ኮንጎ እና የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ ተልዕኮ | ዓለም | DW | 28.03.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ኮንጎ እና የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ ተልዕኮ

የተመድ የፀጥታ ጥ/ም/ቤት በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ውስጥ የተሠማራውን እና በምህፃሩ « ሞኑስክ» ተብሎ የሚታወቀውን የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ ተልዕኮ በአንድ ዓመት አራዝሞዋል፣ ይሁንና፣ አሁን በሀገሪቱ የሰላም አስከባሪ ወታደሮች ቁጥር በ2000 እንዲቀንስ 15 ሀገራት የሚጠቃለሉበት ምክር ቤት የተመድ ፀ/ጥ/ም/ቤት በአንድ ድምፅ ወስኖዋል።

ይሁን እንጂ ፣ ጓዱ የተሠማራበት የምሥራቃዊ ኮንጎ ፀጥታ ሁኔታ አሁንም አለመሻሻሉን ያመለከቱት ጊጋ የተባለው የጀርመናውያኑ የፖለቲካ ጥናት ተቋም ተንታኝ ናዲን አንዞርግ የተመድ ፀጥታ ምክር ቤት የጦሩን ቁጥር የቀነሰበትን ውሳኔ ጠቃሚነት አጠያይቀዋል።

« በወታደራዊው ርምጃ ሲመለከቱት የጦሩ ቁጥር መቀነስ የሚያስገኘው ፋይዳ የለም። ምክር ቤቱ ይህን ውሳኔ የወሰደው የኮንጎ መንግሥት ያቀረበውን ጥያቄ በማገናዘብ ፖለቲካዊ ምክንያት የተነሳ ነው ብየ አስባለሁ። »

የፖለቲካ ተንታኟ እንዳስረዱት፣ የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ መንግሥት ቢያንስ 7,000 የሰላም አስከባሪው ጓድ ወታደሮች ከሀገሩ እንዲወጡ ነበር የጠየቀው። የኮንጎ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሬይመንድ ሺባንዳ ከጥቂት ጊዜ በፊት ለፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ሀገራቸው የፀጥታ ጥበቃውን ኃላፊነት ራሷ መወጣት እንዳለባት እና ሰላም አስከባሪው ጋድም ሀገራቸውን ለቆ መውጣት እንደሚገባው አስታውቀዋል።

Martin Kobler UNO-Mission Kongo

የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ እና ኃላፊው ማርቲን ኮብለር

የተመድ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች እአአ ከ15 ዓመታት በፊት፣ እአአ በ1999 ዓም ነበር ምሥራቃዊውን ኮንጎ ለማረጋጋት ሲባል መጀመሪያ ጊዜ በዚያ የተሠማሩት። እአአ ከ2010 ዓም ወዲህም የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ፣ በምህፃሩ « ሞኑስክ » የሚል መጠሪያ በመያዝ ሀገሪቱን የማረጋጋቱን ተልዕኮ ቀጥሎዋል። በተለይ በምሥራቃዊ ኮንጎ በመንግሥቱ አንፃር የሚዋጉትን ያማፅያን ቡድኖችን መታገል፣ ሲቭሉን ሕዝብ ደህንነት መጠበቅ እና ያካባቢውን ጊዚያዊ ሁኔታ ማረጋጋት የተልዕኮው ዋነኛ ዓላማ ነው።

ከ20,000 የሚበልጡ ወታደሮች ያሉት እና በዓመት 1,4 ቢልዮን ዶላር በጀት የተመደበለት ይኸው በኮንጎ የተሠማራው ሰላም አሰከባሪ ጓድ የዓለሙ መንግሥታት እስከዛሬ ያሠማራው ትልቁ እና ውዱ መሆኑ ይነገራል። የጓዱ ተልዕኮ ከሁለት ዓመት በፊት በፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ እስከተጠናከረበት እና ጀርመናዊው ዲፕሎማት ማርቲን ኮብለር የ«ሞኑስክ»ን አመራር እስከያዙበት ጊዜ ድረስ ጓዱ ለብዙ ዓመታት ውጤት አልባ ሆኖ ነበር የቆየው። ጓዱ እአአ በ2013 ዓም ከኮንጎ ጦር ጋ ባንድነት በመሆን ባካሄደው ጥቃት ዘመቻ «ኤም 23 » የተባለውን ያማፅያን ቡድን ከትልቋ የምሥራቅ ኮንጎ ከተማ ጎማ ሊያስወጣ እና በቡድኑ ላይ ድል ሊያስመዘግብ ችሏል። ይህም በኮንጎ ዜጎች ዘንድ በ«ሞኑስክ» አኳያ የነበረው አሉታዊ አመለካከት፣ ማለትም፣ ጓዱ የሲቭሉን ህዝብ ደህንነት ሳይሆን የራሱን ደህንነት ነው የሚያስጠብቀው በሚል የነበረው አስተሳሰብ እንዲቀየር አድርጓል።

የኮንጎ ጦር እና ሞኑስክ ከአንድ ወር ገደማ በፊት ከ1994 የርዋንዳ የጎሳ ጭፍጨፋ በኋላ ወደ ምሥራቅ ኮንጎ በመሸሽ በዚያ በመንቀሳቀስ ላይ በሚገኙት በሁቱ ዓማፅያን አንፃር ለማካሄድ ያሰቡት ዘመቻ በትብብር ጉድለት ከከሸፈ በኋላ የኮንጎ ጦር ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሄሊኮፕተሮች እና በከባድ ጦር መሳሪያ ለብቻው ጥቃት ጀምሮዋል። በዚህም ለ« ሞኑስክ » ኃላፊዎች የሰላም አሰከባሪው ስምሪት አስፈላጊ አለመሆኑን ለማጉላት ሳይሆን እንዳልቀረ በርሊን የሚገኘው ሳይንስና ፖለቲካ ጥናት ተቋም ተንታኝ ዴኒስ ቱል ገምተዋል። ይሁንና፣ ጓዱ አስተማማኝ ተባባሪ ሳይኖረው ስራውን መስራት እንደማይችል ነው ቱል ያስረዱት።

« ጓዱ አብሮት ተባብሮ ሊሰራ የሚችል ተጓዳኝ እስከሌለው ድረስ የተቀመጠለትን ተልዕኮ የማሟላት አቅም የለውም።

የኮንጎ ጦር ለብቻው በጀመረው ዘመቻ ድል ማስመዝገቡን ቢገልጽም፣ ባካባቢው የሚገኝ የአንድ ሲቭል ማህበረሰብ ድርጅት ፕሬዚደንት ፎስተ ካታንጋን የመሳሰሉ ብዙዎች ዓማፅያኑ ላጭር ጊዜ ብቻ ሳያፈገፍጉ እንዳልቀረ ነው የሚገምቱት።

« ዓማፅያኑ ካካባቢው መባረር ብቻ ሳይሆን ቢያዙ እንመርጥ ነበር። እርግጥ፣ የጦሩን ርምጃ እናደንቃለን፣ ግን ዓማፅያኑ ወደለቀቁት አካባቢ ሊመለሱ እና የበቀል ርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ ብለን ነው ነው የምናስበው። ስለዚህ የሀገር አስተዳደር እና የመከላከያ ሚንስቴሮች ዓማፅያኑ የለቀቁትን አካባቢ የሚጠብቅ ፖሊስ ማሠማራት ይገባቸዋል። »

የኮንጎ ጦር ድል ዘላቂነትን የጀርመናውያኑ የፖለቲካ ጥናት ተቋም ተንታኝ ናዲን አንዞርግም ተጠራጥረውታል።

« የተለያዩ ያካባቢው ታዛቢዎች እንደሚሉት፣ ፕሬዚደንት ካቢላ ባካባቢው አለመረጋጋቱ የሚቀጥልበትን ሁኔታ ይፈልጉታል፣ ይህን ሁኔታ ላካባቢው ህዝብ አስፈላጊውን አቅርቦት ማሟላት ላልቻሉበት ድርጊት እንደ ምክንያት ሊጠቀሙበት ይችላሉ። »

አርያም ተክሌ/ሂልከ ፊሸር

Audios and videos on the topic