«ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ብቻ ነው የምንፈልገው»- በጅቡቲ ያሉ ኢትዮጵያውያን | ወጣቶች | DW | 21.06.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

«ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ብቻ ነው የምንፈልገው»- በጅቡቲ ያሉ ኢትዮጵያውያን

የዛሬው የወጣቶች ዓለም እንግዳዎቻችን ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ናቸው። አንዳንዶቹ እንደውም ኢትዮጵያን ጨርሶ አያውቋትም። ታድያ ለምን ወደ ኢትዮጲያ መሔድ ፈለጉ?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:32

«ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ብቻ ነው የምንፈልገው»- በጅቡቲ ያሉ ኢትዮጵያውያን

ጅቡቲ ውስጥ የሚገኙ ሶስት የስደተኛ መጠለያዎች ከተዘጉ በኋላ የአሊ አዴ የስደተኞች መጠለያ ብቸኛው እና ትልቁ ነው። በዚሁ መጠለያ ከ15 ሺ በላይ ስደተኞች ይኖራሉ። አብዛኞቹ ሶማሊያውያን ናቸው። ሲቀጥልም ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ይገኙበታል። የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ስልጣን ከያዙ በኋላ ከመጠለያው ወደ ኢትዮጵያ መመለስ የሚፈልጉት ኢትዮጵያዊያን ቁጥር 850 ደርሷል። ከነዚህ መካከል የ17 ዓመቱ ሳሙኤል ይገኝበታል። « እዚሁ ነው ተወልጄ ያደኩት»የ10ኛ ክፍል ተማሪ ነው።በእንግሊዘኛ፣ በሶማሊኛ እና አረቢኛ ቋንቋ የሚሰጠውን ትምህርት ይከታተላል። አሁን የሚፈልገው ነገር ግን ወደማያውቀው የወላጆቹ ሀገር ኢትዮጵያ መሄድ ነው። « ከዚህ በኋላ ከአባቴ ጋር ወደ ሀገር ነው መመለስ የምፈልገው። በርግጥ ሀገሬን አላውቀውም ግን ከአባቴ እና ከሚዲያ እንደማየው የተመቻቸ እና ጥሩ ሀገር እንደሆነ ነው። አሁን የምፈልገው ከአባቴ ጋር ተመልሼ ትምህርቴን ተምሬ የተሻለ ቦታ ለመድረስ ነው»

የተሻለ ቦታ ለመድረስ የሳሙኤል ጎረቤት የሆነችው አፅናፍ ወርቅም ትመኛለች። የ14 ዓመቷ ታዳጊ ተወልዳ ያደገችው እንደ ሳሙኤል እዛው የአሊ አዴ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ነው። 
 «አባቴ እዚህ ነው የሞተው እናቴ በሽተኛ ናት። እዛ ሄጄ ባሳክማት ብዬ ነው»አፅናፍ ወርቅ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ተመዝግበን እየጠበቅን ነው ትላለች።  

Karte Horn von Afrika Golfstaaten EN


የአሊ አዴ የስደተኞች መጠለያ ከተመሰረተበት እኤአ በ1991 ዓ.ም. ጀምሮ በስደተኝነት እዛው የሚኖሩት አቶ አሰፋ እንዴት ወደዚህ አካባቢ እንደመጡ ያስታውሳሉ። « ያኔ ወታደር ነበርኩኝ። በአሰብ በጦርነቱ ምክንያት ወደዚህ መጣን። ሀገር ቤት መመለስም አልተቻለም። » ኢትዮጵያውያኑ ከመጠለያው መውጣት የሚፈልጉበትም ምክንያት ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር በምህፃሩ «UNHCR» የሚያገኙት ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ እንደሆነ አቶ አሰፋ ይናገራሉ። 

ሽመልስ ቅርብ በሚባል ጊዜ ወደ ስደተኞቹ ጣቢያ ከገቡት መካከል ነው። ይሁንና 10 አመት እዛው አስቆጥሯል። ከኢትዮጵያ የወጣው የሀገሪቱ ፖለቲካ ስላላስደሰተው እንደነበር ይናገራል። አሁን ግን እሱ እንደሚለው ሁኔታዎች ስለተሻሻሉ መመለስ ይፈልጋል። ወዴት እንደሚሄድ ግን አያውቅም።

በጅቡቲ የUNHCR ተጠሪ የሆኑት አብዱላይ ባሪ ለዶይቸ ቬለ (DW) እንደገለፁት መስሪያ ቤታቸው ኢትዮጵያውያኑ የሚመለሱበትን መንገድ እያመቻቸ ይገኛሉ። «በቅርቡ 250 ሰዎች ይመለሳሉ። እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በUNHCR መካከል ውይይት ሲካሄድ ነበር። አሁን ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ስደተኛ ለሆኑት እውቅና ሰጥቷል። ምክንያቱም ሁለት አይነት ቡድኖች ናቸው እዚህ የሚገኙት። አንዳንዶቹ ተቀባይነት ያገኙ ስደተኞች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ አሁን ድረስ ጥገኝነት ጠያቂዎች ናቸው።  በጅቡቲ ፖሊሲ መሰረት ደግሞ ሁሉም ጥገኝነት ጠያቂዎች በቅድሚያ ስደተኝነታቸው እውቅና ማግኘት ይኖርበታል። እስካሁን 850 የሚጠጉ ሰዎች (ኢትዮጵያውያን) መመለስ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። በስደተኝነት እውቅና ያገኙት ግን 250 ያህሉ ብቻ ናቸው። እና እነዚህ ሰዎች በቅርቡ በሚቀጥለው ወር መጀመሪያ እንዲመለሱ ነገሮችን እያሰናዳን እንገኛለን። »


የUNHCR ተጠሪው ስደተኞቹ  ወደ ኢትዮጲያ ሲመለሱ በትክክል ወዴት እንደሚሄዱ ባያውቁም ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እንደሚላኩ ሰምተዋል። እስካሁን መመለሳቸው የተጓተተበትም ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ነው ብለዋል።« እስካሁን የዘገየበት ምክንያት መንግሥት ሰዎቹ የሚመለሱባቸው አካባቢዎች ደህንነታቸው የተረጋገጠ መሆኑን ማጣራት ስለፈለገ ነው። እንደምታውቁት ኢትዮጵያ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭት አለ። አሁን ግን 250 ሰዎችን መላክ እንደምንችል አረጋግጠውልናል።»
እነዚህ 250 ኢትዮጵያውያን አብዛኞቹ በቤተሰብ ደረጃ ያሉ ሲሆኑ አንዳንድ በተናጥል ያሉም እንደሚገኙበት የUNHCR ተጠሪ አብዱላይ ባሪ ገልፀዋል። በጉዳዩ ላይ ጅቡቲ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ባይሳካም ኤምባሲው በሳምንቱ መጀመሪያ በፌስቡክ ገፁ ላይ ይፋ እንዳደረገው ጅቡቲ ውስጥ በጸጥታ ኃይላት ተይዘው ከነበሩ ኢትዮጵያውያን መካከል  23 ያህሉን ሰኔ 6 ቀን 2011 ዓ.ም ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ተችሏል።

Grenze Dschibuti Äthiopien Flüchtlinge IOM

በጅቡቲ ድንበር የኢትዮጵያ ስደተኞች


በተለይ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ስልጣን ከያዙ በኋላ በፖለቲካ እና በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገር የወጡ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ ነው። አብዛኞቹም ወጣቶች ሲሆኑ በቁጥጥር ስር ውለው በየእስር ቤቱ ለአመታት ሲሰቃዩ የነበሩ እና አሁን በመንግሥት ድጋፍ ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ናቸው። ከአራት ወር በፊት ከ800 በላይ ኢትዮጵያውያን ከታንዛንያ ሲመለሱ ከሳውዲ አረቢያ ደግሞ ልክ የዛሬ ወር የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በምህረት አዋጅ ከሳውዲ አረቢያ እስር ቤቶች የተለቀቁ 1085 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ገብተዋል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይላትን ለመሸምገል ካርቱም ደርሰው ሲመለሱም እንዲሁ ከእስር ቤት የተፈቱ 78 ኢትዮጵያውያን ይዘው መመለሳቸው ተዘግቧል። 

ከጅቡቲ የአሊ አዴ የስደተኞች ጣቢያ ወደ ሀገራቸው መመለስ ስለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ሁኔታ የቃኘውን የወጣቶች ዓለም ዝግጅት በድምፅ መስማት ይችላሉ።

ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች