ውይይት፦የኢትዮጵያዉያን የስደት አዙሪት ማቆምያዉ መቼ ይሆን? | ኢትዮጵያ | DW | 25.08.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ውይይት፦የኢትዮጵያዉያን የስደት አዙሪት ማቆምያዉ መቼ ይሆን?

በየክፍለ ከተማዉ በየወረዳዉና እና ቀበሌዉ ያሉ ወጣቱን እያደናቀፉ ያሉ ሰዎች ለመሰደድ ዋና ምክንያት ናቸዉ። ዱባይ ላይ የ 16 እና 17 ዓመት ልጆች ከፎቅ ተወርዉረዉ ሲሞቱ፤ ሲሰቃዩ፤ እነዚህ ልጆች በምን አይነት አግባብ ነዉ፤ የቀበሌ መታወቅያ አዉጥተዉ ፓስፖርት ይዘዉ አዉሮፕላን ተሳፍረዉ የመጡት ብለን መጠየቅ ይገባል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 31:35

ኤንባሲዎች ለዜጎቻቸዉ ደህንነትና መከበር ዘብ ይቁሙ

ኢትዮጵያ ብዙ ዜጎችዋ ከሚሰደዱባት ሃገር አንዷ ናት። በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብዋ በተለይም ወጣቱ በአብዛኛዉ ወደ አዉሮጳ መካከለኛዉ ምስራቅ እና ደቡብ አፍሪቃ ይሰደዳል ። ኢትዮጵያዉያኑ በስደት ዓለም እስር፤ ስቃይ ፤ መደፈር ይጋፈጣሉ፤ በስደት ጉዞም አብዛኛዉ የአዉሪ እና የባህር ሲሳይ ሆነዋል። ቀደም ባሉት ጊዜያት ወጣቱ ከኢትዮጵያ በብዛት የሚሰደደዉ በፖለቲካዉ በጭቆና ምክንያት እንደሆነ ይነገር ነበር። ይሁንና የፖለቲካዉ ጫና ተወገደ ከተባለ በኃላም ስደቱ አላባራም። ባለስልጣናት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ  በተለያዩ ሃገራት የሚገኘዉን ዜጋ ወደ ኢትዮጵያ ቢመልሱም ቢመልሱም ወጣቱ በእጥፍ መሰደዱ እንደቀጠለ ነዉ።  ዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት «HRW» በቅርቡ ባወጣዉ መግለጫ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከ250 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያንን ከሳዑዲ አረቢያ መመለሳቸዉን አስታዉቋል። እነዚህ ወደ ሃገራቸዉ የተመለሱት ዜጎች በምን ሁኔታ ላይ እንደሆኑ በግልፅ ባይታወቅም፤ አብዛኞቹ ግን መልሰዉ ለመሰደድ ሙከራ ሲያደርጉ በጉዞ ላይ ከፍተኛ ስቅየት እንደሚደርስባቸዉ ነዉ የተነገረዉ። የኢትዮጵያዉያንን ይህን የስደት የዑደት ለማስቆም ግን ሃገሪቱ ሁነኛ የሚባል ፖሊሲ የቀረፀች አይመስልም። የፍልሰተኞች ጉዳይን የሚያጠኑ ምሁራን በበኩላቸዉ «የስደት ምክንያት» ብለዉ የሚያስቀምጡት ከፖለቲካ ጫና በተጨማሪ ሥራ አጥነት ድህነት የኑሮ መወደድን ነዉ። እነዚህን ለማስወገድ እና ስደትን ለመቅረፍ መንግስትና የሚመለከታቸዉ ወገኖች ግልፅ የሆነ እቅድ አስቀምጠዋል? እንጠይቃለን።  ዉይይታችንም  የኢትዮጵያዉያን የመሰደዳቸዉ ምክንያት፤ የሚደርስባቸዉ ችግርና መፍትሄዉን ነዉ የሚቃኘዉ። በዚህ ዉይይት ላይ የተሳተፉት አቶ ዓለማየሁ ሰይፈስላሴ   «IOM»  የዓለም ዓቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት በኢትዮጵያ የህዝብ ግንኙነት ኃለፊ  ፤ አቶ ዩርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ ዩርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ፤ ከኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፍሪቃ በሚደረገው ፍልሰት ላይ ከፍተኛ ጥናት ያደረጉ እና መንገደኛ የሚል መጽሐፍ የፃፉ የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያ፤ ጋዜጠኛ መሳይ አክሊሉ፤ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለ 7 ዓመታት በስራ ላይ ሳሉ «ተስፋ አቢሲኒያ» የተሰኘ የመረዳጃና የመረጃ ልውውጥ ማህበር በመመስረት በመካከለኛዉ ምስራቅ ማለትም በሳዑዲ፣ በየመን፣ በቤሩት፣ በኳታር፣ በኩዌት፣ የኢትዮጵያዉያንን እንግልት በቅርበት ያዩ፤ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በብስራት ኤፍ ኤም 101,1 ሬዲዮ ጣቢያ ላይ «ተስፋ አቢሲኒያ»ን በማስቀጠል  በሬዲዮ ፕሮግራሙ ለወጣቱና ለተመላሽ ስደተኞች የስራ አማራጮችን በመጠቆም በስራ ላይ የሚገኙ ናቸዉ።

የተወያዮች ያነስዋቸዉ ነጥቦች

«ኢትዮጵያን ወጣቶች የመሰደድ ምክንያቶችን፤ በሚጋጥማቸዉ እንቅፋቶች ላይ መወያየት አለብን ። መንግስት ለስራ ፈጠራ በቢሊዮን የመደበዉን ገንዘብ እነማን ናቸዉ የሚጠቀሙበት ብለን መጠየቅ አስፈላጊ ነዉ።» «ወጣቱ ሃገር ዉስጥ በተንዛዛ ቢሮክራሲ እየተደናቀፈ እጅግ አሳፋሪ የሆነ ነገር እየተፈፀመበት ነዉ። » «በየክፍለ ከተማዉ በየወረዳዉና እና ቀበሌዉ ላይ ያሉ ወጣቱን እያደናቀፉ ያሉ ሰዎች ለወጣቶቹ የመሰደድ ዋና ምክንያት ናቸዉ።» «መንግሥት ዜጎቹ እንደ አሸዋ ሲረግፉ፤ የባህርና የአዉሬ ሲሳይ ሲሆኑ ዝም ብሎ ማየት የለበትም» «በየሃገራቱ ያሉ ኤንባሲዎች ለዜጎቻቸዉ ደህንነትና መከበር ዘብ መቆም ይኖርባቸዋል። »  «በሳዑዲ፣ በየመን፣ በቤሩት፣ በኳታር፣ እና ኩዌትን ጨምሮ በስድስቱ ገልፍ ሃገራት ዉስጥ ኢትዮጵያዉያን ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈፀማል። ኢትዮጵያዉያን በእነዚህ ሃገራት የመጨረሻ እቤት ዉስጥ ካለ እንስሳ በታች የሚታዩ፤ የዜግነት መብታቸዉ ያልተጠበቀ ከፍተኛ ግፍ እየተፈፀመባቸዉ የሚገኙ ዜጎች ናቸዉ።» «በአረብ ሃገራት አብዛኛዉ ችግር የሚፈጠረዉ በኤንባሲ እና ቆንስላ ሰራተኞች ምክንያት ነዉ። አንድ የኤንባሲ ተወካይ የራሱን ዜጋ በሌላዉ አረብ ፊት የሚያንቋሽሽ ከሆነ ሌሎች ዜጎች በኛ ዜጎች ላይ የሚፈፅሙትን ጥቃት እንዴት መከላከል ይቻላል?» « እንደዉም በድፍረት ለመናገር፤ በሚደፈሩ የራሳችን ዜጋ ሴቶች ላይ ገንዘብ የሚደራደሩ፤ ገንዘብ የሚቀበሉ፤ አሳልፈዉ የሚሸጡ ዲፕሎማቶች ወይም የኤንባሲ ሰራተኞች እስካሉ ድረስ በምን አይነት መልኩ ዜጎቻችንን መመታደግ እንችላለን?»  «ሕገወጥ ወይም ያለወረቀት መስራት አንዱ መዘዝም ይህ በዜጎች ላይ የሚደርስ ንቀት ነዉ»  «ዱባይ ላይ የ 16 እና 17 ዓመት ልጆች ከፎቅ ተወርዉረዉ ሲሞቱ፤ ስቃይ ደርሶባቸዉ እያገኘን ነዉ። እነዚህ ልጆች በምን አይነት አግባብ ነዉ፤ የቀበሌ መታወቅያ አዉጥተዉ ፓስፖርት ይዘዉ አዉሮፕላን ተሳፍረዉ የመጡት ብለን መጠየቅ ይገባናል» « ኢትዮጵያ ወደ አዉሮጳ የሚሰደዱትን ዜጎች ጉዞ ብናይ የሚያልፏቸዉ ሃገራት ጥቂት ናቸዉ። ወደ ሃረብ ሃገራትም ቢሆን ቀይ ባህርን አልፈዉ ወደ አረብ ሃገራት ይሆናል የሚገቡት። ወደ ደቡብ አፍሪቃ የሚፈልሱ ወጣቶች ግን ስድስት የአፍሪቃ መዳረሻ ሃገራትን አቋርጠዉ ሕይወታቸዉ ከባህር መስመጥ አደጋና ከአዉሬ ከተረፈ ነዉ ደቡብ አፍሪቃ የሚገቡት። አሁን አሁን ደሞ መዳረሻ ሃገራቱ ቁጥጥር በማጥበቃቸዉ ወጣቶቹ በሕንድ ዉቅያኖስ ዳርቻ በኩል አድርገዉ ነዉ የሚያቋርጡት። እናም ሜዲተራንያን ባህር ላይ የሚደርሰዉ አደጋ አይነት ሕንድ ዉቅያኖስም በርካታ ኢትዮጵያዉያን እየሞቱ ነዉ። ግን ዓለም አቀፉ ሚዲያ ትኩረት ስላልሰጠዉ ሻፋን አላገኘም።» « 80 % ዉ አፍሪቃዊ የሚሰደደዉ በዝያዉ በአፍሪቃ አሕጉር ባሉ ሃገሮች ብቻ ነዉ። 20 % ዉ ነዉ ወደ አዉሮጳ እና ሃረብ ሃገራት የሚሰደደዉ።»  «ኢትዮጵያዉያን ስድስት የአፍሪቃ ሃገራትን አቋርጠዉ ደቡብ አፍሪቃ ከደረሱም በኋላ እልም ባለዉ ገጠር የሞኖሩ ኢትዮጵያዉያን ቁጥር ጥቂት አይደለም። በዚህ ገጠር ዉስጥ ደሞ ፤ የእፅ ዝዉዉር፤ የጦር መሳርያ ዝዉዉርና ስራ አጥነት የበዛበት እጅግ አደገኛ የሆነ ቦታ ነዉ» «በደቡብ አፍሪቃ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያዉያን  እጅግ የተከበሩ በኤኮኖሚም ደረጃ ለሃገሪቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦን የሚያደርጉ ናቸዉ » « ይሁንና ሱቆቻቸዉ ይዘረፍል፤ ይገደላሉ ብዙ በደልም ይፈፀምባቸዋል» ይህን ለመታደግ የኢትዮጵያ ኤንባሲ እና የቆንጽላ ጽ/ቤት ከዜጎቹ ጋር በትብብር ሊሰራ ይገባል።» «በሳዉዲ አረብያ ከ 600 እስከ 700 ሺህ ኢትዮጵያዉያን እንደሚኖሩ ይገመታል። በተባበሩት አረብ ኢሜሪቶች፤ በቤይሩት እና በሳዉዲ አረብያ ኢትዮጵያዉያን ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት የሚፈፅምባቸዉ ሃገራት ናቸዉ። በቤሩት እስከ 450 ሺህ ኢትዮጵያዉያን እንደሚኖሩ ይታመናል። ወደ አረብ ሃገራት የሚደረገዉ ጉዞ በይፋ ከተዘጋ በኋላ እንኳ በተቀመጠዉ መረጃ በሳምንት እስከ 3000 ኢትዮጵያዉያን በኢትዮጵያ አየር መንገድ አቋርጠዉ ወደ ቤይሩት ይገቡ ነበር።»  «በደቡብ አፍሪቃ ይህን ያህል ኢትዮጵያ ይገኛል ተብሎ ቁጥሩን መናገር ባይቻልም እስከ 300 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያዉያን ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል። ይህ ቁጥር መንግስት ፈቃድ ሳይሰጠዉ ያለወረቀት የሚኖረዉን ሁሉ ይጨምራል። » « ከአለፈዉ ሁለት ዓመት ወዲህ ከሳዉዲ አረብያ ብቻ ወደ 266 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ተመለሰዋል። በየሳምንቱ ወደ 10 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ወደ ሃገራቸዉ  ይመለሱ ነበር።  ደቡብ አፍሪቃን ጨምሮ ከሌሎች ሃገራት 8494 ኢትዮጵያዉያን ከነዚህ መካከል 300 የሚሆኑት ከየመን የተመለሱ ናቸዉ። »

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ
 

Audios and videos on the topic