ኹዋንታናሞ፥ ቃል-እቅድ ሲራዘምባት | ዓለም | DW | 25.01.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ኹዋንታናሞ፥ ቃል-እቅድ ሲራዘምባት

ተጠርጣሪዎቹን ወደ ኢሊኖይ የማዛወሩ እቅድ-ሥልት አነጋግሮ ሳያበቃ የመን የከረመዉ ናይጄሪያዊዉ ወጣት የአሜሪካን የመንገደኞች አዉሮፕላን ለማጋየት ሲመክር መያዙ ነገሩን እቅድ ሥልቱን ሁሉ ቅራ ቀኝ ያላጋዉ ይዟል

default

የኹዋንታናሞ እስረኞች

25 01 10


ኩባዎች እንደ ዉብ ደሴታቸዉ-ያደንቋታል።-እንደ ቆንጆ-ጠንካራ ልጃገረድ መፍለቂያ ግዛታቸዉ ያወድሷቷል።ኹዋንታናሞ።ኹዋንታላሜራ-እያሉ።ከትልቅ ግዙፍ፥ አይበገሬ ጎረቤታቸዉ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ይወዛገቡባታል።ከ1903 (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጀምሮ የሚቆጣጠሯት ግን አሜሪካኖች ናቸዉ።የኩባ፥ የሔይቲና የሌሎች የካረቢክ አካባቢ ሐገራት ሥደተኞች ሲሰፍሩባት-አሜሪካኖችን ካሜሪካኖች፥ አሜሪካኖች ካካቢዉ ሐገራት ጋርም ብዙ አወዛግባ ነበር።ተጠርጣሪ አሸባሪዎች ከታሰሩባት ወዲሕ ደግሞ አለምን ታከራክር ይዛለች።በቅርቡ ደግሞ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማን ቃል-አባይ አደረገች።ይሕ ነዉ የዛሬ ጉዳያችን።አብራችሁን ቆዩ።

ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ-ጥር 20 2009።ቃለ መሐላ ፈፀሙ።ዋይት ሐዉስ ገቡ።በሁለተኛዉ ቀን-የመጀመሪያ ትልቅ ዉሳኔያቸዉን አስታወቁ።ጥር-ሃያ ሁለት።

«እንደ ፕሬዝዳት በዩናይትድ ስቴትስ ሕገ-መንግሥትና ሕጎች በተሰጠኝ ሐላፊነት መሠረት፥ ባሁኑ ወቅት በመከላከያ ሚንስቴር አማካይነት ዃንታናሞ ማቆያ ማዕከል በሚገኙት (በታሰሩት) ግለሰቦች ላይ ሊደርስ የሚችለዉን አግባብ ያልሆነ በደል ለማስቀረት፥ ከሐገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም፥ ከዉጪ መርሕ እና ከዩናይትድ ስቴትስ የፍትሕ-ሥርዓት ጋር በተጣጣመ መልኩ የኩዋንታናሞን ማቆያ ማዕከል እንዲዘጋ ከዚሕ በታች ያለዉን አዋጅ አፅድቄያለሁ።የመዝጋቱ ሒደቱ ካሁን ጀምሮ ኹዋንታናሞ አንድ አመት ባልበለጠ ጊዜ ዉስጥ ይዘጋል።»

የፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ እቅድ ትዕዛዝ ከተሰማ ባለፈዉ ሮብ አመት ደፈነ።ማቆያ ጣቢያዉ ግን የወትሮዉ ነዉ።በፈለጉት ጊዜ ወደ ፈለጉት መሔድ፥መብረር የሚችሉ ወፎች ይዘምሩበታል። ወታደሮች በጥብቅ ይቆጣጠሩታል።ተጠርጣሪ አሸባሪዎችም ያዉ ከሁለት ሺሕ ሁለት ጀምሮ እንደነበረዉ አንድም ይፀልዩ፥ አለያም ይመረመሩበታል።

ባለፈዉ የኢትዮጵያዉያን ክረምት ማዕከሉን እንዲጎበኙ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የፈቀደላቸዉ ጋዜጠኞች በድምፅ ከቀደት-ጥቂቱ ይንኑ ከመመስከር ባለፍ-አዲስ ነገር ብዙ አልነበ

Binyam Mohamed erster freigelassner Häftling aus Guantanamo

ኢትዮጵያዊዉ ተጠርጣሪ ቢንያም መሐመድ

ረዉም።

የኹዋንታኖሞ-የባሕረ-ሠላጤ ወይም ወሽመጥ።በ1494 አገር አሳሽ ክርስቶፎር ኮሎምቦስ መሕለቁን በአካባቢዉ ሲጥል ፖርቶ ግራንዴ፥ አላዉ።ታላቁ ወደብ እንደማለት።የአካባቢዉ ነባር ነዋሪዎች (ታይኒዎች ነዉ የሚባሉት) የወደፊት ቅኝ ገዢዎቻቸዉ ለግዛታቸዉ የሰጡትን አዲስ ስም አልተቀበሉትም።እኒያ አሳ አስጋሪዎች በሰየሙት ፀኑ ኹዋንታናሞ እንዳሉት።

የስጳኞች አገር አሳሽ፥ ቅኝ ገዢዎች፥ ከአካባቢዉ ነዋሪዎች ጋር፥ኩባዎች ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ሲወዛገቡባት፥አሳ አጥማጆች፥ መርከበኞች፥ ነጋዴዎች፥ ወታደሮች፥ስደተኞች ሲፈራረቁባት ዘመነ-ዘመናት አስቆጥራለች። ዛሬም ያቺ የባሕር በር-አሜሪካዊ ጓንታናሞ፥ ጂታሞ ሲላት፥ ኩባዊዉ ኹዋንታናሞ እያለ በኔነት ካሜሪካዊዉ ጋር ይወዛገብባታል።

ዩናይትድ ስቴትስ በ2002 ባብዛኛዉ አፍቃኒስታንና ፓኪስታን ዉስጥ የተማረኩ ተጠርጣሪ አሸባሪዎችን እዚያች ደሴት ማሰሩን የመረጠችዉ በሐገሪቱና በአለም አቀፍ ሕግ ደንቦች መሰረት የተጠርጣሪዎቹ ይዞታ ሊያስነሳ የሚችለዉን ጥያቄና ክርክር ለማስወገድ ነበር።በወቅቱ በስልጣን ላይ የነበረዉ የፕሬዝዳንት ቡሽ መስተዳድር ባለሥልጣናት እንደሚሉት ተጠርጣሪዎቹ አንድ ወይም ከዚያ በላይ ሐገራት ከሌላ ሐገር ወይም ሐገራት ጋር በገጠሙት ጦርነት የተማረኩ ሳይሆኑ ከየቦታዉ የተጠረቃወሙ አሸባሪ ወሮበሎች ናቸዉ።

በዚሕም ምክንያት የጦር ምርከኞች ይዞታን የሚደነግገዉ የጄኔቫዉ ሕግም ሆነ፥የእስረኞችን የሰብአዊ መብት ይዞታን መጠበቅ የሚያስገድደዉ የራስዋ የአሜሪካ ሕግ ለኹዋንታናሞ እስረኞች ሊያገልግል አይችልም ባዮች ነበሩ።የቡሽ መስተዳድር እርምጃ፥ በተለይ ደግሞ ሚስጥር ለማዉጣት በሚል በተጠርጣሪዎቹ ላይ የተፈፀመዉ ግፍ የዲሞክራሲያዊቱን ሐገር፥ሥም ክፉኛ አግዱፏል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ እንዳስታወቁት ተጠርጣሪዎቹ ሚስጥር እንዲያወጡ በሚል በኤሌክትሪክ እየተንጨረጨሩ፥ ዉሐ ዉስጥ እየተደፈቁ፥ እንቅልፍ እየተከለከሉ፥ ርቀነ-ገላቸዉን እንዲቆሙ-እንዲቀመጡ ተገድደዋል።እድሜያቸዉ ለአካለ-መጠኝ ያልደረሱ ተጠርጣሪዎች ሳይቀሩ የዚሕ ግፍ ሰለባ መሆናቸዉ ከመብት ተሟጋቾች አልፎ፥ የአለም ፖለቲከኞ

Barack Obama Konzert Let Freedom Ring

ዕቅድ-ዉል ሳተ

ች መነጋገሪያ ርዕሥም ነበር።

በፕሬዝዳት ቡሽ መስተዳድር ላይ የሚሰነዘረዉ ወቀሳ ትችት ባየለበት በዚያ ዘመን ቡሽን ለመተካት ይፎካከሩ የነበሩት እጩዎች በተለይም የዲሞክራትክ ፓርቲዎቹ እጩዎች ያን የሐገራቸዉ ክብር፥ ማዕረግ፥ ስም-በጎ ዝና ያጎደፈዉን እስር ቤት እንዘጋለን የማይሉበት ምክንያት አልነበራቸዉም።

ኦባም በምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅት አደርገዋለሁ ያሉትን ለማለት ሥልጣን ከያዙ በሕዋላ ሁለት ቀን አልፈጀባቸዉም።አሉት።

«ኹዋንታናሞ አንድ አመት ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ ይዘጋል።»

የኦባማ ቃል-ለሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፥ ለፍትሕ ተቆርቋሪዎች፥ ለአንዳድ ፖለቲከኞችም በርግጥ የምስራች ነበር።እዚያ እስር ቤት ለነበሩት ተጠርጣሪዎች ደግሞ ታላቅ ጉጉት።እስረኞቹን ከሚጠብቁት የአሜሪካ ወታደሮች አንዱ ያኔ ያስተዋለዉም ይሕንኑ ነበር።

«በጣም ተደስተዉ ነበር።ታዉቃለሕ።ከዚሕ ለመሔድ በጣም ተዘጋጅተዉ ነበር።ኹዋንታናሞን ለመልቀቅ ጓጉተዉ ነበር።ከዚያ ጊዜ በሕዋላ ግን ብዙ ወራት አለፉ።እና አሁን ነገሮች ሁሉ እሳቸዉ (ኦባማ) ሥልጣን ከመያዛቸዉ በፊት እንደነበሩት ናቸዉ-የሚል አስተሳሰብ ነዉ-ያላቸዉ።»

ኦባማ ሥልጣን በያዙ-ቃል በገቡበት ወቅት 240 ተጠርጣሪ አሸባሪዎች ኹዋንታናሞ ማቆያ ጣቢያ እንደተያዙ ነበር።የኦባማ ቃል-ዉል መሳቱ ባለፈዉ ሮብ ሲመሰከር ሁለት መቶ ያሕል እስረኞች እዚያዉ ናቸዉ።

ባንድ አመት ዉስጥ ወደየሐገራቸዉ ወይም ወደ ሰወስተኛ ሐገር የተላኩት እስረኞች አርባ ብቻ ናቸዉ ማለት ነዉ።ተጠርታሪዎቹ ወደየትዉልድ ሐገራቸዉ ቢላኩ በሰብአዊ መብት ረገጭነታቸዉ የሚታወቁት፥ አምባገነን የየሐገሩ መንግሥታት የተጠርጣሪዎቹን ይበልጥ ያሰቃዩ፥ ይበድሏቸዋል የሚል ትልቅ ሥጋት ነበር።

ተጠርጣሪዎቹ ከአምባገነን ገዢዎቹ በደል ካመለጡ ምናልባት አሸባሪዎችን ይቀላቀሉ ይሆናል-የሚለዉም ጥርጣሬም የጎላ ነበር።ሥጋት ጥርጣሬዉን ለማቃለል የተገኘዉ መፍትሔ ተጠርጣሪዎቹ ራስዋ ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ወደተለያዩ ሐገራት እንዲላኩ፥ እና በመደበኛ ፍርድ ቤት መዳኘት የሚገባቸዉም በየሚሔዱበት ሐገራት ይዳኙ የሚል ነበር።

የፕሬዝዳት ቡሽ መስተዳድር ያንን ማቆያ ጣቢያዉን እንዲዘጋ ግፊት ከሚያደርጉት ሐገራት አብዛኞቹ የአዉሮጳ ሐገራት ነበሩ።ተጠርጣሪዎቹን ለመቀበል ዝግጁነታቸዉን የገለጡ የአዉሮጳ ሐገራትም ነበሩ።የኦባማ መስተዳድር ማቆያ ጣቢያዉን ለመዝጋት ሲወስን ግን ብዙዎቹ ቅሌን ጨርቄን ይሉ ገቡ።ከነዚሕ አንዷ ጀርመን ናት።

ዩናይትድ ስቴትስ ራስዋ ለአዉሮጶች ይሁን ለሌሎች ጥሩ ምሳሌ መሆን አለመቻሏ ነዉ-እንቆቅልሹ።የተወሰኑ እስረኞቹ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ግዛት ይዛወሩ የሚለዉን ሐሳብ የፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ መስተዳድር ተቃዋሚ የሪፐብሊካኖች ፓርቲ አይቀበለዉም።ከራሳቸዉ ከኦባማ ፓርቲ ከዲሞክራቶቹ ባለሥልጣናት መካካል ሴናተር ጂም ዌብን የመሳሰሉት ሐሳቡን አለመቀበላቸዉ ነዉ-ግራዉ።

«ማድረግ አለብን።ኹዋንታናሞን በተገቢዉ ጊዜ መዝጋት ይገባናል።መዝጋት የሚገባን ግን ሰዎችን ወደዚሕ (ወደ ዩናይትድ ስቴትስ) በማዛወር አይደለም።»

የፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ የአመት-እቅድ ቃል ዉሉን ስቷል። ግን ፕሬዝዳንቱ ባቋማቸዉ እንደፀኑ ነዉ።መስተዳድራቸዉ ከእስረኞቹ መካካል አንድ መቶ ያሕሉን ኢሊኖይ ግዛት ወደሚገኘዉና ጥብቅ ቁጥጥር ወደሚደረግበት እስር ቤት ለማዛወር ማቀዱን ባለፈዉ ታሕሳስ አስታዉቋል።

ተጠርጣሪዎቹን ወደ ኢሊኖይ የማዛወሩ እቅድ-ሥልት አነጋግሮ ሳያበቃ የመን የከረመዉ ናይጄሪያዊዉ ወጣት የአሜሪካን የመንገደኞች አዉሮፕላን ለማጋየት ሲመክር መያዙ ነገሩን እቅድ ሥልቱን ሁሉ ቅራ ቀኝ ያላጋዉ ይዟል።እስካሁን ድረስ ኹዋንታናሞ ከሚገኙት ሁለት መቶ ያሕል ተጠርታሪዎች ዘጠናዉ የየመን ዜጎች ናቸዉ።ይሕ ነዉ-ምስቅልቅሉ።የፕሬዝዳት ኦባማ ቃል አቀባይ ሮበርት ጊብስ በቅርቡ እንዳሉት ግን ኹዋንታናሞን የመዝጋቱ እቅድ ይዘግይ እንጂ አይታጠፍም።የመኖችን ግን፣-

«ማቆያ ሥፍራዉ ከዚሕ ቀደም በገባነዉ ቃል መሠረት ይዘጋል። ተጨማሪ (እስረኞችን) ወደየመን ማስተላለፉ ግን ባሁኑ ጊዜ ጥሩ ሐሳብ አይደለም።»
-----------------------------

ኹዋንታናሞ-ዛሬም እንደ ጥንቱ፥ ታከራክር-ታወዛግባላች ቃል-እቅድ ታሳጥፍ ወይም ታራዝማለች። ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

Agenturen,Dw

Anna Engekelke

Negash Mohammed

Tekle Yewhala


Audios and videos on the topic