ወደ ማርስ የሚታሰበው ጉዞና አደገኛው ጨረር | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 14.08.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ወደ ማርስ የሚታሰበው ጉዞና አደገኛው ጨረር

እ ጎ አ በ 2030 ምናልባትም ከዚያ ቀደም ብለው ሰዎች ወደ ማርስ ይጓዙ ይሆናል። ለጤና የሚስማማ አየር በሌለባት ፣ ሣር ቅጠል በማይታይባት፣ ቀይ አቧራ በሸፈናት ማርስ ፤ እንዴት ኅልውናቸውን ጠብቀው ይቆያሉ? በጤናስ መመለስ ይቻላል ወይ? ወደ ማርስ

default

ጉዞን የሚያሰላስሉት የኅዋ ምርምር ድርጅቶች፣ የሥነ -ፈለክ ሊቃውንት፣ ጠፈርተኞችና መሰሎቻቸው በየጊዜው የሚያነሱ የሚጥሉት ጉዳይ ነው።

ማርስ ደርሶ ለመመለስ ፣ በአሁኑ ሥነ ቴክኒክ ፣ 500 ቀናት ማለትም አንድ ዓመት ከ 135 ቀናት ገደማ የሚወስድ ሲሆን ፣ ለጉዞው፣ ቀለብ ማዘጋጀትም ሆነ ስንቅ መሰነቅ እንደሚቻል፣ በተለያዩ ጊዜያት በተካሄዱ ምርምሮች ሳይረጋገጥ አልቀረም። ጀርመናዊው ተመራማሪ ፣ ፎልከር ማይቫልድ ፣ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በዩታህ ምድረ በዳ ፣ በቤተ ሙከራ በተካሄደ እንደማያጠራጥር ነው የተናገሩት።

Mars

ከጀርመን የበረራና የአየርና የኅዋ ጉዞ -ነክ መ/ቤት የተላኩት፤፣ የ 31 ዓመቱ ጎልማሳ ፣ የኅዋ በረራ ጉዳይ ኢንጂኔር ቮልከር ማይቫልድ፤ ከ 5 ባልደረቦቻቸው ጋር በአንድ ጠባብ ቤተ- ሙከራ ፣ 2 ሳምንት በወሰደ ምርምር የተሳተፉ ሲሆን፤ ምርምሩ በማርስ እንዴት መኖር እንደሚቻል መላውን ሳያስገኝ እንዳልቀረ ነው የገለጡት። ጉዞው፤ በተጣበበ ክፍል፣ ውሃም በመቁንን የሚታደልበት ነው ፣ መታጠብ የሚቻለውም ከስንት አንድ ጊዜ ነው። ትኩስ ምግብ አይገኝም። የሚተነፈስ ንፁህ አየር የሚገኘው፣ ጠፈርተኞቹ የሚተነፍሱትን የተቃጠለ አየር ከሚያጣራ መጠኑ የማቀዝቀዣ ያክል መጠን ካለው መሣሪያ ነው። ይሁን እንጂ ይህ በቂ ባለመሆኑ ወደፊት፤ ለአንድ ከተማ ህዝብ የሚበቃ ያህል ፣ አየር የሚያጠራ መሣሪያ ሠርቶ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ነው ማይቫልድ የገለጡት። ምግብን በተመለከተ፤ በጠባብ ቦታ በሰው ሠራሽ ዘዴ አትክልት ፣ ቅጠላ ቅጠል በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲመረት የሚደረግበት ብልሃትም አልታጣም፤ ምንም እንኳ በሰው ሠራሽ ዘዴ የተቀነባበረ ቢሆንም ፣ ጠፈርተኞቹ ፣ የተፈጥሮ ድምፅ እንዳይለያቸው የፏፏቴ፤ የአእዋፍም ሆነ የአንቁራሪት ድምጽ እንዲሰሙ መደረጉ፤ ጭንቀትን ሊያስረሳ እንደሚችል ታምኖበታል። በዩታህ በቤተ ሙከራ የተካሄደው የጉዞ ልምምድ ፣ ከማርስ ተጨባጭ ይዞታ ጋር እስከዚህም የሚያመሳስለው ሁኔታ የለም የሚባለው። ። ማርስ ላይ የሰው ክብደትም ሲሦ ያህል ነው ። አየሩም የተለየ ነው።

ከሁሉም ከባዱ አደጋም ሆነ ፈተና ከኅዋ የሚፈነጥቀውን ጨረር የመቋቋሙ ሁኔታ ነው።

እ ጎ አ ኅዳር 26 ቀን 2011 ዓ ም ከኬፕ ካናቭራል ፍሎሪዳ መጥቃ ከ 9 ወራት ገደማ በኋላ (ነሐሴ 6 ቀን 2012 ) ማርስ ላይ ያረፈችው Curiosity የተባለችው 900 ኪሎጋራም የምትመዝነው መንኮራኩር እስካሁን የምትልካቸው የተለያዩ መረጃዎች፤ ወደ ማርስ መጓዝ የሚለውን ጽኑ ፍላጎትም ሆነ የማወቅ ጉጉት እንዲጨምር ሳያደርግ እንዳልቀረም ነው የሚነገረው። «ኩዩሬሲቲ»፣ ጭና ከወሰደቻቸው ጠቀሚ የምርምር መሣሪያዎች አንዱ፤ በሰሜን ጀርመን የኪል ዩንቨርስቲ የፊዚክስ ሊቃውንት የሠሩት የአደገኛ ጨረር መጠን መለኪያው መሳሪያ ነው። በዚያው ዩንቨርስቲ የፊዚክስ ተመራማሪ Jan Köhler ስለማሳሪያው ተግባር እንዲህ ነበረ ያብራሩት---

«መርማሪው መሣሪያ ፣ በማርስ ያለውን አደገኛ የጨረር ዓይነት ይመዝናል። ብዙ ዓይነት አደገኛ ጨረር መኖሩ የታወቀ ነው። ንዑሱ የፍተሻ መሣሪያችን ፤ በዛ ያለውን የተለያየ አደገኛ የጨረር ዓይነት ለክቶ ለሰውም ሆነ በማርስ ለሚቀመጥ ሃይወት ላለው ነገር ያለውን እስከምን ድረስ አደገኛ እንደሆነ በስሌት ያመላክታል።»

አደገኛ ጨረር, የሚለካው መሣሪያ በተቻለ መጠን አነስ ብሎ ፤ የኮካ ኮላ ቆርቆሮ ያክል ሆኖ የተሠራው 2,5 ቢሊዮን ዶላር የፈጀው የኩዩሮሲቲ የማርስ ተልእኮ የጫናቸው መሣሪያዎች የረቀቁ ባይሆኑ ኖሮ ይበልጥ ወጪ ባስወጣ ነበር። በማርስ ባቻ ሳይሆን መሣሪያው በንኮራኮር ውስጥ ጠፈርተኞች የሚያጋጥማቸውን በብርሃን ፍጥነት ከኅዋ የሚፈነጥቅጨረርን ይመዝናል። ከጨረሮችም፣ የአቶም ፍንጣቂዎች፣ የራጂ ጨረር የመሳሰሉትንም ይለካል። በፀሐይ እንደሳተ ገሞራ የሚፈነዳውን ቶን እሳት ጨረር መጠንም ይለካል። ስለዚህ ፤ ያን ኮዖለር እንዳሉት፤ ይኸው የጨረር መለኪያ መሣሪያ መንኮራኩሯ ማርስ ላይ ካረፈች በኋላ ሳይሆን 9 ወራት ከመሬት ወደ ማርስ በተጓዘችበት ጊዜም ሁሉ ነበረ የጨረሩን መጠን መለካት የቻለው።

«በጉዞው ወቅት በመንኮራኩሯ ውስጥ የጨረሩ መጠን እንዲለካ አድርገናል። ይህ አስገራሚና ጠቃሚ ጉዳይ ነው። አንድ ጊዜ ወደፊት ጠፈርተኞችን ወደ ማርስ ለመላክ ብንፈልግ ፣ የሚያጋጥማቸውን የጨረር መጠን እንዲያውቁት ይደረጋል ማለት ነው።»

የአሜሪካው ብሔራዊ የበረራና የኅዋ አስተዳደር መሥሪያ ቤት (NASA)እ ጎ አ በ 2030 ሰዎችን ወደ ማርስ የመላክ እቅድ አለው። የኪል ዩንቨርስቲ የፊዚክስ ተመራማሪዎች ከመለኪያው መሣሪያ እንደተገነዘቡት፤ ጠፈርተኞቹ በየቀኑ 1,8 ሚሊሲቨርት ጨረር ያገኛቸዋል። ይህ ም ጀርመናውያን ዜጎች በነፍስ ወከፍ በያመቱ ከተፈጥሮ የሚያገኙት የጨረር መጠን ጋር ተመሳሳይ ነው ማለት ነው።

ታዲያ ማርስ ላይ ፣ አንዱ፣ ከአደገኛ ጨረር መከላከያው ዘዴ ጥላ ከሚመስል ተራራ ጥግ ፣ ይበልጥ የሚሻለው ደግሞ በማርስ ትኅተ ምድር ወይም ዋሻ መቆየት ይሆናል።

ይህ ሁሉ ምርምርና ወጪ የሚደረግባት ፣ ከመሬት ቀጥላ ሌላኛው የሰዎች መኖሪያ ልትሆን ትችላለች የምትባለው ቀይዋ ፕላኔት ከምድራችን ጋር ምን ያመሳስላታል ምንስ የተለየች ያደርጋታል፤ ካለፈ ዝግጅታችን የሠፈሩ አንዳንድ መረጃዎችን እንጥቀስ----

ማርስ፣ ከምድራችን ፣ አንዳንዴ ቀረብ ፤ አንዳንዴም ይበልጥ ፈንጠር ብላ ትገኛለች። እርሷ ቀረብ ፣ ምድርም ጠጋ ስትል፤ በ 54,6 ሚሊዮን ኪሎሜትር ብቻ ነው ተራርቀው የሚገኙት። ይህ የሚሆነው፤ ምድራችን ከፀሐይ ፈንጠር ብላ ፣ ማርስም ወደ ፀሐይ ይበልጥ ጠጋ ብላ ምኅዋሯ ላይ ስትገኝ ነው ማለት ነው። እ ጎ አ በ2003 ዓ ም እንደተረጋገጠው መሬትና ማርስ የተራራቁት በ 56 ሚልዮን ኪሎሜትር ነበረ። ከዚህ አንጻር ደግሞ በምኅዋር ከሚራራቁባቸው ምኅዋሮች ላይ ሲደርሱ፣ 401 ሚሊዮን ኪሎሜትር አፈንግጠው ሊገኙ ይችላሉ። በአማካይ ግን በሁለቱ መካከል የ 225 ሚሊዮን ኪሎሜትር ርቀት መኖሩ እሙን ነው።

ከፀሐይ ፣ በርቀት፤ 4ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ማርስ፤ (ከሜርኩሪ፤ ቬኑስና መሬት ቀጥላ መሆኑ ነው)ከምድራችን ጋር የምትመሳሰልባቸው አንዳንድ ሁኔታዎች አሉ። የማርስ ከፍተኛ የሙቀት መጠን 25 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ድረስ ከፍ ይላል። ማርስ፤ እንደ መሬትም 4 ወቅቶች ነው ያሏት፤ እርግጥ ነው፤ የከባቢ አየሯ ቅዝቃዜ አያድርስ የሚያሰኝ ነው ! ከዜሮ በታች 125 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ድረስ ይወርዳል። ደግሞም ፣ እንደምድራችን አየር፣ ወጣ ብለው የሚተነፍሱት አየር አይደለም ያላት። አንዱ ትልቅ ልዩነትም ይህ ነው። የማርስ ከባቢ አየር 95 ከመቶው የተቃጠለ አየር (ካርበን ዳይኦክሳይድ) ሲሆን 3% ናይትሮጂን፤ 1,5% ደግሞ አርገን ነው። ውሃ መገኘቱ ተረጋግጧል፣ ኦክስጂን ግን የለም።

Das Marsgesicht von 1976

ለንጽጽር ያህል ፤ የመሬት ከባቢ አየር፤ 78 ከመቶ ናይትሮጂን፣ 21 ከመቶ ኦክስጂን፤ 1% አርገን፣ እንዲሁም 0,3% ካርበን ዳይኦክሳይድ ነው።

አንድ የማርስ ቀን፣ 24,6 የመሬት ሰዓት ነው።

አንድ የማርስ ዓመት=1,88 የመሬት ዓመት= 687 የመሬት ቀናት= 669 የማርስ ቀናት መሆኑ ነው።

ታዲያ ፤ ወደዝች ፕላኔት ነው የሚተነፈስ አየር ሳይቀር ተሰንቆ ፣ የ 520 ቀናት የደርሶ-መልስ ጉዞ እየታሰበ ያለው። ሐሳቡ፤ እውን እንዲሆን ፣ ከዚህ ቀደም በሩሲያ ፤ ከ 2 ዓመት ገደማ በፊት ተሞክሮ በተሳካ ሁኔታ መደምደሙ የሚታወስ ነው።

የኅዋ ምርምር ነክ ጠበብት እንዳሉት፤ ወደ ማርስ አስተማማኝ ተልእኮ ለማከናወን ሥነ ቴክኒኩ ፣ ገና ዐሠርተ-ዓመታት ይቀሩታል። የሩሲያ ጠፈርተኞችና የጠፈር መንኮራኩር መርኀ ግብር ኀላፊ አሌክሴይ ክራስኖቭ፣ እንዳሉት ፣ ይኸው የልምምድ ተልእኮ ፣ ወደ ማርስ የሚደረገው ተጨባጭ ተልእኮ የተሳካ ይሆን ዘንድ ገንቢ መረጃ ለማሰባሰብ ረድቶናል ። የማርስ 500 ሙከራ 15 ሚሊዮን ዶላር (10,9) ሚሊዮን ዩውሮ ወጪ ያስወጣ ሲሆን አብዛኛውን የከፈለችው ሩሲያ ስትሆን፤ የአውሮፓው ኅብረት ድርጅት እና ጀርመንም ለፕሮጀክቱ ክፍለዋል።

ወደ ማርስ ለሚደረግ ጉዞ፣ ጠፈርተኞች፣ በተለያዩ ዐብያተ ሙከራ ያደረጉት ምርምር በተሣካ ሁኔታ መደምደሙ ነው በየጊዜው የሚነገረው። አብዛኛው ቀሪ ሥራ ከእንግዲህ የሳይንቲስቶች ይሆናል። በመቶዎች የሚቆጠሩትን የቤተ ሙከራ ክንውኖች ፣ መመርመርና ወደ ማርስ አንድ ቀን ሰዎች ለሚጓዙበት ተልእኮ ፤ የሚያስፈልገውን ሁሉ ለማሟላት መጣር፣ ሳይንቲስቶችን በእርግጥ የሚፈትን ብርቱ ተግባር ነው የሚሆነው።

የአሜሪካው NASA ፤ «ማሪነር» እና «ቫይኪንግ » በተሰኙት መንኮራኩሮቹ በኩል ከቅርብ የተነሱ የማርስ ፎተግራፎችን ለዓለም ህዝብ በማቅረብ ፣ አድናቆትን ማግኘቱ የታወቀ ሲሆን፤ የፈረሰችውን ሶቭየት ኅብረት የተካችው ፤ በኅዋ ምርምርም ከዓለም ውስጥ የመጀመሪያቱ ሀገር ሩሲያ ፤ እስካሁን ድረስ ፈንጠር ወዳለው የኅዋ ክፍል መንኮራኩር ልካ አታውቅም።

ተክሌ የኋላ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic