ወጣት ሙስሊም አክራሪዎች በጀርመን | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 09.09.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

ወጣት ሙስሊም አክራሪዎች በጀርመን

«ለቅዱስ ጦርነት» እየተባለ በምዕራብ ሀገራት የሚገኙ ወጣት ሙስሊሞች እየተሰበኩ መሰደዳቸውን ቀጥለዋል። ለዚህም ለቅዱስ ጦርነት የሚሰብኩ እና የሚመለምሉ ጀርመን ሀገርም አልጠፉም። በሶርያ ብቻ ከ 74 ሀገራት የተመለመሉ 12 000 የሚደርሱ የውጭ ሀገር ዜጎች እንዳሉ ይገመታል።

ከአንድ አምስተኛ የሚበልጡት በተለይ አረብ ተፋላሚዎች የመጡት ከምዕራብ ሀገራት ነው። ከነዚህ ውስጥ 400 የሚሆኑት ደግሞ ከጀርመን። ይህንን አሀዝ ነው በአክራሪ ቡድኖች ላይ ጥናት የሚያደርገው ተቋም ICSR በቅርቡ ይፋ ያደረገው መረጃ የሚያሳየው። «ቅዱስ ጦርነት» በሚል ለሚንቀሳቀሱት ወጣት ሙስሊሞችን ማደራጀት ከመቼውም በላይ አሁን ቀላል ሆኗል። ጀርመን ሀገር ውስጥ ከሚኖሩት 4 ሚሊዮን ሙስሊኖች መካከል አክራሪ እስልምናን የሚያራምዱት ከ 5ሺ -10ሺ እንደሚደርሱ ቢገመትም ፤ ተግባራቸው ላይ ግን ስኬታማ ናቸው። በየመንገዱ ቅዱስ ቁራንን ያድላሉ ፣ ጉባኤ ይጠራሉ፣ ቡድኖች ይመሰርታሉ። በተለይ በገንዘብ ደካማ የሆኑትን እና ተስፋ ያጡ ወጣቶችን እያሰባሰቡ ፤ የቡድናቸው አባል እንዲሆኑ ይመለምላሉ። ፍሎሪያን ኤንደረስ ፤ ከጀርመን የስደተኞች እና የፈላስያን ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት ፤ ምንም እንኳን ወደ አክራሪነት ለመግባት መንገዱ የተለያየ ቢሆንም ምክንያታቸው ግን ተቀራራቢ ነው ይላሉ።« ለምሳሌ የህይወት ትርጉም ማጣት፣ በኑሮ የሚገጥሙ ቀውሶች፣ የግል እጣ ፋንታ የመሳሰሉት አንድ ተጨባጭ ቦታ ላይ ያደርሳቸዋል። ይህን በተመለከተ ደግሞ አክራሪ የእስልምናን ርዕዎት ዓለምን የሚቀበሉበት አጋጣሚ ይፈጥራል።»

የ« አይ ኤስ» ቡድን የመገናኛ ብዙኃን እጅግ ዘመናዊ ነው። ሙያዊ ብቃት ባላቸው ሰዎች የተቀረፁ ፊልሞች እና በዘመናዊ ሁኔታ የተቀረፁ እና ሶርያ እና ኢራቅ ያለውን ጦርነት የሚያንፀባርቁ ምስሎች ይታያሉ። እንዲሁም እነዚህ በኢንተርኔት ተሰራጭተዋል። ይህ ለአንዳንድ ወጣቶች ሶርያ ድረስ ሳይሄዱ በስፍራው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ተሰምቷቸው እና ከጎን የሚቆሙበት መንገድ ይፈጠራል ይላሉ ፍሎሪያን ኤንደረስ።

«ለበርካታ ወጣቶች የአንድ ማህበረሰብ አካል መሆን ወሳኝ ነው። ይህ ሳላፊስቶች ጋ ትልቅ ስፍራ አለው። ራስን ትልቅ አድርጎ መመልከት። አንድ ሰው ደግሞ የዚህ ቡድን አካል ሲሆን ከሌሎች ከፍ የማለት ስሜት ይሰማዋል።»

አብዛኛውን ጊዜ ከጀርመን ወደ ውጊያ አካባቢ የሚላኩት ወጣት ሙስሊዮች፤ ለአጥፍቶ ጠፊነት ይመደባሉ ። ከሶስት ወር ገደማ ለምሳሌ ፊሊፕ በርግነር የተባለ ወጣት ሞሱል ውስጥ 20 ሰዎችን ጨምሮ ለሞት ዳርጓል። ቢያንስ 5 ጀርመናዊ አክራሪ ሙስሊሞች ኢራቅ ውስጥ አጥፍተው ጠፍተዋል። እነዚህ ግን በይፋ የሚታወቁት ናቸው። እውነተኛው ቁጥር ከዚህ ከፍ ሊል ይችላል። ለጦርነት የሚያነሳሱ ቪዲዮዎች በኢንተርኔት ተሰራጭተዋል። አብዛኞቹ ተጠርጣሪ ጀርመናውያንን ቪዛ መከልከል እንኳን ከባድ ያደርገዋል። ምክንያቱም እንደ ቱርክ የመሳሰሉት ሀገራት ለመሄድ ቪዛ አያስፈልጋቸውምና። ለደህንነት አስከባሪ መስሪያ ቤቶች ሁኔታው እጅግ ውስብስብ ሆኖባቸዋል። ማርዋን አቡ ታም እንደገለፁት። አብዛኞቹ ወደ ሶርያ ሊዋጉ የሄዱት ሙስሊም ጀርመናውያን በትክክል ምን ዓይነት ወንጀል እንደፈፀሙ እንኳን ለመከታተል ይዳግታል ሌሎች እዛ ሲደርሱ የሚያዩት አስደንቅጧቸው ወደ መጡበት ሀገር ይመለሳሉ። ሌሎቹ ደግሞ ይላሉ አቡ ታማ፤« ከዛ ደግሞ ሌሎች ምናልባትም ተልኮ ይዘው ወደ ጀርመን የተመለሱ ይኖራሉ። ይህ ማለት ይህን ሶርያ እና ኢራቅ የሚያካሂዱትን ጦርነት ወደዚህ ይዘው እዚህ ለማንፀባረቅ ወደ ጀርመን የሚመጡ አሉ። እነዚህ እጅግ አደገኞቹ ናቸው።ምክንያቱም ጥጋትን እንደ አግባን አድርገው ስለሚያምኑ። በአጠቃላይ ግልፅ ያልሆነ እና የተወሳሰበ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው።

ዴኒስ ስቱተ / ልደት አበበ

Audios and videos on the topic