ዉይይት፤ የተቃዉሞ ሰልፍ በኢትዮጵያ | ኢትዮጵያ | DW | 07.08.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ዉይይት፤ የተቃዉሞ ሰልፍ በኢትዮጵያ

ባለፈዉ ዕሁድ ጎንደር ከተማ አደባባይ የወጣዉ ሕዝብን ጥያቄዎች የተከታተሉ ታዛቢዎች እንደሚሉት የሕዝቡ ጥያቄ የወልቃይት የአስዳደር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ እና የሰብአዊ መብት፤ የዴሞክራሲ፤ የፍትሕና የነፃነት መሆኑን ያንፀባረቁ ነበሩ

አውዲዮውን ያዳምጡ። 28:33

የተቃዉሞ ሰልፍ በኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ መንግሥት የሚከተላቸዉን መርሆች በተለይም በሕዝብ ላይ ያደርሰዋል የሚባሉ የመብት ረገጣ፤ አፈና፤እስራትና ግድያን በመቃወም ለረጅም ጊዜ በተለያዩ አካባቢዎች ብርዥ ጥርዥ ይሉ የነበሩ የአደባባይ ተቃዉሞዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲሕ እየተደጋጋሙ፤እየተጠናከሩና በርካታ አካባቢዎችን እያዳረሱ ነዉ።የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ያነሱት የመብት ጥያቄ በመንግሥት ዘንድ አጓጉል ተተርጎሞ እርቅ ለማፈላለግ የተሰየመዉን ኮሚቴ መሪዎችን በማሰሩ «ድምፃችን ይሰማ» የሚል ሕዝባዊ ንቅናቄ ከፈጠረ አራተኛ ዓመቱን ደፈነ። በኦሮሚያ መስተዳድር የአዲስ አበባ የማስፋፊያ ዕቅድን በመቃወም ሰበብ ባለፈዉ ሕዳር የተቀሰቀሰዉ ሕዝባዊ ቁጣና ተቃዉሞ አሁንም መጠኑን እየቀያየረ በተለያዩ ከተሞች፤ እና ከፍተኛ የትምሕርት ተቋማት እንደቀጠለ ነዉ።

ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጓች ድርጅቶች እንዳስታወቁት የመንግሥት የፀጥታ ሐይላት ተቃዉሞዉን ለመደፍለቅ በወሰዱት የሐይል እርምጃ ከአራት መቶ በላይ ሰላማዊ ሰዎች ገድለዋል።ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን ጨምሮ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ታሥረዋል።ሌሎች በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች በተለይም ወጣቶች ተሰደዋል።

በቅርቡ በአማራ ክልል በተለይ በሰሜን ጎንደር መስተዳድር የቅማንት ሕዝብ የማንነት ጥያቄ አንስቶ ሌላ የተቃዉሞ ምክንያት ሆኗል።የወልቃይት ጠገዴ ነዋሪዎች ደግሞ በትግራይ መስተዳድር መከለላቸዉን በመቃወም ወይም አካባቢያቸዉ በአማራ መስተዳድር ስር እንዲካለል በመጠየቅ ያነሱት ጥያቄም ወደ ግጭትና የአደባባይ ሰልፍ ተለዉጧል።

ባለፈዉ ዕሁድ ጎንደር ከተማ አደባባይ የወጣዉ ሕዝብን ጥያቄዎች የተከታተሉ ታዛቢዎች እንደሚሉት የሕዝቡ ጥያቄ የወልቃይት የአስዳደር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ እና የሰብአዊ መብት፤ የዴሞክራሲ፤ የፍትሕና የነፃነት መሆኑን ያንፀባረቁ ነበሩ።በኦሮሚያና በአማራ መስተዳድር የሚደረገዉ የአደባባይ ሰልፍ እንደሚቀጥልም በማሐበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰራጩ ዘገቦች ጠቁመዋል።በዛሬዉ ዉይይታችን የሕዝቡን ጥያቄ፤ የመንግሥትን አፀፋና መፍትሔዎቹን ባጭሩ እንቃኛለን።

ነጋሽ መሐመድ

ልደት አበበ

Audios and videos on the topic