ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጐ ፈቃድ አገልግሎት በኢትዮጵያ   | ኢትዮጵያ | DW | 10.08.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጐ ፈቃድ አገልግሎት በኢትዮጵያ  

የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለምስጠት አንድ ሽህ ወጣቶች ወደ ተለያዩ ክልሎች ተሰማርተዋል። በሚሄዱበት ቦታ የትምህርት እገዛ እንደሚሰጡ፣ የአከባቢ ፅዳት ላይ እንደሚሳተፉ፣ የደም-ልገሳ እንደሚያደርጉ እና ሌሎችም እንቅስቃሴዎች ላይ እንደሚሰማሩ ይጠበቃል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:14

የበጐ ፈቃድ አገልግሎት በኢትዮጵያ  

በዚሁ የበጎ ፈቃድ ስራ ከሚሳተፉት አንድ ሽህ ወጣቶች ዉስጥ 150 ዎቹ ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል መሆናቸውን የክልሉ የወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሚልክያስ እስራኤል ለዶይቼ ቬሌ ገልፀዋል። ወጣቶቹ ወደተለያዩ ክልሎች በመሄድ የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡበት ጊዜ ከነሃሴ አንድ እስከ ነሃሴ  15 ቀን 2010 ዓ/ም  ነው።

በአገሪቱ ላለፉት ስምንት ዓመታት ያክል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ለክረምት የእረፍት ጊዜ ወደ አከባቢያቸዉ ሲመለሱ  በዚያ ለሚገኙ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በትርፍ ጊዜያቸዉ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸዉ ይታወሳል። ካለፉት ሁለት ዓመት ጀምሮ ደግሞ «ድንበር ተሻጋሪ» የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ወጣቶች የበጎ ፊቃድ አገልግሎታቸውን በመስጠት ላይ መሆናቸውን የደቡብ ክልል የወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሚልክያስ እስራኤል ይናገራሉ። ድንበር ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በትክክል ምን ማለት እንደሆነ  አቶ ሚልክያስ  አብራርተዋል።

አሁን «ወሰን ተሻጋሪ» የሚል ስያሜ የተሰጠው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከቃላት ለዉጥ በስተቀር በፊት ሲባል ከነበረዉ «ድንበር ተሻጋሪ» የበጎ ፍቃድ አግልግሎት የተለየ አይደለም፣ ልዩ የሚያደርገው አንድ ነገር ቢኖር  ጠ/ሚንስቲሩ «የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ አገራዊ ለዉጥ እንዲያመጣና ልማቱን እንዲደግፍ ታስቦ መደረግ» አለበት ማለታቸዉ ነዉ ሲሉ አቶ ሚልክያስ እስራኤል ለዶይቼ ቬሌ አስረድተዋል።

ከአንድ ሺህ ወጣቶች ዉስጥ በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ለሚሰማሩት ወደ 200 ለሚጠጉት በትላንትናዉ እለት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሚልዮን ማትዮስ፣ የወጣቶች እና የስፖርት ፣ የትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች፣ እንድሁም፣ ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል እንደተደረገላቸዉ የኮሙኒኬሼን ዳይሬክተሩ አቶ ሚልክያስ ገልፀዋል። በሃዋሳ ከተማ የተሰማሩት እነዚህ ወጣቶች ከዛሬ ጀምረው እስከ ነሃሴ 20 ድረስ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ይሰጣሉ።

የ25 ዓመቱ ወጣት ጋማችስ ታደሰ የበጎ ፍቃድ ስምሪት ከሚጀምሩት ወጣቶች ዉስጥ አንዱ ነዉ። ወደ ሃዋሳ የመጣዉ ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ከዱከም ከተማ ሲሆን ከሚዛን-ቴፕ ዩኒቨርስቲ የሜካንካል ኢንጅንየሪንግ ትምህርት ተመራቂ ነዉ። ጋማችስ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መስጠት መቀጠሉን ይናገራል። የአሁኑን ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፍቃድ አሰጣጥ ከበፊቱ ለየት ያለ ሆኖ አግኝቶታል። ከጅምሩ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ለመስጠት ያነሳሳዉን ምክንያት፣ እንዲሁም፣ ባለፈው ማክሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለወጣቶቹ ያደረጉት አቀባበል እና ንግግር ይህንኑ ተነሳሽነቱን ይበልጡን እንዳጠናከረለት  አመልክቷል።

የወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  አቶ ሚልክያስ እስራኤል አክለው እንደገለጹት፣ በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ወጣቶቹ 20 በሚሆኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አስጣጥ ዘርፎች ውስጥ እንዲሰማሩ እቅድ ተይዟል። የወጣቶቹ  ተሳትፎ ከትምህርት እገዣ እስከ ደም ልገሳ ድረስ ያሉ ዘርፎቹን ይሸፍናል።

ከተለያየ ክልል የተሰማሩት ወጣቶች የተለያየ ባህል ያላቸው መሆኑና የተለያየ  ቋንቋ ተናጋሪዎች መሆናቸው በሚሰጡት አገልግሎት ላይ ጫና እንደማያሳድር አቶ ሚልክያስ ገልፀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወጣቶቹን ሰብስበው ባወያዩበት ወቅት ወጣቶቹ የየአከባቢውን ባህል፣ ቋንቋ እንዲሁም ሃይማኖት ማክበር እንዳለባቸዉ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

ወጣቶቹ በተሰማሩበት ቦታ የሚያስ,ፈልጋቸውን የመኝታ፤ የምግብ እንድሁም የመጓጋዣ ወጭ ክልሉ እንደሚሸፍን አቶ ሚልክያስ ቢያስታውቁም፣ «በእጃቸው ምንም ገንዘብ አይሰጣቸዉም» ብለዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ በአሁኑ ወቅት የበጐ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ  ወጣቶች ቁጥር 13.6 ሚሊዮን መሆኑን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ይጠቁማሉ።

አርያም ተክሌ

መርጋ ዮናስ 

Audios and videos on the topic