ወደ ወገን መመለስ | ኤኮኖሚ | DW | 30.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

ወደ ወገን መመለስ

የራሷን የፋሽን ኩባንያ የመፍጠር ሕልም የያዘችዉ ወጣት በአሁኑ ጊዜ የደንበኞቿን አድናቆት ያተረፉ የቆዳ እና የሸማ ምርቶችን ለገበያ ማቅረብ ጀምራለች። አሜሪካዉያን ቤተሰቦች በማደጎ ወስደዉ ያሳደጓት አባይ ሹልዝ፤ ያለመችዉን እዉን ለማደርግ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰች ሁለት ዓመት ሆናት።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:55

አባይ ሹልዝ

ለ15 ዓመታት ከኖበረችበት ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ትዉልድ ሀገሯ ኢትዮጵያ ተመልሳ (ለራስዋ ገቢን)፤ለወገኖቿ የሥራ ዕድልን ለገበያዉ ደግሞ አዲስ ዲዛይን ይዛ ቀርባለች። የራሷን ኩባንያ መሥርታ «በኢትዮጵያ የተሠራ» የሚለዉን ምርቷን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ የነበራት ሕልም ነዉ አባይ ሹልስን ወደ ሀገሯ የመለሳት። አዲስ አበባ ዉስጥ ለሁለት ዓመታት ብቻ የቆየች ቢሆንም እያበበ በመሄድ ላይ የሚገኘዉ የእጅ ቦርሳ እና ሌሎች የቆዳ ዉጤቶች እንዲሁም የሸማ ምርት የኒዉዮርክን ፋሽን ሳምንት እና አንዳንድ ፋሽን ላይ የሚያተኩሩ መጽሔቶችን ትኩረት ስቧል። አባይ ZAAF የሚል መለያ የያዙ ምርቶችን ለገበያ ማቅረብ የጀመረዉ አዲስ ኩባንያ መሥራች እና ዳይሬክተር ናት። ZAAF የሚለዉን መለያ የያዙት ዉድ ምርቶች ማለትም የአንገት ልብሶች፣ የእጅ እና የገንዘብ መያዛ ቦርሳዎች በሙሉ የሚሠሩት በእጅ ነዉ። ለወጣቷ የዲዛይን ባለሙያ እነዚህ ሁሉ ምርቶች የሚሠሩበት ጥሬ ዕቃ ምንጭ ትልቅ ትርጉም አለዉ።

«ኢትዮጵያዉ ዉስጥ እነዚህን ምርቶች የምናዘጋጅባቸዉን የጥሬ ዕቃ ዓይነቶች ለመምረጥ የምንችለዉን ጥረት እናደርጋለን። ለምሳሌ ይህ የቀበቶ ጫፍ ማያያዣዉ የተሠራዉ ከላም ቀንድ ሲሆን ይህም ከዚሁ ከኢትዮጵያ በመሆኑ ሲታይም ያማረና ዉድ ያደርገዋል።»

ኢትዮጵያ ዉስጥ ወላጆቻቸዉን ያጡ ልጆች በሚያድጉበት ስፍራ የሕጻንነት ጊዜዋን ያሳለፈችዉ አባይ በ11 ዓመቷ ቴክሳስ አሜሪካ በሚኖሩ ቤተሰቦች በማደጎ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ወሰዷት። እዚያ በቆየችባቸዉ ዓመታትም ኤኮኖሚክስ እና ስነጥበብን በመማር ለአሁኑ ሥራዋ መሠረት ጥላለች። ሌላ ሀገር ሄዳ ማደግ እና መማሯ ከሀገሯ በመንፈስ እንድትርቅ ያላደረጋት አባይ ሹልስ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ የጀመረችዉ ያማሩ የቆዳ ዉጤቶች እና ሌሎች ምርቶች አቅራቢ ኩባንያዋ በአሁኑ ወቅት ለ17 ወጣት ሴቶች እና ወንዶች ወገኖቿ የሥራ ዕድል ፈጥሯል። በሥሯ ተቀጥረዉ የሚገኙት ሠራተኞች ከአለቅነቷ ይልቅ አርአያነቷን ይናገሩላታል።

ድምጽ «አባይ እንደአለቃ አይደለችም፤ እንደታላቅ እህት ነች። ታሠለጥነናለች፤ ትከታተለናለች። እዚህ ከመጣሁ ጀምሮ ለእኔ ጥሩ ሰዉ ናት።»

ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች የራሷን ዲዛይኖች ለመሥራት ትሞክር የነበረዉ አባይ ሹልዝ እንዲህ ወዳለዉ የሥራ መስክ ለመግባት ለአምስት ዓመታት አስባበታለች።

ለኩባንያዋ ሥራ መነሻ ገንዘብ ያገኘችዉ ከቤተሰቦቿ ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ የንግዱ እንቅስቃሴ ጥሩ ነዉ ግን ደግሞ የራሱ የሆኑ ተግዳሮቶች አሉት።

«እዚህ የንግድ ሥራ ለማካሄድ ያሉት ተግዳሮቶች የታወቁ ናቸዉ ብዬ እገምታለሁ፤ መሠረታዊ ከሆኑት ለምሳሌ ኤሌክትሪክ ይቋረጣል፤ ሰዎች በሰዓታቸዉ አይገኙም፤ በእዉነቱ ይህ በጣም አስቸጋሪ ነዉ፣ እንደዉ ባጠቃላይ የዕለት ተዕለት ዉሎዉ ተመሳሳይ አይደለም።»

ገና ተማሪ እያለች የንግድ እንቅስቃሴ ትኩረት ትሰጥ እንደነበር የምንትናገወዉ አባይ የምትሠራዉን በጥንቃቄ ማከናወን ትሻለች። ለገበያ ለምታቀርባቸዉ ምርቶቿ የሚሆነዉ ጥሬ ዕቃ ራሷ ናት በአግባቡ የምትመርጠዉ። በቀጣይ ለሚዘጋጁት ምርቶች የሚነዉን ቆዳ ከእርሷ የሥራ ቦታ ብዙም ሳይርቅ ከሚገኘዉ የቆዳ ፋብሪካ ታዟል። የታዘዘዉን ለማምጣት ሄዳ ትመለከታለች።

«ይህ ቡናማ ቆዳ። ትንሽ የተጎዳ ወገን አለዉ ሆኖም ግን ቀሪዉ ግሩም ነዉ። አሁን ይህን ይመልሱና የተሻለ አዘጋጅተዉ ያመጡልናል። የተሻለ ጥራት ያለዉን ማለት ነዉ።»

የZAAF ምርቶች ደረጃቸዉን የጠበቁ እና ዉድ ተደርገዉ መታየት ከጀመሩ ቆይተዋል። ጥራታቸዉም ትልቁን ሚና ይጫወታል። በዚህ ምክንያትም ከደንበኞቿ ምስጋና ይጎርፍላታል።

«የኢትዮጵያን ጥበብ በሚያሳዩ ንድፎቻቸዉ፣ በጨርቁ እና በቆዳዉ ጥራት የZAFFን መለያ ወደያዙ ምርቶች ተስቤያለሁ። እንደተጠቃሚም ጥራቱ እና የባለሙያዎቹ ጥበብ በደንበኝነት እንድትቆይ ይጋብዛል።»

አንድ የእጅ ቦርሳ እስከ 700 ዶላር ያወጣል። በአዉሮጳ እና በአሜሪካ ቅርንጫፍ ሱቆችን ለመክፈት የምትመኘዉ አባይ ሹልዝ፤ አዳዲስ ዲዛይኖችን በየጊዜዉ ታወጣለች። ዓለም አቀፉን ዉድድር አልፋ ያሰበችዉን ታሳካዉ እንደሁ ወደፊት የሚታይ ይሆናል።

ናዲና ሽቫርስቤክ/ ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic