ዉዝግብ ያስነሳዉ የዛምቢያ ምርጫና ዉጤቱ | የጋዜጦች አምድ | DW | 02.10.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ዉዝግብ ያስነሳዉ የዛምቢያ ምርጫና ዉጤቱ

ባለፈዉ ማክሰኞ በዛምቢያ የተካሄደዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የመነሻ ዉጤት በአገሪቱ ዉዝግብ ቀስቅሷል።

ፖሊስና ተቃዋሚዎች በዛምቢያ

ፖሊስና ተቃዋሚዎች በዛምቢያ

የፕሬዝደንት ሌቪ ሟናዋሳ የፖለቲካ ተቀናቃኞች የምርጫዉ ዉጤት ሆን ተብሎ እሳቸዉን ለመጥቀም ተሞክሮበታል ባይ ናቸዉ።

በዚህም ሳቢያ ብዙም የፖለቲካ ዉዝግብ ታይቶባት በማይታወቀዉ አፍሪካዊት አገር አመፅ ተቀስቅሷል። ሟናዋሳ ግን «ሰላም ወዳድ ዛምቢያዉያን» ከጎናቸዉ እንዲቆሙ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በዛምቢያ የተካሄደዉ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዉጤቱ በይፋ ከመነገሩ በፊት የተሰማዉ የመጀመሪያ ዙር ማመላከቻ ፕሬዝደንት ሌቪ ሟናዋሳ ተመልሰዉ በስልጣን መንበራቸዉ እንደሚደላደሉ ያመላከተ ነዉ።

በዚህ መሰረትም በህዝብ ድምፅ መመዘኛ ዉጤቶች ዋና ተፎካካሪ ናቸዉ ተብለዉ የነበሩት የአርበኞች ግምባር በእንግሊዝኛዉ ምህፃሩ (PF) መሪ ሚካኤል ሳታ ሁለተኝነትንም አጥተዉ የሶስተኛነትን ደረጃ ይዘዋል።

ያልተጠበቁት ሌላኛዉ ተፎካካሪ ዛምቢያዊዉ ባለፀጋ የንግድ ሰዉ ሃካይንዴ ሂቺሌማ ሳታን በአንድ ነጥብ በልጠዉ ሁለተኛ ሆነዉ ቀረቡ።

ምርጫዉ ከተካሄደባቸዉ 150 ጣቢያዎች መካከል ትናንት የደረሰዉ የ120ዉ ዉጤት ቆጠራ እንዳሳየዉ ሟናዋሳ 42 በመቶ፤ ሂቺሌማ 28፤ ሳታ ደግሞ 27በመቶ ድምፅ ነዉ ያስመዘገቡት።

ዉጤቱ እንደተሰማም በተቃዋሚዎቹ ጎራ የተቀሰቀሰዉ ዉጤቱ ተጭበርብሯል የሚለዉ ክስ ደጋፊዎቻቸዉን ለአመፅና የተቃዉሞ እርምጃ ሉሳካ ጎዳናዎች ላይ አዉጥቷል።

ሳታ ሟናዋሳንና የመድበለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ በእንግሊዘኛዉ ምህፃር MMD የተሰኘዉን ፓርቲያቸዉን ከ400,000 በላይ የድምፅ መስጫ ወረቀት በማበላሸት ወይም በመስረቅ ከሰዋል። ለዚህም አደገኛ አፀፋ ይከተላል በሚል ዝተዋል።

ደጋፊዎቻቸዉንም ፖሊሶች ላይ ድንጋይ ለመወርወርና ጎማዎችን በየጎዳናዉ ከማቃጠል፤ አልፈዉም በከተማዋ የሚገኙ ትላልቅ ሱቆችን እንዲሁም የገበያ አዳራሾችን ዘርፈዋል።

«የምርጫዉ ድምፅ እንዲሰረቅ አንፈቅድም» ነበር ያለዉ አንድ የተበሳጨ የተቃዋሚዉ ኃይል ደጋፊ።

ለሁለተኛ ጊዜ ምርጫዉን በማሸነፍ በመንበረ ስልጣናቸዉ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለመሰንት የተሰናዱት ፕሬዝደንት ሟናዋሳም ምርጫዉ ነፃና አግባብ ባለዉ መንገድ የተካሄደ መሆኑን አበክረዉ በማሳሰብ የሚደረጉትን የተቃዉሞ እርምጃዎች በፖሊስ ኃይል ለመመከት መዘጋጀታቸዉን ለህዝቡ ገለፁ።

ፖሊስም ጎዳና ላይ የተቃዉሞ ድምፃቸዉን የሚያሰሙትንና፤ አንዳንድ የዓመፅ እርምጃ የሚወስዱ የተቀናቃኝ ፓርቲ ደጋፊዎችን በአስለቃሽ ጭስ ለመበተን ሲታገል አመሸ።

የዛምቢያ የምርጫ ኮሚሽን አጠቃላይ የምርጫዉን ዉጤት ያሰማል ተብሎ የተጠበቀዉ ትናንት ቢሆንም የተቀሰቀሰዉ የህዝብ ቁጣና አመፅ እንዳይባባስ በመስጋት ይመስላል ለማዘግየት ተገዷል።

የዚምባቡዌን የመሬት ፖሊሲ በመደገፋቸዉ በጥያቄ ምልክት ዉስጥ የገቡት የ69ዓመቱ ሚካኤል ሳታ ምርጫዉን በተመለከተ አቤቱታ እያሰሙ ባለበት ወቅት ምርጫዉን ለመታዘብ ዛምቢያ የሚገኙት የዉጪ ታዛቢዎች ምርጫዉ ነፃና ግልፅ ነበር ብለዋል።

እንደዉም የምርጫዉ ሥርዓትና የተካሄደበት መንገድ ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነዉ የሚል እማኝነታቸዉንም ሰጥተዋል።

ምርጫዉን እንደተከታተሉት የአገር ዉስጥ፤ የዓለም ዓቀፍ ማለትም የአዉሮፓ ህብረትና የጋራ ብልፅግና ታዛቢዎች ገለፃ ከሆነ በዛምቢያ የተካሄደዉ ምርጫ የአገሪቱን የፖለቲካ ብስለት ያሳየ ነዉ።

በዚህኛዉ ምርጫ ወቅት እንዳለፉት ጊዜያት ማጭበርበርም ሆነ አጋጣሚዉን ለመጠቀም የተደረገ ሙከራ የለም።

በምርጫዉም ከተመዘገቡት ፬ሚሊዮን መራጮች መካከል ፫.፱ሚሊዮኑ ህዝብ ድምፁን ሰጥቷል። ሟናዋሳን ለዉጤት ያበቃቸዉ ስልጣን ከያዙባት ከዛሬ ፰ዓመት ጀምሮ በምጣኔ ሃብቱ ረገድ ለማስመዝገብ የሞከሩት መጠነኛ ለዉጥ መሆኑ ይነገራል።

ተቃዋሚዎቻቸዉ ደግሞ የተባለዉ እድገትም ሆነ ለዉጥ ስር የሰደደዉን የዛምቢያን ድህነት፤ ስራ አጥነትን ማስወገድ ያልቻለ፤ የመሰረተ ልማትን ችግር ያልቀረፈ መሆኑን ይናገራሉ።

ማሳያቸዉም የሟናዋሳ የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ እርምጃም ሆነ ከምዕራዉያኑ ያገኙት የቢሊዮን ዶላሮች የእዳ ስረዛ ተራዉን የዚምባቡዌ ዜጋ በቀን ከአንድ ዶላር በታች በሆነ ገቢ ከነቤተሰቡ ከመተዳደር አላደነዉም የሚል ነዉ።

ያም ሆነ ይህ የ58ዓመቱ ሟናዋሳ ለሁለተኛዉ የስልጣን ዘመናቸዉ የሚያበቃቸዉን ድጋፍ ከምርጫዉ ዉጤትና ከታዛቢዎቹ ተለግሰዋል።