ወጣቱና ሱሰኝነት | ወጣቶች | DW | 01.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

ወጣቱና ሱሰኝነት

በሱስ ተጋላጭ የሆነው አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ወጣቱ እንደሆነ ይነገራል። በአቻ ጓደኞች ጉትጎታ ወደ ሱስ እንዲገቡ አንዱ ምክንያት እንደሆነም የሱስ ተጠቂዎች ይነገራሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:29

አሳሳቢው ወጣት የሱስ ተጋላጮች ቁጥር መብዛት

በሱስ የተጠመዱ ወጣቶች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን መጨመሩ፤ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዳለም ይነገራል። በሲጋራ፣ አልኮልና ጫት ሱሶች የሚጠመዱት እነዚሁ ወጣቶች፤ ጊዜ፣ ሰአትና ቦታ ሳይመርጡ በየጥጋጥጉ ሱሳቸው ለማርካት ይቦዝናሉ። በሱስ ተጋላጭ የሆነው አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ወጣቱ እንደሆነ ይነገራል። በአቻ ጓደኞች ጉትጎታ ወደ ሱስ እንዲገቡ አንዱ ምክንያት እንደሆነም የሱስ ተጠቂዎች ይነገራሉ። እስራኤል ሰለሞንም ይህንኑ ነው የሚለው፤ ለአስር አመታትም በሱስ ችግር ውስጥ የነበረ ወጣት ነው። በሱስ ተጠቂዎች ማገገሚያ ማእከል አንድ ወር ከ15 ቀን ክትትል ከተደረገለት በኋላ ከሱስ ነጻ ሆኗል። በመጀመሪያ የሱስ ህይወት ሲገባበት ቀላልና ደስ የሚል ይመስላል ይላል። ሆኖም ቀስ በቀስ ለሱስ ተገዥ እንደሚያደርግ ይናገራል። «ወደ ሱስ ህይወት የገባሁት በጓደኛ ግፊት ነው። የስድስተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ። ጓደኞቼ ሲጋራና መጠጥ በተደጋጋሚ እንደሞክረው ይሰጡኝ ነበር። ከነሱ ጋር የማሳልፈው ጊዜ ተጽዕኖ ፈጥሮ ልሞክረው በሚል ሲጋራ ከዛም መጠጥ ጀመርኩ። ጫትም መቃም ካናቢስ ማጨስ ጀመርኩ። የሱስ ተገዥ ሆንኩኝ። ቤተሰቦቼ ከሱስ እንድወጣ በተደጋጋሚ ይነግሩኝ ነበር። በሰዓቱ አልቀበልም ነበር። በመጨረሻ ነገሮች ሲብስብኝ ትልቅ ውድቅት ውስጥም ስገባ ሱሰኛ መሆኔን ተቀበልኩ። እናቴ ቅዱስ ፓውሎስ ትሰራ ነበር። ቅዱስ ፓውሎስ ሆስፒታል ተኝቼ ለአንድ ወር ከ15 ቀናት ያህል ህክምና አገኘሁ። አሁን የአራኛ ዓመት የዩኒበርስቲ ተማሪ ነኝ። ዘንድሮ እመረቃለሁ። ትዳርም መስርቻለሁ።» ወጣት ጎሳዮ ኢንሳ  ከሁለት ወር ከሰባት ቀን ቆይታ በኋላ ዛሬ ከማገገሚያ ማእከሉ ይወጣል። ስላሳለፈው ህይወትና አሁን ስለሚገኝበት ሁኔታ እንዲህ ይላል። «ጫትና መጠጥ ሱሰኛ ነበርኩ። ከስምንት ዓመት በላይ ተጠቅሜያለሁ። ዩኒበርሲቲ እያለሁ ለጥናት በሚል የጀመርኩት። ሱስኛ መሆን በኢኮኖሚው በጤናም ከባድ ተጽዕኖ አለው። ኣሁን ባለሁበት ሁኔታ ምንም ሱስ የለብኝም።»

የሱስ ተጠቂዎች የዐዕምሮ ጤና እክሎች ሊያጋጥማቸው ይችላል። ከቤተሰብም ከማህበረሰቡም ጋር ላይስማሙም ይችላሉ። ዶ/ር ሰለሞን ዳቢ በቅዱስ ፓውሎስ ሆስፒታል ሳይካትሪስት ናቸው። ሱስ እንደችግር ታይቶ የህክምና ክትትል  አለው ይሉናል። የሱስ ተጠቂዎችንም ከሁለት ወር እስከ ሶስት ወር በማገገሚያ ገብተው የተለያየ የህክምና ክትትል እንደሚደረግላቸው ይናገራሉ። «ሱስ የህክምና ችግር ነው ብለን የምናስበው ከሰውየው ቁጥጥር ውጭ አንድ ንጥረ ነገር ደጋግሞ መውሰድ ብቻ ሳይሆን ለማቆም ሲሞክር አለመቻል ደረጃ ሲደርስና በየቀኑ ሌሎች ነገሮች ትቶ በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሲያደርግ እና የሚወስደውን ነገር በየጊዜው እየጨመረ ሲሄድ በሱስ ተይዟል ተብሎ ይገመታል። በመጀመሪያ ችግሩ ምን ያህል ደረጃ ላይ ነው ያለው ብለን እናያለን። ሱሱን ለማቆም እንዲወስን ይደረጋል። ቀጣዩ እንዲያቆም እናደርጋለን። ህብረተሰቡ ሱስ በህክምና መታከም እንደሚቻል ተገንዝቦ ለችግሩ ተጠቂ ለሆኑት ድጋፍ እንዲያደርግ ለመጠቆም እወዳለሁ።»

አዲስ ህይወት የሱስ ተጠቂዎች ማገገሚያ ማእከል ከተቋቋመ አንድ አመት ከአምስት ወራት ሆኖታል። ሱስ ተጠቂዎች ለማገዝ የሱስ ተጠቂዎች ለሁለት ወራት በማእከሉ ከሱስ የሚወጡበትና የሚያገግሙበት ቦታም ነው። ማእከሉ ከቅዱስ ፓውሎስ ሆስፒታል ጋር በጋራ ይሰራል። ሲስተር ይርገዱ ሀብቴ በቅዱስ ፓውሎስ ሆስፒታል ነርስ ናቸው።  ቀደም ሲሊ ያነጋገርነው እስራኤል ሰለሞን ከአራት ልጆቻቸው መሀል አንዱ ነው።  ልጃቸው የሱስ ተጠቂ መሆኑ ይህን ማእከል ለማቋቋም ምክንያት እንደሆናቸው ይናገራሉ። በማዕከሉ ሥራ ቅዱስ ፓውሎስ ሆስፒታል ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ገልጸዋል። ትውልዱ በሱስ ተገዥ እየሆነ ነው ሲሉም ያናገ,ራሉ። «ተጎድቻለሁ ብዙ እምባ ነው ያፈሰስኩት። ልጄ በሱስ ህይወት ውስጥ 10 ዓመት ቆይቷል። እሱ ፈቃደኛ ሆኖ ቅዱስ ፓውሎስ ሆስፒታል ተኝቶ ታክሞ ዳነልኝ። የማገገሚያ ማዕከሉን እሱ ሲድንልኝ ነው ለመስራት ያቀድኩት። የማገገሚያ ማዕከሉ ያለበት ደረጃ እንዲደርስ ቅዱስ ፓውሎስ ሆስፒታል ትልቁን ድርሻ ይይዛል። በማዕከሉ 74 ልጆች ተኝተው ታክመዋል፤ 150 በተመላላሽ ህክምና አግኝተዋል። ከማዕከሉ ሲወጡ ትልቅ ለውጥ ነው የሚታይባቸው።» በቅዱስ ጳውሎሱ የሱስ ተጠቂዎች ማገገሚያ ማእከል እስካሁን 74 ሰዎች ተኝተው 150 ደግሞ በተመላላሽ ታክመዋል።

ነጃት ኢብራሂም

ኂሩት መለሰ 

 

 

Audios and videos on the topic