ወደ 50ሺህ ሰዎች ከሞያሌ ተፈናቅለዋል፦ የከተማዉ ከንቲባ | ኢትዮጵያ | DW | 12.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ወደ 50ሺህ ሰዎች ከሞያሌ ተፈናቅለዋል፦ የከተማዉ ከንቲባ

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ በኦሮሚያ ክልል በሞያሌ ከተማ የመከላከያ ሠራዊት በወሰደው ርምጃ ጥቂት የማይባሉ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፎ፣ ብዙዎችን በማቁሰል ብቻ አልተገታም። በከተማዋ እና በአካባቢዉ ያሉት ቀበሌዎች ዉስጥ የሚኖሩት ወገኖችንም ለስደት ዳርጓል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:05

የሺህዎች ስደት ከኢትዮጵያ-ሞያሌ ወደ ኬንያ- ሞያሌ

የዓይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ እንደገለፁት ለደህንነታቸዉ በመስጋት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በኬንያ ድንበር ዉስጥ ወደምትገኘዉ ወደ ሞያሌ እየተሰደዱ ነው። እማኞቹ የገለፁትን የሞያሌ ከተማ ከንቲባ አቶ አስቻለው ዮሐንስ ለዶይቼ ቬሌ አረጋግጠዋል።

በዛሬዉ ዕለት በከተማዉ የተወሰነ እንቅስቃሴ መኖሩን የተናገሩት አቶ አስቻለዉ፣ በሸዋ-በር፣ በአርባሌና በሌሎች ቀበሌዎች ዉስጥ የሚኖረው ሕዝብ እየሸሹ እንደሚገኝም አክለዉ ገልፀዋል። ከዚህም ሌላ ዛሬ ከአካባቢዉ ወጣቶች ጋር የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት የተመለከተ ዉይይት እያደረጉ እንደሚገኙ አቶ አስቻለዉ ተናግረዋል።

በሞያሌ ከተማ በሸዋ-በር ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ እና ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የፈለጉ ግለሰብ ቀበሌያቸዉን ጨምሮ፣ በአርባሌ፣ በ01፣ በ02፣ በጫሙቂ፣ በመላቢ፣ በጡቃ፣ በአርገኔ፣ በመዶ፣ በሙዲ አምቦ ይኖር የነበረው ሕዝብ የመከላክያ ሠራዊት እያደረሰ ይገኛል ባለው «አፈና» ብዙ ሰዎች እየተሰደዱ እንደሆነም ይናገራሉ። «በዛሬዉ ቀን የሞያሌ ከተማ ሰዉ የማይኖርባት ኦና ነዉ የምትመስለዉ። አስፋልቱ ባዶ ነዉ። ሁሉም ቤቱን ዘግቶ ወደ ኬንያ ተሰዷል» ይላሉ የሞያሌ ከተማ ነዋሪዉ። 

የአራት ወንዶች እና የሁለት ልጃገረዶች አባት የሆኑት አንድ ግለሰብ ልጆቻቸዉን ከነባለቤታቻዉ ጋር ወደ ኬንያ መላካቸዉን ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። እሳቸዉ በሸዋ-በር ለምን እንደቀሩና ስለ ደህንነታቸዉ ጉዳይ ሲጠየቁም «በሸዋ-በር ዉስጥ ንብረት አለኝ። ቤት አለኝ፣ 10 ፍየሎች አሉኝ። በእንዲህ አይነት ጊዜ ንብረት ሊዘረፍ ይችላል መባሉንም ስለሰማሁ ንብረቴን ጥዬ ለመሄድ ሰጋሁ። መቼም ሞት አይቀርምና ንብረቴን ልጠብቅ ብዬ ነዉ የቀረሁት» ብለዋል። 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአገሪቱ ስላም እና መረጋጋት ያመጣል ቢባልም በተቃራኒዉ ነገሮችን እያባባሰ እንደሚገኝ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ይናገራሉ።

አቶ በቀለ አክለዉም መንግሥት ቶሎ ብሎ ለችግሩ መፍትሄ ካልሰጠዉ አገሪቱ ወደ-የት እንደምትሄድ «ለማንም መግለፅ የሚያስፈልግ አይመስለኝም» ብለዋል።
በቅርቡ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ ድንበሮች ላይ በተከሰተዉ ግጭት ወደ አንድ ሚሊዮን ሰዎች መፈናቀላቸዉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት አሳዉቋል።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሠ 

Audios and videos on the topic