ዉይይት፣ ኢትዮጵያ፣ የምርጫ ዝግጅትና ዉዝግብ | ኢትዮጵያ | DW | 23.05.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ዉይይት፣ ኢትዮጵያ፣ የምርጫ ዝግጅትና ዉዝግብ

ከዚሕ ፈንጠር ያሉ ወገኖች ደግሞ የሕዝብ ቆጠራ አለመደረጉን፣ በየአካባቢዉ የሚደረገዉን ግጭት፣ ሁከት፣ ዉዝግብ፣ አሁን ደግሞ የዝግጅት የመጓደል ጣጣ ያልተለየዉን ምርጫ «ቢቀርስ» እስከማለት የደርሱ አሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 32:15

ጣጣ የበዛበት ምርጫ ፋይዳ አለዉ ይሆን?

 

ኢትዮጵያ ዉስጥ አምና ግንቦት መደረግ የነበረበት ብሔራዊ ምርጫ መጀመሪያ በፀጥታ መታወክና የሕዝብ ቆጠራ አለመደረጉን ጨምሮ «የዝግጅት እጥረት» በተባለ ምክንያት ለአምና ነሐሴ፣ከነሐሴ ደግሞ «የኮሮና ተሕዋሲ ሥርጭት» በሚል ሥጋት ወዳልተወሰነ ጊዜ ተራዝሞ፣ የኋላ ኋላ ዘንድሮ ግንቦት ማብቂያ ሊደረግ ተወስኖ ነበር።ምርጫዉ በተለይ ከነሐሴ ወዳልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ያስከተለዉ ሕገ-መንግሥታዊ ዉዝግብ ወትሮም በጠብ ይፈላለጉ የነበሩትን የአዲስ አበባና የያኔዎቹን የመቀሌ ገዢዎች ልዩነት አካርሮ ከጥቅምት እስከ ዛሬ ትግራይ ዉስጥ ለሚደረገዉ ጦርነት፣ ግጭትና ሁከት ዋና ምክንያት ባይሆን እንኳ ሰበብ ሆኗል።ትግራይን ዉስጥና በየአካባቢዉ የሚደረገዉን ጎሳ ለበስ ፖለቲካዊ ግጭት፣ ግድያ፣ ሁከትና አለመግባባትን  ምክንያት የሚጠቅሱ ፖለቲከኞች፣ የዉጪ መንግስታትና የፖለቲካ ተንታኞች  ከምርጫ በፊት ብሔራዊ ዉይይት እንዲደረረግ ያቀረቡትን ጥያቄና ምክር የኢትዮጵያ መንግስትና «የመንግሥት ደጋፊ» ተብለዉ የሚታሙ ፖለቲከኞች አልተቀበሉትም።

ብሔራዊ ዉይይት ይቅደም ከሚሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቢያንስ ሁለቱ ሐሳባቸዉ ዉድቅ ከመሆኑ በተጨማሪ በየፓርቲዎቹ ላይ ደረሰ ባሉት ጫናና ግፊት ምክንያት እራሳቸዉን ከምርጫዉ አግልለዋል።የምርጫ-ይደረግ-ዉይይት ይቅደም ክርክር ደርዝ ሳይበጅለት ሁለቴ የተራዘመዉ ምርጫ ለተጨማሪ ሁለት ሳምንት መራዘሙን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታዉቋል።ምርጫዉ በሁለት ሳምንት ለመራዘሙ የተሰጠዉ ምክንያት የመራጮች ምዝገባንና ሌሎች የቅድመ-ምርጫ ዝግጅቶችን ለማጠናቀቅ የሚል ነዉ።ለምርጫዉ መራዘም የተሰጠዉ ምክንያት ቦርዱ ይሁን በምርጫዉ የሚካፈሉ ፖለቲከኞች የዕቅድ-ዝግጅታቸዉ መሠረት ጥናት፣ተጨባጭ እዉነት ወይስ ስሜትና የ«አገኝ ባጣ» ይሆን ወይ የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም።

 

ኢትዮጵያ ወትሮም ባልተቃለለዉ የፀጥታና የኮሮና ወረርሽኝ ላይ በተለይም ደጋና ወይና ደጋዉ አካባቢዋ ወደ ክረምቱ ሲጠጉ ምርጫ ማድረግ ይቻልላል ወይ? ሌላዉ ጥያቄ ነዉ።ከዚሕ ፈንጠር ያሉ ወገኖች ደግሞ የሕዝብ ቆጠራ አለመደረጉን፣ በየአካባቢዉ የሚደረገዉን ግጭት፣ ሁከት፣ ዉዝግብ፣ አሁን ደግሞ የዝግጅት የመጓደል ጣጣ ያልተለየዉን ምርጫ «ቢቀርስ» እስከማለት የደርሱ አሉ።በዚሑ መሐል ግን ተጨማሪዉ የሁለት ሳምንት ጊዜ በምርጫዉ ላለመሳተፍ የወሰኑትን የፖለቲካ ፓርቲዎች ለማግባባት ቢጠቀሙበትስ የሚል የሩቅ ተስፋ የሚመስል ሐሳብ መሰንዘሩ አልቀረም።ምርጫዉን የማራዘም ሐሰብና ሐሳቡ ያስከተለዉ አስተያየት የዉይይታችን ትኩረት ነዉ ሶስት እንግዶች አሉን።

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች