ወደ ማርስ ጉዞ፤ አሳሽ መንኮራኩር | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 08.08.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ወደ ማርስ ጉዞ፤ አሳሽ መንኮራኩር

ወደ ሰማይ በማንጋጠጥ ፤ ደማቋን ጨረቃ ፤ ብርሃንና ሙቀት የምትለግሠውን ፀሐይ፣ ተወርዋሪ ከዋክብትን፣ ፕላኔት ብትሆንም ከፀሐይ ብርሃን መልሳ የምታንፀባርቀውን ፣ የምሽትም ሆነ የንጋት ኮከብ የምትሰኘውን ፣ ቬኑስን ፣ በአጠቃላይ ሥፍር ቁጥር የሌላቸውን


ወደ ሰማይ በማንጋጠጥ ፤ ደማቋን ጨረቃ ፤ ብርሃንና ሙቀት የምትለግሠውን ፀሐይ፣ ተወርዋሪ ከዋክብትን፣ ፕላኔት ብትሆንም ከፀሐይ ብርሃን መልሳ የምታንፀባርቀውን ፣ የምሽትም ሆነ የንጋት ኮከብ የምትሰኘውን ፣ ቬኑስን ፣ በአጠቃላይ ሥፍር ቁጥር የሌላቸውን ከዋክብት በመመልከት ፤ ይህን የተፈጥሮ ውበት ስንቱ ይሆን የሚያደንቀው? የሩቁን ፤ ስለ ኅውና ፤ በኅዋም ውስጥ ያልታወቀውን ነገር ምንነት ለማወቅ መጓጓት ጤናማ የሰው ባህርይ ነው።

--ከሰው በፊት፣ አሳሽ መንኮራኩር --

ከአያሌ ዐሠርተ-ዓመታት ጥረትና ሳይንሳዊ ምርምር በኋላ ፤ እንሆ ከትናንት በስቲያ በመሃል አውሮፓ የበጋ ሰዓት አቆጣጠር 7 ሰዓት ከ 32 ደቂቃ ላይ ፣ የዩናይትድ እስቴትስ ብሔራዊ የበረራ፣ የኅዋ ምርምርና አስተዳደር መ/ቤት (NASA) ያመጠቃት፣ 900 ኪሎግራም የምትመዝነው አሳሽ መንኮራኩር (Curiosity) ያላንዳች ሳንክ ነበረ ማረፏ የተረጋገጠው። አነስ ያለ የአስፖርት መኪና መጠንና 6 ተሽከርካሪ ጎማ ያላት ተንቀሳቃሽዋ ቤተ-ሙከራ «ኪዩሬሲቲ»፣ በማርስ ደቡባዊው ንፍቀ ክበብ፤ ከምድር ሰቋ አቅራቢያ 5 ኪሎሜትር ከፍታ ካለው Mount Sharp ከተባለው ተራራ ሥር «ጌል ክሬተር » ከተሰኘው የበረደ እሳተ ገሞራ ጠርዝ ላይ ነው ያረፈች።
የዩናይትድ እስቴትስ የበረራና የኅዋ አስተዳደር መሥሪያ ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ቻርለስ ቦልደን----
«ማርስ ላይ ለማረፍ መዘጋጀታችን ነው ወይስ ምንድን ነው?»
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣«


ከዚህ ቀደም ታይቶ ያልታወቀ፤ የረቀቀ የሥነ ቴክኒክ እርምጃ ምንጊዜም ወደፊትም ቢሆን ብሔራዊ ኩራትን ያጎናጸፈ ድርጊት ሆኖ የሚታወስ ነው » ብለዋል።
የ NASA ዋና አስተዳዳሪ ቻርለስ ቦልደን፣ በተላከችው የምርምር መንኮራኩር የተለያዩ ሳይንሳዊ ምርምሮች እንዲከናወኑ አስተዋጽዖ ያደረጉትን መንግሥታት ፣ ጀርመንን ሩሲያን፣ ፈረንሳይን ፤ ካናዳን፤ ፊንላንድናና ፤ እስፓኝን ጭምር አመሥግነዋል።
የተሣካው የዩናይትድ እስቴትስ መንኮራኩር ተልእኮ፣ዋና ዓላማ በማርስ ህይወት ነበረ? ፥ ወደፊትስ ፣ ህይወት ያለው ነገር ሊኖርባት ይችላል ወይ ፥የሚለውን ወሳኝ ጥያቄ ለመመለስ የታሰበበት ነው። በአውሮፓው የኅዋ ምርምር መ/ቤት፣ ጀርመናዊው ጠፈርተኛና ጠፈርተኞች የሚላኩበት የኅዋ ምርምር ክፍል ዋና ስራ አስኪያጅ ቶማስ ራይተር----
«አሁን የምንጠብቀው ድንቅ የሆኑ ሳይንስዊ መረጃዎችን ነው። በማርስ ላይ ህይወት ነበረ? አሁንስ ይኖር ይሆን? ያም ሆነ ይህ፣ ከ 2 ወይም 3 ዐሥርተ-ዓመት በኋላ፤ ሰዎች ጎረቤታችን ወደሆነችው ፕላኔት መጓዛቸው የማይቀር ነው።»
በኑክልየር ኃይል የምትንቀሳቀሰው 2,5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገባት ፤ Curiosity ፤ በሥነ ቅመማ ፤ እንዲሁም በአፈርና ቋጥኝ ምርምር ላይ በማትኮር፤ በሚመጡት 2 ዓመታት አንድ ቢሊዮን ገደማ ዕድሜ ሳይኖረው እንዳልቀረ በሚነገርለት የቀይዋ ፕላኔት (ማርስ)አፈርና ድንጋይ ላይ ይሆናል ፍተሻዋን የምታካሂደው።

የሳይንሳዊ ልብ ወለድ ጽሑፍ ጀማሪ እየተባሉ የሚደነቁት ፈረንሳዊው የሥነ-ጽሑፍ ሰው ጁልስ ገብርኤል ቨርን ፤ «ጉዞ ወደ ጨረቃ» የተሰኘውን ታዋቂ ድርሰታቸውን፣ እ ጎ አ በ 1873 ካሳተሙ ከአንድ መቶ ዓመት ገደማ በኋላ ነበረ ሰዎች ኅዋን ማሰስ የጀመሩት ፤ ወይም ፤ መጽሐፉ በታተመ በ 9 6 ኛው ዓመት ነበረ ሰው ጨረቃ ላይ ለማረፍ የበቃው።


ሰውም ውሻም ወደ ኅዋ በመላክ ቀዳሚውን እርምጃ የወሰደች የቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ያሁኗ ሩሲያ ነበረች። እ ጎ አ ፤ እስከ 1989 ዓ ም የቀዝቃዛው ጦርነት ማክተሚያ ድረስ በተናጠል ሁለቱም መንግሥታት በኅዋ ምርምር ረገድ ይፎካከሩ እንጂ፤ ከዚያ ወዲህ፤ በኅብረት ሆኗል ዐበይት ኅዋ ነክ ተጋባሮችን የሚያከናውኑት። ለቀድሞዋ የሶቭየት የጠፈር ጣቢያ MIR ም ሆነ ለአሁኗ ዓለም አቀፍ የኅዋ ጣቢያ (ISS)አስፈላጊ ቁሳቁሶችን የሚያመላልሱትም በአሜሪካ መንኮራኮርና በሩሲያዋ ሶዩዝ መንኮራኩር እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን ፣ ዩናይትድ እስቴትስ አልፎ -አልፎ በመንኮራኮሮች ተልእኮ ረገድ አደጋዎች እንዳገጠሟት አይዘነጋም። ሆኖም ፣ የማጓጓዣ መንኮራኩሮችን ተግባር ለመግታት መንስዔ ነው ያለችው የወጪ መብዛትን ነው። ያም ሆኖ ይህ፤ የኮሎምቢያ በመጨረሻም፣ ከአንድ ዓመት በፊት ፣ እ ጎ አ ሐምሌ 31 ቀን 2011 ዓ ም፤ የአትላንቲስ መንኮራኩር ተልእኮ ከእነአካቴው መሰረዙ ይታወሳል። ከዚያ ወዲህ ወደ ዓለም አቀፉ የኅዋ የምርምር ጣቢያ የተለያዩ ቁሳቁሶችንም ሆነ ስንቅ ለማመላለስ ዩናይትድ እስቴትስ የምትጠቀመው በሩሲያ ሶዩዝ መንኮራኩሮች ነው። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ ፤ ዕቃ ለማመላለስም ሆነ የኅዋ ቱሪስቶችን የስበት ኃይል ከሌለበት የኅዋ ክፍል አድርሰው ለመመለስ የተዘጋጁ የግል ድርጅቶች ብቅ- ብቅ ብለዋል። የኅዋ ቱሪስቶችን ለማጓጓዝ የመጀመሪያው የግል፤ ወደ ኅዋ መሣፈሪያ ጣቢያ፣ በኒው ሜክሲኮ ፌደራል ክፍለ ሀገር ይገነባል። እጅግ የጠነጠኑ ሀብታሞች ኅዋ ደርሶ ለመመለስ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለመክፈል ዓይናቸውን እንደማያሹ ምልክቶች ታይተዋል።
ጀርመናዊው ጠፈርተኛ (አስትሮኖት) ቶማስ ራይተር ፣ የ Curiosity ተልእኮ እንደሚሳካ ከመጀመሪያውም ብሩኅ ተስፋ እንደነበራቸው የገለጡ ሲሆን፤ ወደፊት ወደማርስ ሰውን ለመላክ ቢፈለግና ፤ ዕድሉ ከተሰጣቸው ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። ማርስ ደርሶ ለመመለስ እርሳቸው እንዳሉት ከ 2 ዓመት በላይ ስለሚወስድ ከዚያ በፊታ ብዙ ቴክኒካዊ ችግሮች እንዲወገዱ ጥረት መደረግ ይኖርበታል በተለይ አደገና ጨረርን ለመከላከል!። ከ 20 ወይም ከ 30 ዓመት በኋላ፣ የሆነው ሆኖ ፣ ሰው ማርስ ሊያርፍ እንደሚችል አልጠራጠርም ሲሉም ቶማስ ራይተር ገልጸዋል።ወደ ማርስ ለመጓዝ፣ አስቀድሞ ልምምድ ተድርጓል። በሩሲያ የኅዋ ምርምር መሥሪያ ቤትና በአውሮፓው የኅዋ ድርጅት ትብብር፣ ሞስኮ አቅራቢያ 6 ጠፈርተኞና ተመራማሪዎች፤ እ ጎ አ ፣ ከሰኔ 3 ,2010 እስከ ኅዳር 4 ፤ 2011 ፤ ባጠቃላይ 520 ቀናት ከውጭው ዓለም ጋር ሳይገናኙ፣ ጊዜያቸውን በጠባብ ቦታ፣ ቤተ-ሙከራ( ላቦራቶሪ )በመሠለ ሥፍራማሳለፈቸው ይታወሳል። የዚህ ፣ ብርቱ ዲሲፕሊንም ሆነ መሥዋእትነት ጠያቂ መርኀ-ግብር ተሳታፊዎች፤ 3 ሩሲያውያን፣ አንድ የፈረንሳይና አንድ የኢጣልያ ተወላጅ እንዲሁም አንድ ቻይናዊ ነበሩ።
ለአንድ ዓመት ተኩል ገደማ፣ የምርምሩ ተሳታፊ 6 ሰዎች በዚያው ተንቀሳቃሽ ባልሆነ መንኮራኩር ውስጥ ፤ በልዩ የመገናኛ ዘዴ ካልሆነ በስተቀር ከሚኖሩበት አዳራሽ ውጭ ሌላ የማየት ዕድል አልነበራቸውም። ይህም የተከናወነው፤ ልክ ወደ ማርስ በመንኮራኩር በመጓዝ ላይ እንዳሉ የሚሆነውን እንዲያገናዝቡ ታስቦ ነበር።
-------
በማይንቀሳቀሰው መንኮራኩር፤ ለአያሌ ወራት የተለማመዱት 6 ጠፈርተኞች፤ መንኮራኩራቸው ወደ ኅዋ አይምጠቅ እንጂ፤ በታሸገው የመንኮራኩር አዳራሽ በቆዩበት ጊዜ፤ ልክ ወደ ኅዋ እንደሚጓዙ ሆኖ እንዲሰማቸው ነበረ ሁኔታዎች የተስተካከሉት። የሚመገቡት ፣ ወደ ኅዋ የሚጓዙ ጠፈርተኞችም ሆኑ በዓለም አቀፉ የኅዋ ጣቢያ የሚገኙ ጠፈርተኞች የሚ መገቡትን ነበር። ልዩነቱ፤ አሌክሳንድር ሱቮሮቭ እንደሚሉት፤ በዓለም አቀፉ የኅዋ የምርምር ጣቢያ ለሚሠሩ ጠፈርተኞች በየጊዜው ስንቅ እንደሚላከው፤ ሞስኮ ውስጥ በማይንቀሳቀሰው መንኮራኩር 520 ቀናት ለሚቆዩት ያ ዓይነቱ እድል አልተሰጣቸውም። ለአንድ ዓመት ተኩል ገደማ የሚበቃቸውን ስንቅ ፤ይዘው ነበረ የገቡት።
6,«እስካሁን ከተደረጉት ቤተ-ሙከራዎች ሁሉ፤ ያሁኑ ነው ከተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተመሳሳይነት ያለው። የሆነው ሆኖ በዚህ ቤተ-ሙከራ ከማናከናውናቸው ሁለት ጉዳዮች መካከል፤ ከኅዋ የሚያጋጥም የጎጂ ጨረር ነጸብራቅና ክብደት ማጣት ናቸው። የጎጂ ነጻብራቁን ፈተና በአንስሳት ላይ ሞክረነዋል። የክብደት ማጣትን ችግርም ፤ ሰዎች አንድ ዓመት ሙሉ ከአልጋ ሳይንቀሳቀሱ እንዲቆዩ በማድረግ አሳይተናል። »የማርስ 500 ፕሮጀክት ከተደመደመ በኋላ፤ አባዛኞቹ ተሳታፊዎች፣ በኅዋ ምርምር ረገድ እንዳተኮሩ የሚቀጥሎ መሆናቸውን ነው የሚገልጡት። ሁሉም፤ የሰው ልጅ ምናልባት ወደ ማርስ መጓዝ የሚችልበት ሁኔታ ከ 20 ም ሆነ ከ 30 ዓመታት በኋላ ቢሣካም ፤ ከዚሁ ጋር በተያያዝ ምርምር መቀጠል ጽኑ ፍልጎታቸው መሆኑን ነው ያስታወቁት። ከአነዚህ አንዱ የ 32 ዓመቱ የህክምና ዶክተር ሩሲያው አሌክሳንድር ሶሞልዬቭስኪ ናቸው።
«ሰው ወደ ማርስ በመንኮራኩር እንዲጓዝ ዝግጅት የሚደረግበት ሁኔታ ዐቢይ ሳይንሳዊ ግብ ነው። ይህም በአጠቃላይ ለሳይንስ እመርታ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው። አንድ የጠፈር መንኮራኩር ወደ ሌላ ፕላኔት ለማምጠቅ፤ በመጀመሪያ፣ የተያያዙ አያሌ ሳይንሳዊ ችግሮች መፍትኄ ሊገኝላቸው ይገባል። ይህም ሲሆን ውጤቱ፤ በሌሎች ዘርፎችም ቢሆን ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል። ለምሳሌ ያህል፤ አንዳንድ ልዩ የምግብ ዓይነቶችን ማሠናዳት፤ የአእምሮና አካል ችሎታን ማዳበር፤ የሩቅ የህክምና አገልግሎትን ማስፋፋት ይቻላል። ስለዚህ፤ የኅዋ ጉዞ ወይም በረራ ለብዙ ችግሮች መፍትኄውን ማስገኘት ይችላል።»
ወደማርስ ሰው የሚላክበት የጠፈር መንኮራኩር ጉዞ፤ አሁንም ቢሆን የብዙ ዐሠርተ-ዓመታት ዝግጅትን የሚጠይቅ ነው። ሰው ባልተሣፈረባቸው መንኮራኮሮች፣ የእስካሁኑ ተልእኮ 50 ከመቶ የተሣካ ሲሆን ገና መፍትኄ የሚያሻቸው ችግሮች መኖራቸውን ጠቋሚ ነው።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ እ ጎ አ 2030 ዓ ም አጋማሽ ሳያልፍ አስተማማኝ የሆነ መንኮራኩር ተሠርቶ ሰዎች ወደማርስ የሚጓዙበት እርምጃ እንዲሣካ ጥሪ ማስተላለፋቸው አይዘነጋም።
«ማርስ 500 ፕሮጀክት» ይህን ዓላማ እውን ለማድረግ እጅግ ጠቃሚ ተመክሮና ዕውቀት ማካፈሉ አይቀርም።ተክሌ የኋላ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 08.08.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15lkn
 • ቀን 08.08.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15lkn