ወጣት የሽመና ባለሙያዎች | ባህል | DW | 20.05.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

ወጣት የሽመና ባለሙያዎች

ኢትዮጵያውያን የልብስ ቅድ ባለሙያዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባህላዊ አልባሳትን በዓለም አቀፍ የፋሽን ገበያ ለማስተዋወቅ የሚያደርጉት ጥረት እየተሳካላቸው ይመስላል። አልባሳቱን የሚያመርቱት የሽመና ባለሙያዎች ግን የሚያገኙት ገቢም ይሁን ከማኅበረሰቡ የሚሰጣቸው ክብር ተገቢ አይደለም እየተባለ ይተቻል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:17
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:17 ደቂቃ

ወጣት የሽመና ባለሙያዎች

የ27 አመቱ ወጣት አለባቸው ምሕረቴ ጓደኞች ከዩኒቨርሲቲ ሊመረቁ ጉድ ጉድ እያሉ ነው። አለባቸው በ2004 ዓ.ም. የአስረኛ ክፍል የመልቀቂያ ፈተና ውጤቱ 3.6 የነበረ ቢሆንም ትምህርቱን የመቀጠል ፍላጎት ግን አልነበረውም። ወጣቱ የመረጠው የሽመና ሙያ የሥራ ባህሪ ፈታኝ ከመሆኑም ባሻገር በማኅበረሰቡም ዘንድ የተናቀ ነበር።

አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገው ወንደሰን ለበርካታ ዓመታት የሰራበትን የሽመና ሙያ የተማረው ከቤተሰቦቹ ነው። ወንደሰንም እንደ አለባቸው ሁሉ የሽመና ሙያ ፈታኝ እንደ ሆነ ይስማማል።

ኢትዮጵያ ላይ ጥጥ ተፈልቅቆ፤ ተፈትሎ እና ተዳውሮ በሸማኔ ድንቅ ሙያ ከድር እና ማግ ጋር ተሸምኖ የተመረተ አንድ ሸሚዝ አሜሪካ እና አውሮጳ ላይ ከ155 እስከ 255 ዶላር ይሸጣል። በእርግጥ የልብስ ቅድ-ባለሙያዎቹ እጅም አለበት። እነዚህ አልባሳት በድረ-ገጽ ሲተዋወቁ ሙሉ በሙሉ በእጅ መሠራታቸው እና በባህላዊ ስልት መመረታቸው የሸማቾችን ቀልብ ለመሳብ በማስታወቂያነት ግልጋሎት ላይ ይውላል። ይህ ለወጣት የሽመና ባለሙያዎች የሚዋጥ አይመስልም። አለባቸው የልብስ ቅድ ባለሙያዎቹ የኢትዮጵያ ባህላዊ አልባሳት በአዳዲስ እና ቀልብ ሳቢ ንድፎች ተቀባይነታቸውን ማሳደግ መቻላቸውን ቢስማማም የሽመና ባለሙያዎቹ የሚያገኙት ክፍያ ግን ፍትሐዊ እንዳልሆነ ያምናል።

ለዘመናት የበዓላት እና የሰንበት ተደርገው የተፈረጁት የኢትዮጵያ አልባሳት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በልብስ ቅድ-ባለሙያዎች ጥረት በዓለም አቀፉ የፋሽን ኢንደስትሪ ትኩረት ማግኘት ጀምረዋል። ሥመ-ጥሩዋን የኢትዮጵያ ሞዴል ሊያ ከበደን የመሰሉ ባለሙያዎችም የኢትዮጵያ ባህላዊ አልባሳትን ለምዕራባውያኑ አኗኗር እና ምርጫ በሚመች መንገድ በማቅረብ ንግዱ ዉስጥ ገብተዋል።

አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ባህላዊ አልባሳት የቅድ ባለሙያዎች ግን የሽመና ባለሙያዎች አይደሉም። አለባቸው እና ወንደሰንም ወደ የባህላዊ አልባሳት ቅድ ሥራ እና ንግዱ ገብተዋል። ወንደሰን ከሽመና ሥራው ጎን ለጎን የልብስ ቅድ ሙያን በግሉ ተምሯል።

አለባቸው የሽመና ሙያን ፍለጋ ትምህርቱን ትቷል። መኖሪያውንም ከጎንደር ወደ ባህር ዳር ቀይሯል። የሽመናን ሙያ እስከ አዲስ አበባ እና አክሱም ዘልቆ ቀስሟል። ግን ይህ ሁሉ በቂ አይደለም። ዛሬ ላይ በኃላፊነት የሚመራውን አለባቸው እና ማስተዋል የሽመና ሥራ ኅብረት ሽርክና ማኅበር ለመመሥረት ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፏል።

ወንደሰን የሽመና ሙያን በቅርበት ማወቁ በልብስ ቅድ ሙያውም ይሁን በንግድ ሥራው ውስጥ ስኬታማ እንዲሆን እንዳገዘው ይናገራል። አሁን ከ24 ሸማኔዎች ጋር በትብብር የሚሠራው ወንደሰን የባህላዊ አልባሳት መሸጫ ሱቅ ባለቤትም ነው።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic