ውይይት፦ የኢህአዴግ ውህደት ይሳካልን? | ኢትዮጵያ | DW | 10.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ውይይት፦ የኢህአዴግ ውህደት ይሳካልን?

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሰሞኑ በጽህፈት ቤታቸው በነበረ ስብሰባ ላይ ኢህአዴግ አንድ ሀገራዊ ፓርቲነት በቅርቡ እንደሚቀየር አሳውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በተጨማሪ የሶማሌ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ እና ሀረሪ ክልል ገዢ ፓርቲዎች አዲስ በሚመሰረተው ውህድ ፓርቲ ውስጥ እንደሚካተቱ ገልጸዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 30:00

ውይይት፦ የኢህአዴግ ውህደት ይሳካልን?

የአራት የፖለቲካ ድርጅቶች ጥምረት የሆነው ገዢው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባርን (ኢህአዴግ) ወደ አንድ አገራዊ ፓርቲ የመቀየሩ ውጥን መነሳት ከጀመረ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህ ጉዳይ በየሁለት ዓመቱ በሚካሄደው የኢህአዴግ ጉባኤ ወቅት በየጊዜው ሲነሳ ቆይቷል፡፡ ባለፈው መስከረም ወር በሀዋሳ  በተካሄደው የድርጅቱ ጉባኤም ውሳኔው በይደር ለሌላ ጊዜ ተላልፏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ነበር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሰሞኑ በጽህፈት ቤታቸው በነበረ ስብሰባ ላይ ኢህአዴግ አንድ ሀገራዊ ፓርቲነት በቅርቡ እንደሚቀየር ያሳወቁት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በተጨማሪ የሶማሌ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ እና ሀረሪ ክልል ገዢ ፓርቲዎች አዲስ በሚመሰረተው ውህድ ፓርቲ ውስጥ እንደሚካተቱ ገልጸዋል። ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ገለጻ ተከትሎ የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ውህደቱን የተመለከተ ጥናት ሲከናወን መቆየቱን እና አሁን ከማጠቃለያ ላይ መድረሱን አብራርተዋል።

በኢህአዴግ ላይ ጥናት ያካሄዱ ምሁራን ኢህአዴግ ከግንባርነት ይልቅ ውህድ ፓርቲ ቢሆን እንደሚመረጥ በተደጋጋሚ ሲጠቁሙ ቆይተዋል። ምክንያታቸው ምንድነው? ኢህአዴግ ውህድ ፓርቲ ይሁን ሲባል አሁን ካለው የግንባር አወቃቀር በምን ይለያል? በብሔር መደራጀት በገነበበት ነባራዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ኢህአዴግ አሁን ያለውን አወቃቀሩን ቀይሮ ወደ አንድ ፓርቲነት መምጣት ወይም መዋሃድ አያስቸግረውምን?

የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እርስ በእርሳቸው ያስተሳስራቸው የዓላማ አንድነት መሸርሽሩ በተለያየ መልክ ይንጸባረቃል። ለምሳሌነትም እስከ ቅርብ ዓመታት ከግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል “አድራጊ ፈጣሪ ነው” ይባል የነበረው ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ኢህአዴግ ድርጅታዊ መስመሩን መሳቱን እና ከሚመራበት የማዕከላዊ ዲሞክራሲያዊነት መርህ ማፈንገጡን በተደጋጋሚ መተቸቱን ማንሳት ይቻላል። በዚህ አይነት ሁኔታ ግንባሩ ለመዋሃድ ዝግጅቴን ጨርሻለሁ ማለቱ ምን ያህል ከእውነታው ጋር የተጣጣመ ነውን? የፖለቲካ እና የህዝብ አስተዳደር ምሁራን በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ የተመረኮዘ ውይይት በሳምንታዊ መሰናዷችን ላይ አድርገዋል። 

በ“እንወያይ” መሰናዷችን የተሳተፉት የፖለቲካል ሳይንስ ምሁራኑ አቶ ሰለሞን ገብረዮሃንስ ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ፣ አቶ ማህዲ ጊሬ ከጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ እንደዚሁም በሀንጋሪ ብሔራዊ የፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ በህዝብ አስተዳደር የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት አቶ ታከለ በቀለ ናቸው። ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ

 

Audios and videos on the topic