ውግረት በናይጀሪያ | የጋዜጦች አምድ | DW | 29.09.2003
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ውግረት በናይጀሪያ

ናይጀሪያ ውስጥ አንድ የይግባኝ ፍርድቤት የ፴፩ ዓመት አሚና ላዋልን ከወንጀል ክስ ነፃ አድርጓታል። ይኸው የይግባኝ ፍርድቤት የሻረው፣ ሴትዮዋ ጋብቻ አጎደፈች ተብላ በእስላማዊው ሕግ ሻሪኣ መሠረት በድንጋይ ተወግራ እንድትገደል አንድ ፍርድቤት በመጋቢት ፲፱፻፺፬ የበየነባትን ውሳኔ ነው። አሁን ታዲያ፥ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ናይጀሪያ ውስጥ ውግረቱን በሚመለከተው ክርክር ረገድ እስላማውያኑን ጥጥር-መስመረኞች ማሸነፋቸው ይሆን? መልሱ አሉታዊ ነው። ትግሉ ገና ወደ ጥሩ ፍፃሜ አልተሸጋገረም።

በናይጀሪያ ርእሰከተማ አቡጃ ብዙ የኅብረተሰብእ እና የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ቡድኖች፣ እንዲሁም ዲፕሎማታዊ አካባቢዎች በክፍለሀገር ካትሲና ላዕላዩ ሸሪኣ-ፍርድቤት በአሚና ላዋል አንፃር ተላልፎ የነበረውን የውግረት ብያኔ ትናንት እንደሻረው የተነገረውን ዜና እጅግ ነበር የረኩበት፤ እንዲያውም ናይጀሪያ ውስጥ ይኸው አሰቃቂ ጉዳይ የተዘጋ ሆኖአል በማለት ሳይደሰቱም አልቀሩም። ግን ዝንባሌው ለደስታ የሚያበቃ ሆኖ አይደለም የሚታየው። ሀገሪቱ ውስጥ በሌሎች ክፍላተሀገር በተደረሱ የውግረት ብያኔዎች ረገድ ገና እንደተንጠለጠሉ የሚገኙ ሌሎች የይግባኝ አቤቱታዎች አሉ። በእነዚያው ክፍላተሀገር “እስላማዊው ሕግ”/ሸሪኣ ቋሚ ሕግ ሆኖ፣ በፍትሐብሔርና በወንጀለኛ መቅጫም ሥርዓት እንደፀና ይገኛል። እንዲያውም ከናይጀሪያ የሚሰማ ሌላም አሳሳቢ ዜና አለ---ይኸውም፣ አሁን የውግረቱ ብያኔ ከተሻረ በኋላ ብዙ ሳይቆይ በክፍለሀገር ባውቺ አንድ ሸሪኣ-ፍርድቤት በሕፃናት ላይ ብልግና ፈፀመ በተባለ በአንድ ተከሳሽ ላይ የውግረት ብያኔ ማስተላለፉ ነው። ይህም ጨርሶ ያጋጣሚ ጉዳይ አይደለም---የውግረእት ብያኔው ፍርርቅ በዚያች የፖለቲካ መዋለልና ቀውስ በሚጎላባት የብዙ ብሔረሰቦችና ሃይማኖቶች ሀገር ትንሹን፥ ኢምንቱን የዴሞክራሲ ሙከራ እንኳ ለማሰናከል የሚሹትን የእስላማውያኑን ጥጥር-መስመረኞች ትግል ነው የሚያንፀባርቀው። ሰሜን ናይጀሪያ ውስጥ እስላማውያኑ ጥጥር-መስመረኞች--መሠረተኞች--በእሳት ነው የሚጫወቱት። እነርሱ በመንግሥትና በዓለማዊው ሥርዓተ-መስተዳድር አንጻር ለሚያደርጉት ትግል ሃይማኖትን የፖለቲካና የሕግጋት መሣሪያ ያደርጉታል። እነዚሁ የናይጀሪያ እስላማውያን ጥጥር-መስመረኞች በነይጀሪያ--በተለይም የእስልምናው እምነት በሚጎላበት በሀገሪቱ ሰሜን--ኋላቀርነትንና ድህነትን ለመታገል እስልምናን እንደ ርእዮት ሊጠቀሙበት የሚችሉ ይመስላቸዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን፣ በሰሜናዊው የናይጀሪያ ከፊል በጥጥር መስመረኞቹ እጅ ያለው እስልምና ከእነርሱ በስተቀር ሌላ ማንም ሰው ሊያዝ እንደማይችል ለማእከላዊው መንግሥትና በኤኮኖሚ ለተራመደው ለክርስቲያናዊው የሀገሪቱ ደቡብ ለማሳየት የሚጠቀሙበት የሥልጣን መሣሪያ ነው።

ለዚሁ ትግላቸው ሀገሪቱን ምሥቅልቅል ውስጥ ቢዘፍቋት ደንታ አያደርጉም። እንዲያውም፣ ሀገሪቱ ውስጥ መላው ሕዝብ ሥጋት ላይ የሚወድቅበት ሁኔታ፣ ሙስሊሞች በድንጋይ ተወግሮ የመገደል እጣ ሊደርስባቸው እንደሚችል የሚነዛው ዛቻ እነዚያኑ ጥጥር-መስመረኞች ነው የሚጠቅመው። እነርሱ የሚያልሙት፣ ናይጀሪያ ውስጥ በእነርሱ ሥር እስልምናና እስላማዊው ሥርዓተ መንግሥት የሚሠፍንበትን ሁኔታ ነው።

ግን የናይጀሪያ እስላማውያን ጥጥር-መስመረኞች ከምንጊዜውም ይልቅ አሁን ከዚሁ ግባቸው በጣም ርቀው ነው የሚገኙት። የእሳቱ ጨዋታ አንድ ቀን ድልን እንደሚያመጣላቸው አሁንም ያምኑበታል፣ የግባቸውን ከንቱነት ገና አላጤኑትም። የእስልምና መሣሪያነትና ውግረት እንደማያዋጣ በየጊዜው ነው ግልጽ የሚሆነው። ምክንያቱም፥ ሕጋዊ፣ ሞራላዊ-ሥነምግባራዊና ፖለቲካዊ መሠረት የለውምና። ግን ይኸው ግንዛቤ ጊዜ ያስፈልገዋል፣ እስከዚያው ድረስ ታዲያ--ግንዛቤው እስኪጎላ ድረስ--ናይጀሪያ ውስጥ በሃይማኖት የሚሸፋፈነው ግዙፉ ፖለቲካዊ ምስቅልቅል እንዳሠጋ ይቆያል።


ተዛማጅ ዘገባዎች