ወራትን የዘለቀው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ውይይት | ኢትዮጵያ | DW | 26.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ወራትን የዘለቀው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ውይይት

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በውጭ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ 80 የሚሆኑ ሀገር አቀፍና የክልል ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ውይይት ሲካሄድ ሰንብቷል። አንድ ዓመት ከጥቂት ወራት ለቀሩት ሀገራዊ ምርጫ ዝግጅት በማድረጉ ሂደት ፓርቲዎቹ በጋራ ለመሥራት የሚያግባቧቸውን ነጥቦች ላይ መነጋገራቸውን  በውይይቱ የተሳተፉት የመኢአድ እና ኦፌኮ አመራሮች ለDW ገልጸዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:59

«የመግባቢያ ሰነዱ በሁለት ሳምንት ይፈረማል»

በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ወይም አሁን በሚጠሩበት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከ80 እንደሚበልጡ ይነገራል። በሀገር ውስጥ የቆዩት ፓርቲዎች እንዲህ ያለ የጎንዮሽ ውይይት ማለትም ፓርቲዎቹ እርስበርስ ለሚያደርጉት ውይይት አዲስ አይደሉም። ፓርቲዎቹ በውጭ ሆነው ይንቀሳቀሱ የነበሩትን አክለው አብረው ለመሥራት የሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ ሲነጋገሩ ሰንብተዋል። በውይይታቸውም በተለይ በፓርቲዎች ምክር ቤት ሁሉም ፓርቲዎች በእኩል ይወከሉ የሚለው ላይ አፅንኦት ሰጥተው መነጋገራቸውን የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት መኢአድ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙሉጌታ አበበ አስረድተዋል። መኢአድ ከዚህ ቀደም የፓርቲዎቹ የመግባቢያ ሰነድ ብዙ ችግሮች እዳሉበት ሲያሳስብ እንደነበር እና አሁን ተስተካክሏል ያሉትንም ገልጸዋል።

«አንደኛ የምክር ቤቱ መቀመጫ ከዚህ በፊት በቀረበው አይነት አይደለም እኛ ባስቀመጥነው አይነት ነው ተሻሽሎ የመጣው፤ ሁለተኛ የኮሚቴዎችም አቀማመጥ፤ የሥነስርዓት ኮሚቴ፣ የቅሬታ ሰሚ እና ጉዳዮችን አጣርቶ የሚያቀርብ፣ የሚዲያም ኮሚቴ በተመለከተ እንዲካተቱ የፈለግናቸው ኮሚቴዎች ተካተዋል። እዚያ ላይ ግን አንዳንድ ወደኋላ ያለፍናቸው አንቀጾችም ላይ ማስተካከያ ሰጥተናል። ስለዚህ አሁን ፓርቲዎች በአቻነት እና ተከባብረው መሥራት እንዲችሉ አንዱ አንዱን እንዳይተነኩስ፤ አንዱ የሌላውን አባል እንዳያማልል፤ ፓርቲዎችን ይገዛል የሚል የቃል ኪዳን ሰነድ ነው የተነጋገርንበት።»

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ የኦሮሞ ፌደራሊስት ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ይህኛውን መድረክ ለየት የሚያደርገው በፓርቲዎቹ መካከል የታየው የመግባባት መንፈስ እንደነበር ገልጸውልናል። ፓርቲዎቹ ወደሚያግባባቸው ነጥብ ለመድረስም ከአብላጫ ድምፅ ይልቅ አንዱ ሌላውን ማሳመን ላይ ማተኮሩንም ዘርዝረዋል።

«መጀመሪያ ስንጀምር እንግዲህ ሁሉንም በመስማማት ነገሮችን ሁሉ ለመጨረስ ነው፤ ክርክር ይደረግበታል፤ ሰፊ ክርክር ጊዜ ይወሰዳል። ስለዚህ አንዱ የታቀወመውን ሌላው ለማሳመን ጥረት ተደርጎ በተቻለ መጠን በመስማማት አንድ ላይ በመቀራረብ በአብላጫ ድምፅ ሳይሆን በተቻለ መጠን አግባብቶ ሁሉም በስምምነት የሚያልቅበት አይነት ነገር ነው ስናካሂድ የነበረው። በዚሁ ሂደት ነው የጨረስነው።»

ከዚህ በፊት የነበረውን የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከመሠረቱት አንዱ የነበረው መኢአድ በወቅቱ ገዢው ፓርቲ የሥነምግባር እና የጋራ ምክር ቤቱን ደንብ ጥሷል በሚል መግለጫ ሰጥቶ በይፋ ራሱን ማግለሉ ይታወሳል። የአሁኑ ላይ ግን ያኛውን የሚተካ ነው ይላሉ አቶ ሙሉጌታ፤፣

«በገዢ ፓርቲ በኩል በጠራራ ፀሐይ የሥነምግባሩን እና የጋራ ምክር ቤቱን ስለጣሰ መግለጫ ሰጥተን ነበር እኛ የወጣነው ከዚህ በፊት። ያኛውን ምክር ቤት ገዢው ፓርቲ በጓዳ አስቀምጦ በጉያው ይዞ ይጠቀምበት የነበረውን ምክር ቤት የሚተካ ምክር ቤት ነው በምልአተ ጉባኤ እንዲመራ የተደረገው።»

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በቅርቡ አጋር ድርጅቶቹን ሁሉ ያቀፈ አንድ ሀገራዊ ፓርቲ የመሆን ዝግጅት ላይ መሆኑን ሊቀመንበሩ ይፋ አድርገዋል። በሀገርም ሆነ በክልሎች ስም ቁጥራቸው የበረከተው የፖለቲካ ፓርቲዎችስ ለሕዝቡ ምርጫ ዓይን የሚገቡበትን ተመሳሳይ ስልት ቀይሰው ይሆን? የመኢአድ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙሉጌታ ፓርቲያቸው ነገ ይፋ የሚያደርገው ርምጃ እንዳለ ጠቁሟል። አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸው።

«እስካሁን ድረስ ሁሉም የየራሱን ፕሮግራም ይዞ ነው፤ ወደአንድነት የመምጣቱ ጉዳይ በሂደት የሚታይ ይሆናል። አሁን እንግዲህ እንደሚታየው ኦዲኤፍ የምንለው በአቶ ሌንጮ ለታ የሚመራው ከኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ተዳምሯል። እንዲሁም ደግሞ በጀነራል ኃይሉ ጎንፋ እና በጀነራል ከማል ገልቹ እነዚህ አንድነት መጥተው ከኦፒዲኦዎች ጋር አብረው እየሠሩ ነው። በሂደት ወደመቀላቀሉ አይነት እንግዲህ ሊሄዱ ይችላሉ ስለዚህ ጥሩ አዝማሚያ እየታየ ነው።»

ፓርቲዎቹ የተግባቡበት ሰነድ ላይ የምርጫ ኮሚሽን ባለበት ከሁለት ሳምንታት በኋላ ፊርማቸውን ያኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች