ወጣቱና የሥራ ዕድል  | ወጣቶች | DW | 12.01.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

ወጣቱና የሥራ ዕድል 

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚታዩ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ጀርባ የወጣቶች የሥራ እድል ማጣት በምክንያትነት ከሚጠቀሱ ጉዳዮች አንዱ ነው። በመኾኑም ለስደት የሚዳረጉ መበራከታቸው ይነገራል። መንግሥት በአማራ መስተዳደር ከ74 ሺህ በላይ ወጣቶች በ4 ወራት የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ብሏል። በእርግጥ ለወጣቱ በተባለው ልክ የሥራ ዕድል ተመቻችቷል?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:25

በእርግጥ ወጣቱ እንደተባለው የሥራ ዕድል ተመቻችቶለታልን?

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይ የወጣቱ ቊጣ ጎልቶ ይስተጋባል። የቁጣው መንስዔ ዘርፈ-ብዙ ነው። የአስተዳደር በደል፣ ወገንተኝነት፣ ችላ መባልና ሥራ አጥነት ከብዙዎቹ ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው። ቁጣው ባየለበት በዚህ ጊዜ መንግሥት በአማራ መስተዳደር ለሚኖሩ ከ74 ሺህ በላይ ወጣቶች በ4 ወራት ውስጥ የሥራ ዕድል መፈጠሩን  ዐሳውቋል። ሥራ አጥነት በርካቶችን ለአደገኛው የባሕርና የበረሃ ስደት ከሚዳርጉ የተለያዩ ምክንያቶች አንዱ ነው። «የጠፉ ፍልሰተኞች» የሚባለው ድረ-ገጽ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2017 በዓለም ዙሪያ 5,362 ፍልሰተኞች በስደት ላይ ሕይወታቸውን ማጣታቸውን አትቷል። በ2016 ቊጥሩ 7,807 ነበር። የሥራ ዕድል ተፈጠሮላቸዋል የተባሉት ወጣቶች ምን ይላሉ? 

ስሟን መግለጥ ያልፈለገችው ሥራ አጥ ወጣት ነዋሪነቷ በሰሜን ኢትዮጵያ ደቡብ ወሎ ውስጥ ነው። 6 ዓመታት ከኖረችበት የዓረብ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰችም 4 ዓመታት ተቆጥሯል። የምትደግፋቸው ደካማ እናት እና አንድ ህጻን ልጅ አላት። «የምተዳደረው በተገኘው አጋጣሚ እየለፋኹ፤ እየሸቀልኩ በማገኛት ጥቂት ገቢ ነው» ትላለች።  

«በቃ ምንም ነገር የለ፤ በቴሌቪዥን ሥራ አለ ምናንም ሲሉን ነበር የመጣነው። ግን  ሥራ የለም፤ በቴሌቪዥን ሥራ አለ ተብሎ እንመራለን ብለን ነበር ወደ ሀገር ቤት የመጣነው። ከዛ ግን  ሀገር ስንገባ ምንም ነገር የለም። እንግዲህ ዙሮ ዙሮ አንዳንዴ ሐብታም ካለበት  እየሠራን ምናንምን እንትን እንላለን።»

ኢትዮጵያ ውስጥ ወጣቶች ለሚያነሷቸው ተቃውሞዎች የቁጣው ዋነኛ ሰበብ ሥራ አጥነት ነው ሲል መንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜያት ይናገራል። በርካቶች ሥራ አጥነት የሰበቡ አንዱ ምክንያት ኾነ እንጂ ዋናው ነገር ሌላ ነው ይላሉ። መንግሥትንም «ዐውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም» ሲሉ ይተቻሉ። ገዢው መንግሥት ቁጣውን ያበርድልኛል ሲል በተደጋጋሚ ጊዜያት ለወጣቶች በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የሥራ ዕድሎችን መፍጠሩን ይናገራል። ከሰሞኑም በአማራ መስተዳደር በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በሚፈልጉት የሥራ ዘርፍ የአጭር ጊዜ ሥልጠና እና ብድር እንደተሰጣቸው ገልጧል። ሌላኛው የሥራ ዕድል ተሰጠ በተባለበት አካባቢ ነዋሪ የኾነው ወጣት ሞሐመድ ይማም በውስጡ ያለውን ለመተንፈስ ዕድሉን አጥቶ እንደቆየ በመግለጥ ይንደረደራል። 

«እሳኩን ድረስ የሚጠይቀን ነበር ያጣነው። ወጣቱ ብዙ በጫትም በለው በሲጋራም በለው በብዙ ሱሶች እየተጠቃ ያለው በየመንገዱ በረሐብእና በውኃ ጥም እየወደቀ ወደ ዓረብ ሀገር እሄዳለሁ እያለ ያለው  በሥራ ማጣት ምክንያት ነው። አኹን እዚህ አማራ ክልል ይኽን ያኽል ንብረት፤ ይኽን ያኽል ብር ተለቋል፤ ይኽን ያኽል ዶላር ተለቋል ይባላል፤ የት እንደሚገባ ግን ዐይታወቅም።  ለምሳሌ አኹን 2010 ነው አይደል በኢትዮጵያ? በ2009 ላይ የተለቀቀ ካለ የ2009ኞችን ያሳልፉና ለ2010 አንድ ሺህ ኹለት ሺህ ተለቀቀ ይባላል።  በብድር ይደረግላቸው ይባላል። ጭራሽ ብር የሚባል ነገር እስካሁን ድረስ የለም። በጣም ዝቅ ያለና የወረደ ነው ያለው። ምንም ነገር በዐይን ያየነው ነገር የለም። ተንኮላሽቶ ነው ያለው።»

ወጣት ሞሐመድ ኑሮን ለማሸነፍ ተሰዶ ከነበረበት ዓረብ ሀገር ከተመለሰ አምስት ዓመት ተቆጥሯል። በሚኖርበት አካባቢ «ሠፍኗል» ያለው የወገንተኝነት አሠራር እሱን ጨምሮ ወጣቱን እንዳማረረው አክሎ ገልጧል። በተደጋጋሚ «ሥራ ይሰጣችኋል ተብለን ብንመዘገብም ምንም ጠብ ያለ ነገር የለም» ያለው ወጣት ሞሐመድ አጋጣሚውን ካገኘ ፍላጎቱ ወደ ዓረብ ሀገር መመለስ ነው። 

ወጣት ብርትኳን ሥራ የላትም፤ የምትኖረው ከቤተሰቦቿ ጋር ነው። «መንግሥት እስካኹን የፈጠረልን ነገር የለም፤ ምንም ሥራ የሚባል ነገር አላየኹም» ብላለች። እንደ ሞሐመድ ኹሉ አጋጣሚውን ብታገኝ ወደ ዐረብ ሀገር መሄድ ፍላጎቷ ነው። 

«ውሸት ነው፤ እስካኹን ድረስ አንዴም ኹለቴም ሦስቴም ምዝገባ አድርገውልናል ግን ምንም ያገኘነው ነገር የለም። ወጣቱ እስካኹን ምንም አልተሰጠውም። እኔ እስካኹን ምንም አልሰማኹም። በእኛ ወረዳ እስካኹን ምንም የተገኘ ነገር የለም።»
የሚባለው እና የሚደረገው ነገር «ለየቅል ነው» ያለችው ወጣት ብርቱኳን ትዳር ከያዙት ውጪ ልክ እንደሷ ሁሉ ሥራ አጥ ጓደኞቿ ወደ ዓረብ ሀገር መሰደዳቸውን ተናግራለች። 
የወልድያ ነዋሪ የኾነው ሌላኛው ወጣት በመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቀጥሮ ይሠራል። እንደተባለው በተለያዩ አጋጣሚዎች የሥራ ዕድሎች ይፈጠራሉ ብሏል። 

«ስለእሱ እንኳን ይሄ መረጃ ለእኔ አዲስ ነው፤ 75 ሺህ ምናም ሥራ እንፈጥራለን ይባላል ሁልጊዜ። ግን ያ ስንት ታቅዷል ሥራ ለመፍጠር፤ ስንት ያኽል ቀረ፤ ስንት የሚለው ግን ብዙም እሱ እንኳን አልከታተለውም። ግን አንዳንድ ከጓደኞቼ ፤ ከሥራ ባልደረቦቼ ይህን ያኽል ሥራ መፍጥረና፤ በከብት ርባታ፤ በዶሮ ምናምን እንዲህ አድርገን ፈጥረናል ምናምን ይላሉ። አንዳንዴ በማየው ደግሞ በኮብል ስቶን፣ ኮንቴነሮችን ጥርጊያ ላይ በማድረግ  በዚያ ነው ራሴ ባየሁት ነው እንጂ ከመገናኛ አውታሮች ምናምን እንደዚህ ብዙ መረጃ የለኝም»

ስሙ እንዳይገለጥ የፈለገው የሐብሩ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ሥራ አጥ ነው። መንግሥት አመቻችቻለሁ ያለውን ሥራ ለማግኘት በተደጋጋሚ ቢመዘገብም ምንም እንዳልተፈጠረ ገልጧል። 

«ቢያንስ እስከ ሦስት አራት ጊዜ ተመዝግቤ ዐውቃለሁ፤ ተመዝግበን ዕናውቃለን እዚኹ ያለው ወረዳ ላይ ማለት ነው። በዚህ ዓመት አኹን በቅርብ ጊዜ ተመዝግበናል። ከዛ በፊትም ተመዝግበናል፤ ግን ምንም ነገር የለም። ምንም ሥራ የለም። ማንኛው ወጣት የተባለ በጠቅላላ ሥራ የለውም። አኹን ከውች ርዳታ ምናምን ተብሎ ይላካል፤ የት እንደሚያደርሱት ዐይታወቅም። ስም ይመዘግቡናል ከተመዘገበ በኋላ ምንም የሚታወቅ ነገር የለም። እንደዚህ ነው እንደዚህ ነው ይሉናል ዜሮ ነው በቃ።  ዝም ብሎ ነው። ወሬ ምናምንም ነገር የለም በቃ በዛው ይቀራል።»

ለመንግሥት ቅርበት ባላቸው የመገናኛ አውታሮች 18 ሺህ 283 ወጣቶች በአማራ መስተዳደር ተደራጅተው ብድር እንዳገኙ ዘግበዋል። መገናኛ አውታሮቹ ካለፈው ዓመት አንስቶም እስካኹን ድረስ ለ822 ሺህ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሮ 709 ሚሊዮን ብር ብድር መሰጠቱን ይገልጻሉ። የአብሮ ወረዳ ነዋሪ ወጣቱ የሥራ እድሉ እና ብድሩ የሚሰጠው ለተወሰኑ ሰዎች ነው ይላል። 

«አኹን ምን አለ መሰለህ አንዳንድ የአመራር ልጆች አንዳንድ ልጆች ይኖራሉ። ለንደዚህ አይነት አንዳንድ ልጆች ለአመራር ልጆች ብቻ ነው እንጂ የሚሰጠው ሥራ ያጣ ወጣት አኹን ቁች ብሎ ምንም ነገር የሌላቸው ሰዎች አሉ። ሥራ መሥራት እየቻለ ሥራ አጦ ምንም ገንዘብ የሌላቸው ሰዎች መሥራት ያልቻሉ ሰዎች አሉ። እነዛ ግን ዜሮ ነን በቃ። እስካሁን ዝም ብለን ምንም ያገነኘው ነገር የለም።»

ወጣት ሞሐመድ የሥራ ማጣቱ የሚያንገላታው እሱን ብቻ ሳይኾን እሱን መሰል ሌሎች ወጣቶችን ጭምር እንደኾነ በምሬት ይገልጣል።

«እኔ ለራሴ ቀረብን ብዬ ሳይኾን የምነግርህ በቃ በኅብረተሰቡ እና በወጣቱ ላይ ያለውን ጉዳት እና ጭቆና ነው የምነግርክ። ምክንያቱም እኔ አኹን አልተረዳኹም ምናምን ብዬ ስነግርህ  ወይንም ሥራ አልያዝኩም ብዬ ስነግርህ ለእኔ ለግሌ ሊመስልህ ይችላል። ግን እነደዚህ ኾኖ ሳይኾን ያለው እንዳለ በሙሉ መንገድ ላይ ወድቀው ነው የምታገናቸው፤ ከሥራ ማጣት አኳያ ቁጭ ይላሉ። ምንም የሥራ ዕድል የሚባል ነገር የለም። ብቻ ይወራል፤ እንደዚህ በኢንተርኔት ላይ፤ እናንተም እዚህ ትለቁልናላችሁ ይኼን ያኽል ሺህ ብር ተለቀቀ ይባላል ግን የት እንደሚገባም ዐይታወቅም።»

መንግሥት በሺህዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሬያለው ማለቱን በተመለከተ በፌስቡክ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ደግሞ የሚከተሉት ይገኙበታል። የሠላም ሠላማዊትን እናስቀድም፦ «እንዴት ሆኖ?» ትላለች ሠላም። «ለሪፓርት በተዘጋጀ ወረቀት ካልሆነ በሰተቀር ተግባራዊ የሥራ እድል የተፈጠረ አይመስለኝም፡፡ ጉራ ብቻ፡፡» የሚል አስተያየት ሰጥታለች። «እርካሽ የሰው ጉልበት በሚል የመንግስት ፓሊሲ 1 ወር ለፍተው የ10 ቀን ወጪ እማይሸፍን ሥራን ሥራ አትበለው ጉልበት ብዝበዛ ነው» ያለው ካሌብ እዮብ ነው። ክንዱ አብይ ደግሞ አስተያየቱን በሳቅ ምልክት ያስቀድማል። «ኧረ አታስቁኝ፤ 74,000 ስደተኛ መኾን አለበት፤ በሰቀቀን» ብሏል። 
 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች