ወደ ሃገራቸዉ የሚሄዱ ስደተኞች መኖርያ ፈቃድ እገዳ | አፍሪቃ | DW | 15.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ወደ ሃገራቸዉ የሚሄዱ ስደተኞች መኖርያ ፈቃድ እገዳ

ስዊዘርላንድ ዉስጥ ተገን ተሰጥቷቸዉ እዚያ የሚኖሩና የዕረፍት ጊዜያቸዉን ትዉልድ ሀገራቸዉ የሚያሳልፉ ስደተኞች የጥገኝነት መብታቸዉ ሊነጠቁ እንደሚችል ተመለከተ። የሀገሪቱ የፍትህ ሚኒስትር ሲሞኒታ ሶምአሩጋ ጉዳዩን የስዊዘርላንድ የብሔራዊ ሸንጎ እንዲያየዉና በሕግ እንዲያፀድቅ ጠይቀዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:20

የስደተኞች መኖርያ ፈቃድ እገዳ


«ኖየ ዙሪሸር ሳይቱንግ» የተሰኘዉ የስዊዘርላንድ ጋዜጣ ባለፈዉ ሳምንት ባወጣዉ ዘገባ እንዳስነበበዉ፤ የሀገሪቱ የፍትህ ሚኒስትር ሲሞኒታ ሶምአሩጋ ጉዳዩን የስዊዘርላንድ የብሔራዊ ሸንጎ እንዲያየዉና በሕግ እንዲያፀድቅ ጠይቀዋል።


የስዊዘርላንድ የፍትሕ ሚንስትር ሲሞኒታ ሶምአሩጋን ጠቅሶ የስዊዘርላንዱ ዕለታዊ ጋዜጣ፤ እንደዘገበዉ በስዊዘርላንድ ተገን የጠየቁና የዕረፍት ጊዜያቸዉን በትዉልድ ሃገራቸዉ የሚያሳልፉ ዜጎች የተሰጣቸዉ የተገን መብት ይነጠቃል። እንደዘገባዉ ሚኒስትርዋ በብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ይህንኑ ነጥብ አንስተዉም በጥብቅ አሳስበዋል። ይህ እገዳ በአብዛኛዉ ተገን የሚጠይቁትንና የስደተኝነት እዉቅና የተሰጣቸዉን ብቻ ሳይሆን፤ በስዊዘርላንድ ለረጅም ዓመታት የሚኖሩና ዜግነት ያገኙ ትዉልደ ኤርትራዉያንን እንደሚመለከት ገልጸዋል። የሃገሪቱ የስደተኛ ጉዳይ ቢሮ ኤርትራዉያን ስደተኞች ለብሔራዊ በዓላትና ለነጻነት ቀን ወደ ኤርትራ ጉዞ ማድረጋቸዉን እንደሚያዉቅ ተዘግቦአል። እንድያም ሆኖ የተረጋገጠ መረጃ አለመኖሩ ነዉ የተዘገበዉ። ስዊዘርላንድ ዉስጥ ነዋሪ የሆኑት ትዉልደ ኤርትራዊዉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና ጠበቃ ዶክተር ዳንኤል ረዘነ መኮንን እንደሚሉት በርግጥ ይህን የሚያደርጉ ካሉ ተገቢ ርምጃ ነዉ።


ይህ ስዊዘርላንድ ዉስጥ ይፀድቃል የተባለዉ ሕግ ምናልባት አዲስ ይሆናል፤ በኖርዌይ ግን ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ዓመት ሆነዉ ያሉን በስዊድን ነዋሪ የሆኑት ትዉልደ ኤርትራዊት የስደተኞች መብት ተሟጋች ሜሮን እስጢፋኖስ በበኩላቸዉ፤
« በስዊዘርላንድ አዲስ ይሆናል በኖርዌይ ግን ይህ ሕግ ተግባራዊ መሆን የጀመረዉ ከአለፈዉ ዓመት ጀምሮ ነዉ። በኖርዌይ ያለዉ ሕግ ኤርትራዊ ወይም ኢትዮጵያዊ ከሆንክ ወደነዚህ ሃገራት አልያም ወደ ሱዳን መሄድ አትችልም ነዉ የሚለዉ። በርካታ ኤርትራዉያን ወደ ሱዳን ሲሄዱ ፓስፖርታቸዉ ላይ ያለዉ ማህተም ሱዳን እንደነበሩ ነዉ የሚያሳየዉ። ኤርትራ ከደረሱ በኋላ ግን ኤርትራ መግባታቸዉን የሚያሳይዉን ማኅተም አያስደረጉም። ስለዚህም ስርዓቱን እያታለሉ ነዉ። ኖርዌይዎች ይህን ጉዳይ ተረድተዉ ማንም ሰዊ ፈቃድ ከሌለዉ ተመልሶ መሄድ አይችልም የሚል ሕግ አዉጥተዋል። ወደ ፖሊስ ሄዶ ወደ ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ አልያም ወደ ሱዳን ለምን መጓዝ እንዳስፈለገዉ አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርበታል። ይህን ሳያደርግ የተጓዘ ሰዉ ከተደረሰበት፤ የተገን መብቱ መብቱ ሊገፈፍ ይችላል። ይህ ሕግ ነዉ በኖርዌይ ከአለፈዉ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ የሆነዉ።»


የስዊዘርላንዷ የፍትህ ሚኒስትር ሲሞኒታ ሶምአሩጋ በሀገራቸዉ ተገን ተሰጥቷቸዉ የዕረፍት ጊዜያቸዉን ትዉልድ ሀገራቸዉ የሚያሳልፉ ስደተኞች የተሰጣቸዉን የመኖሪያ የጥገኝነት መብት ለመግፈፍ የሚያስችል የሕግ ረቂቅ በዚሁ የአዉሮጳዉያኑ የበጋ ወራት ዉስጥ ለስዊዘርላንድ ምክር ቤት እንደሚያቀርቡም ተመልክቶአል።


አዜብ ታደሰ


ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic