1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ውይይት፦ መልስ የሚሹ የሲዳማ ክልልነት ጥያቄዎች

ሰኞ፣ ኅዳር 22 2012

የሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄ በዞኑ በሚኖሩ ነዋሪዎች ከፍተኛ ድጋፍ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣው የመጀመሪያ ደረጃ የህዝበ ውሳኔ ውጤት አሳይቷል። ሲዳማ 10ኛው የኢትዮጵያ ክልል ለመሆን በዋዜማ ላይ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ዞኑ ወደ ክልልነት ከመሸጋገሩ ጋር የተያያዙ፣ መልስ የሚሹ ጥያቄዎች አሁንም ይነሳሉ።

https://p.dw.com/p/3U1Ur
Äthiopien Ethnie der Sidama
ምስል DW/S. Wegayehu

ውይይት፦ መልስ የሚሹ የሲዳማ ክልልነት ጥያቄዎች

በደቡብ ክልል ስር ያለው የሲዳማ ዞን በክልልነት ለመደራጀት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ባለፈው ሳምንት የህዝበ ውሳኔ ተካሂዷል። ህዝበ ውሳኔውን ያስፈጸመው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እንዳስታወቀው በህዝበ ውሳኔን ድምፅ ከሰጡ የዞኑ ነዋሪዎች ውስጥ 98.5 በመቶው ሲዳማ ራሱን ችሎ ክልል እንዲሆን ደግፈዋል። ዞኑ በደቡብ ክልል ውስጥ እንዲቀጥል የቀረበው ምርጫ ያገኘው ድምጽ ከሁለት በመቶ በታች መሆኑም ተገልጿል።

ደም ያፋሰሰው የሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄ ከጫፍ ሊደርስ የቀረው የስልጣን ርክክብ ብቻ ነው። ሲዳማ የኢትዮጵያ 10ኛ ክልል ሆኖ በይፋ ለመመዝገብ በዋዜማ ላይ ባለበት በዚህ ወቅት አሁንም በግልጽ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ።

Äthiopien Sidama stimmen für Teil-Autonomie
ምስል DW/S. Muchie

የኢትዮጵያ ህገ መንግሥት የፌደራል መንግስት የተዋቀረው በክልሎች ነው ይላል። በህገ መንግስቱ አንቀጽ 46 ላይም “የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አባላት” ናቸው ያላቸውን ዘጠኝ ክልሎች በዝርዝር ያስቀምጣል። ሲዳማ 10ኛ ክልል መሆኑ በህዝበ ውሳኔ መረጋገጡን ተከትሎ የህገ መንግስት ማሻሻያ ማድረግ ግድ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ። ሲዳማ የክልልነት ሙሉ ዕውቅና ለማግኘት በእርግጥም በህገ መንግስቱ የክልሎች ዝርዝር ላይ መስፈር ይኖርበታልን?

ሲዳማ ክልል ሆኖ በይፋ ሲቋቋም ከነባሩ የደቡብ ክልል ጋር በሚያካሄደው ፍቺ ላይ ከሚነሱ ጥያቄዎች አንደኛው የሀብት ክፍፍል ነው። የደቡብ ክልል ምክር ቤት ባለው ጥቅምት ወር ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት በነባሩ “የደቡብ ክልል ባለቤትነት ስር የቆዩ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ሀብቶች በኢትዮጵያ የንብረት ክፍፍል ህግ መሰረት ይፈጸማል” ብሏል። እነዚህ ሀብቶች ምንድናቸው? የክፍፍል ሂደቱስ ምን ሊመስል ይችላል?

የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ከተነሳ ጀምሮ ሲያወዛግቡ ከቆዩ ጉዳዮች ውስጥ የሀዋሳ ከተማን “ማን በባለቤትነት ያስተዳድራት” የሚለው ይገኝበታል። የደቡብ ክልል ምክር ቤት በባለፈው ወር ጉባኤው የሀዋሳ ተጠሪነት አዲስ ለሚቋቋመው ክልል እንዲሆን ወስኗል። ነገር ግን ነባሩ የደቡብ ክልል “ወደፊት አማራጭ የአስተዳደር ከተማውን እስኪያመቻች ድረስ ለሁለት ሀገራዊ ምርጫዎች ከተማውን በጋራ እንዲጠቀም ወስኗል። ይህ ውሳኔ የይገባኛል ጥያቄውን በአግባቡ ፈትቷል ወይስ ወደፊት በዚህ ምክንያት ችግሮች ሊከተሉ ይችላሉ?

Äthiopien: Sidama stimmen über Autonomie ab
ምስል AFP/M. Tewelde

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሲዳማ ህዝበ ውሳኔ በፊት እልባት ሊያገኙ ይገባቸዋል ካላቸው ጉዳዮች አንዱ የነበረው በሲዳማ የሚኖሩ የሌሎች ብሔረሰብ አባላት ህጋዊ የመብቶች ጥበቃ ጉዳይ ነው። በዚህ ረገድስ ተገቢው መፍትሔ ተቀምጦለታል?

እነዚህን ጥያቄዎች በሚነሱበት ውይይት ላይ የተሳተፉት አቶ ፍላታ ጊጊሶ -በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የህግ መምህር፣ ዶ/ር ዘመላክ አይተነው- በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፌደራሊዝም እና አስተዳደር ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር እንደዚሁም አቶ ደያሞ ዳሌ በደቡብ ክልል መንግስት ውስጥ የሚሰሩ የፖለቲካ ሳይንስ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያ ናቸው።

ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ