ወጣቶች እና ኤች አይ ቪ | ባህል | DW | 22.07.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

ወጣቶች እና ኤች አይ ቪ

በዓለማችን በአሁኑ ወቅት 36,7 ሚሊዮን ሰዎች ከኤች አይ ቪ ጋር እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግሥታት ጸረ-ኤድስ ድርጅት ሠነድ ይገልጣል። እስከ ባለፈው ታኅሳስ ወር ድረስ ለአንድ ዓመት በተደረገው ክትትል ደግሞ ከ2,1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተሐዋሲው በደማቸው ውስጥ የተገኘባቸው ኾነው ተመዝግበዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:34

ኤች አይ ቪን ፍልሚያ

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2015 ዓመት ብቻ ባለው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ1,1 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ከኤድስ ጋር በተያያዘ ኅመምም ሞተዋል።ኤች አይ ቪ ኤድስ በዓለማችን ይበልጥ የተስፋፋው በአፍሪቃ እንደሆነ ነዉ የሚነገረዉ። በየቀኑ ኤች አይ ቪ በደሙ ውስጥ ከሚገኝበት የዓለማችን ነዋሪ መካከል ከግማሽ በላይ፦ ማለትም 66 ከመቶ ያኽሉ የሚገኘው ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪቃ በሚገኙ ሃገራት ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሚቀጥሉት 14 ዓመታት ውስጥ የኤች አይ ቪ ኤድስ መዛመትን ለማስቆም አቅዷል። ኾኖም የተሐዋሲውን ስርጭት ለመግታት የሚደረጉ ዘመቻዎች መቀዛቀዝ እና የገንዘብ ልገሳው መቀነስ የዕቅዱ መሳካት ላይ ጥርጣሬ አሳድሯል። የተባበሩት መንግሥታት ጸረ-ኤድስ ድርጅት ዳይሬክተር ሚሼል ሲዲቤ ዕቅዱ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2030 ስለመሳካቱ ስጋታቸውን በደርባኑ ጉባኤ መክፈቻ ቀን ሰኞ ገልጠዋል። «አኹን በያዝነው አሠራር የምንቀጥል ከኾነ የኤድስ መዛመትን በ2030 ዓመት ማስቆም አንችልም» ሲሉም አክለዋል።

ለመኾኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ወጣቶች ስለኤች አይቪ ኤድስ ግንዛቤያቸው ምን ይመስላል? ይኽን በተመለከተ በፌስቡክ ገጻችን አወያይተን ነበር። ለውይይት ያቀረብነው ርእሳችን እንዲህ የሚል ነበር፦ «ከያዝነዉ ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ ደርባን ደቡብ አፍርቃ ላይ 21ኛዉ ዓለም አቀፍ የኤድስ ጉዳኤ በመካሄድ ላይ ይገኛል። ከሰሃራ በስተደቡብ በሚገኙ የአፍሪቃ ሃገራት ዉስጥ 25.6 ሚሊየን የሚሆን ሕዝብ HIV በደሙ ዉስጥ እንደሚገኝ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃዎች ያመለክታሉ።

ቀደም ሲል ሰዎች ከበሽታዉ ራሳቸዉን እንዲከላከሉ የተደረጉ ጥረቶች በተሐዋሲዉ የሚያዙትንም ሆነ የሞቱትን ቁጥር ለመቀነስ እንዳስቻለ ሲነገር ቆይቷል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ስለበሽታዉ ሊደረጉ የሚገቡ ጥንቃቄዎችን የሚያስገነዝብ ቅስቀሳ በመቀዛቀዙ አዳዲስ በተሐዋሲዉ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እንዳይበረክት ስጋት መኖሩ እየተነገረ ነዉ። በየአከባቢያችሁ የHIV/AIDS በተመለከተ የሚደረገዉ የማስተማር ቅስቀሳን እና የሕክምና ክትትሉ ምን ይመስላል?» በርካታ አስተያየቶች ደርሰውናል።

ስልካቸውን በዋትስ አፕ እና በፌስ ቡክ የላኩልንን የዶይቸ ቬለ የአማርኛው ክፍል አድማጮች እና ተከታታይ ወጣቶች ደውለን አነጋግረናል። ያነጋገርናቸው ወጣቶች በአጠቃላይ የተሐዋሲውን ስርጭት ለመግታት የሚደረጉ ዘመቻዎችበተለይ ካለፉት አራት እና አምስት ዓመታት ወዲህ እጅግ ተቀዛቅዟል ብለዋል። ይኽም ስርጭቱ እንዲጨምር ሰበብ ሳይኾን አይቀርም ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል። ማኅበረሰቡ ላይ ዳግም ግንዛቤ በመስጠት መታደግ ይገባልም ብለዋል።

ሙሉ ዘገባው ከታች የድምጽ ማዕቀፉ ውስጥ ይገኛል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic