ውጊያ በምሥራቃዊ ኮንጎ | አፍሪቃ | DW | 30.10.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ውጊያ በምሥራቃዊ ኮንጎ

በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ምሥራቃዊ አካባቢ «ኤም 23» በመባል በሚታወቀው የዓማፅያን ቡድን እና በመንግሥት መካከል ጥቃቱ ዛሬም መቀጠሉ ተገለጸ።

በሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች መካከል ካለፈው የሣምንት መጨረሻ ወዲህ እንደገና በመካሄድ ላይ ባለው ውጊያ «ኤም 23» በኮንጎ ጦር ትልቅ ሽንፈት እንደደረሰበት በሀገሪቱ የተሰማራው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ ገልጾዋል። በወታደራዊ ርምጃ የሚገኝ ድል ብቻውን ግን ምሥራቃዊ ኮንጎን እንደማያረጋጋ አክሎ አሰረድቶዋል።

በምሥራቃዊ ኮንጎ እንደገና በጦሩ እና ባማፂው ቡድን «ኤም 23» መካከል በቀጠለው ውጊያ የመንግሥቱ ጦር ዛሬ የዓማፅያኑ ጠንካራ ሠፈር ከሆኑት መካከል አንዱ የሚባለውን ቡናንጋን መያዙን አስታውቋል። ቀደም ባሉ ቀናትም የጦር ኃይሉ ከጎረቤት ርዋንዳ ጋ በሚያዋስነው ድንበር የሚገኙ የኪዋንዣ እና የሩትሹሩ መንደሮችን እና የሩማንጋቦ የጦር ሠፈርን ከዓማፅያኑ ማስለቀቅ መቻሉን ገልጾዋል።

በአዲሱ የጦር ዘመቻው ላይ በኮንጎ በተሰማራው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ የሚረዳው የኮንጎ ጦር በምሥራቃዊ የሀገሩ ከፊል ያለፉት ሀያ ወራትን የቀጠለውን ዓመፅ ለማብቃት የ «ኤም 23» ጠንካራ ሠፈሮች ወደሆኑት ምቡዚ እና ሩንዮኒንም እየገሰገሰ መሆኑን አንድ ያካባቢው ነዋሪ ለዜና ምንጭ ሮይተርስ በስልክ ገልጾዋል። የ«ዩኤንኤችሲአር» ተወካይ ሉሲ ቤክ እንዳስታወቁት፣ ከ5000 የሚበልጡ ያካባቢው ነዋሪዎች አዲሱን ውጊያ እየሸሹ ወደ ዩጋንዳ ተሰደዋል።
በኬንያ የሚገኙ የፖለቲካ ተንታኝ አህመድ ራጃብ እንደጠቆሙት ግን፣ የመንግሥቱ ጦር በጎረቤት ርዋንዳ ይረዳል የሚለውን «ኤም 23»ን ከብዙ አካባቢ ቢያስለቅቅም፣ በምሥራቃዊ ኮንጎ አዲስ ከተቋቋመ እና ራሱን «ኤም 18» ብሎ የሚጠራ ሌላ ያማፅያን ቡድን አዲስ ጥቃት ያሰጋዋል።
« የ«ኤም 23» ተዋጊዎች በርግጥ የጦሩን ጥቃት ለመቋቋም መታገላቸው ባይቀርም፣ ከያዙዋቸው ሠፈሮች በኮንጎ ጦር ከመባረራቸው በፊት እንደነበሩት ጠንካራ አይሆኑም። ይሁንና፣ አሁን የተቋቋመው ራሱን «ኤም 18» ብሎ የሚጠራው አዲስ ያማፅያን ቡድን የ«ኤም 23» ዓማፅያንን ለማጥፋት እና በምሥራቃዊ ኮንጎ ሰላም ለማውረድ እየሞከረ ላለው የሀገሪቱ መንግሥት ግዙፍ ችግር ይፈጥርበታል። »
በኮንጎ 3000 ወታደሮች ያሰለፈው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ መሪ ማርቲን ኮብለር ጓዱ የሕዝቡን ደህንነት የማስጠበቁን እና አካባቢውን የማረጋጋት ተልዕኮውን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን ቢገልጹም፣ ወታደራዊ ርምጃ ብቻውን መፍትሔ እንዳልሆነ በማመልከት ተቀናቃኞቹ ወገኖች ወደ ድርድሩ ጠረጴዛ እንዲመለሱ ጠይቀዋል ።


« ሲቭሉን ሕዝብ የመከላከል ኃላፊነት አለብን። ይህንኑ ተልዕኳችንን ለመወጣት ነው እዚህ ያለነው። ከዚሁ ጎን ለጎን ግን ውዝግቡን ለማብቂት የሚያስችል ፖለቲካዊውን መንገድ መከተል ይኖርብናል። »
ይህ ግን በወቅቱ የሚሳካ አይመስልም። ያለፉት 12 ወራትን በሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች መካከል በካምፓላ ዩጋንዳ ሲካሄድ የቆየው የሰላም ድርድር ከጥቂት ቀናት በፊት ካላንዳች ውጤት ተበትኖዋል። ለዚህም ዓማፅያኑ ለቡድናቸው መሪ ምሕረት እንዲደረግ ያቀረቡት ጥያቄ ተጠያቂ መሆኑ ተገልጾዋል። የትላልቆቹ ሀይቆች አካባቢ የአብያተ ክርስትያን ድርጅቶች ጥምረት የኮንጎ ተመራማሪ ኢሎና አወር ፍሬገ እንደሚሉት፣ የኮንጎ መንግሥት ያማፅያኑን ጥያቄ በመቀበል ፈንታ ጥቃቱን ማጠናከሩን ነው የመረጠው። ይህ ርምጃው ግን ሰላም ማምጣቱን ይጠራጠሩታል፣
« ያማፂውን ቡድን ላጭር ጊዜ ከጎማ ማባረር (ማስወጣት)ቢችልም፣ ለውዝግቡ መፍትሔ አገኘ ማለት አይደለም። እንዳዲስ ተሰባስበው እና የጦር መሳሪያ ትጥቃቸውን አሟልተው ወደ ቀጣዩ ፍጥጫ ያመራሉ። »
የ«ኤም 23» ዓማፅያን አዲሱ ውጊያ ቶሎ ካላበቃ በስተቀር ከሰላሙ ድርድር እንደሚርቁ ነው ቢዝቱም፣ የኮንጎ መንግሥት ዓማፅያኑ ትጥቃቸውን ካልፈቱ ጥቃቱን እንደሚያጠናክር ነው ያስታወቀው።

ሂልከ ፊሸር/አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic