ውቅያኖስ በድንኳ ፕላኔት፥ፕሉቶ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 23.11.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ውቅያኖስ በድንኳ ፕላኔት፥ፕሉቶ

ምድር ከፀሐይ ከምትርቀው 40 ጊዜ እጥፍ ትርቃለች፤ ድንኳ ፕላኔት ፕሉቶ። ይኽች ከፕላኔቶች ወዲያ በርቀት የምትገኘው ድንክ ፕላኔት፥ ለዘመናት እንቆቅልሽ ሆና ቆይታለች። ከእነ አምስት ጨረቆቿ ከሥርዓተ-ፀሐይ ሽክርክሪት ጠርዝ ላይ ተንሳፋ ምሥጢር ሆና ዘመን ፈጅታለች። ካለፉት ስድስት ወራት አንስቶ ግን ፕሉቶ በየጊዜው አስደናቂነቷ እየጎላ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:02
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
11:02 ደቂቃ

ውቅያኖስ በድንኳ ፕላኔት

የድንኳ ፕላኔት ፕሉቶ  ከርሠ ምድር ለሕይወት አመቺ በሆነ የበረዶ ቅይጥ የውቅያኖስ ውኃ የተሞላ መሆኑን የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ያመለክታሉ። አዲስ አድማስ (New horizone) የተሰኘችው ኅዋ ቃኝ መንኲራኲር እፕሉቶ ጥግ ደርሳ ድንኪቱን ፕላኔት ትበረብር ይዛለች። በበረዶ ግግር በተሞላው ከርሰ ምድሯ ፕሉቶ ከምድር የማይተናነስ የበረዶ ቅይጥ የውቅያኖስ ውኃ ሸሽጋ ኖራለች። ቋጥኞች፣ የበረዶ ግግሮች፤ አሁን ደግሞ የበረዶ ቅይጥ ውኃዋ ተደርሶባታል። ድንኳ ፕላኔት ፕሉቶ።   

እንደ ሥነ-ፈለክ እና ጠፈር ተመራማሪዎች ከሆነ ፕሉቶ ከፀሐይ 5.9 ቢሊዮን ኪሎ ሜትር ትርቃለች። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1930 ዓመት መገኘቷ ይፋ ከተደረገ ወዲህ መጠኗ ብዙ ሲያጨቃጭቅ ቆይቷል። ፕሉቶ ፕላኔት ናት አለያስ ድንክ ፕላኔት ሲሉም ሳይንቲስቱ ሞግተዋል። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2006 ዓለም አቀፉ ሥነ-ፈለክ ኅብረት (IAU)  ፕሉቶን ድንክ ፕላኔት ብሎ ሲሰይም ሦስት መስፈርቶችን በመዘርዘር ነበር።

በደቡብ አፍሪቃ፤ ኖርዝ ዌስት ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪው ዶክተር ጌትነት «አንደኛው መስፈርት ፕላኔቷ በፀሐይ ዙሪያ መሽከርከር አለባት፣ ሁለተኛ የራሷ የሆነ ጠንከር ያለ ስበት ያስፈልጋታል፤ ሦስተኛበዙሪያው በቅርብ የሚሽከረከሩ ነገሮች መኖር የለባቸውት» ሲሉ ሦስቱን መስፈርቶችን አብራርተዋል። ሁለቱን መስፈርቶች የምታሟላው ፕሉቶ ሦስተኛውን መስፈርት ስለማታሟላ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2006 ሳይንቲስቱ ፕሉቶ፦ «ፕላኔት መሆኗ ቀርቶ ድንክ ፕላኔት መሆን አለባት ብለው ወሰኑ» ሲሉም አክለዋል። 

ዶክተር ጌትነት እርስ በእርስ የሚሽከረከሩ ጥንድ ከዋክብት (binary stars)የሽክርክሪት ባሕሪያትን በመቃኘት ጥልቅ ጥናት አከናውነዋል። ፕሉቱ አነስተኛ ከመኾኗ የተነሳ ከፕላኔት ጁፒተር 67 ጨረቆች መካከል ከአንደኛው ትልቁ ጨረቃ እንኳ በመጠን እንደምታንስ ተናግረዋል። 


 
አዲስ አድማስ የተሰኘችው ኅዋ ቃኝ መንኲራኲር ተጠግታ እንደለካችው ከሆነ የፕሉቶ ገሚሰ-ክበብ አውታር (diameter) 2370 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው። ምናልባትም ከኢትዮጵያ ሰሜናዊ ጫፍ እስከ ናይሮቢ ያለውን ርቀት የሚሸፍን ቢሆን ነው። ይኽ ርቀት ከምድር አንጻር ሲሰላ 18.5% እንደሚደርስ የዩናይትድስ ስቴትሱ ብሔራዊ የበረራ ሳይንስ እና የኅዋ አስተዳደር (NASA) አስታውቋል። እንደው በጥቅሉ ፕሉቶ የጨረቃን ሲሦ ብታህል ነው ማለቱ ይቀላል።

አዲስ አድማስ የተሰኘችው ኅዋ ቃኚ መንኲራኲር እዚህች ድንክ ፕላኔት ምኅዋር ውስጥ ገብታ ለመቃኘት ለዐሥር ዓመት ግድም ከንፋለች። «ኒውሆራይዘን መንኲራኲር የናሳ ሳተላይት ናት ወደ ኅዋም የመጠቀችው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ006 ነው» ያሉት ዶ/ር ያብባል ታደሠ መንኲራኲሯ ፕሉቶ ጋር «ለመድረስ ረዥም ጊዜ ነው የፈጀባት» ብለዋል። «ፕሉቶ ጋር ከመጠጋቷ በፊትም ጁፒተር የተሰኘችው ፕላኔት ጋር ተጠግታ በርካታ ዳሠሣዎችን በማከናወን እስከዛሬ የማናውቀውን አዲስ ምስል ልካለች» ሲሉ አክለዋል። 

ዶ/ር ያብባል ታደሠ ያልታሰሰውን የኅዋ ክፍል ለማጥናት በሚገነባው በዓለም ትልቁ የሬዲዮ ቴልስኮፕ ላይ ጥናት ለማከናወንም ደቡብ አፍሪቃ ይገኛሉ። በአውሮጳ የኅዋ ተቋም የጠፈር አፈጣጠር ምሥጢርን ለመፍታት አሠሣ በሚያደርገው የፕላንክ ሳተላይት የሚሰበሰቡ መረጃዎችን የሚተነትኑ ሣይንቲስትም ናቸው። ወደ ፕሉቶ ከዓመታት በፊት የተላከችው መንኲራኲር ፕላኔቶችን እና የኅዋ አካላትን ማጥኛ በርካታ መሣሪያዎች በውስጧ እንደተገጠሙላት ዶ/ር ያብባል ተናግረዋል።  

መንኲራኲሯ በነዚህ መሣሪያዎቿ ባነሳችው ምስሎች እና መረጃዎች በመታገዝም ሳይንቲስቱ ስለፕሉቶ ምንነት ጥልቅ ግንዛቤ እያገኙ መኾናቸውን አስታውቀዋል። በተለይ ፕሉቶ ላይ የታየው የልብ ቅርጽ እና ቻሮን የተሰኘችው የፕሉቶ ጨረቃ ጉዞ አቅጣጫ ጥምረት ተመራማሪዎችን ድንኪቱ ፕላኔት በረዶ ቅይጥ ውኃ አላት የሚል ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ አስችሏል። «ቻሮን ከፕሉቶ ጨረቆች ትልቋ ናት» ያሉት ዶክተር ያብባል የዚህች ጨረቃ እና «ፕሉቶ ላይ የተገኘው የልብ ቅርጽ አቅጣጫ የተጣመረ አለያም የተንሰላሰለ በመሆኑ ፕሉቶ ውስጥ በረዶ ቅይጥ ውኃ ለመኖሩ ማስረጃ» እንደሆነ አብራርተዋል። ዶክተር ያብባል የጨረቃዋ እና የፕሉቶ ቅርፅ አቅጣጫ መመሳሰል «ሞገድ አለያም ስበት ለመኖሩ ጠቋሚ ነው» ብለዋል።

ፕሉቶን የሚዞሯት አምስት ጨረቆች ናቸው።  ኬርቤሮስ፣ ቻሮን፣ ሃይድራ፣ ኒክስ እና ስቲክስ። በእነዚህ አምስት ጨረቆች ታጅባ ከሥርዓተ-ፀሐይ ጠርዝ ላይ የምትገኘው ትንሺቱ ፕሉቶ ቅዝቃዜዋ ወደር አይኝለትም። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ዶ/ር ጌትነት ሲያብራሩ «አንድ ፕላኔት አለያም ድንክ ፕላኔት ከፀሐይ እየራቀ በሄደ ቁጥር እየቀዘቀዘ ነው የሚሄደው» ብለዋል። «ከጁፒተር ጀምረን፣ ሣተርን፣ ኡራነስ፣ ኔፕቲውን፣ ፕሉቶ እያልን ስንሄድ ቅዝቃዜያቸው በዛው እየጨመረ ነው የሚሄደው። ያ ማለት ወደ በረዶ የመቀየርም ባሕሪ አለው ማለት ነው።»

በእርግጥምከፀሐይ በርቀት የምትገነው ፕሉቶ የተዋቀረችው በበረዶ ግግር ነው ሲሉ ሳይንቲስቱ ይናገራሉ። «የበረዶ እና የውኃ ቅልቅል አለ ነው የተባለው። አንዳንዶች የከርሠ-ምድር ውኃ ሲሉ ይጠሩታል። በብዛት አይታይም። ከላይ ያለው የፕሉቶ አካል በረዶ የሠራ አካል ነው» ሲሉ ትንታኔ የሰጡት ዶ?ር ጌትነት «ናይትሮጂን፣ ሚቴን እና ካርበን ሞኖክሳይድ ጋዞች ራሳቸው ፕሉቶ ላይ በበረዶ መልክ ነው ያሉት» ብለዋል። «የውኃው ክፍል ያለው ከነዚህ የበረዶ ግግሮች ስር ከ100 እስከ እስከ200 ኪሎ ሜትር ጥለቀት ላይ ነው የሚገኘው። ውኃው ክፍል ራሱ ወደታች 100 ኪሎ ሜትር ጥልቀት አለው።»

ድንኪቱ ፕላኔት ፕሉቶን ለማጥናት የተላከችው የናሳ መንኲራኲር መጠነ-ሰፊ መረጃዎችን ወደ ምድር ልካለች። መንኲራኲሯ ያነሳቻቸውን የምስል ክምችቶች እና ግዙፍ መረጃዎ ወደ ምድር ለመላክ የ15 ወራት ጊዜያት ፈጅቶባታል። እናም ይኽን ተልዕኮዋን አጠናቃ ከሥርዓተ-ፀሐይ ውጪ በማቅናት ላይ ትገናለች። «ኒው ሆሪዞን ለሁለት ዓላማ ነው የተላከችው» በማለት ዶክተር ጌትነት ያብራራሉ። «አንደኛው ፕሉቶን ለማጥናት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከፕሉቶ ቀጥሎ 1.6 ቢሊዮን ኪሎ ሜትር የራቀ ሌላ ኪዩፐር ቤልት (Kuiper Belt object) የሚባል ቁስ  አለ። መንኲራኲሯ ወደዚያ እያቀናች ነው» ብለዋል። በፕሉቶ ላይ ጥናቷን የጨረሰችው ቃኚ መንኲራኲር የመጨረሻ ግቧን ስትፈጽም እንደሌሎቹ መንኲራኲሮች እንድትከስም አትደረግም። ይልቁንም ከዚህ ቀደም ጥናታቸውን አከናውነው ከሥርዓተ-ፀሐይ በመውጣት በጥልቊ ኅዋ ላይ እንደተለቀቁት የናሳ ሁለት ሳተላይቶች በራሷ ጊዜ እየተንሳፈፈች እንድትጓዝ ትደረጋለች። እዛ ከመሄዷ በፊት ግን አንድ የመጨረሻ ግብ ይቀራታል። «እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር 2019 ላይ ከፕሉቶ ቅርበት ላይ የምትገኝን ሚጢጢ ፕላኔት (asteroids) ታጠናለች» ብለዋል። ዶክተር ያብባል አክለው ሲገልጡም መንኲራኲሯ «ትሪሊዮን ወደ ሆኑ ቁሶች ወዳሉበት ኪዩፐር ቤልትም» እንደምታቀና ገልጠዋል። 

አዲስ አድማስ (New horizone) መንኲራኲር ከሥርዓተ-ፀሐይ ውጪ ስትወጣ የፀሐይ ብርኃን በጣም ደካማ ስለሚሆን ያለኃይል በዘፈቀደ ነው የምትጓዘው። እስካሁን በፕሉቶ ምኅዋር ላይ ሆና የሰበሰበችው ግዙፍ መረጃ በሳይንቲስቱ እየተተነተነ ነው። ምናልባትም 6.5 ጌጋ ባይት መጠን ያላቸው መረጃዎቹ በፕሉቶ ሕይወት ያለው ነገር ስለመኖሩ ወይንም የነበረ ስለመሆኑ ፍንጭ ይሰጡ ይሆናል። አዲስ አድማስ ግን ለተጨማሪ መረጃ  የዓመታት ጉዞዋን ቀጥላለች። ፍለጋው አያበቃም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic