1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወደ ቀያቸው የተመለሱ የትግራይ ተፈናቃዮች ደስታና መመለሱ የዘገየባቸው ተፈናቃዮች ቅሬታ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 25 2016

ከሰሜን ምዕራብ እና ደቡብ ዞኖች የተፈናቀሉ ዜጎች እየተመለሱ ሲሆን፥ k,ምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉ እና በቁጥር የሚበዙት ግን አሁንም በመጠልያዎች የክረምቱ ወቅት ለማሳለፍ ተገደዋል። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር፥ ተፈናቃዮች የመመለስ ስራ ቀዳሚ ተግባሬ አድርጌ እየሰራሁበት ነው ይላል።

https://p.dw.com/p/4j0lP
Tigray Dürre Lebensmittelmangel
ምስል Million Haileselassie/DW

ወደ ቀያቸው የተመለሱ የትግራይ ተፈናቃዮች ደስታና መመለሱ የዘገየባቸው ተፈናቃዮች ቅሬታ

በትግራይ በጦርነቱ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀዬአቸው የመመለስ ስራ ቀጥሏል ። በርካቶች ደግሞ የሚመለሱበት ቀን እየጠበቁ ናቸው። በተለይም ከሰሜን ምዕራብ እና ደቡብ ዞኖች የተፈናቀሉ ዜጎች እየተመለሱ ያለ ሲሆን፥ የምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉ እና በቁጥር የሚበዙት ግን አሁንም በመጠልያዎች የክረምቱ ወቅት ለማሳለፍ ተገደዋል። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር፥ ተፈናቃዮችን የመመለስ ስራ ቀዳሚ ተግባሬ አድርጌ እየሰራሁበት ነው ይላል። ከጦርነቱ በኃላ ጭምር በትግራይ ከፍተኛ ማሕበራዊ ቀውስ ፈጥረው እየቀጠሉ ካሉ ችግሮች መካከል አንዱ የጦርነቱ ተፈናቃዮች አሁንም ወደቀዬአቸው አለመመለስ ነው።

ይህ መቋጫ እንዲያገኝ እየሰራ መሆኑ የሚገልፀው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር፥ ከፌደራል መንግስቱ ጋር በተደረገ መግባባት በተለይም ከደቡብ ትግራይ ዞን እንዲሁም ከሰሜን ምዕራብ ፀለምቲ አካባቢ የተፈናቀሉት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደቦታቸው መመለስ መጀመራቸው ይገልፃል። ይህ ተፈናቃዮችን የመመለስ ሂደት እየቀጠለ ያለ ሲሆን በያዝነው ሳምንትም ቢሆን፥ በዓብይ ዓዲ እና ዓዲግራት ሌሎች አካባቢዎች በመጠልያዎች የነበሩ ተፈናቃዮች ወደ ፀለምቲ እየተመለሱ ነው። በአዲግራት የነበሩና ከፀለምቲ አካባቢ የተፈናቀሉት 1200 ተፈናቃዮች ከከትላንት በስትያ ጀምሮ ወደቀዬአቸው መመለስ መጀመራቸው በአስተዳደሩ ተገልጿል። የትግራይ ጦርነት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸዉ መመለስ ጀመሩ

አንድ ተመላሽ ተፈናቃይ "ደስታዬ ወደር የለውም። በጣም ደስ ብሎኛል። እንደኛ የመመለስ ዕድሉ ያላገኙ ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው እንዲመለሱ ነው የምመኘው" ብለዋል። 

Tigray Dürre Lebensmittelmangel
ምስል Million Haileselassie/DW


በሌላ በኩል በማይጨው፣ መኾኒ፣ መቐለ እና ሌሎች አካባቢዎች የነበሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ከአላማጣ እና አካባቢው የተፈናቀሉ ዜጎችም ወደቀዬአቸው ተመልሰዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ ሌሎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉ ዜጎች የመመለሻቸው ግዜ እየጠበቁ ነው። ገብረመድህን ታረቀ ከጦርነቱ ተፈናቃዮች መካከል ነው። ከ10 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ወደ አላማጣ መመለሳቸው
አቶ ገብረመድህን "በአጠቃለይ ተፈናቃይ መመለስ መጀመሩ ጥሩ ተስፋ ነው ፈጥሮልን የቆየው። አሁን ላይ ግን በጣም መዘግየት አለ። በተለይም የምዕራብ ትግራይ ተፈናቃይ ስለመመለሱ አሁን ላይ የተባለው ነገር ስለሌለ ተስፋ እየቆረጠ ነው። ተስፋችን ቤታችን እንገባለን፣ ከመለመን እንገላገላለን፣ ሰርተን እንበላለን ነው። መዘግየቱ ግን የነበረን ተስፋ እንዲሟጠጥ እያደረገው ነው" ብለዋል።

Tigray Dürre Lebensmittelmangel
ምስል Million Haileselassie/DW

በተለይም አቅመ ደካሞች የክረምቱ ወቅት ተጨምሮ በመጠልያ ጣብያዎች የከፋ ሕይወት ላይ መሆናቸው ተፈናቃዮቹ ያስረዳሉ። የራያ አላማጣ ተፈናቃዮች መመለስና ውዝግቡ

የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ተፈናቃዮችን የመመለስ ስራ ቀዳሚ ተግባሩ አድርጎ እየሰራ መሆኑ ይገልፃል። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ "ሊፈፀም በሚገባው ፍጥነት ሊፈፀም ባለመቻሉ፥ ብዙ ስቃይ እንኳን ቢያመጣም አሁን ባለው፥ በራያ እና ፀለምቲ ረዥም ግዜ ቢወስድም በአንፃራዊነት ጥሩ በሚባል ደረጃ የተጀመሩ ስራዎች አሉ" ብለዋል።
ወደ ራያ እና ፀለምቲ የተጀመረው ተፈናቃዮች የመመለስ ስራ በቅርቡ ወደ ምዕራብ ትግራይም እንደሚፈፀም የግዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት ጨምረው ገልፀዋል።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ