ዉጥረት የጋረደዉ የአፍጋኒስታን ምርጫ | ዓለም | DW | 05.04.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ዉጥረት የጋረደዉ የአፍጋኒስታን ምርጫ

አፍጋኒስታን ውስጥ ዛሬ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሲካሄድ ዋለ። ፕሬዚዳንት ሃሚድ ካርዛይን የሚተካ ለመምረጥ ወደ 12 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ ለምርጫ መጠራቱ ተመልክቷል።

አፍጋኒስታንን ለሁለት የስልጣን ዘመን በሬዚዳንትነት ያገለገሉት ሃሚድ ካርዛይ፤ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን መወዳደር አይችሉም። ይህ የዛሬዉ ምርጫ ለአፍጋኒስታን ቀጣይ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ወሳኝ እንደሆነ እና በተለይም በሃገሪቱ ሰፍሮ የሚገኘዉና እስከያዝነዉ የጎርጎረሳዉያን ዓመት መጨረሻ ተልኮን አጠናቆ ሃገሪቱን ለቆ ይወጣል የተባለዉ ከየሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት ማለትም «ኔቶ» ቀጣይ እርምጃ ምንነትን አመላካች ነዉ ተብሏል። በአፍጋኒስታን ለፕሬዚዳንት እጩነት ከቀረቡት መካከል የቀድሞዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዱላህ አብዱላህ፤ እና ሳሚ ራዙል እንዲሁም የቀድሞዉ ዓለም ባንክ ኤኮኖሚ ጉዳይ ባልደረባ ሻራፍ ጋሃኒ ይገኙበታል። በሌላ በኩል ዛሬ በአፍጋኒስታን የተካሄደዉ ምርጫ በሃገሪቱ ለሳምንታት የዘለቀዉ የሽብር ጥቃት ከፍተኛ ስጋት ጋርዶት ነዉ የዋለዉ። በሃገሪቱ የሚንቀሳቀሰዉ አክራሪዉ እስላማዊዉ የታሊባን ሽምቅ ተዋጊ ቡድን በመካሄድ ላይ ያለዉን ምርጫ ለማደናቀፍ በተደጋጋሚ ጥቃት በመጣል ሙከራ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል።

Afghanistan Präsidentschaftswahl 2014

በምርጫው በርካታ አፍጋኒስታውያን መካፈላቸው ተገልጿል።

ዛሬ የሚካሄደዉን ምርጫ ለመዘገብ በዝግጅት ላይ ሳለች ትናንት አንዲት ዓለማቀፍ እዉቅናን ያገኘች ጀርመናዊት የፎቶግራፍ ጋዜጠኛ መገደልዋ ይታወቃል። እንደ አሶሽየትድ ፕረስ ዘገባ ጀርመናዊትዋ የፎቶግራፍ ጋዜጠኛ አንያ ኒድሪንግሃዉስ ትናንት አርብ የተገደለችዉ ከአንድ የአፍጋኒስታን ፖሊስ በተከፈተባት የጥይት ተደብድባ ነዉ። አብራት የነበረችዉ ካናዳዊት ጋዜጠኛ በፅኑ ቆስላ እዝያዉ በአፍጋኒስታን የህክምና ክትትል ላይ መሆንዋ ተመልክቶአል። በሌላ በኩል በአፍጋኒስታን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እየተደረገ ባለበት በዛሬዉ ቀን የጀርመንዋ መከላከያ ሚኒስትር ኡዙላ ፎን ደር ላየን የጀርመን ጦር በአፍጋኒስታን ስላደረገዉ የተሳካ ተልኮ አወደሱ። ሚንስትሯ ዛሬ «ቢልድ» ለተሰኘዉ ጋዜጣ በሰጡት ቃል ምንም እንኳ የጀርመን ጦር በአፍጋኒስታን አመርቂ ተግባር ቢፈፅምም፤ በተልዕኮ የወደቁ የጦሩን አባላት ጀርመን የሚረሳዉ አይሆንም። እንድያም ሆኖ የጀርመን ተልዕኮ ለሃገሪቱ ነዋሪ ብዙ መሻሻልን አምጥቷል ሲሉ ፎን ድር ላይን ተናግረዋል። በአፍጋኒስታን ዛሬ ወደ ስምንት ሚሊዮን ህጻናት ትምህርት ቤት መሄድ ችለዋል፤ ከስምንት ሚሊዮን ህጻናት መካከል ደግሞ ገሚሱ ሴቶች መሆናቸዉ ተመልክቷል። በአፍጋኒስታን በአሁኑ ወቅት ያለዉ አዲስ ትዉልድ አብዛኛዉ መጻፍ እና ማንበብ እንደሚችልም ተዘግቧል። ምንም እንኳን በአሁኑ ግዜ በሃገሪቱ በየቦታዉ ጥቃት እየታየ ህዝቡ ለምርጫ ቢወጣም፤ እንዲህ አይነቱ ርምጃ በታሊባን አስተዳደር አለመታየቱን የጀርመንዋ የመከላከያ ሚንስትር ኡዙላ ፎን ደር ላየን ተናግረዋል። የጀርመን የልማት ትብብር ሚኒስትር ጌርድ ሙለር በበኩላቸዉ አዲስ የሚመረጠዉ የአፍጋኒስታን መንግስት፤ ለዉጭ ሃገር መዋለ ንዋይ አፍሳሾች፤ የተሻለ አሰራርን ይዞ እንዲቀርብ ከወዲሁ ጠይቀዋል።

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ