ወጣቱ እንዴት ግጭትን መፍታት ይችላል? | ወጣቶች | DW | 06.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

ወጣቱ እንዴት ግጭትን መፍታት ይችላል?

በፖለቲካ፤ በዘር፤ በሐይማኖትም ይሁን በሌላ ሰበብ በሚነሱ ግጭቶች ወጣቶች በግንባር ቀደምትነት ተሳታፊ ናቸዉ። ተሳትፎዋቸውም አብዛኛውን ጊዜ በሰላማዊ መልኩ ሳይሆን በግጭት ሲያበቃ ይስተዋላል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:54

እንዴት ፖለቲካዊ ግጭትን መፍታት ይቻላል?

አብዛኛውን ጊዜ ወጣቶች ለአመፅ ተነሳሳሽ የሆኑ ቡድኖች ተደርገው ይወሰዳሉ። በአረብ ሀገራት በተካሄደ የህዝብ ተቃውሞ የተሳተፉ ወጣቶች እንደውም ለአለመረጋጋት እና ብጥብጥ መንስኤ ተደርገው ይታያሉ። ግን ለምን ሰላማዊ ሰልፎዎች ወይም ተቃውሞዎች ወደ አመፅ ያመራሉ። በዋና ምክንያትነት የሚጠቀሰው በመንግሥት ዘንድ ፖለቲካዊ ተደማጭነት አለማግኘት ነው። ባለፉት ሁለት አመታትም ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በተደጋጋሚ አደባባይ ወጥተዋል። ሀሳባቸውን እንዴት ገለፁ? ስርዓቱስ ምን ያህል ሰማቸው? ወጣቶች እንዴትስ ግጭቶች እና ቀውሶችን ማስወገድ ይችላሉ? የአፍሪቃውያንን ሀሳብ፣ ጭንቀት እና ተስፋ በሚዳስሰው የዛሬው 77 ከመቶው ዝግጅት የምናነሳቸው ጥያቄዎች ናቸው።

ስሙን ብሶት ብሎ የገለፀልን ወጣት በአማራ ክልል በወልድያ ከተማ በጥር ወር አጋማሽ ላይ በተካሄደው ተቃውሞ ላይ ባይካፈልም የሆነውን በቅርብ ርቀት ተከታትሏል። መንግሥት የወሰደው ርምጃ ወጣቱን ወደአላስፈለገ አቅጣጫ መርቷል የሚለው ብሶት የተደረጉት ተቃውሞዎችም በመንግስት ዘንድ ተሰሚነት ያገኛሉ የሚል እምነት የለውም። « ምክንያቱም የስትራቴጂ ችግር ስላለ ነው» ይላል።

በባህር ዳር ከተማ የሚኖረው እና ያነጋገርነው ሌላው ወጣት በ 2008 ዓም በሀገሪቱ በተካሄደ ተቃውሞ ሰልፍ ላይ ተካፍሎ ነበር። በወቅቱ የተደረገው ሰልፍ አሁን ከሚደረጉት ተቃውሞዎች በተሻለ መልኩ ነበር የተፈፀመው ይላል። « ታስቦ ታቅዶ ተነጋግረውበት የተሰራ ነው።» ሌላው ልዩነት ደግሞ በወቅቱ የተደረገው ተቃውሞ ሰልፍ መፍትሄ ማስገኘቱ ነው ይላል ወጣቱ። ከዛን ጊዜ በኋላ መንግሥት በሀገር ደረጃ ለወጣቱ 10 ሚሊዮን መድቦ ድጋፍ እየሰጠ ነው።» ይሁንና የባህር ዳሩ ወጣት በመንግሥት ላይ ያለው አቋም አሁንም አልተቀየረም። እንደዛም ሆኖ ዘንድሮ በተካሄዱ ተቃውሞዎች ላይ አልተገኘም። ይህም በወጣቶች ዘንድ የተወሰዱ ርምጃዎች ስላላስደሰቱት ነው።

በተለይ ባለፉት ጊዜያት የወጣቱን ተሳትፎ በሰፊው ያስተናገዱት እንደውም ስሜታዊነት ታይቶባቸዋል የተባሉት በኦሮምኛ ቄሮ በሚለው የወጣቶች ቃል ስር አደባባይ የወጡት ወጣቶች ናቸው። ቶላ ከነዚህ አንዱ ነው። «ተቃውሟቸውን ያሰሙት በሰላማዊ መንገድ ነው። በሰውም ሆነ በንብረት ላይ የደረሰ ውድመት የለም። ነገር ግን በእኛ በኩል ተደብድቦ ሀኪም ቤት የሚመላለስ፣ እጁ የተሰበረ፣ ማዕከላዊ ታስሮ ጉዳት የደረሰበት ተዘቅዝቆ የተገረፈ ነው ያለው።»ቶላ መንግሥት በወጣቱ ላይ ወሰደ የሚለው አፀፋ ይፋ ብቻ አይደለም።  « መፈክሮችን ሲያሰሙ የነበሩ ሰዎች ወደ ማዕከላዊ እስር ቤት ተወስደዋል፣ ከባድ የሆነ የስፖርት ቅጣት፣ ሰላማዊ ጥያቄዎችን የሚያነሱ ሰዎችን እንደ ዋና አመፅ ቀስቃሽ አድርጎ በመውሰድ የተለየ ከባድ ስፖርት እንዲሰሩ ተደርገዋል፣ ተደብድበዋል።»

ኢትዮጵያ ውስጥ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ የተቃውሞ ሰልፎች በአደባባይ ባይካሄዱም ቤት ውስጥ የመቀመጥ እና የስራ ማቆም አድማ፣ ነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎች እንዳይቀሳቀሱ ማድረግ፣ የመሳሰሉ ተቃውሞዎች ተካሂደዋል። ከሳምንቱ መጀመሪያ አንስቶ ሀገሪቱ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ማግኘቷ ደግሞ ተቃውሞውን ረገብ ያደረገው ይመስላል። ይሁንና በመንግሥትም ይሁን በጥያቄ አቅራቢዎቹ መካከል ያለው ውጥረት መባቻ አላገኘም።  ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ለዶይቸ ቬለ በጹሁፍ እንዳስረዱት ሁሉም ወጣት በአንድ አይነት መንገድ ሳይሆን በተለያየ መንገድ ተቃውሞውን ገልጿል። « ሰላማዊ ሰልፍ በመወጣት፤ ሀይል የተቀላቀለ ኣመጽን በማድረግ፤ ንብረትን በማውደም፤ ባሉበት የመንግስት፤ የፓርቲና የማህበረሰባዊ ተቋማት ውስጥ የፖለቲካ ሀሳባቸውን የሚደግፉ ሰዎችን በማሰባሰብ፤ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ጠንካራ ክርክሮችን በማድረግ፤ ሰልፎችን በቪዲዮ በመቅረጽና መረጃን የመለዋወጥ ስራን በመስራት ነው። »

ይላሉ ተንታኙ። እንደሳቸው አስተያየት መንግስት ይህንን የወጣቱን ጥያቄ በተወሰነ መልኩ ቢረዳውም በጣም ግን ብዙ ሊያደርገው የሚገባ ነገር አለ።  «በተወሰነ መልኩ ተረድቶታል የምለው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ተጨማሪ የገንዘብ አቅርቦትና የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልገው በመረዳት ሀገር ዓቀፍ ንቅናቄ መጀመሩ ነው። ነገር ግን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና የስራ እድል ማግኘት ለሁሉም ነገር ብቸኛ መፍትሄ አይደለም። ትርጉም ያለው የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የውሳኔ ሰጪነት ሚና፤ ከቁጥርና ከንግግር ማድመቂያ ያለፈ የወጣቶች ተሳትፎ መዳበር፤ ከላይ ካነሳነው በወጣቶች መካከል ለሚገኙ መመሳሰሎችና ልዩነቶች ተገቢውን ትኩረትና ምላሽ የሚሰጡ የፖሊሲ አቅጣጫዎች በጣም በአፋጣኝ ያስፈልጋሉ። ሁሉንም ወጣት በጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት ውስጥ ለማደራጀት ማሰብና ይህን አቅጣጫ ከሁሉ የበለጠ ወይም ብቸኛ መፍትሄ አድርጎ መውሰድ ስህተት ነው። በሀገሬ ሰርቼ መለወጥ አልችልም ብሎ ለሚያስብ ወጣት፤ በብሄሬ ወይም በሀይማኖቴ የተነሳ በደልና ጭቆና ይደርስብኛል ለሚል ወጣት፤ ሀሳቤን በነጻነት ብገልጽ እታሰራለው፤ እሰቃያለው ብላ ለምታስብ ወጣት፤ የመንግስት አሰራር ለገዢው ፓርቲ አባላት ብቻ የተመቻቸ፤ ለቁጥጥርና ለስለላ የሚውል፤ በሙስና የተወታተበ ነው ብላ ለምታምን ወጣት በጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት ውስጥ ተደራጅ ወይም ተደራጂ የሚለው ምላሽ ውሃ አያነሳም።»

በማለት የመንግሥትን አካሄድ የገለጹት ተንታኙ መንግሥት የተቃዋሚዎችን ጥያቄ የሚመልስበትም መንገድ የወጣቱን አቅጣጫ ወደ አንድ ወይም ወደ ሌላ መንገድ ሊመራ ይችላልም ብለዋል። «በመንግስት በኩል የሚመቻቹ የኢኮኖሚ እድሎችን ለመጠቀም ሲል ገዢውን ፓርቲ በገፍ የመቀላቀል፤ በገዢው ፓርቲ መዋቅር ውስጥ ሆኖ ስውር የፖለቲካ እንቅስቃሴን የማድረግ እድልን  ሊያመቻች ይችላል። በሌላው በኩል ደግሞ ጥያቄያቸው በአግባቡ ያልተመለሰላቸው ወጣቶች  መልሰው መላልሰው ጥያቄያቸውን በተለይ ደግሞ ፖለቲካዊ ጥያቄያቸውን ማንሳታቸው አይቀርም።»

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች