲና በቀድሞው ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ የመጨረሻ የአገዛዝ ሰሞን ጠ/ሚንስትር ይሆኑ ዘንድ ተሹመው የነበሩት የቀድሞው የአየር ኃይል ዋና አዛዥ፣ አህመድ ሻፊቕ ደጋፊዎች መካከል ፍጥጫን ያስከተለ መስሏል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች፤ በዛሬው ዓርብ ለጸሎትና ስግደት፣  ሰንደቅ ዓላማ  እያውለበለቡ  ወደ ታህሪር (ነጻነት)አደባባይ የጎረፉ ሲሆን፤ የሙሐመድ ሙርሲ ወገኖች፤ የምርጫውን ውጤት ለመቀልበስ ማድባት ተይዟል በማለት ሲከሱ፣ የአህመድ ሻፊቕ ወገኖች፣ በበኩላቸው፤ የምርጫ ኮሚሽኑን  ባለሥልጣናት በማስፈራራት ድሉን   ለእነርሱ እንዲወስኑላቸው  ይጥራሉ፣  አለበለዚያም ከተሸነፉ ብጥብጥ ለማስነሳት ይዘጋጃሉ ሲሉ  አጸፋዊ ወቀሳ ሰንዝረዋል። በመኻሉ፤ ግብፅን በተጨባጭ ሁኔታ አሁን በመግዛት ላይ ያለው የጦር ኃይሉ ም/ቤት ፣ የህዝብን ጥቅም ለመጉዳት ጥረት በሚያደርግ በማንኛውም ሰው ላይ «ጥብቅ» እርምጃ ይወሳዳል የሚል ማስጠንቀቂያ አሰምቷል።

የወደፊቱን ፕሬዚዳንት ማንነት ለማወቅ ፤ በአጠቃላይ ሰኔ 9 እና 10 ,2004 የተካሄደውን የምርጫ  ውጤት ለመስማት አጥብቀው ከሚሹት ግብጻውያን መካከል ፣ ባድር ሞሐመድ ሰዒድ የተባሉት የካይሮ ኑዋሪ እንዲህ ነበረ ያሉት--

«የምርጫው ውጤት ሳይነገር እስካሁን መዘግየቱ ፤ አሥግቶኛል። ሁኔታውንም ውጥረት እንዲከሠትበት ነው ያደረገው። ለምንድን ነው የምርጫውን ውጤት ፤ ይህ ነው ብለው ቁርጡን የማይነግሩን?!»

የምርጫ ኮሚሽኑ መሪ ፋሩቕ ሡልጣን፤ ውጤቱ ፤ ነገ  ቅዳሜ ወይም እሁድ በይፋ መነገሩ አይቀርም ሲሉ ያስታወቁ ሲሆን፤  በምርጫው ፤ የማጭበርበር ተግባር ተፈጽሟል መባሉ ኮሚሽኑን በሥራ ተጠምዶ እንዲሰነብት ማድረጉንም  አያይዘው ነው የገለጡት።

ባለፉት ዙር ምርጫዎች እንደተከሠተው፤ በህይወት የሌሉ ሰዎች ስም ጭምር ተመዝግቦ ተገኝቷል። አንዳንዶቹ ፣ እንዲያውም አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁለት ጊዜ ነው ስማቸው በምርጫ ወረቀት ላይ ስማቸው  ሠፍሮ  የተገኘው። እናም ፤ የሙስሊም ወንድማማች ማኅበር እጩ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ሙርሲ፣ ተፎካካሪአቸውን  አህመድ ሻፊቕን፣ የመራጮችን ድምፅ ገዝተዋል ሲሉ የወቀሱ ሲሆን፤  አህመድ ሻፊቕ በበኩላቸው፤ ሙርሲ 1,5 ሚሊዮን ገደማ የምርጫ ካርዶችን አሳትመው አቅርበዋል። ይህም መራጮችን ለማደናገርና ምልክት ሳይደረግ ፣በቀጥታ እንደመረጡ የሚያስመስል  ነው ፤ እንደ ሻፊቕ አባባል። ኮሚሽኑ ፤ እስካሁን፤ ለማጭበርብር  ተብሎ የቀረቡ ናቸው ከተባሉት የምርጫ ካርዶች መካከል  ያረጋገጠው፣ 400 ገደማ የሚሆኑትን ነው።

Ägypten Premierminister Ahmed Shafik

 የቀድሞው የሙባረክ አገዛዝ ታማኝ የነበረው የምርጫ ኮሚሽን፤ የተጠቀሰውን 1,5 ሚሊዮን የምርጫ ካርድ  ውድቅ ካደረገ፤ ያላንዳች ጥርጥር ፣አህመድ ሻፊቕ ፣አዲሱ የግብፅ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ።
የግብፅ መንግሥት ዋና ጋዜጣ ኧል አህራም፤ የምርጫ ኮሚሽኑ፣ በዚያው በሀገር ውስጥ እንዲሁም የግብፅ ጦር ኤይል ዋና ደጋፊ ከሆነችው ዩናይትድ እስቴትስ፣ ብርቱ ተጽእኖ መኖሩን ሳይጠቁም አላለፈም። አሜሪካ ለዴሞክራሲ የተገባው ቃል ባፋጣኝ ምላሽ ያግኝ ነው የምትለው። ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሂልሪ ክሊንተን፣ « ሁሉንም የሚያቅፍ የዴሞክራሲ ሂደት» ይኑር ነው ያሉት። «ጦር ኃይሉ በይበልጥ ጫና ማሳረፍና መቆጣጠር ፣ ወይም ህገ-መንግሥታዊውን ሥልጣን ማሠናከል የለበትም »  ነው ያሉት።  

የተሃድሶ ለውጥ አራማጅ መሆናቸው የሚነገርላቸው፤ የቀድሞው የ ተ  መ  ድ  ዲፕሎማትና የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ፤ ግብጻዊው የፖለቲካ ሰው ሙሐመድ ኤል ባራዳይ ፤ «የህዝቡ ጥቅም፤ ከጠብብ የጥቅም ሽኩቻ ይልቃል» ማለታቸውነው የተጠቀሰው።  ኤል ባራዳይ፤ «አሁን የሚፈለገው፣ ባስቸኳይ የእርቀ ሰላም ኮሚቴ ተቋቁሞ ፤ አገሪቱ፤ ከፖለቲካና ህግ ነክ  ቀውስ የምትገላገልበትን መላ ይፈልግ » ነው ያሉት።

ለብዙዎች ግብፃውያን፤ ለተደራጁ እስላማውያኑ ንቅናቄዎች ፣ እንዲሁም፣  ሃይማኖት በመንግሥታዊ አስተዳድር ላይ አንዳች ተጽእኖ እንዳይኖረው የሚፈልጉት፤ ለዘብተኛ አቋም ያላቸው ወገኖች፣ እንደሚሉት፤ ሻፊቕ ቢያሸንፉ ፣ ከጦር ኃይሉ ምክር  ቤት ጋር ተጣምረው፣ ፓርላማውን በመቆጣጠር ህገ-መንግሥት ወደ ማርቀቁ ቢሸጋገሩ፤ ተወገደ ብለው ያሰቡት፤ የ 60 ዓመታቱ ወታደራዊ አገዛዝ አገግሞ፣  በእርግጥ ይቀጥላል ማለት ነው። ሻፊቅ ተመረጡ ማለት ምን ማለት ይሆናል? ሙሐመድ ከሊፋ የተባሉት የሙስሊም ወንድማማች ማኅበር ባልደረባ እንዲህ ይላሉ--

«እርሳቸው ተመረጡ ማለት፤ በቀጥታ ወታደራዊ መፈንቅለ-መንግሥት ተከናወነ ማለት ነው። ምርጫው እንዲሁ የተጭበረበረ እንደነበረም ይጠቁማል። ህዝቡ አይቀበለውም፤ እኛም አደባባይ በመውጣት አዲስ አብዮት እናካሂዳለን።»

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 22.06.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15K26
 • ቀን 22.06.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15K26