ወጣቶችና የአዳዲስ ግኝቶች ውድድር | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 28.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ወጣቶችና የአዳዲስ ግኝቶች ውድድር

ሥነ ቴክኒክ እየተስፋፋ በመጣበት ፤ በአሁኑ በ 21ኛው ክፍለ-ዘመን ፣ ሥራ ከመፈለግ ፣ ሥራ መፍጠር ይሻላል የሚል እምነት ያላቸው በኢንዱስትሪ በበለጸጉትና በአዳጊ ሀገራትም የሚገኙ ወጣቶች ቁጥር የመጨመር ምልክት እየታያበት መሆኑ ይነገራል ።

ወጣቶች ፤ የአገራቸው ሥርዓተ-ትምህርት፣ የተለያዩ ድርጅቶች ፣ ተቋማትና ማሕበረሰቡም ካበረታታቸው ፤ ለራስና ለወገን ማለት ለሀገር የሚጠቅም ተግባር የማከናወን ዕድላቸው ይበልጥ ብሩሕ ነው የሚሆነው።

ሱሃስ ጎፒናት የተባለው ህንዳዊ ወጣት« 18 ዓመት እስኪሞላኝ መጠበቁ በኋላ ያ ዕድል ሊያመልጠኝ ይችላል» በማለት በ 14 ዓመቱ በ« ኢንተርኔት ካፌ» ጀምሮ አሁን ባለኩባንያ መሆኑን ያስረዳል። ሥራ አጥነትን ለመታገል ድህነትን ለመቅረፍ ፤ ብዙ ሕዝብ ያላት ህንድን መሰል ትልቅ ሃገር በየጊዜው በርከት ያሉ የሕብረት ሥራ አንቀሳቃሺዎች ወይም ኩባንያዎች ያስፈልጓታል ባይ ነው፣ ሱሃስ ጎፒናት! ለአዲስ ግኝት ፤ ለፈጠራ ሥራ ትልቅ ዋጋ የሚሰጡና የሚያበረታቱ ፤ ሞዲን የመሰሉ መሪ ሕንድ ማግኘቷ ማለፊያ ገድ ነው፤ ለታታሪ ወጣቶች ተምሳሌነት ናቸውና ይላል! ጠ/ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ አምና በግንቦት ከተመረጡ ወዲህ በመሠረተ ልማት ፕሮጄክቶች፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማስፋፋት፣ ባቡር ሀዲድ ለመዘርጋት፣ ከተሞችን ዘመናዊ አቅድ አስይዞ ለመገንባት በሰፊው ማቀዳቸው ነው የሚነገርላቸው። በዳቮስ ፣ የዓለም የኤኮኖኖሚ መድረክ ተገኝተው ከዓለም የፖለቲካና ኤኮኖሚ መሪዎች ጋር ለመወያያት ዕድል ካጋጠማቸው 50 ወጣቶች መካከል የ 29 ዓመቱ ፊሊፒናዊው ሀኪም ሃርቪ ሊዋንግ አንዱ ሲሆን የሞቃት ሀገራት በሽታ ፤ ልማትን የቱን ያህል እንደሚያጓትት ፤ በሽታን ታግለው ሳያሸንፉ ጎስቋላ ኑሮን ማሻሻል ዘበት ነው ይላል። Global Shapers Community የተሰኘው ድርጅት መሥራች ወጣቱ ጀርመናዊ ክላውስ ሽቫብ፣ ከ 50 ከመቶ በላይ የዓለም ሕዝብ ዕድሜው ከ 30 ዓመት በታች በመሆኑ ፣ በልማት ዘርፍ የወጣቶች ተነሳሺነት የግድ ነው ባይ ነው። በነዳጅ ዘይት ሃብታሟ ቬነዝዌላ ፣ የብዙ ሰዎች ጎስቋላ አኗኗር የሚያሳዝን በመሆኑ የወጣቱን ትውልድ ብርቱ ጥረት እንደሚጠይቅ የገለጸው አንድረስ ጎንዛለዝ -ሲለን ነው። የማህበረሰብን ሕይወት ለማሻሻል ለኤኮኖሚ ዕድገት መሠረት በሆነው ሳይንስና ቴክኖሎጂ በመመራመር አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል ካሳዩትና በማሳየትም ላይ ከሚገኙት የወጣቶች ድርጅቶች መካከል ፣ የጀርመኑ ፤ Jugend forscht «ወጣቱ ይመራመራል» የተባለው ይገኝበታል። ዘንድሮ 50 ኛ ዓመቱን

Individual Access Control

በግንቦት ወር ያከብራል፤ ከውድድር ጋር ! ያም ሆኖ በዘንድሮው ክብረ- በዓል ያለፉት 50 ዓመታት የምርምር ውጤቶች በልዩ ሁኔታ መዘከራቸው የማይቀር ነው። ያ ከመሆኑ በፊት ለዘንድሮው የወጣቶች የሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ምርምር ፤ ውድድሩ ፣ በዚህ ሳምንት ነው የተጀመረው። በ 84 የጀርመን ማዕከላት 11,500 ወጣቶች የነደፏቸው ፕሮጀክቶች፤ በአያሌ አርእስት ላይ ያተኮሩ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ተንቀሳቃሽ ንዑስ ጠፍጣፍ ኮምፒዩተር ለድንገተኛ አደጋ ርዳታ ተፈላጊ ጥቅም ይሰጥ ዘንድ ተጨማሪ ምልክቶችን ለማካተት የሚመራመሩ ወጣቶች አሉ ። በነፋስ ኃይል ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ከሚተከሉ የብረት ማማዎች የሚሽከረከረው ግዙፍ ፉሪት የቤት ግድግዳዎችን ይሠነጥቅ ይሆን? በዚህ ረገድም ለመመራመር የተዘጋጁ ወጣቶች መኖራቸው ተወስቷል። እውን ፕላስቲክ፣ የብረታ ብረት ክፍሎች፤ ባትሪና የተቀመመ ፈሳሽ ንጥር (ኬሚካል ) ያለው ፣ የኤሌክትሮኒክስ ሲጋራ (ባጭሩ ኢ- ሲጋራ የሚባለው)፣ ከመደበኛው ሲጋራ ፣ ለጤንነት የተሻለ ነው ወይ? ይህንም በምርምር ለማጣራት የተሠማሩ ወጣቶች አሉ።

በ 2015 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት ፣ ከዚህ ወር አንስቶ እስከመጪው ታኅሳስ ማለት ነው፣ የ «ዩገንድ ፎርሽት» 50ኛ ዓመት እንደሚከበር ድርጅቱ ከዋና ጽ/ቤቱ ከሐምበርግ ይፋ አደርጓል። «ወጣቱ ይመራመራል » የሚለውን ድርጅት እ ጎ አ በታኅሳስ ወር 1965 ዓ ም እንዲቋቋም ያበቁት የ STERN (ኮከብ) መጽሔት ዋና አዘጋጅ የነበሩት ሄንሪ ናነን ናቸው። አርአያ ያደረጉት የዩናይትድ ስቴትሱን Science Fairs « የተሰኘውን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውድድር ነው። ናነን « የነገ ተመራማሪዎችን እንፈልጋለን » የሚል መሪ ቃልም ሆነ መፈክር ነበረ ያኔ ይዘው የተነሱት ።ይሁንና ለድርጅቱ መቋቋም ዋና መንስዔ ምን ነበር? በሐምበርግ ፤ የ« ዩገንድ ፎርሽት » የፕረስና የህዝብ ግንኙነት ተጠሪ ወ/ሮ ሌና ክርስቲያንሰንን ፣ ድርጅቱ ለምን ዓላማ ሲባል እንደተቋቋመ ጠይቄአቸው ነበር።

«ያኔ የጀርመን ሥርዓተ ትምህርት ጠንካራ ሒስ ይሠነዘርበት ነበር። «የትምህርት ደረጃ መውደቅ» የሚሰኘው አባባል የመፈከር ያህል በማስጠንቀቂያነት የሚዘወተር ጉዳይ ሆኖ ነበር። ታዲያ ሄንሪ ናነን ይህ ቃል ፣ በጋዜጠኞች አንደበትና ብዕር እንዲሁ እየተነሣ- እየተጣለ እንዲታለፍ ስላልፈለጉ፣ ለወጣቱ ትውlrድና ለጀርመን ሕዝብ የሚበጅ አንድ ነገር እንዲከናወን ፈለጉ። ስለሆነም እንደተጠቀሰው፣ በ 1965 ይህን የወጣቶች የውድድር መድረክ ፈጠሩ ። »

Bundessieger von Jugend forscht - Technik Der Bundessieger beim Wettbewerb Jugend forscht im Fachgebiet Technik, Florian Schnös aus Schweinfurt (Bayern)

ድርጅቱ ፤ በማሕበረሰብ ተነሳሽነትና በጋዜጠኛው አስተባባሪነት ነው እውን ሊሆን የቻለው፤ 50 ዓመት ጸንቶ የቆየው ወጣቶችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ የሚያወዳድረው ድርጅት ፣ በአሁኑ ጊዜ ከ 250 የማያንሱ የተለያዩ ማሕበራት፤ ምርምር የሚያበረታቱ ታላላቅና መለስተኛ ኩባንያዎች ከፍተኛ የትምህርት እንዲሁም የምርምር ተቋማት በያመቱ በሚያዋጡት ከ 10 ሚሊዮን ዩውሮ በላይ ገንዘብ ነው ስራውን የሚያካሂደው። ውድድሩ የተጀመረው በምዕራብ ጀርመን ብቻ እንደነበረ የታወቀ ነው።

« በመጀመሪያ ላይ በእርግጥ የምዕራቡ የጀርመን ክፍል ወጣቶች ብቻ ነበሩ የሚሳተፉት ። በ 1965 በመጀመሪያው ዓመት ውድድር የተሳተፉት 244 ብቻ ነበሩ። ይሁንና ባለፉት 50 ዓመታት የተሳታፊዎቹ ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ፣ አሁን በያመቱ የሚሳተፉት ወጣት ተወዳዳሪዎች ቁጥር ከ 11,00 በላይ መድረሱ ታውቋል። »

50 ዓመት ረጅም ጊዜ ነው ፣ ጀርመን በእነዚህ ዓመታት በአጠቃላይ በኤኮኖሚ የደረሰችበትን ደረጃ ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂም ምን ያህል እንደደረጀች ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለንጽጽር ሲቀርብ ቁልጭ ብሎ የሚታይ ጉዳይ ነው። የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር ፤ ለኤኮኖሚ ዕድገት ትልቅ ደጀን መሆኑ ስለተመሠከረለትም ነው ጀርመን ለዚህ ዘርፍ በየደረጃ ው ዐቢይ ግምት የምትሰጠው። ለመሆኑ በዚህ «ዩገንድ ፎርሽት » ወጣቱ ይመራመራል በተባለው ውድድር ሳቢያ ፤ ባለፉት 50 ዓመትት ከተመዘገቡት አመርቂ ውጤቶች የትኞቹ ይሆኑ? ወ/ሮ ሌና ክርስቲያንሰን---

«ያለፈው 50 ዓመት ፣ በሰፊው ውድድር የታየባቸው ፣ ማራኪ የፈጠራ ውጤቶችም የተመዘገቡበት ዘመን ነው ። አንዱ ታዋቂ ምሳሌ ፣ እ ጎ አ በ 1974 በተካሄደው የወጣቶች የሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ውድድር የተሳተፈው የሰላ አእምሮ ያለው Andreas von Bechtolsheim ነው። ትምህርቱን በመከታተል ላይ እንዳለም ነበረ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተጉዞ ፣በካሊፎርኒያ ፣ «ሲሊከን ቫሊ » SUN የተባለ ታዋቂ ኩባንያ ለማቋቋም የበቃው። ዕውቀቱንና ገንዘቡን በ «ጉግል» ሥራ ላይ ያዋለም ነው። Bechtolsheim የኮምፒዩተር ልዩ ዕውቀት ያለው የቀድሞው የጀርመን «ዩገንድ ፎርሽት» ተወዳዳሪ የነበረ ወጣት ነው። ብዙዎች የመለስተኛ ኩባንያዎች መሥራቾችና አባላት የሆኑ ፣ የ«ዩገንድ ፎርሽት » ተሳታፊዎች መኖራቸውም የታወቀ ነው። ሌላው ሳይጠቀስ የማይታለፈው ደግሞ ማሬክ ሐዘ ነው። እርሱም በ «ወጣቱ ይመራመራል» ዐውደ ርእይ፣ ልዩ ብስክሌት ሠርቶ ያሳየ ነው። በአሁኑ ጊዜ የብስክሌት ፋብሪካ አቋቁሞ ሰው ተጋድሞ የሚያሽከረክረውን ባለ 3 ተሽከርካሪ ብስክሌት ጭምር በማምረት የተሳካለት ሲሆን ፤በዛ ያሉ ሠራተኞችም ቀጥሮ በማስተዳደር ላይ ይገኛል። » በወጣቱ ይመራመራል» በሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ተራቀው በመጨረሻ ፣ ያማረ-የሠመረ ተግባር በማከናወን ላይ የሚገኙም አሉ።»

የ«ዩገንድ ፎርሽት» 50 ኛው ዓመት ክብረ በዓል ድግስ የሚዘጋጀው ፤ በራይንላንድ ፋልትዝ ፌደራል ክፍለ ሀገር በሉድቪግስሐፈን ከተማ ነው። ከ ግንቦት 18-22 2007 ! እንዴት እንደሚከበር ፤ ክርስቲያንሰን እንዲህ አብራርተዋል።

Symbolbild: Jugend forscht

«BASF በሚል የጀርመንኛ ምህጻር በሚታወቀው ኢንዱስትሪ ኩባንያ ውስጥ ነው የወርቅ ኢዮቤልዩን ከውድድር ጋር በግንቦት ወር የምናከብረው። BASF ራሱ በዚህ በ «ወጣቱ ይመራመራል» ታሪክ ባለድርሻ ነው። ባለፉት 50 ዓመት በውድድሩ ያልተለየ ኩባንያ ነው። በዓሉና አከባበሩ፣ ከታሰበው በአንድ ቀን እንዲራዘም ይደረጋል። ከተሳታፊዎች ጋር በመላ በዚያ ከሚያቀርቧቸውም ፕሮጀክቶቻቸው ጋር ነው የምናከብረው። ፐሮጀክቶቻቸውንም ፤ ዳኞች መርምረው አወዳድረው ብይን ይሰጣሉ። የፌደራሉ መንግሥት ፕሬዚዳንትም፣ በበዓሉ በመገኘት ለአሸናፊዎች ሽልማት ይሰጣሉ። ዐቢዩ ብሔራዊ የውድድር መድረክ ያለፉት ዓመታት ሥራዎችም የሚገመገሙበት ነው የሚሆነው። በ 50 ኛው ዓመት

« ወጣቱ ይመራመራል» ክብረ -በዓል፣ ማራኪ የቀድሞ ተፎካካሪዎችን ታሪኮች ፣ ዓመቱን በመላ ለህዝብ እናሳውቃለን። ከቀድሞ የውድድር ተሳታፊዎች ጋር በትልቅ አዳራሽ ዐቢይ ጉባዔ ይደረግና በሰኔ ወር ብሬመን ላይ ይከበራል። ዓመቱን በመላ በዝቅተኛ ደረጃ ልዩ የሆነ የበዓል አከባበር ይደረጋል።»

ወጣት ኢትዮጵያውያን ባጠቃላይም የአፍሪቃም ሆነ የሌሎች አዳጊ ሃገራት ወጣቶች በጀርመና ከሚካሄደው የወጣቶች ሳይንስና ቴክኖሎጂ ውድድር ምን ዓይነት አስተምህሮት ያገኙ ይሆን?

«ካለን ተመክሮ እንዳየነው፤ «ዩገንድ ፎርሽት» (ወጣቱ ይመራመራል) በእርግጥ በተለያዬ ዘርፍ የተሳካላቸውን ባለሙያዎች ለማፍራት በቅቷል።ይህ ሊሆን የቻለው ተማሪዎቹ በ Jugend forscht ራሳቸው ስለሚመራመሩ ፣ ሰፊ ጥረት ስለሚያደርጉ ነው። የራሳቸውን ርእሰ- ጉዳይ መርጠው ፣ በጥሞና ለብቻቸው፤ አንዳንዴም በመምህራን ወይም አሠልጣኞች ርዳታ ጭምር ምንጊዜም ላቅ ያለ ትኩረት ስለሚሰጡት ነው። በዋናነት ግን ራሳቸው ከአእምሮአቸው አፍልቀው ነው የሚሠሩ ።ይህ ደግሞ ፤ ለየት ባለ መንገድ ፣ ወጣቶች እያንዳንዳቸው ወደ ሳይንስ ዘልቀው እንዲገቡና ፣ በምርምሩ መጥቀው እንዲወጡ ያበቃቸዋል።»

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic