ዉጥረት የነገሰበት የኮንጎ ምርጫ | የጋዜጦች አምድ | DW | 20.07.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ዉጥረት የነገሰበት የኮንጎ ምርጫ

በዲሞክራቲክ ኮንጎ ሐምሌ 23 ቀን 1998ዓ.ም የሚካሄደዉ የምክር ቤትና የፕሬዝደንት ምርጫ በአገሪቱ ታሪክ ከ40 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከናወን ነዉ።

ይህም በኮንጎ ከ1990 እስከ 1995ዓ.ም. ድረስ ሲካሄድ ለነበረዉና ወደአራት ሚሊዮን ህዝብን ለፈጀዉ የእርስ በርስ ጦርነት ማክተሚያ እንደሚሆን ይገመታል።

በኮንጎ ምርጫዉ በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ ድጋፍ የሚሰጡ 780 ወታደሮችን ፌደራል ጀርመን ልካለች። ሆኖም ምርጫዉ እንዲህ በተቃረበበት ጊዜም ኮንጎ የተረጋጋች አይደለችም።

በዲሞክራቲክ ኮንጎ ለምርጫ በሚደረገዉ የቅስቀሳ ሂደት ግጭቶች እየተባባሱ ነዉ የሄዱት። ሰላም እንደሌለ በሚነገርባት በምስራቃዊ የኮንጎ ግዛት ለምርጫ ቅስቀሳ በተሰባሰቡ ወገኖች ላይ ጥቃት ተሰንዝሯል።

ያልታወቁ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስም በሰላማዊ ሰልፉ ከተሳተፉት ሰባቱ ህይወታቸዉን አጥተዋል። በሌላ ስፍራ ደግሞ እንዲሁ ተመሳሳይ ጥቃትና ጉዳት ደርሷል።

አንድ እጩ ተወዳዳሪ ነፍሳቸዉን ለማዳን ወደጎረቤት አገር ወደዑጋንዳ ለመሸሽ ተገደዋል። ሌሎች ደግሞ የተባበሩት መንግስታትን ተገን ጠይቀዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት በዓለም ዙሪያ ካሰማራዉ ይልቅ በኮንጎ ያሰማራቸዉ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ይበረክታሉ።

ኪንሻሳ ዉስጥ ደግሞ ዉጥረቱ ተባብሷል። ፖሊስ በአስለቃሽ ጭስና በዱላ ሰልፈኞች ያልበተነበት ቀን የለም።

ማክሰኞ ዕለት 300 የሚሆኑ ሰላማዊ ሰልፈኞች ኮንጎ ለኮንጓዉያን የሚል መፈክራቸዉን እያዜሙ ጎዳና ላይ ወጥተዋል።

ይህም የዉጪ አገር ወታደሮችን በአገራቸዉ መሰማራታቸዉን እንደማይፈልጉ በግልፅ ነዉ ያሳየዉ። የሐምሌ 23ቱን ምርጫ አስመልክቶ ለጸጥታ ጥበቃ ከጀርመን የሄዱት ወታደሮች ከሌሎች የአዉሮፓ ሰላም አስከባሪዎች ጋር በመሆን ዋና ከተማዋ ኪንሻሳ ነዉ የሚገኙት።

እስከትናንት በስተያ ድረስም በኪንሻሳ የሚቆዩት 280 ወታደሮችና ጋቦን በተጠንቀቅ የሚጠብቁት 500የጀርመን የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ተጠናቀዉ በአካባቢዉ ደርሰዋል።

የጀርመን የመከላከያ ሰራዊት ኃላፊ ኪንሻሳን በጎበኙበት ወቅት ወታደሮቹ በኮንጎ የሚቆዩት ለአራት ወራት ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

ወደኮንጎ የተላከዉ ወታደራዊ ቡድን ሊቀመንበር በርንሃርድ ጌርትስ ደግሞ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎች ከወዲሁ አልታሰቡም ይላሉ።

«በማንኛዉም ወቅት ግጭት ሊከሰት እንደሚችል ሁሉም ያዉቃል። በሽግግሩ መንግስት ዉስጥ ከሚካተቱት መካከል ከቀድሞ የሚሊሻ መሪዎች መካከል አንዱ የራሱን ሚሊሻዎች ሊያነሳሳ ይችላል። ሁሉም ይህን በጥንቅቃቄ ያስተዉላሉ፤ ለምሳሌ 400 ሰላማዊ ዜጎችን የጫነች አዉሮፕላን ከአንጎላ ተነስታ እዚህ አረፈች። በስፍራዉ የነበሩት የእኛ ወታደሮች በአንድ ላይ ሲወጡ ያዩዋቸዉ ሰዎች የፕሬዝደንት ካቢላ ጠባቂዎች መስለዋቸዉ ነበር። ሆኖም ያንን ማረጋገጥ አልቻሉም፤ ይህም ለእነሱ ደህንነት አያረጋግጥም ብዬ አስባለሁ።»

በምርጫ ሂደት ሊያጋጥም የሚችለዉ የተለመደ ሁኔታም ከግምት አልገባም። የምርጫ ታዛቢዎች ከወዲሁ ድምፅ ለመስጠት ከተመዘገቡት መካከል የ1.3 ሚሊዮን ሰዎች የስም ዝርዝር እንደጠፋ ተናግረዋል።

መረጃዎቹ ተሰርቀዋል ወይም ወድመዋል ሌሎቹ ደግሞ አይነበቡም። ከዚህ ሌላ ታዛቢዎቹ የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ላይ የታየዉን ከፍተኛ ልዩነት መዝግበዋል።

ይኸዉም መገናኛ ብዙሃኑ ምርጫዉን በተመለከተ ሁለት ሶስተኛ እጅ ለፕሬዝደንት ካቢላ ቀሪዉ ደግሞ የእሳቸዉ ተቃዋሚ ለሆኑት 31 ተወዳዳሪዎች ነዉ ሽፋን የሚሰጡት።

ለማንኛዉም በገለልተኝነት የአዉሮፓ ህብረት 2,000 ሰላም አስከባሪ ወታደሮች በምርጫዉ ወቅት ፀጥታ ለመጠበቅ እዚያ ልኳል።

ባላቸዉ ግንኙነት ሳቢያ ፈረንሳይ ፕሬዝደንት ካቢላን ትደግፋለች። በርንሃርድ ጌርትስ ደግሞ ሁኔታዉ ለጀርመን ወታደሮች ጥሩ ስሜት አይፈጥርም የሚል ስጋት አላቸዉ።

«የእኛ ወታደሮች ለተሰለፉበት አላማ ጥሩ ስልጠና የወሰዱ ናቸዉ። ምክር ቤቱ ሃላፊነት ሰጥቶ መንግስት በመመሪያ ወደስፍራዉ ስለላካቸዉ ያንን ተግባራዊ ከማድረግ ዋደኋላ አይሉም። ሆኖም በመዝናኛ ስፍራ ከሌሎች ጋር ተሰብስበዉ ስለሁኔታዉ ሲወያዩ እንዲህ ያለዉን ነገር ሲረዱ ወደእዚያ ስፍራ የተላኩበት ነገር ትርጉሙን በፍፁም ሊረዱት አይችሉም።»