ኸርዝ ኮህለር በማዳጋስካር | የጋዜጦች አምድ | DW | 07.04.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ኸርዝ ኮህለር በማዳጋስካር

የጀርመን ፕሬዝደንት ኸርዝ ኮህለር በአፍሪካ የሚያደርጉትን ጉብኝት ቀጥለዉ ማዳጋስካር ገብተዋል። በዚያም ቆይታቸዉ ከአገሪቱ ፕሬዝደንት ጋር የተፈጥሮ አካባቢን በመንከባከብና የተፈጥሮ ሃብቶችን በአግባቡ በመጠቀም ዙሪያ ተነጋግረዋል።

ኮህለር በማዳጋስካር

ኮህለር በማዳጋስካር

በሁለቱ ሀገራት መካከል ሊኖር የሚገባዉ የምጣኔ ሃብትና የፖለቲካ ግንኙነትም ትኩረት ከተሰጣቸዉ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ ናቸዉ።
በ2003ዓ.ም የዓለም የገንዘብ ምንዛሪ ተቋም ዳይሬክተር በነበሩበት ወቅት የጀርመኑ ፕሬዝደንት ሆርዝ ኮህለር አገሪቱን ሲጎበኙ ከማዳጋስካሩ ፕሬዝደንት ማርክ ራቫሎማናና ጋር ተገናኝተዋል።
በመዲናዋ አንታናናሪቮ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም ከዚያን ጊዜ ወዲህ በማዳጋስካር ያዩትን የፖለቲካ መሻሻል አድንቀዉ ነዉ የተናገሩት።
«በ2003ዓ.ም ካደረኩት የመጀመሪያዉ ጉብኝቴ ወዲህ አሁን ያረጋገጥኩት በማዳጋስካር በርካታ ለዉጥ መደረጉን። ያም ደግሞ በዚች አገር የምጣኔ ሃብቱን እድገት ለማምጣትና ድህነትን ለማስወገድ በሚረዳ መልኩ በትክክለኛ አቅጣጫ እየተጓዘች መሆኑን በግልፅ ያሳያል።»
የማዳጋስካር ፕሬዝደንት ማርክ ራቫሎማናና ለተዳከመዉ የአገራቸዉ የምጣኔ ሃብት የሚረዳ ያሉትን ማስተካከያ አድርገዋል።
የፖለቲካ ተቺዎች እንደሚሉት ግን ፕሬዝደንቱ አገሪቱን የሚመሩት እንደአንድ የንግድ ድርጅት ባለቤት የሚወስዱ ዉሳኔዎችን ሁሉ በግላቸዉ እያደረጉ በመሆኑ ለዉጥ የሚባለዉ ጉልህ አይደለም።
በኮህለር አስተያየት ደግሞ በመጪዉ ዓመት በአገሪቱ በሚካሄደዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የተባለዉ የፖለቲካ መሳሻል ሁሉ የሚታይ ይሆናል።
የማዳጋስካር ፕሬዝደንትም ቢሆኑ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታዉና የልማቱ እርምጃ ብዙ እያለፋቸዉ መሆኑን በመግለፅ ምርጫዉ ሙሉ በሙሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቁጥጥር ያለበት እንደሚሆን ነዉ ያረጋገጡት።
ማዳጋስካር በከፍተኛ ደረጃ በዉጪ መንግስታት የገንዘብ ድጋፍ የምትንቀሳቀ አገር እንደመሆኗ ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች ከተወያዩባቸዉ ነጥቦች መካከል ትልቅ ስፍራ የተሰጠዉ ነበር።
«በዉይይታችን ካስደሰተኝ አንዱ ነጥብ የጀርመን ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸዉን ወደዚህ አፍስሰዉ በማዳጋስካር የምጣኔ ሃብት እድገት ለማምጣት መልካም የመንግስት አስተዳደር ቁልፍ መሆኑን መስማማታችን ነዉ።»
ከፈረንጆቹ 1970 እስከ 1995 ዓ.ም, ድረስ በሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም የዳከረችዉ ማዳጋስካር ብሄራዊ ምጣኔ ሃብቷ አሽቆልቁሏል።
በዚህ ሳቢያ በዉጪ የልማት እርዳታ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የምትደገፍ ስትሆን ግንባር ቀደም ደጓሚዋም ፈረንሳይ ናት።
ጀርመንም ከ40 ዓመታት በላይ ማዳጋስካርን ስትደግፍ ቆይታለች። ባለፈዉና በዘንድሮዉ ዓመትም በድምሩ 15.5 ሚሊዮን ዩሮ ነዉ ማዳጋስካር መልካም የመንግስት አስተዳደርን ለማስፈን፣ ኤችአይቪ ኤድስን ለመከላከልና የተፈጥሮ ሃብቷን ለመጠበቅ የተደረገላት የገንዘብ ድጋፍ።
በጉብኝታቸዉ ወቅት ኮህለር የደረሱበትም የጀርመን ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸዉን በማዳጋስካር ለማፍሰስ እንዲችሉ የሚያበረታታ ስምምነት መኖሩን ነዉ።
በተጨማሪም ለማዳጋስካር የምጣኔ ሃብት እድገት ጀርመን የንግድ ምክር ቤቱን ለማጠናከር በሚደረገዉ ጥረት በስልጠና ለመርዳት ዝግጁነቷን አስታዉቀዋል።
በዚያም ላይ የጀርመን የቁጠባ ባንክ ለማዳጋስካር ጥቃቅን የብድር አገልግሎቶች የሚዉል ድጋፍ እንደሚሰጥ ተስማምተዋል።
የተፈጥሮ ሃብትን ለመጠበቅ ማዳጋስካር የወሰደችዉ እርምጃም ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለዓለምም የሚበጅ እንደሆነ ኮህለር በመጥቀስም ጥረቱን አወድሰዋል።