1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ውዝግብ ያስነሳው የክልሎች ልዩ ኃይሎች ጉዳይ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 2 2015

መንግሥት ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገውና የክልሎች ልዩ ኃይሎችን በአገራዊ የፀጥታ መዋቅር ውስጥ የማስገባት ያለው ውጥን በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ አስተያየቶችን አስተናግዷል ። ውሳኔው እና ውሳኔውን ለመተግበር የተጀመረው እንቅስቃሴ በተለይ በአማራ ክልል ብርቱ ተቃውሞ ገጥሞት በበርካታ ከተሞች መደበኛ እንቅስቃሴም መታወኩ ተዘግቧል ።

https://p.dw.com/p/4Ps7G
Infografik Karte Äthiopien AM

ስለ ክልል ልዩ ኃይል የሁለቱ ፓርቲዎች አስተያየት

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ሳምንት ውስጥ ይፋ ያደረገውና የክልሎች ልዩ ኃይሎችን በአገራዊ የፀጥታ መዋቅር ውስጥ የማስገባት ያለው ውጥን በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ አስተያየቶችን አስተናግዷል ። ውሳኔው እና ውሳኔውን ለመተግበር የተጀመረው እንቅስቃሴ በተለይ በአማራ ክልል ብርቱ ተቃውሞ ገጥሞት በበርካታ ከተሞች መደበኛ እንቅስቃሴም መታወኩ ተዘግቧል ። 

ባለፈው ሐሙስ ምሽት የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት የክልል ልዩ ኃይሎችን አፍርሶ እንደገና ለማደራጀት መወሰኑን ተከትሎ በአማራ ክልል አለመረጋጋቶች መፈጠራቸው ይታወቃል ፡፡ በተለይም የፌዴራሉ መንግስት እቅዱን ለመተግበር እየተንቀሳቀሰ ነው መባሉን ተከትሎ በክልሉ በተለያዩ አከባቢዎች መንገድ የመዝጋትና ሂደቱን የመቃወም ሁኔታዎችም በስፋት ተስተውሏል ፡፡
ይህ የመንግስት ውሳኔ በመግለጫ መገለፁን ተከትሎም የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጡት የአቋም መግለጫ አንድ ጠንካራ የአገር መከላከያ በመገንባቱ መርህ ጋር የሚጣረዝ አቋም እንደሌላቸው ገልጸው፤ በተለይም በአማራ ክልል ልዩ ኃይልን የመበተኑ ጊዜ አሁን መሆን አይገባም በሚል ውሳኔውን ግን ነቅፈውታል ፡፡ 

ከዚህ በተቃራኒ ግን ሰሞነኛውን የመንግስት ውሳኔ የደገፉ የፖለቲካ ድርጅቶችም አሉ ፡፡ ለአብነትም የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሰሞነኛውን የፌዴራል መንግስት የክልሎች ልዩ ኃይሎችን በትኖ በመከላከያ እና በፌዴራል ፖሊስ የማዋቀር ውጥኑን ከደገፉት ይጠቀሳል ፡፡ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ሙላቱ ገመቹ ለዶይቼ ቬለ እንደገለጹትም፡ “እኛ እንደፓርቲ ከዚህ ቀደምም ኢ-ህገመንግስታዊ ነው ብለን ተቃውመናል ፡፡ አሁንም መንግስት አንድ ማዕከላዊ ኃይል እገነባለሁ ብሎ መንቀሳቀሱን እንደግፋለን ፡፡ ሰብዓዊ መብት እንዳይረገጥ ህግም እንዲከበር የሚበጅ ነው እንላለን፡፡ ለሂደቱም እንቅፋት መሆን ተገቢ አይደለም የሚል እምነት ነው ያለን” ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ግን ባለፈው ሳምንትም የመንግስት ልዩ ኃይሎችን በመበተን ወደ ብሔራዊ የፀጥታ መዋቅሮች የማካተት ውጥንን ተቃውመው መግለጫ ካወጡት የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ የሆነው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ነው፡፡ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር በቃሉ ዓላምረው በተለይም በአማራ ክልል ውጥረት የፈጠረው የልዩ ኃይል ታጣቂዎችን አፍርሶ ከብሔራዊ የፀጥታ መዋቅር ጋር መቀላቀል ጥረት በሌሎች ክልሎች መጀመሩን ይጠረጥራሉ፡፡ ኃላፊው “ወቅቱን ያልጠበቀ እርምጃ በመሆኑ መንግስት ውሳኔውን ሊቀለብስም ይገባል” ነው ያሉት፡፡ የአማራ ክልል “በጠላቶች የተከበበ ክልል ነው” ያሉት ፖለቲከኛው “ከመሰል ርምጃ አስቀድሞ ህገመንግስት ማሻሻልና አሁናዊውን የፌዴራል ስርዓት መዋቅርንም ማፍረስ እንደሚገባም” ነው በአስተያየታቸው ያመለከቱት፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የክልሎች ልዩ ኃይል መዋቅርን በማፍረስ በአገር መከላከያ እና በፌዴራል ወይም በክልሎች ፖሊስ መዋቅር ስር ለማደራጀት መወሰኑን በማስመልከት ባለፈው ሳምንት ይፋ ባደረገበት መግለጫው፤ የየክልሉን ልዩ ኃይሎች ወደ ተለያዩ የፀጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ የሚስችላቸውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማካሄድ ያስፈለገው የአገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ የሚያስችል አንድ ጠንካራ የተማከለ ሠራዊት ለመገንባት ነው፡፡

ጉዳዩ በተለይም በአማራ ክልል ውዝግብ ማስነሳቱን ተከትሎ ዓርብ ምሽት መግለጫ ያወጣው የክልሉ መንግስትም ሂደቱ በአመራሮች መግባባት የተፈፀመና በሁሉም ክልሎች የሚተገበር መሆኑን በማመልከት፤ የክልሉን ህዝብ ፍላጎት የሚጣረዝ ድርጊት አለመፈጸሙን አመልክቷል፡፡

የክልሉ ፕሬዝዳት አቶ ይልቃል ከፋለ ትናንት በሰጡት መግለጫም፤ ውሳኔው በክልልና በፌዴራል መንግስት ስምምነት የተወሰነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ውሳኔው በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ እንደሚሆን ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ ለውሳኔው ገቢራዊነትም ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር ውይይት መደረጉን አንስተዋል፡፡ ውሳኔው አገርን የማጽናት መሆኑን በመግለጽም የአማራ ክልል ህዝብንም ሆነ የክልሉን ልዩ ኃይል የሚጎዳ ውሳኔ አልተወሰነምም ነው የተባለው፡፡ 

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ትናንት በይፋዊ ማህበራዊ ገጻቸው ባሰራጩት ረዘም ያለው መግለጫም፤ “ከዚህ  በኋላ ክልሎች የፖሊስ ኃይላቸውን አጠናክረው ወንጀልን በመከላከልና አካባቢያዊ ጸጥታን በማስከበር ላይ ብቻ ያተኩራሉ” ብለዋል:: ዐቢይ አክለውም፤ “ከየትኛውም ኃይል የሚሰነዘር፣ የሀገርን ድንበር፣ ህልውናና ሉዓላዊነት የሚዳፈር ኃይል ሲነሣ ደግሞ የመከላከያ ሠራዊቱ እርምጃ ይወስዳል” ነው ያሉት::  ለዚህ የሚሆን አደረጃጀትም በተግባር ላይ መዋሉን ገልጸው፤ “የክልሎች ፉክክርና ትብብር በልዩ ኃይል ግንባታ ሳይሆን በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ ልማትና በዴሞክራሲያዊ ባህል ላይ ይሆናል” ነው ያሉት። ውሳኔው ለኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ለሕዝቡ ሰላም ሲባል ዋጋ ተከፍሎም ቢሆን ተግባራዊ ይደረጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይገባቸው የሚቃወሙትን ለማስረዳት ብሎም የአፍራሽነት ሚና በሚጫወቱት ላይ ተገቢው የሕግ ማስከበር ርምጃ ለመውሰድ በቂ ዝግጅት ተደርጓልም ነው ያሉት ፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ