ዉጥረት በትንሿ ቶጎ | የጋዜጦች አምድ | DW | 21.02.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ዉጥረት በትንሿ ቶጎ

አዲሱ የቶጎ መንግስት ህገ መንግስቱን በሚፃረር መልኩ ባካሄደዉ ፕሬዝዳንታዊ ሹመት ከአገር ዉስጥም ሆነ ከዉጪ እየደረሰበት ያለዉን ተቃዉሞ መቋቋም የማይችልበት ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስላል። ቅዳሜ ዕለት በዋና ከተማዋ ሎሜ የተካሄደዉን ህዝባዊ ተቃዉሞ ተከትሎ የምዕራብ አፍሪካ አገራት የምጣኔ ሃብት ማህበረሰብ በእንግሊዝኛዉ ምህፃረ ቃሉ ኤኮዋስ በአስተዳደሩ ላይ ማዕቀብ እንደሚጥል አስታዉቋል።

ገና ስልጣን ላይ ከመዉጣታቸዉ ከያቅጣጫዉ ተቃዉሞ የወረደባቸዉ ጌናስግቤ አዲስ ምርጫ እስኪካሄድ ለ60 ቀናት ብቻ በስልጣን ላይ ልቆይ የሚል አዲስ ድርድር ሃሳብ አርብ ዕለት አቅርበዋል።
ያም ሆኖ ግን ቅዳሜ ዕለት የናይጀሪያዉ ፕሬዝዳንት ኦሉሴንጎን ኦባሳንጆ በዋና ከተማዋ አቡጃ ከቶጎ ልዑካን ጋር ዉይይት ካካሄዱ በኋላ ሃሳቡን ዉድቅ አድርገዉታል።
ይህንንም ተከትሎ ቶጎ በአሁኑ ሰዓት ከኤኮዋስ አባልነቷ ለጊዜዉ የመታገድና የአገሪቱ ከፍተኛ ባላስልጣናትም ከአገር እንዳይወጡ የሚያግድ ዉሳኔ ተጋርጦባታል።
ቅጣቱ በዚህ አያበቃም ኤኮዋስ ገና የአፍሪካ ህብረትን፤ የአዉሮፓ ህብረትንና የተባበሩት መንስግታትን የቶጎ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከአገራቸዉ ዉጪ ያላቸዉን ንብረት ማንቀሳቀስ እንዲያግዱ ይጠይቃል።
ድርጊቱነመቃወም በሎሜ 30,000 የሚገመት ህዝብ ነበር ቅዳሜ ዕለት የስድስት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ቅስቀሳ ተከትሎ የጌናሲግቤን ሹመት በመቃወም ሰልፍ የወጣዉ።
ተቃዉሞዉን የሚገልፅ ፅሁፍና መፈክር ያነገበዉ ሰልፈኛ በከተማዋ በርካታ መንገዶች አድርጎ ነዉ በመጨረሻ በከተማዋ መካከል በሚገኘዉ አደባባይ ተሰባስቦ የጋራ ድምፁን ያሰማዉ።
የቀድሞዉ ፕሬዝዳን ወዳጅ እንደሆኑ የሚነገርላቸዉ ፈረንሳይና መሪዋ ዣክ ሺራክ ላይም ህገ ወጡን መንስግስት ይደግፋሉ በሚል ተቃዉሞ በመሰንዘር የፈረንሳይን ባንዲራ ሰልፈኞቹ ያቃጠሉ ቢሆንም የደረሰ ያፀፋ ጥቃት አልተዘገበም።
ሰላማዊ ሰልፉን ካስተባበሩት ወገኖች መካከል የአንደኛዉ ቡድን ዋና ፀሃፊ እንደገለፁት አዲሱን ፕሬዝዳንት ከስልጣን ለማዉረድ ከተቃዉሞ ሰልፉ ሌላ መሳሪያ የላቸዉም።
በንግድ ዘርፍ የተሰማሩ አንዲት የሎሜ ኗሪም ከአለም ህብረተሰብ ድጋፍ ከማግኘቱ በፊት ይህንን ህገ ወጥ መንግስት ህዝቡ መቃወም ይኖርበታል በማለት ከቶጎ መሪዎች የቀረበላቸዉን ጥያቄ ዉድቅ በማድረጋቸዉ ኦባሳንጆን አመስግነዋል።
ተመሳሳይ ተቃዉሞ ከሳምንት በፊት በተደረገበት ወቅት ከባለስልጣናቱ በኩል በተወሰደ የጥቃት እርምጃ አንድ ሰዉ ወዲያዉ ሲገደል አራት ሰዎች ገደማ ሳይሞቱ እንዳልቀሩና በርካቶችም ጉዳት እንደደረሰባቸዉ ነዉ የተነገረዉ።
በሌላ በኩልም አዲሱን ፕሬዝዳንት በመደገፍ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች በቀድሞዉ የኢያዴማ መኖሪያ አካባቢ ተሰብስበዉ ነበር።
እንደሚሉትም አንዳንድ ተቺዎች ምርጫ በአገራዉ መካሄድ አለበት በማለት ቢጠይቁም ምርጫዉ ሲካሄድ ጌናሲግቤ የእነሱ እጩ ናቸዉ።
ጌናሲግቤም ለደጋፊዎቻቸዉ ባደረጉት ንግግር ለፕሬዝዳንነት ለመወዳደር እጩነታቸዉን የተቀበሉት መሆናቸዉንና ለምርጫዉ ዝግጅት ኤኮዋስ ይረዳናል ብለዉ ተስፋ እንደሚያደርጉ ነዉ የገለፁት።
የአገሪቱን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል የኢያዴማን ሞት ተከትሎ በቶጎ የተደረገዉ ሁሉ አስፈላጊና አስቸኳይ እርምጃ ነበር ባይ ናቸዉ ጌናስግቤ።
በቀላሉ ሊቢጣጠሱ የሚችሉ ማህበራዊ መስተሳስሮች ባሏት እንደ ቶጎ ባለች አገር የመሪዋን ሞት ተከትሎ የሚፈጠረዉ የስልጣን ክፍተት የማይታዩ መዘዞች ነበሩት እንደቸዉ አገላለፅ።
በቶጎ ላይ የሚጣለዉ ዕገዳ ከሚያሰጋቸዉ አገራት መካከል የባህር በር የሌላትና አብዛኛዉን የወጪ ንግዷን የምታካሂደዉ በቶጎ ወደብ የሆነዉ ቡርኪናፋሶ ግንባር ቀደም ናት።
የቡርኪና ፋሶ ፕሬዝዳንት ብሌዝ ካምፓዎሬ ግን ጌናሲግቤን ወደፕሬዝዳንነት የሚያወጣ ምንም አይነት አጋጣሚ እንደሌለ በመግለፅ ሁሉንም የሚያሳትፍ ምርጫ ባስቸኳይ መካሄድ አለበት አሳስበዋል።
የሚያስተሳስራቸዉ ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅም ይኖራል በሚል ስጋት ይመስላል በርካታ የአካባቢዉ የፓለቲካ ተንታኞች የኤኮዋስ አባል አገራት ጠንከር ያለ ዉሳኔ ላይወስዱ ይችላሉ የሚል ስጋት ይዟቸዋል።
አንድ ቤኒናዊ የፓለቲካ ተንታኝ እንደሚሉት ከሆነ ከአባል አጋራት ሁሉ ምናልባት በዉሳኔቸዉ የሚፀኑና የሚገፉበት በነዳጅ ዘይትም ሆነ በጦር ኃይል በአካባቢዉ ግዝፈዉ የሚታዩት የናይጀሪያዉ ኦባሳንጆ ብቻ ናቸዉ።
የአገሪቱ ህገ መንግስት በሚያዘዉ መሰረት ፕሬዝዳንት ከስልጣን ሲለቅ የቶጎ ብሄራዊ ሸንጎ አፈጉባኤ ፋምባሬ ናትቻባ ነበሩ በሁለት ወራት ዉስጥ አዲስ እስኪመረጥ የፕሬዝዳንትነት ስልጣኑን መያዝ የሚገባቸዉ።
በአሁኑ ወቅት ግን ፋምባሬ ናትቻባ በስደት ጎረቤት አገር በሆነችዉ ቤኒን ነዉ የሚገኙት።