ወጣቶች እና የመብት ጥያቄዎቻቸው | ባህል | DW | 16.12.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

ወጣቶች እና የመብት ጥያቄዎቻቸው

ዓረቡ ዓለምን በሕዝባዊ አብዮት ያጋመው ንቅናቄ እንዲቀጣጠል መሰረት የጣለው ቱኒዚያዊው ወጣት ራሱ ላይ ቤንዚን አርከፍክፎ በእሳት ካቃጠለ አርብ ታህሳስ 6፣ 2004 ዓ.ም. አንድ አመት ሞላው። ፍራፍሬ ነጋዴው ይህ የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ወጣት የጀመረው ግላዊ ዓመፅ ዛሬ በዓመቱ ሚሊዮኖችን አነቃንቋል።

ግብፃዊያን በታህሪር አደባባይ ለተቃውሞ

ግብፃዊያን በታህሪር አደባባይ ለተቃውሞ

ሞሐመድ ቦአዚዝ፣ አስማ ማሃፉዝ፤ ሁለቱም የዓረቡ ዓለምን ሕዝባዊ አብዮት ያነቃቁ ወጣት ሰሜነኞች ናቸው። ከመሀከላቸው የተዘረጋውን የሊቢያ በረሀ ተሻግረው ግራ ሲል ትንሿ ቱኒዚያን፣ ወደ ቀኝ መለስ ሲል ደግሞ የአባይ በረከት ተንበሽባሿ ግብፅን ትንፋሽ እስኪያጥራቸው ድረስ እንዲነቃነቁ መሰረት ጥለዋል። አንባገነን መሪዎቻቸውን ለውርደት፣ ለሽሽት ዳርገዋል ብሎም ከዘብጢያ ዶለዋል። ቆየት ብሎ ቢሆንም ታዲያ ከመሀከላቸው የተዘረጋውን የሊቢያ በረሃ ለ4 አስርት ዓመት ቀጥቅጠው የገዙት ሌላኛው አምባገነንንም «በሰፈሩት ቁና» እንዲሉ አስብለውባቸዋል።

ድምፅ፥ መፈክር

መዘዙ የሚጀምረው ከወደ ቱኒዚያ ነው፤ ልክ የነገ አንድ ዓመት ግድም። ፍራፍሬ ነጋዴው ቦአዚዝ ምንም እንኳን ከዩኒቨርሲቲ የተመረቀ ወጣት ቢሆንም ጊዜውን ሰውቶ በተማረባት ሐገሩ ስራ በቀላሉ ሊያገኝ አልቻለም። እነ ቤን አሊ ግን ቱኒዚያን በፕሬዚዳንትነት ከማስተዳደር ይልቅ ጉሮሮዋን ፈጥርቀው ሐገሪቱን ትንፋሽ አሳጥተዋት ነበር ማለት ይቀላል። እንደቦአዚዝ ሁሉ አብዛኛው ነዋሪ ለዘመናት በአምባገነንነት በገዙት መሪዎቹ ፍዳውን ከመብላት አልፎ በድህነት እየተሰቃየ ነው። ወጣቱ ቦአዚዝ የጀመራት አነስተኛ የፍራፍሬ ንግድም ብትሆን ተስፋ የምታጭር አይነት አልነበረችም። ቦአዚዝ ሰርክ ከፖሊስ ወከባ ሊድን አልቻለም። በዚያች ቀን ግን ፖሊስ አነስተኛ መደብሩን አፈራርሶ፣ ፍራፍሬዎቹን ጭኖ፣ ቦአዚዝንም ጎሻሽሞ እንደዋዛ እብስ ይላል። እናም ቦአዚዝ በራሱ ላይ ፈረደ።

ራሱን በእሳት ያቃጠለው ቱኒዚያዊ ወጣት

ራሱን በእሳት ያቃጠለው ቱኒዚያዊ ወጣት

ቦአዚዝ በፖሊስ ከተጎሳቆለ በኃላ በቀጥታ ያመራው ወደ ከተማው ማዘጋጃ ቤት ነበር። እዚያ እንደደረሰም ክቡር ገላው ላይ ቤንዚን አርከፈከፈና እሳት ለቀቀበት። እናም እንዲህ እያለይጮህ ነበር «ይህ ድህነት ይብቃ፣ ስራ አጥነቱ ያክትም!» ወጣቱ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ህይወቱ ታልፋለች፤ ብዙም ሳይቆይ ታዲያ ቱኒዚያ በሌሎች ወጣቶቿ በተቃውሞ መንደድ ትጀምራለች።

ድምፅ፥ ዓመፅ፣ ተኩስ

የያኔው የቱኒዝያ አምባገነን መሪ ፕሬዚዳንት ቤን አሊ ዓመፁን ለማክሸፍ ሲላቸው በማስፈራራት አንዳንዴም ለስለስ በማለት ሞካከሩት፤ ለውጥ ግን አልነበረም። ግፋ ሲልም ዓመፁን ለመምታት ሰዎቻቸውን ሁሉ በያለበት አሰማሩ፤ የቻሉትን ገደሉ፣ አሰሩ ቱኒዚያውያን ግን ከሞት በላይ ቢኖር እንኳ በዚያም የቆረጡ ይመስሉ ነበር። ዋና ከተማዋ ቱኒስን ጨምሮ መላ ቱኒዝያ ተንቀጠቀጠች። በመሀል ግን ደፋር መስለው ለመታየት የሞከሩት ፕሬዚዳንት ቤን አሊ ባለቤታቸውን አስከትለው፣ የቱኒዚያን ወርቅና ገንዘብ ሸካክከፈው ቱኒስ ሲጠበቁ አዳራቸውን ሳዑዲ አረቢያ አድርገው ተገኙ። ኮበለሉ፣ አልተመለሱም። ቱኒዚያውያን ግን በፈንጠዚያ አነጉ። በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገራዊ ምርጫ አከናውነው የፈቀዱትን ፓርቲ የፈለጉትን መሪ መረጡ።

ድምፅ፥ ደስታ ጭብጨባ

ነገሩ ሰሜን አፍሪቃ አናት ቱኒዚያ ላይ ተጀመሮ እዚያው ተከውኖ ባለበት አልተዳፈነም። ይልቁንስ የነፃነቱ አየር የሊቢያ በረሀን ለጊዜው በአናቱ ተሻግሮ በስተቀኝ የምትገኘዋ ግብፅ ላይ ከባድ አቧራ ማስነሳቱ ተነገረ። ለካ እዚያም እንደ ቱኒዚያ ሁሉ ሌላ አንዲት የ26 ዓመት ወጣት ተሰናድታ ኖሯል። አስማ ማሃፉዝ ትባላለች። የሚከተለውን መልዕክት ራሷ በቪዲዮ ቀርፃ እ.ኤ.አ.ጃንዋሪ 25 ቀን ኢንተርኔት ውስጥ ለቀቀችው። መልዕክቷ ግልፅ እና አጭር ነበር።

«እንደ ሰብዓዊ ፍጡር ለመኖር ትንሽም ብትሆን ፍላጎቱ ካለን፤ ጃንዋሪ 25 ወደ ጎዳናዎቹ ወጥተን መብቶቻችንን መጠየቅ አለብን። »

ግብፃውያን ወታደሮች ሠላማዊ ሰልፈኞቹ ፊት ቆመው

ግብፃውያን ወታደሮች ሠላማዊ ሰልፈኞቹ ፊት ቆመው

መልዕክቱን ባስተላለፈችበት የፌስ ቡክ አድራሻዋ ጥሪዋን አክብረው መስዋዕት ለመሆን የሚሽቀዳደሙት ወጣቶች ቁጥር ከቀን ቀን እየተበራከተ ሄደ። አስማ ማሃፉዝ አንድ ብቻዋን ያስተላለፈችው መልዕክት በቀላሉ 70 ሺህ ሌሎች ወጣቶች ልብ ውስጥ ገባ። ከውጭ ሀገራት ሳይቀር ወጣቶቹ ተጠራርተው 70 ሺህውም ዝነኛውን የታህሪር አደባባይ እንደ ድንገተኛ ሙላት አጥለቀለቁት። ወጣት ማይ ኤልማህዲ በዶቼ ቬሌ ሬዲዮ የአረብኛ ክፍል ውስጥ በጋዜጠኝነት ታገለግላለች። በወቅቱ ከካይሮ በፌስ ቡክ የተላለፈውን ጥሪ ተቀብላ ነው ከጀርመን ግብፅ ታህሪር አደባባይ የተገኘው። ያኔ ከወጣቶቹ ጋር ሌት ቁሩ፣ ቀን ፀሀዩ እንዲያ ሲፈራረቅባችሁ ስሜታችሁ ምን ይመስል ነበር ስል ጠይቅኳት፣

«በቃ እጅግ በንቅናቄ የተሞላ እና ታይቶ የማይታወቅ ተሳትፎ ነበር። ሰዉ ፍርሀቱ ከውስጡ ፈፅሞ ጠፍቶ እንደነበር መገንዘብ ይቻል ነበር። እናም ሰልፈኛው ከየትም ይምጣ ከየት፣እምነቱ ስራው ምንም ይሁን ምን ለማንም ግድ አልነበረውም። ብቻ ያኔ እዚያ ያለው ሰው ሁሉ አንድ ተመሳሳይ ሰው የሆነ ያህል ነው የተሰማው። የሁሉም ፍላጎት የሙባረክ ከስልጣን መውረድ ነበር። በሐገሪቱ የተንሰራፋው ሙስና ተወግዶ ሰዉ የተሻለ ህይወት ይኑር ነበር ጥያቄው። እናም በቃ እጅግ የሚስገርም ነበር። ግብፅ እንዲያ ሆና አይቻት አላውቅም፤ የሀገሬም ሰው እንዲያ ይሆናል ብዬ አልጠበኩም ነበር።»

በእርግጥም ግብፃውያን ለ60 ዓመታት አይተውት የማያውቁትን ነፃ እና ዲሚክራሲያዊ ምርጫ አጥብቀው የናፈቁ ነበር የሚመስሉት። በነገራችን ላይ ጎረቤት ሊቢያም ብትሆን ቀደም ሲል ከቱኒዚያ ተምዘግዝጎ ያለፋት የለውጥ ንፋስ በዙር ተመልሶ ያወዛውዛት ጀምሯል። ወደ በኋላ ላይ እንመለስበታለን። ግብፅ ግን እያደር ሲነጋ ዋና ከተማዋ ላይ የሚገኘው የታህሪር አደባባይ ለተቃውሞ በወጡ ዜጎቿ በመጨናነቅ ላይ ነው። በወጣቶቹ አነሳሽነት የጀመረው ተቃውሞ ቀስ እያለ ሁሉንም ያካተተሕዝባዊ አብዮት ወደመሆን ተቀየረ ትላለች ግብፃዊቷ የዶቼቬሌ ጋዜጠኛ።

«በመጀመሪያ ላይ ወጣቶች በተለይ ደግሞ በፌስቡክ ኢንተርኔት ላይ የተጠራሩት እና ለመምጣት ቃል የገቡት 70 ሺህ ነበሩ። እናም 70 ሺውም በቃሉ መሰረት ወደ አደባባይ ወጥቷል። ከዚያም ቁጥሩ ከዕለት ዕለት እየጨመረ ነው የሄደው። በእርግጥ መጨረሻ አካባቢ ላይ ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ ፆታ፣ እድሜ፣ እና የኑሮ ደረጃ ሳይለይ የማህበረሰቡ ሁሉም ክፍል ማለት ይቻላል ከአደባባይ ወጥቶ ነበር። በስተመጨረሻ ላይ ወጣቶች ብቻ አልነበሩም። ሆኖም ወጣቶቹ ከፍተኛ ሚና ነው የተጫወቱት። እነሱ ናቸው ያነቃቁት። »

ወጣቶቹ ያነቃቁት ሐዝባዊ አብዮት በርካታ ህይወት ገብሮ፣ ብዙዎችን ለአካል ጉዳት ዳርጎ፣ ጥቂት የማይባሉትን ዘብጥያ ወርውሮ ከአስር ወራት በኋላም ቢሆን የምስራቹን ይዞ ብቅ አለ። ሌላኛው አምባገነን መሪ ከግብፅ የፕሬዚዳንትነት ስልጣናቸው እንደሚወርዱ ይፋ ሆነ። መላ ግብፅ በፌሽታ ተሞላ። በሁለተኛ ወሩ እንደተባለው የቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሞባረክ ከስልጣናቸው መውረዳቸው ዕውን ሆነ፤ አብዛኛው ግብፃዊ በደስታ ሰከረ።

ድምፅ ፥ ደስታ

ሆስኒ ሞባረክ ስልጣን በለቀቁ በአራተኛ ወሩ ግድም ክስ ተመስርቶባቸው ፍርድ ቤት ወጣ ገባ ሲሉ ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ ሆኗል። ቆየት ብሎ ግን የፍርድ ሂደቱ በዝግ ችሎት መካሄዱና «ጉልቻ ቢቀያየር » እንዲሉ በግብፅ ወጣቶቹ በፈለጉት መልኩ ለውጥ ባለመታየቱ የታህሪር አደባባይ ዳግም በተቃውሞ መዋጡ ቲይቷል። ግብጽን ከሆስኒ ሞባረክ በኋላ በጊዜያዊነት እያስተዳደራት ያለው ወታደራዊው ምክር ቤት ሲሆን በቅርቡ ለሀገሪቱ ለመጀመሪያ የሆነው ሀገር አቀፍ ምርጫ ተካሂዷል። ለወጣቶቹ ትግላቸው ፍሬ ማፍራት ለመጀመሩ ጠቋሚ ሆኖ ታይቷል።

በአጎራባች ሊቢያ የታየው ግን ከቱኒዚያም ከግብፅም የከፋውና ከፍተኛ እልቂት የታየበት ነበር። ሊቢያን ከ40 ዓመታት በላይ የግላቸው አድርገው እንደገዟት የሚነገርላቸው ኮሎኔል ሞአማር ጋዳፊ ከግራ እና ቀኝ ጎረቤቶቻቸው የታየውን ለውጥ አይተው ላለማየት አለያም ላለመቀበል የተገዘቱ አስመስሎባቸዋል። የሊቢያ ተቃዋሚ ነፍጠኞች በሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ እየታገዙ ነፍጥ ብረታቸውን ማንሳታቸውን ጋዳፊ ከቁብም አልቆጠሩት። የቃል ኪዳን ድርጅቱ የጦር ጀቶች ከ6 ወራት ባነሰ ጊዜያት ውስጥ ለ26,000 ጊዜያት በሊቢያ አየር ተመላልሰዋል። 10,000 የአየር ጥቃት ውርጅብኝም በጋዳፊ አዝንበዋል።

ሞኣማር ጋዳፊ ከባለቤታቸው ጋር

ሞኣማር ጋዳፊ ከባለቤታቸው ጋር

ድምፅ፥ የአየር ጥቃት

ጋዳፊ ግን ይልቁንስ ከተደበቁበት ሆነውም ሳይቀር «አይጦቹን እንዳትምሯቸው» እያሉ መመሪያ ያስተላልፉ ነበር። ቆየት ብሎ ጋዳፊ አይጦች ብለው በዘለፏቸው አማፂያን ቆስለው መያዛቸውን የሚያሳየው የቪዲዮ ምስል ይፋ ሆነ። ወዲያው ግን አሁንም ድረስ ሚስጥራዊ በሆነ መልኩ ጭንቅላታቸው ላይ በጥይት ተመተው ተገደሉ። ሁለተኛ ልጃቸው ከተደበቀበት ወጥቶ እጁን ለአማጺያን ሰጠ። ባለቤታቸው የልጅ ልጆቻቸውን ሰብስበው ቀደም ሲል እግሬ አውጪኝ ብለዋል።

የሊቢያ አምባገነናዊ አገዛዝ አክትሞ ሌላ አድዲስ ምዕራፍ ተከፈተ።

ቱኒዚያዊው ወጣት ሞሐመድ ቦአዚዝ ራሱን አቃጥሎ የጀመረው፣ ግብጻዊቷ ወጣት አስማ

ማሃፉዝ በኢንተርኔት ያደራጀችው የነፃነት ጥያቄ እያደር የአረቡ ዓለም ሕዛባዊ አብዮት መሆኑ ታይቷል። ሶሪያን አስጨንቆ የመንን ትንፋሽ አሳጥቷል። በርካታ መሪዎችን ሳይቀደሙ እንዲቀድሙ ለለውጥ አሯሩጦዋል። በነገራችን ላይ ቱኒዚያዊው ወጣት ሞሐመድ ቦአዚዝ እና ግብጻዊቷ ወጣት አስማ ማሃፉዝ በአውሮፓ ህብረት የዘንድሮ የሻካሮቭ ተሸላሚዎች ተብለው ተወድሰዋል። ከሌሎች ሶስት የአረቡ ዓለም ሕዝባዊ አብዮት አቀንቃኞች ጋር በመሆንም የ50,000 ዩሮ ተሸላሚዎች መሆናቸው ይፋ ሆኗል። ከሽልማቱ በላይ ግን በሐገራቸው የማይቻል ይመስል የነበረውን ለውጥ ዕውን አድርጎዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic