ወቅታዊ ፖለቲካዉ በቱሪዝም ላይ ተጽኖ አሳድሮአል?   | ባህል | DW | 17.11.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

ወቅታዊ ፖለቲካዉ በቱሪዝም ላይ ተጽኖ አሳድሮአል?  

«አሁን ያለበት ሁኔታ ከአለፈዉ ዓመት ስናወዳድረዉ ብዙ የቀነሰ አይደለም። ሁለተኛ ምን ያህል ገንዘብ ገብቶአል ለሚለዉ ገና ግልጽ አድርገን አላወቅንም። ነገር ግን አሁንም ቱሪስቶች ሃገሪቱን ይጎበኛሉ፤ ከዝያም አልፎ አንዳንድ መንግሥታትም ነገሩን በማጤን ያስቀመጡትን የጉዞ እገዳ እያነሱ ነዉ።» የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:24
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
16:24 ደቂቃ

ወቅታዊ ሁኔታዉ ጎብኝዎችን አስቀርቶአል?  

በኢትዮጵያ የቱሪዝም ፍሰት መቀነስን ተከትሎ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ታደሰ የሰጡን አስተያየት ነበር ። አንድ ዓመት የሆነዉና በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሰዉ ሕዝባዊ ተቃዉሞ ዓለምአቀፍ ጎብኝዎችን አርቋል፤ ሃገሪቱንም በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ማክሰሩ እየተነገረ ነዉ። በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህላዊ የሆነ ድርጅት በ «UNESCO» የተለያዩ ጥንታዊና የማይዳሰሱ ባህላዊ ጉዳዮችን በማስመዝገብ አንደኛ በመሆንዋ የምትታወቀዉ ኢትዮጵያ

ከአስቸኳዩ አዋጅ በኋላ የቱሪዝሙ ኢንዱስትሪ እያንሰራራ ይሆን? በዚህ ዝግጅት ስለወቅታዊዉ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ፍሰት እንዴትነት የዘርፉን ባለሰልጣናትና አስጎብኝ ድርጅቶችን ጠይቃለን።  

 አብዛኞች ጢስ አልባ ኢንዱስትሪ ሲል ይጠሩታል ፤ የቱሪዝም ዘርፉን። ባለፉት አስርተ ዓመታት ኢትዮጵያ ከጢስ አልባ ኢንዱስትሪዉ ከፍተኛ ተጠቃሚ ሃገራት ከሚባሉት የአፍሪቃ ሃገራት ከመጀመርያዎቹ ተርታም የተሰለፈች ሃገርም እንደሆነች ይታወቃል።  ኢትዮጵያ ጎብኝዎችን እንደማግኔት በመሳብዋ ፤ መስብኦችዋን በዓለም የቅርስ መዝገብ በማስመዝገብ ቀዳሚዉን ስፍራ በመያዝዋ ብቻ ሳይሆን በመልካ ምድርዋ፤ በያዘችዉም ተስማሚ  የአየር ፀባይ ብሎም በአስተማማኝ ደኅንነትዋም ጭምር ነዉ።  በሃገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች የተቀሰቀሰዉን ሕዝባዊ ተቃዉሞ ተከትሎ በርካታ የቱሪዝም ድርጅቶች የሃገር ጎብኝዎች የያዙትን የጉዞ እቅድ መሰረዛቸዉንና ገብያቸዉም መመናመኑን ተናግረዋል። የቱሪዝሙ ፍሰት ባለፉት አስር ወራቶች ዉስጥ እየተመናመነ ቢሄድም በተለይ ከአስቸኳጊዜ አዋጁ በኋላ መዳፈኑን የሚገልጹም አሉ።

ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚገኙ ድረ-ገጾች እንዳስነበቡት በያዝነዉ ዓመት ኢትዮጵያ በቱሪዝሙ ዘርፍ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ለማስገባት እቅድ ይዛለች።  የቢቢሲ የዜና አገልግሎት በኢትዮጵያ የሚገኙትን ወኪሎች ጠቅሶ እንደዘገበዉ ደግሞ በኢንዱስትሪዉ ዘርፍ  ሃገሪቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ከስራለች።

የኢትዮጵያ የቱሪዝም ፍሰት መቀነስን ተከትሎ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ታደሰ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት ሁኔታዉ እየተሻሻለ ነዉ። 

«የዝርዝር መረጃዉ በተለያየ መንገድ እየተተረጎመ ነዉ። በነበረዉ ወቅታዊ ሁኔታ በቱሪዝሙ ዘርፍ ትንሽ መንገራገር ነበረ፤ ከአለፈዉ ዓመት ስናወዳድረዉ ብዙ የቀነሰ አይደለም። ሁለተኛ ምን ያህl ገንዘብ ገብትዋል ለሚለዉ ያለበት ሁኔታን ለማወቅ ገና ነዉ። በአለፈዉ ዓመት ወደ ሦስት መቶ አራት ቢሊየን ዶላር ነዉ የገባዉ ወደ ዘጠኝ መቶ ሃያ አምስት ሺህ አገርጎብኝዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል። ሃገሪቱ ዉስጥ አሁንም ቱሪስቶች በሰፊዉ አሉ ይጎበኛሉ። ከዝያም አልፎ አንድንድ መንግሥታት ያስቀመጡትን የጉዞ እገዳ እያነሱ ነዉ። ስለዚህ ለቱሪስት ሃገሪቱ ሰላም እና ደሕንነቱ የተጠበቀ ሃገር ሆንዋል አሁን፤ ወደፊትም በዝያ ይቀጥላል ብዬ ነዉ የማምነዉ። አዘቃላይ ሃገሪቱም ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖባታል።»

 በአሁኑ ሰዓት የተሻለ የቱሪስት ፍሰት ይኖራል ብለን እንጠብቃለን ያሉን፤የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች ልማት ዳይሪክቶሪት ዳይሪክተር አቶ ቸርነት ጥላሁን በበኩላቸዉ፤

« በአሁኑ ሰዓት ደህና የቱሪዝም ፍሰት አለ ብለን ነዉ የምንጠብቀዉ፤ ያለፈዉን አመት ከተመለከትን እስከ 918 ሺህ ሰዎች መጥተዋል ብለን ነዉ የምናስበዉ፤ እስከ 3,4 ቢሊየን ዶላር በቱሪዝም ተገኝቶአል፤ አሁን በሃገሪቱ የተከሰተዉ

ሁኔታ ተጽኖ ካላሳደረ በስተቀር ይሄ ሁኔታ ይጨምራል ብለን ነዉ የምናስበዉ። ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ በአብዛኛዉ የዱር እንስሳትና ፓርኮችን በተመለከተ ነዉ የሚመጣዉ ቱሪስት የሚጎበኘዉ?»

 

 ከአንድ ዓመት ወዲህ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ሕዝባዊ ተቃዉሞ የሃገሪቱ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል የሚል የተለያየ ዘገባ እየወጣ ነዉ፤ እና ይህ እንዴት ይታያል? ለሚለዉ የኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች ልማት ዳይሪክቶሪት ዳይሪክተር አቶ ቸርነት ጥላሁን በመቀጠል፤

« እንዲህ ዓይነት ሲፈጠር ፤ ሰላምና ቱሪዝን ተያያዥ የሆነ ነገር ነዉ። ተጽኖ የለዉም ብለን አንልም፤ ግን አሁን ጥምቀትንና የላሊበላ በዓል ሲከበር የሚመጣዉን የቱሪስት ፍሰት ከአየን በኋላ ትክክለኛዉን ቁጥር ካወቅን በኋላ ነዉ መናገር የምንችለዉ። እርግጥ አንዳንድ የጉዞ አስጎብኝዎች ጉዞ እንደተሰረዘባቸዉ የሚገልጹት ነገር አለ፤ አሁን ደግሞ የአስቸኳይ ጊዙ አዋጁን በመሻሻል ሁኔታ ሲታይ የቱሪስቶችን ስጋት ይቀንሳል ብለን እናስባለን።»   

ማንነታቸዉን እንዳንናገር የገለፁልን የተለያዩ የአስጎብኝ ድርጅቶች እንደሚሉት ሃገር ለመጎብኘት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣዉ ጎብኝ ቁጥር እጅግ ቀንሶአል፤ ለገና ለጥምቀት ኢትዮጵያን እንጎበኛለን ብለዉ የተመዘገቡ ሁሉ የጉዞ እቅዳቸዉን ሰርዘዋል፤ በዚህ ከቀጠለ እንዴት እንደምናደርግ አናዉቅም፤ ሲሉ ገልፀዋል።    

የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በድረ-ገፁ ባወጣዉ መግለጫ በኦሮምያ እና በአማራ ክልሎች በዋና መንገዶችና ከተሞች በስተቀር ጉዞ ባይደረግ ይመክራል። ይኸዉም ይላል በማብራርያዉ ባስቀመጠዉ ጽሑፍ ወደ ባሕርዳር፤ ጎንደር፤ ላሊበላ፤  ድሪደዋ ፤ አርባምንጭ ከተሞች መጓዝ ያለምንም ችግር ይቻላል። ይህን ተከትሎ በኢትዮጵያ ቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች ልማት ዳይሪክቶሪት ዳይሪክተር አቶ ቸርነት ጥላሁን 

«አሁን ከኤምባሲዎችም ጋር ግንኙነት እየፈጠርን ነዉ። የተፈጠረዉን ሁኔታ ማብራርያና መግለጫ እየሰጠናቸዉ ነዉ። ሁለት፤ ለአስጎብኝ ድርጅቶችም መረጃዉ እየደረሳቸዉ ነዉ። እኛም ራሳችን እየዞርን እያየን ግምገማ እያደረግንም ነዉ። ወቅታዊ ሁኔታዉ ተጽኖ አሳድሮ ይሆናል፤ ግን ይህ የሚቀጥል ነገር አይደለም፤ አሁን ወደ ነበረበት ቦታ እየተመለሰ ነዉ። ለጥምቀት ለገና መምጣት የፈለጉ ጎብኝዎች በነጻነት እየተጓዙ ነዉ ያሉት።»    

በቅርቡ ካለን መረጃ በአፍሪቃ ዉስጥ በጣም ከሚጎበኙ አምስት ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ አንድዋ ናት ያሉን አቶ ቸርነት ጥላሁን ፤

« ኢትዮጵያ ከአፍሪቃ ከሚጎበኙ ሃገራት 17 ኛ ደረጃ ነበረች፤ በቅርቡ «Lonely Planet» ባወጣዉ መረጃ መሰረት ከአፍሪቃ ሃገራት በጣም ከሚጎበኙ ሃገራት መካከል አምስተኛ ደረጃን ይዛለች። የሚዳሰሱ ቅርሶችን በተመለከተ ወደ ዘጠኝ አስመዝግበናል፤ ጊዜያዊ መዝገብ ዉስጥ የገቡም አሉን፤ እንደገና ደግሞ የማይዳሰሱ ቅርሶች በሚል ያስመዘገብናቸዉም አሉን። እና ቅርሶችን ለዓለም አቀፍ ቅርስነት በማስመዝገብ አንጻር ፤ አንደኛ ነን ብለን ነዉ የምንወስደዉ።  በቱሪስት ፍሰት ግን ያለን ደረጃ

Fasil Schloss Gonder Äthiopien (DW/Azeb Tadesse Hahn)

በአሉት መመዘኛዎች መሰረት 17ኛ ነን። አሁን ባለዉ በ «Lonely Planet» መረጃ መሰርት ግን አፍሪቃ ዉስጥ ከሚጎበኙ አምስት ትልልቅ ሃገሮች ዉስጥ ኢትዮጵያ አንድዋ ናት።     

አሁንም ማንነታቸዉን እንዳልገልጽ የጠየቁን የአንድ አስጎብኝ ድርጅት ባለቤት እንደሚሉት ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ መልካምዕድርም ሆነ ጥንታዊ ቅርሳቅር ሁሉንም ዓይነት መስዕቦች አካቶ በመያዙ ከሌሎች አፍሪቃ ሃገራት በይበልጥ ተወዳጅ ነዉ።

ባለፈዉ ሳምንት ከቼክ ሬፐብሊክና ከስሎቫኪያ የመጡ 10 አገር ጎብኝዎች ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሱርማ ጎሳ አባላት ሚዛን ተፈሪ ከተማ አቅራቢያ ሲጎበኙ ጥቃት ደርሶባቸዋል፤ በእጆቻቸዉ የያዙዋቸዉ ንብረቶችም ተዘርፈዋል ፤ ጎብኝዎቹን የያዘዉን መኪና ሲያሽከረክር የነበረዉ ኢትዮጵያዊ ሾፌር በተተኮሰበት ጥይት መገደሉም ታዉቋል።  የቼክ ሬፐብሊክ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ኤሪና ቫለንቶቫ  ሥለጥቃቱ ለዶይቼ ቬለ እንደገለጹት 

«በመሠረቱ በስርቆቱ ሂደት ላይ የተከሰተዉ ነገር የሃገሬዉ ተወላጅ ሹፊር ተተኩሶ ተገድሎአል። ከቼክ ሪፐብሊክ የመጡትን አገር ጎብኝዎች በተመለከተ ምንም ነገር አልደረሰባቸዉም። ከስሎቫክያ የመጡት የጎብኝ ቡድን መካከል አንዲት ሴት ፤ ቆስላለች።

ይህ ድንገተኛ የተከሰተ አደጋ ነዉ እንጂ ኢትዮጵያ ዉስጥ ካለዉ ወቅታዊ ፖለቲካ ጋር ምንም ግንኙነት የለዉም ያሉን አቶ ቸርነት ጥላሁን፤ ጥቃት አድራሾቹ ተይጠዉ በምርመራ ላይ መሆኑን፤ የተዘረፈዉ የሃገር ጎብኝዎች ንብረትም ለማስመለስ ጥረት ላይ መሆኑን ገልፀዉልናል።  

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታን አስታኮ በሃገሪቱ ስላለዉ የቱሪዝም ፍሰት ለመዳሰስ ቃለ ምልልስ የሰጡንን እያመሰገንን፤ ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ 

 

Audios and videos on the topic