ወባን ለማጥፋት የሙዚቃ ዝግጅት በሴኔጋል | የጋዜጦች አምድ | DW | 15.03.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ወባን ለማጥፋት የሙዚቃ ዝግጅት በሴኔጋል

የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል ታዋቂ አፍሪካዉያን የሙዚቃ ባለሙያዎች ያዘጋጁት ህያዉ አፍሪካ Africa Live የተሰኘ የሙዚቃ ዝግጅት በሴኔጋል ዳካር ተካሄደ። የሙዚቃ ዝግጅቱ ለህዝቡ ስለበሽታዉ መከላከያ ዘዴዎች እያስተማሩ ለሌላዉ አለም ወባን ለመከላከል ተጨማሪ ገንዘብ፤ መድሃኒትና አጎበር እንደሚያስፈልግ የነገሩበት አጋጣሚ ነዉ።

በወባ መከላከያ አጎበር በተሰራዉ መድረክ ላይ የተደረደሩት የአፍሪካ ኮከብ የሙዚቃ ሰዎች በሴኔጋላዊዉ ዩሱ ንዱር መሪነት በአፍሪካ በየ30 ሰከንዱ አንድ ህፃን የሚገለዉን የወባ በሽታ ከአህጉሪቱ ለማጥፋት ጥሪ አቅርበዋል።
ወባን ከአፍሪካ ለማጥፋት ይህ የታላቅ ነገር መጀመሪያ ነዉ በማለትም ንዱር ህያዉ አፍሪካ የሙዚቃ ዝግጅትን ለመታደም በስፍራዉ ለተገኙት ከ30 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተመልካቾች ንግግር አድርጓል።
በተጨማሪም ይህ ልንከላከለዉ የምንችለዉ ነገር ግን በየቀኑ የ2 ሚሊዮን ህፃናትን ህይወት የሚቀጥፈዉን የአፍሪካ ሱናሚ የምንዋጋበት ጊዜዉ ደርሷል ሲልም ያለዉን ተስፋ ገልጿል።
እንደ የተባበሩት መንግስታት ግምት ከ300 እስከ 500 ሚሊዮን የወባ በሽተኞች በየአመቱ በተለያዩ የአለም ክፍሎች በሚገኙ የጤና ጣቢያዎች ይስተናገዳሉ።
በየአመቱ በዚህ ሳቢያ ህይወታቸዉ ከሚያልፈዉ በሚሊዮን ከሚቆጠሩት ህፃናት መካከልም አብዛኛዎቹ የሚገኙት ከሰሃራ በታች ነዉ።
የአለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየዉ 100 ሚሊዮን አጎበር ከማከፋፈል ሌላ ከተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍና ከአለም ባንክ ጋር በመተባበር ከአምስት አመት በኋላ አፍሪካን ከወባ ለመታደግ አቅዷል።
የድርጅቱ የወባ መከላከያ ክፍል ሃላፊ የሆኑት ዶክተር ፋቱማታ ናፎ ትራዎሬ እንደሚሉት ተፈላጊዉ ጥሬ ዕቃ በተሟላላቸዉ አነስተኛ ፕሮጀክቶች እንደሞከሩት በተባለዉ ጊዜ ዉጤታማ መሆን ይቻላል። ህያዉ አፍሪካ የተሰኘዉን የሙዚቃ ዝግጅትን የተመለከተ ማንኛዉም ሰዉ ወባ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ተረድቶ የራሱን አስተዋፅኦ ለማድረግ ይነሳሳል የሚል ተስፋ እንዳላቸዉም ትራዎሬ ይናገራሉ።
በአለም የድሃ ድሃ ለሆነችዉ የአፍሪካ አህጉር ወባን ለመከላከል የሚያፈልጋት የገንዘብ መጠን እጅግ ከፍተኛ ነዉ።
እንደ ትራዎሬ ስሌት 12 ቢሊዮን ዶላር ወይም 9 ቢሊዮን ዩሮ በአመት ያስፈልጋታል ይህም ለጤና ከሚመደበዉ በጀት 40 በመቶዉን ይይዛል።
በሌላ በኩል ጃፓን በመድሃኒት የተነከረና ለአምስት አመት የሚያገለግል የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር የያዝነዉ የፈረንጆቹ አመት ሳያልቅ በብዛት ለማምረት መወሰኗን አስታዉቃለች።

ሆኖም የዩኒሲኤፍ የበጎ ፈቃድ አምባሳደር የሶል ወፍ በመባል የምትታወቀዉ ቤኒናዊቷ አንዠሊክ ኪጆ ሃላፊነቱ በምዕራባዉያን ለጋሾች ላይ ብቻ መጣል የለበትም ትላለች።
በተወዳጁ ድምጿ ሳቢያ የአዉሮፓ ጉብኝት ጉዞዋን ለ36 ሰአታት አቋርጣ ዳካር የተገኘችዉ ኪጆ የአፍሪካ መሪዎች ራስ ወዳድነታቸዉንና ስስታቸዉን ወደ ጎን አድርገዉ ህዝባቸዉን ከወባና ከሌሎች በሽታዎች ለመታደግ ሃላፊነቱን ይወስዳሉ የሚል ተስፋ እንዳላት ገልፃለች።
አያይዛም ለችግሮቻችን የበለፀጉ አገራት መንግስታትን ተጠያቂ የምናደርጋቸዉ ከሆነ የኛ መንግስታትስ ተጠያቂ የማይሆኑበት ምን ምክንያት አለ ስትል ጥያቄ አቅርባለች።
የአፍሪካ ህዝቦች የማይገባቸዉ አይደሉም የምትለዉ ኪጆ አፍሪካዉያን እንደሌላዉ አለም ዜጋ በክብር ሊያዙና ራሳቸዉን መከላከል እንዲያዉቁ ሊያሳዩዋቸዉ የሚገባ ህዝቦች ናቸዉ ብላች።
ህያዉ አፍሪካ የተሰኘዉ ዝግጅት በርካታ ተወዳጅ የሙዚቃ ስራዎችን ነበር በአይነት ለታዳሚዎቹ ያቀረበዉ።
በመድረኩ የአፍሮ ኩባና የሴኔጋል ዘይቤን አጣምሮ የሚጫወተዉ የባኦባብ የሙዚቃ ቡድን፤ የፈረንሳዩ የራፕ ቅላፄና የአፍሪካ ሂፕ ሆፕ ዘይቤዎች ከተለያዩ ጭፈራዎች ጋር ቀርበዋል።
በሩዋንዳ የእርስ በርስ ግጭት ጦስ ወደ ፈረንሳይ ተሰዶ የነበረዉ ታዋቂዉ የሩዋንዳ የሙዚቃ ሰዉ ኮርኒሊ ከስደቱ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ መድረክ በቀረበበት ጊዜ የበርካታ ወጣት ሴት ተማሪዎችን አድናቆት አትርፏል።
ቅዳሜ አመሻሹ ላይ የጀመረዉ ይህ የተባበሩት መንግስታት እገዛ ያለበት ወባን ለመከላከል የታለመዉ የሙዚቃ ዝግጅት ለሁለት ቀናት የቆየ ነበር።
በማግስቱ እሁድ በማለዳ ታዳሚዎቹን እያስተማረ ያዝናናዉ የሴኔጋል ብርቅዬ ልጅ ዩሱ ንዱር የዚህ አመት የግራሚ የሙዚቃ ሽልማትን ኢጂፕት ወይም ግብፅ በሚለዉ የሙዚቃ አልበሙ አሸንፏል።